>
8:37 pm - Tuesday June 6, 2023

የራስ ህዝብ ሉአላዊነት ጥያቄ...!!! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ)

የራስ ህዝብ ሉአላዊነት ጥያቄ…!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

አዲስ አበባ በረዥሙ ታሪኳ ልዩ አስተዳደራዊ ቅርፅና መብቶች ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ በ1923 ዓ.ም የአውራጃ አስተዳደር ስርዓት በተጀመረበት ጊዜ አዲስ አበባ ከ44ቱ የአገሪቱ አውራጃዎች አንዷ ነበረች፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን ወርራ በያዘችባቸው አምስት ዓመታት (1928 –1933 ዓ.ም) ከስድስቱ የኢጣልያ ምሥራቅ አፍሪካ ግዛቶች አንዷና የሸዋና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ተደርጋለች፡፡
ከጣልያን መባረር በኋላ በ1934 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሲመሰረትና የጠቅላይ ግዛት አስተዳደር ሲቋቋም አዲስ አበባ በዋና ከተማነቷ ቀጥላ በ1940 ዓ.ም የአገሪቱ 14ኛ ጠቅላይ ግዛትና የጠቅላይ ግዛቶች ማዕከል ሆነች፡፡ እንደገና በ1952 ዓ.ም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስትዋሃድ አዲስ አበባ ልዩ ጠቅላይ ግዛት ተብላ በራስ ገዝነቷ ቀጥላለች፡፡ በንጉሡ ዘመን አዲስ አበባ በአዋጅ ልዩ ጠቅላይ ግዛት ሆና ራሷን ችላ በምትደዳደርበት ጊዜ አራት አውራጃዎች፣ 10 ወረዳዎችና በርከት ያሉ ምክትል ወረዳዎች ይዛ የቆዳ ስፋቷ 122,000 ሄክታር ነበር፡፡
በወታደራዊው ደርግ ዘመንም የአዲስ አበባ አስተዳደር መዋቅራዊ ለውጦችን ቢያስተናግድም መሰረታዊ የከተማዋ ራስገዝነት፣ ማዕከልነትና የቆዳ ስፋት ለውጥ አላሳየም፡፡ በአገዛዙ መጀመሪያ ማለትም በ1968 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማን የከተማ ቦታ ኪራይና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ ለመደንገግ ደርግ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 80/1968 ጋር አባሪ ተደርጎ የቀረበው የከተማዋ ካርታ አዲስ አበባ የትኞችን በዙሪያዋ የሚገኙ ቦታዎች እንደምታካተትና ስፋቷም 122,000 ሄክታር እንደነበር ተመልክቷል፡፡
ደርግ እንደገና በ1981 ዓ.ም የራስ ገዝ አካባቢዎችን፣ የአስተዳደር አካባቢዎችንና አውራጃዎችን ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 26/1981 ባወጀበት ጊዜ የአዲስ አበባን የቀድሞ ይዞታ ሳይነካ አስተዳደራዊ መዋቅሩን በ13 የከተማ ክ/ከተሞች፣ በ20 የገጠር አውራጃዎች ከፍሏቸው ነበር፡፡ በሁለቱም የደርግ አዋጆች መሰረት አሁን “የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን” በሚል ወደ ኦሮሚያ የተካተቱ ቦታዎች በአዲስ አበባ የቀድሞ ይዞታ ስር ነበሩ፡፡
ሀ. የአዲስ አበባ ራስ ገዝነት መገፈፍ
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የሽግግር ወቅት በመባል የሚታወቀው ከሰኔ 1983 – ነሐሴ 1987 በነበሩት አራት አመታት ውስጥ አዲስ አበባ ክልል 14 ተብላ እንደ ሌሎች የህወሐት/ኢህአዴግ ክልሎች ራሷን የቻለች ክልል እንደነበረች ይታወቃል፡፡ በ1987 ዓ.ም የፀደቀውና እስካሁን ያልተሻረው የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 2 የአዲስ አበባ ነዋሪ ራሱን በራሱ ማስተደዳር ይችላል ይላል፡፡ ከ1987 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ  በየጊዜው ሲሻሻሉ የቆዩ የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተሮችም  ቢሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳለው አስፍረዋል፡፡ ሆኖም በተግባር የአዲስ አበባ ሕዝብ የአገሪቱ የፌዴራል ስርአት
•   ህገ-መንግሥታዊ ችግር 
ችግሩ ከራሱ ከህገ መንግሥቱ የሚነሳ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አንቀጽ 49/2 የሚደነግገው የአዲስ አበባ ነዋሪ እራሱን በራሱ ማስተዳደር /Self-Governance/ መብቱን ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ለክልሎች ወይም ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተሰጠውን የእራስን እድል በራስ የመወሰን መብት /Self-determination/ ለአዲስ አበባ ነዋሪ አልሰጠውም፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደዜጋ ከሌሎች ክልሎች ነዋሪዎች በእኩል ደረጃ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማድረግ መብት የለውም፡፡
ሁለተኛ አዲስ አበባ ከሞግዚት አስተዳደር ስር ወጥታ ነዋነሪው በነፃነት በመረጣቸው ወኪሎቹ ሊተዳደር ሲገባ ህገ መንግሥቱ በአንቀጽ አንቀጽ 49/ 3 መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነትን ለፌዴራል መንግስቱ በማድረግ የአዲስ አበባን መብት ገፈፈው፡፡
ሶስተኛ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 61 መሰረት አዲስ አበባ በፌዴሬሽን ም/ቤት ውክልና የላትም፡፡ የፌደሬሽን ም/ቤቱ የሚወከሉት የፌደራል መንግስቱ አባል የሆኑ ክልሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወክለው የሚልኳቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ቢያንስ አንድ ተወካይ የሚኖራቸው ሲሆን ተወካዮቹም የሚመረጡት በየክልሎቹ ምክር ቤት አማካይነት ነው፡፡ አዲስ አበባ በህገ መንግስቱ ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች ከልል በሚባለው የወል ስም ውስጥ ስለማትካተት በፌደራል መንግስቱ አባልነት በፌደሬሽን ም/ቤት ውክልና የላትም፡፡
ይህም በመሆኑ አዲስ አበባ/አዲስ አበቤ/ በህገ መንግስቱ  አንቀጽ 62 ላይ የተዘረዘሩትን እንደ ህግ መተርጎም፣ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት የመወሰን፣  በክልሎች መካከል በሚደረግ አለመግባባት ላይ መፍትሄ የመስጠት፣ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን የመሳሰሉት ተሳትፎ የለውም፣ ተጠቃሚም አይደለም፡፡ ስለዚህም  በሀገሪቱ ወሳኝ ጉዳይም ሆነ በከተማው ጉዳይ ላይ ባይተዋር ያደርገዋል፡፡
•   የከተማዋ ቻርተር ችግር
የአዲስ አበባ አስተዳደር ቻርተር 361/1995 ከተማዋ በራሷ የምትተዳደርበትና የቻርተሩም መነሻው ከህገ-መንግሰቱ አንቀጽ 49/2 እና 55/1 መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህ ቻርተር የወጣው በኤ.ፌ.ዲ.ሪ. ተወካዮች ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፍላጎት በተጨባጭ ተንጸባርቆበታል ለማለት አይቻልም፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ነዋሪዎች በዚህ ቻርተር ዝግጅት ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ያልነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ እንግዴህ በግልጽ እንደምንረዳው ቻርተሩ የፌደራል መንግስቱ ችሮታ እንጂ ነዋሪዎች ለራሳቸው ያዘጋጁትና የመሪዎቻቸውን ሥልጣን የሚወስኑበት ሰነድ አይደለም፡፡
በዚህ ላይ ቻርተሩ የነዋሪዎቹን መብቶች የሚገድቡ በርካታ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ የቻርተሩ አንቀፅ 17 የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስትና ለከተማው ህዝብ መሆኑን ቢደነግግም ፣ ከክልል ምክር ቤቶች አንጻር ስናየው ምክር ቤቱ ያለው ነጻነት ውስን መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህንን ድንጋጌ ስለምክር ቤቱ መበተን ከሚደነግገው ከቻርተሩ አንቀጽ 61 ጋር አጣምረን ስንመለከተው እንደውም ምክር ቤቱ የፌደራል መንግስቱ ምስለኔ እንጂ ነጻነት ያለው አካል ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም የፌደራል መንግሰቱ ምክር ቤቱን ህገ መንግስቱን አደጋ ላይ ጥሏል ወይም የከተማውን ጸጥታ ማስከበር አልቻለም በሚል መበተን ይችላል (አንቀጽ 61/3)፡፡
በቻርተሩ አንቀፅ 39/40/41 መሰረት የአዲስ አባባ ፍ/ቤቶችና ሌሎች የዳኝነት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት የስልጣን ክልል እጅግ በጣም ውስን ሲሆን አብዛኛውን ጉዳይ የመዳኘት ሃላፊነት ለፌደራል ፍ/ቤቶች የተሰጠ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ፍ/ቤቶች ህግ የመተርጎም ስልጣን ከተወሰኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮችና ጥቂት የፍ/ብሔር ጉዳዮች የሚያልፍ አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስን በተመለከተም የቻርተሩ አንቀጽ 27/1 በዋናነት ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑንና የከተማው አስተዳደር ሚና በውክልና ደረጃ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪ የከተማው ፖሊስ ኃላፊነት የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽነርና ም/ኮሚሽነር በቀጥታ የሚሾሙት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው (አንቀጽ 27/2)፡፡ የከተማዋን የፖሊስ አደረጃጀትና ተጠያቂነት ስንመለከት አዲስ አበባ አስተዳደሯ የሚተማመን፣ የነዋሪዎቹንም ሰላም በገለልተኘኝት ያለአድልዎ የሚጠብቅ የፖሊስ ኃይል አላት ለማለት አያስደፍርም፡፡
በተመሳሳይ የተሻሻለው የአዲስ የአባባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 1094/2011 የለወጠው ጥቂት አንቀጾች ብቻ ነው፡፡ አላማውም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የስልጣን ዘመኑ እያለፈ በመሆኑና የፓርቲው ምርጫ የሆኑ ከንቲባዎች በምክር ቤቱ ባለመኖራቸው ወይም ባለመፈለጉ ምርጫ ከማድረግ ይልቅ ሥልጣን የተቆጣጠረው ኦህዴድ ህግ አሻሽሎ ስልጣኑን በፈለገው መንገድ ለመጠቅለል እንዲረዳው ነው፡፡
ለ. የአዲስ አበባ ይዞታ መቀማት
በህወሓት ኢህአዴግ ዘመን አዲስ አበባ የወያኔ የፖለቲካ ቁማር ዋነኛ መጫወቻ ሆናለች፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም የህወሓት የምርጫ ሽንፈት በኋላ አቶ መለስ ዜናዊ ኦህዴድን ከናዝሬት/አዳማ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ አደረገ፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ይዞታ ቀድሞ ከነበረው ከ122 ሺህ ሄክታር ተቀንሶ ‹‹ፊንፊኔ ልዩ ዞን›› በሚል ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲካተት ተደረገ፡፡ በዚህም አዲስ አበባ ይዞታዋ ወደ 54,000 ሄክታር ወረደ፡፡ የከተማው አስተዳደርም በሞግዚት አስተዳደር ስር እንዲገባ  ተደረገ፡፡
ከ1997 ዓ.ም በኋላ ህወሓት በአዲስ አበባ ዙሪያ ብዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መስራት ሲጀምር ከተማዋ እየተለጠጠች ከኦሮሚያ ክልል ጋር “የድንበር አለመግባባት” ችግር ተፈጠረ፡፡  ችግሩን ለመፍታት በ2009 ዓ.ም በዶ/ር አብይ የሚመራ ኮሚቴ የአዲስ አበባን ይዞታ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎች እንዲያጠኑት አደረገ፡፡ ይህ ጥናት በወቅቱ በተጨባጭ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው ይዞታ ከ54,000 ሄክታርም ተቀንሶ 51,355 ሄክታር ብቻ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ይህም የሆነው ምንም አይነት አዋጅ ሳይደነገግ በውስጥ ለውስጥ አሰራር ነበር፡፡
Filed in: Amharic