ጭራሽ በማዕቀብ ሙድ ትይዛለህ…!;;
ታምሩ ተመስገን
የዚህችን የጉዞ ማዕቀብ ጉዳይ በጣም ቀለል አድርገህ ተመለከትካት ኣ! አይደብርህም እንዴ! ጭራሽ ሙድ ምናምን ትይዛለህ ደግሞ! ችግሩ ተለጥጦ ተለጥጦ እንዴት አንገትህ ላይ ቢላዋ እንደሚያሰቀምጥልህ ከረፈደ ይገባሃል! ይሄ ጅማሬአቸው እንጂ መጨረሻቸው እንዳልሆነ አልበራልህም? ባለስልጣኖቹ ለተከለከሉት ቪዛ እኔ ምን አገባኝ ብለህ ከአሜሪካ ጎን ለመቆም ስትጋጋጥ አይሰቀጥጥህም?
ባባ አገርና መንግስትንማ ነጣጥለህ እያየህ እንጂ! ጉዳዩ ካልገባህ ደግሞ ጠጋ ብለህ ጠይቅ፡፡ ባንተ አለማወቅ ውስጥ ግን ሌሎችንም ይዘህ ለመጥፋት አትሞክር፡፡ ነውርም ነው!
/ላስረዳህ/
ወደ አገራችን መካከለኛው ዘመን ልመልስህ፡፡ ያኔ አልጋ የሚባል ጉዳይ ነበር፡፡ አልጋው አገርን ይወክላል፡፡ የተቀባው አልያም ራሱን የቀባው ንጉስ አልጋው ይገባኛል ይልና መሪህ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ መንግስት ሆነ ማለት አይደል፡፡ ታዲያ ያኔ ንጉሱ አልያም መሪው ከህዝቦቹ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገባ በተለይ የወታደሩ ዋናው ጉዳይ አልጋውን አልያም አገሪቱን መጠበቅ ነው፡፡ ለምን መሰለህ ንጉስ ይመጣል ይሄዳል፡፡
የሾመህ ህዝብ ሙድህን ካልመሰጠው ወይ በድርደር አልያም በጉልበት አፈር ከድቼ ያበላህና አልጋህ ላይ ጉብ ይላል፡፡ አገሪቷ ግን ያው ራሷ አገሪቷ ናት፡፡ ለውጡ አልጋው ላይ የሚቀመጠው ነው፡፡ እናልህ ያኔ የውጭ ወራሪ ሲመጣ ለአልጋው ሲገዳደሩ የነበሩት ሁሉ ንጉሱ ስላስቀየመን አሁን የራስህ ጉዳይ ብንለው ኋላ አገራችንን አስበልተን ቆመን የምንወቃቀውበት ቦታ እናጣለንና የውስጥ ጉዳያችን በይደር ይቆይና እንዝመት ይባባላሉ፡፡ ለምሳሌ ከደርቡሽ ጋር እና ከጣሊያን ጋር የተደረጉትን ጦርነቶች ማስታወስ በቂ ነው፡፡
ወደእዚህ ስትመጣ እኔ ለምሳሌ የብልፅግና አድናቂ አይደለሁም፡፡ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን እኔንም አንተንም የሞት ዘገባ ያንያክል የሚያስደነግጠን እንዳይሆን አድረገውናል፡፡ ከአንተም ከእኔም ቤት ወንድሞቻችንን ተነጥቀናል፡፡ ይህ ማለት ግን ለአገራችን ባንድ መቆም የለብንም ማለት አይደለም፡፡ መንግስት ለወንድሞቻችን ሞት ፍትህ ይስጠን ለማለት እኮ መጀመሪያ የምትቆምበት አገር ያስፈልገናል፡፡ አገራችንን ካስበላን በኋላ የት ላይ ቆመን ነው እምንደራደረው? ኢትዮጵያና ብልፅግና ፍፁም የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አገርና መንግስት፡፡ መንግስትን አለመደገፍ ትችላልህ መብትህም ነው በመንግስት አኩርፈህ አገርን ማስጠቃት ግን ከሞራልም አኳያ አያስኬድም፡፡ ደደብ ካልሆንክ ማለቴ ነው!
እንዲህ ስትንዘላዘል እርስበርስ ስትናጭ ነጮቹ አገርህን እንዴት እንሚያፈርሱ ደግሞ ላሳይህ፣
የሶሪያ ወድቀት እንደምሳሌ
ሶሪያውያን ስራ አጣን፣ ማለቂያ የሌለው ሙስና ጀርባችንን አጎበጠው፣ የፖለቲካም ነፃነት ተነፍገናል የሚሉ ጥያቄዎችን አስቀድመው ለተቃውሞ አደባባይ ተገኙ። እንግዲህ ይህ የሆነው እ.አ.አ በ2000 ሲሆን ወቅቱም Bashar al-Assad በሞት ያለፉትን አባታቸውን Hafez ተክተው አስተዳደሩን በተረከቡበት ጊዜ መሆኑን ልብ ልብ በል።
እንቀጥል፣ በ March 2011 አፋኝ ገዥዎችን በመቃወም በጎረቤት ሀገሮች በተነሳው አመጽ በመነሳሳት የደቡብ ምዕራባዊት የሶርያ ከተማ Deraa የዴሞክራሲ ደጋፊ ሰልፈኞች ወደ አመጽ ገቡ። ይሄን ጊዜ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለመበተን ከባድ የኃይል ርምጃ ወሰደልሃ! ነገር ግን ይህ እርምጃ ተቃዋሚዎችን ከአመጽ እንዲቆጠቡ ከማድረግ ይልቅ ጭራሽ መንግስት ስልጣን እንዲለቅላቸው የሚጠይቁ አመፆች በመላ አገሪቷ እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኖ አረፈው። ባባ እዚህ ጋር ነገር ተበላሸ። ሶሪያን ለ10 ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የከተተ ዜጎቿን ለሞትና ለስደት የዳረገ ጉዳይ ተፈጠረ።
ምንመሰለህ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ጠመንጃ አነሱ። መጀመሪያ ያሰቡት እራሳቸውን ለመከላከል ነበር ቆየት ብለው ግን በአካባቢዎቻቸው የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ለማባረር ተጠቀሙበት። Bashar al-Assad ይህን ሲመለከቱ “በውጭ የሚደገፉ ሽብርተኞች” የሚል ታርጋ ለጠፉባቸዋ። ምናቸው ሞኝ ነው በስልጣናቸው ኮ ነው የመጡባቸው! እንደሚጨፈልቋቸውም ቃል ገቡ። ብጥብጡ ተሰራጭቶ እርምጃው ተጠናከረ። በመጨረሻም ሶሪያ ወደማያባራው የእርስበእርስ ጦርነት ማዝገም ጀመረች።
22 ሚሊዮን ዜጎቿ ጦርነቱን ፍራቻ ስደት ወጡ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማፅያን ቡድኖች እዚህም እዛም ብቅ ብቅ አሉ። መላ ሶሪያን አሁን የእርስበርስ ጦርነት እሳት ሊለበልባት መሆኑ እርግጥ ሆነ። ጦርነቱ በማንና በማን እንደሆነ ለየ። መንግስትን በመቃዎም በወጡ ሶሪያዊያንና በBashar al-Assad መንግስት መካከል።
ይሄኔ እነ አይመሬ የውጭ ሀይሎች ገንዘብ፣ መሳሪያና ተዋጊዎችን በመላክ ከሁለቱም ጎራዎች ተሰለፉ። ተመልከት እንዴት ስራቸውን እንደሚሰሩ! ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ አበውህ The Islamic State (IS) ቡድንና al-Qaeda የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም የእርስበርስ ጦርነቱ ተቀላቀሉ። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ የሶሪያ ኩርዶች ግን ከBashar al-Assad ኃይሎች ጋር አለመዋጋታቸው ግጭቱን ሌላ መልክ አስያዘው። Russia፣ Iran፣ Lebanon’s Hezbollah፣ Iraq፣ Afghanistan፣ Yemen፣ ከBashar al-Assad ጎን ቆሙ። US፣ UK እና France የለዘብተኛ ተቃዋሚዎች አጋር ነን አሉ። Turkey ዋነኛ የተቃዋሚዎች ደጋፊ ሆና ቀረበች። እነ እከሌ ተሰባሰቡልሃ! ሶሪያ አበቃላት።
ቦንቦች ከሶሪያ ሰማይ ላይ በሁለቱም ወገኖች ዘነቡ። የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎች ሶሪያን ከመኖር ወደ አለመኖር አሸጋገሯት። ሁሉም ነገር እስከወዲያኛው ድብልቅልቁ ወጣ። እዚህ ጋር ጀምበር ለሶሪያዊያን እስከወዲያኛው ጠለቀች። The Syrian Observatory for Human Rights (SOHR) በ December 2020 ታዘብኩት እንዳለው 387,118 ሰዎች በሶሪያዊያን የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ህይወታቸው አልፋለች።
ከሟቾቹ መካካል 116,911 የሚሆኑት ደግሞ በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸው ሀዘኑን እጅግ መሪር ያደርገዋል። 205,300 ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ ይሙቱ ይዳኑ የት ይግቡ የሚታወቅ ነገር የለም። 88,000 ሰዎችም በመንግስት እስርቤቶች ተሰቃይተው እንደሞቱም ይታመናል። የUN children’s agency Unicef መረጃ ደግሞ 12,000 ህፃናት ሞተዋል አልያም ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ብሏል።
ባባ የሶሪያን የአፈራረስ ሂደት ለማሳያ ነገርኩህ እንጂ ሊቢያን እንዴት አድርገው እርስ በርስ አባልተው እንዳፈራረሷትም አስብ እንጂ፣ የሯንዳውን የዘር ፍጅት ፈረንሳይ እንዴት አድርጋ እንዳቀጣጠለችው አስታውስ (እስከአሁንም ድረስ ከደሙ ንፁህ ነን ቢሉም እንኳን)፣ ግብፅን ለማፍረስ ያደረጉት ሙከራም ትዝ ይበልህ…. ሌላም ሌላም፡፡
ስንጠቀልለው አንተ ቤት ያለው ሞት እኔም ቤት አለ፡፡ አንተ ቤት ያለውን አይነት የፍትህ ጥያቄ እኔም ቤት ነፍ አለ፡፡ ግን ለዚህ ሁሉ መፍትሄ ለማፈላለግ አገርን ማዳን ያንዣበብንን ተረድተን ባንድ መቆም አማራጭ ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡ ለእኛ ባትሆነን ለልጆቻችን የምትሆነን አገር ለማቆየት ስንል በአንድነታችን መደራደር የለብንም፡፡ ያለዚያ ግን በዚች ማዕቀብ ስታሾፍ ቆይተህ ኋላ ውሻ በቀደደው… ሲሆንብም ማንም የሚያስጥልህ የለም፡፡
መልካም ቀን ይሁንልህ!