>

ዜና ቲዩብ ወዴት ዘመም ዘመም! ቴዎድሮስ መዋዒ (ከአዲስ አበባ)

ዜና ቲዩብ ወዴት ዘመም ዘመም!

ቴዎድሮስ መዋዒ (ከአዲስ አበባ)


ትናንት ማታ በዜናቲዩብ ባለቤት የሰማሁትን ስድብ አዘል ሀተታ ማመን አልቻልኩም፡፡ የሚሳደበው ደግሞ ካሉን በጣም ውሱንና ጥቂት የግፉኣን ኢትዮጵያውያን መተንፈሻ ልሣናት አንዱ የሆነውን ኢትዮ360ንና ጋዜጠኞቹን በጠቅላላ ነው፡፡ በሾርኒ የነበረው ዘለፋ አሁን ለይቶለት ስም በመጥቀስ ሆኗል፡፡

የዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤት በኢትዮጵያዊነቱ አይታማም፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ቀደም ሲል በኢሳት ውስጥ ለሀገሩ ብዙ ለፍቷል፡፡ ከሀገር ከመውጣቱም በፊት በግል ጋዜጦች በተለያዩ የብዕር ስሞች ለዚህች ምስኪን ሀገር ደክሟል፤ ለእሥርና ለእንግልትም ተዳርጓል፡፡ የሰሞኑ ወደኦሮሙማው የአቢይ መንግሥት ጠጋ ጠጋ ማለት ማብዛቱ ግን ይህን ሁሉ ልፋት ድካሙን የሚያደበዝዝ ስለመሰለኝ ሰጋሁ፤ ፈራሁለትም፡፡ መካሪ ካለው በጊዜ እንዲስተካከል ቢጠቁሙት ክፋት የለውም፤ ይህ የአቢይ ዘመን ብዙ ሁነኛ ዜጎችን እያሳጣን ነውና አንዳች መፍትሔ ያሻዋል፡፡ ነገሩ “የአበራሽን ጠባሳ ያዬ …” እንዲሉ ዓይነት ነው፡፡

አቢይዝም በርካታ አንቱ የተባሉ ሰዎችን ከክብራቸው ማማ እያወረደ በኦርዌላዊው የጓድ ናፖሊዮን የዓሣማ ጋጣ ውስጥ ፈጥፍጧቸዋል፡፡ የዚህ አዚማም ሰውዬ ምሥጢር አልገባ ብሎኝ በጭንቀት አለሁ፡፡ “አንድ ቀን እኔንም አምላክ ፈርዶብኝ የዚህ መተታም ሰውዬ ሰለባ እሆን እንዴ?” ብዬም ለራሴ እሰጋለሁ፡፡

አለማየሁ ገ/ማርያምን የመሰለ ዓለም አቀፍ ምሁር፣ ዳኛቸው አሰፋን የመሰለ የማኅበራዊ ሣይንስ ሊቅ፣ ሙ.ጥ. ዲ. ዳንኤል ክብረትን የመሰለ ብሔራዊ የዕውቀትና የጥበብ ሙዚየም፣ ሲሣይ አጌናን የመሰለ የእውነተኛ ጋዜጠኝነት የውኃ ልክ፣ ብርቱካን ሚዴቅሣን የመሰለች የሰብኣዊ መብት ተሟጋችና ዕውቅ ፖለቲከኛ፣ አንዳርጋቸው ጽጌን የመሰለ የዕድሜ ልክ የነጻነት ታጋይ፣ … ከነበሩበት ሕዝባዊ ቤተሰብነት ነጥሎ ኩስ የነካው እንጨት ያደረገበትን ፕሮቴስታንታዊ መተት ከእግዚአብሔርና ምናልባትም ከወላጅ አባቱ ከሉሲፈር በስተቀር ማንም አያውቅም፡፡ እንኳንስ በወፌ ቆመች ደረጃ ድክ ድክ የሚልን ይህን የዜና ቲዩብ ልጅ ይቅርና እነዚህን ጎምቱ የሀገር ዋልታና ምሰሦዎች ገበያ ቢወጡ “ባሊህ” (‹ባለዚህ› ለማለት ነው በገጠርኛ ዘዬ) እንዳይባሉ ጥምብ እርኩሳቸውን አውጥቶታል – ሰባተኛው ንጉሣችን፡፡ ተዓምር ነው፡፡ 

በመሠረቱ የማንም አቦካቶ ወይም ጠበቃ አይደለሁም፡፡ የምኖርበት የድህነት ደረጃም ለማንም እንዳልወገንኩ በግልጽ ይናገራል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእውነተኛ ገቢየ እየተቸገርኩ የዕለት ከለት ሕይወቴን የምገፋ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡ ከማንም ምንም ስለማልቀበልም ለማንም ማጎብደድ ሳያስፈልገኝና ሳይኖርብኝም ኅሊናየ ባዘዘኝ እራመዳለሁ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የዜና ቲዩቡን ወንድሜን ጨምሮ (ልጄም ሊሆን ይችላል) ከፍ ሲል የጠቃቀስኳቸው ወንድሞቼ ከዚህ አዚማም ሰውዬ ምንዳ ወይም መቁሽሽ ተቀብለው ሀገራቸውን ይሸጣሉ ብዬ ማመን ይቸግረኛል – ገንዘብ የጫነች አህያ የማትደረማምሰው ምሽግ እንደሌለ ባምንምና ገንዘብንም ጠግቦ ከዚህች ምድር የተሰናበተ ሰው መኖሩን ክፉኛ ብጠራጠርም፡፡ የዜና ቲዩብ ባለቤት ከሀገር ውጭ በመኖሩ በተለይ በአማራው ማኅበረሰብና በአጠቃላይ ደግሞ ኦሮሙማን ለማስፋፋት በሚደረገው ሁለገብ ጥረት በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የዕለት ከዕለት ግፍና በደል አያውቅም ብዬ ማመን ይከብደኛል፡፡ በመተከል፣ በወለጋ፣ በትግራይ፣ በጉራፈርዳ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወሎ፣ በጥቅሉ በመላዋ ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ላይ የዘነበውን የመከራ ዶፍና ያን ተከትሎ የሚታየውን ማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ የሚሊዮኖችን ከመኖሪያ ሥፍቸውና ከእርሻቸው መፈናቀል፣  በማንነታቸው ሳቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ መታሰር፣ መጋዝ፣ መታፈን፤ የቢሮክራሲው የዕዝ ጠገግ አንድ ባንድ በአክራሪ ኦሮሞዎች መያዝ፣ ባንኩም በጀቱም ጦሩም አየር መንገዱም የፌዴራልና የክልል መሥሪያ ቤቱም ሁሉ ከወያኔ ዘመን ባልተናነሰ ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ በአንድ ነገድ መጠቃለሉን ዜና ቲዩብ ቢክደው እውነት አትክደውምና ወደፊት በታሪክ መዝገብ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ኦሮሙማዊ ነውርና ወንጀል ለመሸፋፈን በነዜና ቲዩብ የተሄደው ርቀት ከማስተዛዘብም የሚያልፍ ነው፡፡ ዐይን የተፈጠረው ለምንና ለመቼስ ነው?

ይህን ከፍ ሲል የተጠቀሰውን ኦሮሙማዊ ወንጀልና የብልግና ተግባር እየተከታተሉ በመረጃና በማስረጃ በተደገፈ ሁኔታ ማጋለጥ ጥፋቱ እምን ላይ ነው? በእውኑ እነዚህን ታታሪ ልጆች ባንዳና የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ቅጥረኛ እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ምን ሊባል ይችላል? እንዲህ ማለት ያለበት ኦነግ-ሸኔ ብቻ ነው፡፡

ይህንን ስል የተሰደበው ሚዲያና የተዘለፉት ጋዜጠኞች አይሳሳቱም ወይ አያጠፉም ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ መሳሳትና ማጥፋት ሰውኛ ነው፡፡ የማይሳሳት ሰው፣ ሰው አይደለም – ምናባዊ መልአክ እንጂ፡፡ ሲሳሳት ግን “ሆን ብሎ ነው ወይንስ ሳያውቅ፣ ሰውን ለመጉዳት በሤራና በተንኮል ነው ወይንስ መረጃው ኖሮት ማስረጃ ሳይኖረው በቅንነት የሠራው ጥፋት ነው” ብሎ ማጣራትና ስህተት ተፈጥሮ ሲገኝ በጨዋ ደምብ በመወቃቀስ ማስተካከል ይገባል እንጂ በአንድ ጎራ እንደሚገኙ የሚታመኑ ሰዎች በዚህ ደረጃ መወራረፍ ብስለትን አያሳይም፡፡ መሳደብ ወይም መዘላለፍ ደግሞ የደካማ አስተሳሰብ ውሻል ወይም ወሽመጥ እንጂ የመልካም ሰዎች መገለጫ አይደለም (ውሻልን ለማወቅ አናጢን ጠይቅ፤ ወሽመጥን ለማወቅ ደግሞ ልብስ ሰፊን ጠይቅ)፡፡ ሰዎች የያዙት ሃሳብ እንደማያሸንፍ ሲገምቱ ወይም በክርክር ማሸነፍ ሲያቅታቸው እንደፈረደበት የየጁ ደብተራ ቅኔንና ቀረርቶን በማዛነቅ ታዛቢን ሳይቀር ማደናገር ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡

ዝምታ አንዳንዴ በርግጥም ወርቅ ነው፡፡ በአንድ የትግል ጎራ ውስጥ የተሰለፉ ሰዎች መወቃቀስ ካለባቸው ሳይፈራረጁና ሳይዛዛቱ በጨዋነት ይሁን፡፡ ለማንም በማይጠቅም ይልቁንም ጠላትን በሚረዳ መልኩ ቢናቸፉ የትግሉን ውጤት ባይለውጡትም የትግሉን ዕድሜ ያራዝሙታልና ሰከን ማለቱ ይበጃል፡፡ በስድብና በዘለፋ ዲግሪ የለም – ሀገርም በዚህ አይቀናም፡፡ በስድብና በዘለፋ ባለጌነትንና ሥራየቤታዊ ስብዕናን ከመግለጽ ባሻጋር ብልኅነትንና አስተዋይነትን እንዲሁም የወደፊት ተመራጭነትንም አያመለክትም፡፡ ብዙ መማርንና ማወቅን በስድብ ግዝፈትና በማስቀየም ብልጫ ማሳየት አንችልም – በትግስተኛነትና በሆደ ሰፊነት እንጂ፡፡ ብዙ የተሳደበ ቢሾምና ቢሸለም ኖሮ ጌታቸው ረዳና በረከት ስምዖን ይሄኔ እስር ቤትና ጉድባ ውስጥ ሳይሆን በኦክስፎርድና በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን በሆኑ ነበር፡፡ በእውነት አልታደልንም፡፡ ምሁሩ ምሁርነቱን አጉልቶ ማሳየት የሚፈልገው በምርምርና ጥናት ሥራው ሳይሆን በመጀነንና በጉራ እንዲሁም በክት ስድቦቹ ሰውን በማዋረድ ነው፤ የመንግሥት ባለሥልጣኑም፤ የዕድር ሰብሳቢውም፤ የሰበካ ጉባኤ ሊቀ መንበሩም፣ የሀገር መሪውም …. እንደዚሁ ናቸው፡፡ ጥበብንና አስተዋይነትን የሚያሳዩ ሰዎች እየጠፉ ነው፤ ቢኖሩም መድረኩ ለነሱ ክፍት የማይሆንና እነሱን የሚጠየፍ ነው፡፡ ለማንኛውም ኢትዮ30ዎችም ከዚህ ደብዳቤየ አንዳች ግንዛቤ በመጨበጥ ሰውን ስትተቹ ከአካላዊ እንቅስቃሴያችሁ ጀምሮ ጨዋነትን አሳዩ፤ ንቀትንና ትዕቢትን ከኔም በላይ አዋቂነት ላሣር ማለትን ገንዘባችሁ ከማድረግ ተቆጠቡ፡፡ በዚህች ምድር አንድም የሚያኮራ ነገር የለም፡፡ ራቁታችንን መጣን፤ ራቁታችንን እንሄዳለን፡፡ ሁሉ ነገር እንደጥላ አላፊ ጠፊ ነውና እንከባበር፡፡ መከባበር ብዙ ወጪ የለውም፤ አለመከባበር ግን ብዙ ወጪ አለው – ይሄውና እኔን ሳይቀር ያለ እንቅልፍ አሳድሮ አሁንም ኮምፒውተሬ ላይ ጎልቶኛል – የወዳጆቼ አለመከባበር ያመጣብኝ ጣጣ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ ተከባብረን ሃሳቦችን ብቻ በማጋጨት ልክ እንደኤሌክትሪክ ለሁሉም የሚጠቅም የዕውቀት ብርሃን እንፍጠር፡፡ እንደሸምበቆ ወደላይ እንጂ እንደካሮት ወደታች ማደጉን እንተው፡፡ አልጠቀመንም፤ አይጠቅመንምም፡፡ ከታናናሾቻችንም እንማር፤ ከየትም መማር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡

ወታደር የነበረ፣ በትምህርት እምብዝም ያልገፋ፣ ሀገር ቂጥ ጂንካ አካባቢ የሚኖር ታሪኩ ጋንኪሲ የሚባል ከትምህርትም፣ ከገንዘብም፣ ከዝናም፣ ከአንጻራዊ ሥልጣኔም… የራቀ ተራ ዜጋ ይህን ሁሉ “የተማረና የተመራመረ” ኢትዮጵያዊ ስድስት ደቂቃ በማትፈጅ ሙዚቃው በቂጡ ቁጭ አደረገው! ዶክተር የለ ፕሮፌሰር፣ ልሂቅ የለ ደቂቅ፣ ጠ/ሚንስትር የለ ፕሬዝደንት፣ ኢማም የለ ፓትርያርክ፣ ዲያቆን የለ ቀሲስ፣ ሀብታም የለ ድሃ፣ ታዋቂነት የለ ተሰሚነት … ሁሉንም ባዶውን አስቀረው፡፡ ሁሉንም አፉን አስያዘ፡፡

ምን ብሎ?

በዲሽታ ጊና ዘፈኑ “እኔና አዳም አንድ አባቴ፤ አንቺና ሔዋን አንድ አጥንቴ፤ ታዲያ – ይዤ የመጣሁት ይዤ እምመለሰው፤ አንድም ነገር የለም፤ ታዲያ – ምርጡ ዘር – እንክርዳድ – ማነው ያለው፤ የምድር ሥራ እንጂ እሚያስጠይቅ፤ በሱ ፊት ስንቆም ዘር አያጸድቅም…” ብሎ፡፡ ፈጣሪ ፊቱን በቶሎ ይመልስልን፡፡

Filed in: Amharic