>
5:26 pm - Saturday September 17, 8011

ነፃነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ጉባዔተኞች...!!! (እውነተኛ ታሪክ - አሰፋ ሀይሉ)

ነፃነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ጉባዔተኞች…!!!

(እውነተኛ ታሪክ) ክፍል ፩
አሰፋ ሀይሉ

« A tavern is a place where madness is sold by the bottle. »
       — Jonathan Swift
እስማማለሁ፡፡ «ቡና ቤቶች እብደት በጠርሙስ የሚሸጥባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡» ግን «አቤት! እብደት እንዴት ደስ ይላል?!» የሚለውን ትያትረኛም አውቃለሁ፡፡ ሰው ሁሉ ፈርቶ በጤነኝነት ሳጥን ውስጥ ተከርችሞ በሚኖርባት ዓለም ላይ፣ አንዳንዴ እብደትን መግዛት፣ እና ለተወሰነ አፍታ ነጻነትን መጎናፀፍ እንዴት ደስ ያሰኛል!? ይህ የነጻነት ግሮሠሪ ታሪክ ነው፡፡ 
ከለውጡ ቀደም ብሎ ነው፡፡ እንደ ቀልድ ሶስት ዓመት አለፈ፡፡ አጭር ጠረጴዛ ከበን ተሰይመናል፡፡ በወዳጃችን ነፃነት ግሮሰሪ ውስጥ፡፡ ምሽት ላይ ነው፡፡ ውጪውን ሰልፈኛ አጥለቅልቆታል፡፡ የታክሲ ሰልፈኛ፡፡ የግሮሰሪዋ ሙዚቃ ከአንዱ ወዳንዱ ሲሸጋገር በመሀል ባለችው ጋፕ የሚሰሙት የታክሲ ረዳቶች ድምጾች ናቸው፡፡
ችሎት መዳኒያለም! ዊንጌት መዳኔዓለም! ተክላይማኖት መርካቶ! አወሊያ ላፍቶ! መሣለሚያ አቶቢስተራ! ሜክሲኮ ቄራ! ያዲሳባ ሰፈሮች እየተጠሩ፣ መንገደኛው በምሽት አስፋልቱ ዳር ተሰልፎ፡፡ መንገደኛው እየተጋፋ፡፡ አቤት ያለው ትርምስ፡፡ በሰዓታት ዳምኖ፣ በሰዓታት የሚተንን፣ ሕዘባዊ ማዕበል፡፡ ዋ አዲሳበባ፡፡ ዋ ያዲሳባ ምሽቶች፡፡
አንድ ሁለት እያልን ነው፡፡ ከውስጥ ወደ ውጪ እያየን፡፡ ወጪ ወራጁን፡፡ የምሽት ሰልፈኛውን፡፡ የታክሲ ግፊያውን፡፡ እያየን፡፡ መገፋፋቱ ጋብ እስኪል፡፡ ትጠጣለህ፡፡ የእግረኛው ሰልፍ እስኪሳሳ፡፡ ትጠጣለህ፡፡ ጎዳናው እስኪለቀቅ፡፡ ትጠጣለህ፡፡ የመጠጣት ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡
«ሰልፉን አየኸው? መጨረሻውኮ አይታይም! ማደያው ጋ ደርሷል!» ትላለህ፡፡ አቦል፣ ቶና፣ በረካ፣ ዬን ሳላሣርግ አልወጣም የምትል ቅድመ እወጃህ ናት፡፡ መቼም የታክሲ ሰልፈኛ ቤንዚን ማደያ ገባ ብለህ፣ ተከትለኸው አትገባም፡፡ መኪና አይደለህም፡፡ ደራፍት የሚያምርህ ሰው ነህ፡፡ እና ምን ጥያቄ አለው? ቀኝ-ኋላ-ዙር ብለህ፣ ወደ ነፃነት ግሮሰሪህ ትገባለህ እንጂ፡፡ አንድ ጃምቦ! ፉጄ (ፉጀጋ)! እዚህ ጋ! ድገመኝ አቦ? እንደወረደ! የመረረው ቀን «እንጥልህን ያውርደው!» ይልሃል፡፡
በነጻነት ግሮሰሪ፡፡ አንድ ሁለት እያልን ነው፡፡ ሳቃችን ደምቋል፡፡ በመሐል፣ በአጉል ሰዓት፣ አንድ ትህትና ያልተለየው (ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ያልፈለግኩት)፣ አንድ የቀድሞ የህወኀት ታጋይ ገባ፡፡ በሰልፉ አሳቦ፡፡ የባለግሮሰሪው ወዳጃችን የልብ ወዳጅ ነው፡፡ የመዲናችን ሹምም ነው፡፡
አንድ ቀን ከዚህ ሰው ጋር እያወራን ‹‹ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጂራን እኔ ነኝ ለካድሬነት ሪክሩት ያደረግኩት (የመለመልኩት)›› ብሎኛል፡፡ ለወትሮው ስለራሱ መናገር የማይወድ ሰው ነው፡፡ መቼም በግሮሰሪያችን የማይሰማ ጉድ የለም፡፡ ኤርምያስ በህወኀት ሰዎች ለካድሬነት የመመልመሉ ነገር አልዋጥልህ አለኝ፡፡
ኤርምያስ በመለስ ቱሩፋቶች… መጽሐፉ ላይ የአውራው ፓርቲ አባል የሆነው ገና በ20 ዓመቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ መሆኑን እንደጠቀሰ አስታውሳለሁ፡፡ በእርግጥ የካድሬነት ሥራውን ያሟሸው በአዲሳባ መስተዳድር የዞን መዋቅሮች ውስጥ መሆኑንም ጽፏል ስለራሱ፡፡ ይሄም ጎኔ የተቀመጠ የህወኀቱ ወዳጃችን የአዲሳባ ሹም ነው ብያለሁ፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዬ አለፍኩት፡፡
አንድን ወጣት ለካድሬነት መመልመል ትልቅ ጀብዱ አይሆንም፡፡ ግን ከሀገር ወጥቶ ህወኀትን ክዶ ለዓለም ያጋለጠውን የቀድሞ ካድሬ «እኔ ነኝ የመለመልኩት» ብሎ ማመን – ለአንድ የህወኀት ሹም – ትልቅ አቀበት እንደሚሆንበት አሰብኩ፡፡ እና አመንኩት፡፡ አሁን የቸገረኝ ግን የኤርምያስ ወሬ አይደለም፡፡ ካልጠፋ ጨዋታ፣ ካልጠፋ ቀን፣ ካልጠፋ ሰዓት፣ ይህን በመሰለ የደራ ጨዋታችን መሐል፣ ምን ፍርጃ አንቀዥቅዦ ጠረጴዛችን መሐል ሰነቀረው?
አንዳንዴ እንዲህ ነው – ግሮሠሪ፡፡ ሲያመጣብህ። «አላለልኝም እችለዋለሁ» ነው ያለው ቴዲ አፍሮ? ጠረጴዛ ግንብ አይደል መቼስ፡፡ አጥር አታጥርበትም፡፡ የመግቢያ ቪዛ አትጠይቅበትም፡፡ ግሮሠሪ ጥቁሩንም ቀዩንም እንግዳ ይዞብህ ይመጣል፡፡ ያለህ አማራጭ «ሲመጡ መቀበል ሲሄዱ መሸኘት» ብቻ፡፡
ጨዋታ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ትቀበላለህ፡፡ ከኤርምያስ ለገሰ እስከ ኤርምያስ አመልጋ፣ ወይም ከደራሲ አለማየሁ ገላጋይ እስከ ሚ/ር አለማየሁ ተገኑ – ጨዋታ ሆኖ ከመጣ መቀበል ነው፡፡ ጨዋታን ያመጣዋል፡፡ ጨዋታችን ርዕስ አይመርጥም፡፡ ጂኦግራፊ አይገድበውም፡፡ ዘር፣ ዘመን፣ ጾታ፣ ቀለም፣ ዕድሜ፣ ክልል፣ አህጉር፣ ባህር ውቅያኖስ አይገድበውም፡፡
በዚህች ዓለም ላይ ያለ ርዕስ ሲያልቅብን ወደ ሰማያዊው ዓለም እንሸጋገራለን፡፡ የአቡኑ ቢያልቅብን ስለ ኡስታዙ፣ የአሁኑ ቢያልቅብን ስለ መጪው እያነሳን እንፈጫለን፡፡ ሁሉም ነገር እየተነሳ በሀሳቦች ሙቀጫ ይወቀጣል፡፡ ያቺን ጠረጴዛችንን፣ አሁን ሳስታውሳት፣ ልቤ በናፍቆት ይዋልላል፡፡
ያን ምሽት ጨዋታው ሞቅ እያለ ሄዶ ወደ ለመድነው የፖለቲካ ርዕስ ተሸጋገሮ ነበር፡፡ ወሬው፣ ፍተላው፣ ነቆራው፣ ሰበር ዜናው፣ ትንተናው፣ ትንበያው፣ ቀልዱ፣ ሽሙጡ ሁሉ እየተነሳ በሳቅም በምሬትም ይብጠለጠላል፡፡ አንዳንዴ ክርክራችን ሞቅ ሲል፣ ጉጉ እድምተኞችን ይስብብናል፡፡ አንፈልገውም፡፡ ግን አይቀርልንም፡፡ ወደኛ ጠረጴዛ ሀሳብ ለመቃረምና ከእኛ ጋር አብሮ ለመለፋለፍ ተወስውሶ የሚመጣው አልፎ ሂያጅ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም፡፡
አንዳንዴ ከውጭ ግፊያ ጠልተን፣ ውስጥ ደግሞ ሌላ ግፊያ ሲሆንብን ትክት ይለናል፡፡ እና ባለመናገር አድማ፣ ጉጉ ታዳሚዎችን ኩም አድርገን፣ በክብር እንሸኛለን፡፡ አሁን ግን ጠረጴዛችንን የተቀላቀለው የህወኀት ሰው በአድማ እንዳንገፋው ከበደን፡፡ የባለግሮሰሪው ወዳጃችን የልብ ወዳጅ ሆነብን፡፡ ትህትና የተሞላው ፀባዩም ያዘን፡፡ እና አማራጭ አልነበረንም፡፡ እርስበርስ ተያይተን፣ ወደ ጨዋታችን ቀላቀልነው፡፡
ያቺ ጠረጴዛ ልዩ ነበረች፡፡ አንዳንዴ ትንሽዬ ፓርላማ የምትመስልበትም ጊዜ አለ፡፡ ልዩነቱ የፓርላማው ጉባዔ የሚጠራው ቀን ላይ ነው፡፡ የእኛ በምሽት የምትጠራ ጉባዔ ነች፡፡ የፓርላማው ጉባዔተኞች ስለ ሀገር የሚወያዩት እየተከፈላቸው ነው፡፡ የጠረጴዛዋ ጉባዔተኞች ግን ያለንን ከየኪሳችን ፈጥፍጠን ነው ስለ ሀገር የምንወያየው፡፡
ፓርላማውን የሚቆጣጠረው ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ የእኛ ጠረጴዛ ግን በእኛ በተቃዋሚዎች ብዙሃን  ቁጥጥር ሥር የዋለች ነች፡፡ የገዢው ፓርቲ ተስተናጋጆችም ግን ባንድ ማዕድ ይቀመጣሉ፡፡ በጉባዔተኞቿ መካከል፡፡ በአጭሯ ጠረጴዛችን፡፡ በፍጹም የወዳጅነት መንፈስ፡፡
ብዙ ጊዜ ለየርዕሱና ለየምሽቱ ተስማሚ የሆነ አንድ የራሳችን በጎፈቃደኛ አፈጉባዔም ይሰየምላታል ለጠረጴዛችን፡፡ ጨዋታው ሞቆ ሁሉም ላውራ ባይ ሲሆን፡፡ አንድ ልዩ ነገሯ፣ በእኛ ጠረጴዛ፣ ገዢው ፓርቲ ‹‹የተሰጠዎት ሶስት ደቂቃ አልቋል›› እያለ ተቃዋሚዎችን የሚያሸማቅቅበት ዕድል አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የገዢውን ጠጪዎች የማሸማቀቅ መብት ያለን እኛ ባለጠረጴዛዎቹ ተቃዋሚዎች ነን፡፡ ምክንያቱም ይሄ የቀኑ ፓርላማ አይደለም፡፡ ይህ የምሽቱ ነጻነት ግሮሰሪ ነው፡፡ ሞቅ ያለ ቺርስ! ኧረ ብርጭቆው እንዳይሰበር፣ በህግ አምላክ!?
እግር ጥሎት ክብ ጠረጴዛችንን የተቀላቀለውን ይህን የአውራውን ፓርቲ ሰውም – ቆይ እድሉ አልተሰጠህም፣ ቆይ ያንተ ተራ አይደለም፣ ቆይ እሱ ሃሳቡን ይጨርስ፣ ወዘተ. እያልን ብናሳቅቀውም – ተማርሮ ጉባዔያችንን ረግጦ አልወጣም፡፡ በፀባይ ተረጋግቶ፣ በገገግታ ተሞልቶ፣ የተነሳው የፖለቲካ ርዕስ ሲወቀጥም፣ ሲደነቅም፣ ደስ ብሎት መጫወቱን ቀጥሏል፡፡ ተያየን፡፡ ተመቸን፡፡ አሁንም ቺርስ!
የማይመቸን ሰው እንዴት ያለ ሰው ነው? ያን ለመናገር ይሄን የተመቸንን ሰው ወሬ ማቋረጥ ሊኖርብኝ ነው፡፡ ይሁን አቋርጠዋለሁ፡፡ የማይመቸን ዓይነት ሰው በአንድ ኮሎኔል (ኮማንደር) አምሳል ስላለ – ወደ እርሱ ምሳሌዬ ልሂድ፡፡ የጀመርኩትን ወሬ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
አንድ ቀን አንዱ የአውራው (የወያኔ-ኢህአዴግ) የቆረበ ደጋፊ የሆነ ኮሎኔል ጠረጴዛችንን ተቀላቅሎ ነበር፡፡ ኮሎኔሉ ሳይቸግረው እንደ ቀልድ ዘው ብሎ ወደ ጠረጴዛችን ጉባዔተኞች ተቀላቀለና ለምን ፓርቲዬ ተነካብኝ ብሎ እንደ ማንቸርስተር ዩናይትድ ክለብ – ባልታሰበ ፍጥነት – ከዲፌንስ ወደ ካውንተር-አታክ ገባ፡፡ ወደ ንጹህ ነቆራ፡፡
ነቆራ ግን አልበጀውም፡፡ ሌላ ውርጅብኝን አስከተለ፡፡ በያቅጣጫው ፀረ-ወያኔ የሀሳብ ሞርታር ተራ በተራ ወረደበት፡፡ ሀሳብ የሚቋቋም መስሎን፡፡ ደስ ይለናል ነቆራ፡፡ ሀሳብ እስከሆነ ድረስ፡፡ አግኝተን ነው? ነቆራው በእርጋታ ቀጠለ፡፡ በነቆራ ተጋግሎ በቀጠለው ጨዋታችን መሐል ግን፣ ኮሎኔሉ ከመጠን በላይ ጋለና፣ አቅሉን ሳተ፡፡
የተከተለው ነገር በህይወታችን ከገጠመን አስቀያሚ ገጠመኝ ሁሉ የባሰው ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ኮሎኔሉ ግልፍ ብሎት ከመቀመጫው ተነስቶ በሌላኛው ጓደኛችን (በጠረጴዛዋ ቋሚ ጉባዔተኛችን) ላይ ሽጉጥ መዝዞ ግንባሩ ላይ ተኩሼ ካልደፋሁት አለ፡፡ የግሮሰሪዋን ባለቤት ጨምሮ በስንት ገላጋይ ብርታት ተገላግሎ አፈሙዙን መለሰ፡፡
አንድ ብዙ ጊዜ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ መዋኘት የማይችል ሰው፣ ዘው ብሎ ባህር ውስጥ አይገባም መቼም፡፡ ሀሳብን መቋቋም የማይችል ሰው፣ የሀሳቦች ባህር ውስጥ ዘሎ ለመግባት፣ ምን ያንቀዠቅዠዋል? መልስ የለም፡፡ አንዱ ወዳጃችን ይሄን ስትጠይቀው «ሽፍደት ነዋ!» ይላል፡፡ በንዴት ባወጣው ቃል በሳቅ እንፈርሳለን፡፡
አፈጉባዔው «ቁሌት» በሚለው ቃል ይስተካከል፣ የተጠቀምከው ቃል ጠረጴዛውን አይመጥንም ይላል፡፡ እሺ አልደግመውም፡፡ ግን በፈለገው ቃል ቢጠራም፣ ሰዉን አንቀዥቅዦ የሚያመጣብን ምክንያት ያ ነው! – ጉባዔተኛው በፈገግታ ስምምነቱን ይገልጻል፡፡ እና ሰው መቼም ወሬ አያርመውም፡፡ ሌላ ቀን ደሞ ሌላው አልፎ ሂያጅ በወሬያችን ቁሌት ተስቦ ከች ይላል፡፡ እንተያይና እንስቃለን፡፡ «ተረኛ ሻፋ… »! ይቅርታ ለካ ቃሉ ጠረጴዛውን አይመጥንም! ቁሌትም ግን ከነንዴቱ አይገልጸውም! ኤጭ! ምን ነበረበት ቃሉ ጠረጴዛውን ቢመጥን?
ሌላ ቀን ከባድ ይቅርታ ቀረበልን፡፡ የጠረጴዛዋ ጉባዔተኛም በይቅርታው ጉዳይ በዝግ መከረበት፡፡ ከሰው ስህተት አይጠፋም፡፡ ነቆራን አለመቋቋሙም አሳዝኖናል፡፡ ገና ነውና፡፡ ኮሎኔሉ ይቅርታ ተደረገለት፡፡ ግን እንደ ሆልስቲንና ፍሪዥያን ድርቅን የመቋቋም ችሎታው አነስተኛ ሆኖ ስለተገኘ፣ በሀገር በቀሎቹ በከረዩና ዋንኬ፣ በቦረናና ሐረር ሰንጋዎች መሐል እንዳይቀላቀል ማዕቀብ ተጣለበት፡፡ ለሠላምታ ካልሆነ በቀር፣ ወደ ጠረጴዛችን ሁለተኛ ዝር እንዳይል፡፡ የፈረደበት የነጻነት ግሮሰሪ ባለቤት ውሳኔያችንን አሳወቀው፡፡ እና ለጥቂት ወራት ከግሮሰሪዋ ጠፋ፡፡
ኮሎኔሉ ትዝ ሲለን፣ እንደወጣች ቀረች የሚለውን የቆየ ድርሰት እናስታውስና የት ይሆን ብን ብሎ የጠፋው እንላለን፡፡ ከእኛ ጋር ባይስማማም፣ የግድ ግሮሰሪዋን ጥሎ ይሰደድ አንልም ሰውን፡፡ ደግነቱ – ደንበኞቼን አባራችሁ ኪሣራ ላይ ልትጥሉኝ ነው – አይልም ባለግሮሰሪውም ወዳጃችን፡፡ የሚወጣው ቃል አንድ ብቻ ነው፡፡ ገላገላችሁኝ፣ እግዜር ይስጣችሁ! የሚል፡፡
ችግሩ ግን በእንደ ወጣች ቀረች ድርሰታችን ብዙም ሳንገፋበት፣ በአንዱ ምሽት ላይ፣ እናንተ ግን እንዲህ ስጠፋ የት ወድቆ ቀረ ብላችሁ እንኳ አትፈልጉም? ሰው አጥፍቼያለሁ ብሎ ይቅርታ ከጠየቀ እኮ ‹‹ይቅርታ›› ይሰጠዋል፡፡ ሞቅታ አሳስቶኝ ነው፡፡ በጣም ሲፀፅተኝ ነው የከረመው፡፡ አፍሬ ነው የጠፋሁት፡፡ እያንዳንዳችሁን አስቀይሜያለሁ፡፡ ከልብ ይቅርታ አድርጉልኝ፡፡ በህይወቴ የማላደርገውን ነገር ነው ያደረግኩት፡፡ ብሎ ጉልበታችን ላይ ሊወድቅ አጎነበሰ፡፡
መቼም ትህትናን የተላበሰ ይቅርታ፣ የደደረ ልብን ሁሉ ያቀልጣል፡፡ እንኳን የድራፍት ሞቅታ ተጨምሮበት! ይቅርታ ተደረገለት፡፡ እሱም ወደ ጠረጴዛችን ልቀላቀል አላለም፡፡ ሌላ ጠረጴዛ ላይ የግሮሰሪዋ ባለቤት ብቅ እያለ እያጫወተው አንድ ሁለት ይል ጀመር፡፡ አንዳንዴ ሞቅታ ጥሩ ነው፡፡ የነጻነት ግሮሰሪ ያላየችው ነገር የለም፡፡ ይሄም በታሪኳ ተመዝግቦላታል፡፡ ሽጉጥ መዛዡና የተመዘዘበት እርቀ ሠላም አውርደው በሠላም ጠጥተውባታል፡፡
አንዳንዴም በነሸጣቸው ቀን ከዚህና ከዚያ ጠረጴዛ ላይ ብድግ ብድግ ብለው፣ በሙዚቃው ምት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ አብረው ይወዛወዛሉ፡፡ አንዳንዴ ደሞ ያሰኘው ቀን ጓደኛችን እንዲህ ይላል፡- ገላጋይ ባይገባ ኖሮ እኮ ግንባሬን ሊለኝ ነበር፣ ልጆቼን እንዳላሳድግ፣ ይሄ የተረገመ ወያኔ! በሳቅ እንሞታለን፡፡ ይቅርታ ማድረግ እና መርሳት ለካ ይለያያሉ፡፡ ይቅርታ አድርጎ መርሳት፡፡ Forgive and forget፡፡ ሁለቱንም ባንዴ ማሳካት ከባድ እንደሆነ አይቼያለሁ፡፡ በነፃነት ግሮሰሪ፡፡
በል-በል ሲለው ኮሎኔሉ ብዙ ጊዜ ከሩቅ ሆኖ ቢራ ልጋብዛችሁ ይላል፡፡ በአስተናጋጅ በኩል፡፡ ወይ ራሱ መጥቶ፡፡ እሺ ብለነው አናውቅም፡፡ ለመግባባት፣ እና የጠረጴዛችን አባል ለመሆን ብዙ ጣረ፡፡ አልተሳካለትም፡፡ በመጨረሻ ሁላችንንም ዘጋን፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
አንድ ቀን እኛ እየወጣን፣ ኮሎኔሉ ደሞ ሲገባ በሩ ላይ ተገናኘን፡፡ እና አንድ እጃችንን ለሠላምታ ዘረጋንለት፡፡ ተናግሮት በማያውቀው ጥርት ባለ እንግሊዝኛ ሠላምታ መሰጣጣት እንደማያስፈልገን ነግሮን ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ሳቃችንን አፍነን ወጣን፡፡ እና አስፋልት ለአስፋልት እስኪበቃን ሳቅን፡፡ ለካ ያልተማረ ታጋይ ወታደር ነው ብላችሁ ከሆነ የናቃችሁኝ፣ ይኸው እወቁኝ እንግዲህ፣ እንዲህ ነኝ፣ እያለን ነው፡፡ ‹‹የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው፣ በእንግሊዝ አናግሪያቸው›› እያለን፡፡
ይህ ሰው የዋህ ሰው ነው፡፡ እላለሁ ስለ ኮሎኔሉ ሳስብ፡፡ ለቀረበው ግልጽና መልካም ምላሽ ያለው ሰው እንደሆነ መካደ አይቻልም፡፡ ችግሩ መተዳደሪያ ሥራውና የታጋይ ዘመን በጦርነት ተሞክሮ ውስጥ ያለፈ ጠንካራ (ወይም ደረቅ) ሰብዕናው፣ ከግልፍቱ ጋር ታክሎ፣ አይጠጌ አድርጎታል፡፡ ያ ኮሎኔል ከጠረጴዛችን አባልነት የከለከለው፣ የአንድ ቀን ሽጉጥ መዘዛ ሳይሆን፣ የብዙ ነገሮች ጥርቅም መሆኑ በፍጹም አልገባውም፡፡
ሌላ ቀን ያደረገውን ለምሳሌ ልጥቀሰው፡፡ ድንገት ወደ ግሮሰሪዋ ዘው ብሎ ገባና፣ የተከበረችውን ጠረጴዛችንን ሳያስፈቅድ ወንበር ስቦ፣ ፊታችን ተገሸረ፡፡ አልገረመንም፡፡ ድካም ወይም ዝለት Courtesyዩን አጥፍቶበት ይሆናል ብለን፡፡ የመጀመሪያዋን ቀዝቃዛ ቢራ አስመጥቶ ጭልጥ እንዳረጋት ግን በእፎይታ እየፈገገ እንዲህ አለን፡- ‹‹ዛሬ ምን ሥሰራ እንደዋልኩ ታውቃላችሁ?›› አለን፡፡ ዝም፡፡
ማንንም ሳይጠብቅ እንዲህ አለን፡- ‹‹..ዶ/ር መረራን ኢንተሮጌት ሳደርግ ነው የዋልኩት!››፡፡ ካጎነበስንበት ቀና ብለን አየነው ሁላችንም፡፡ የዚያን ሰሞን ዶ/ር መረራ ጉዲና የወያኔን ክልከላ ጥሶ በውጪ ሀገር ከተቃዋሚዎች ጋር አብረህ ተገኝተሃል ተብሎ ሀገር ውስጥ እንደገባ ወደ ማዕከላዊ ወስደው አጉረውት ነበር፡፡ እና እርስ በርስ ተያየን፡፡
ሁላችንም ከተያየን የሆነ ነገር ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ከንግግር የበለጠ እንግባባለን፡፡ ከዚያች ቃል በኋላ ጠረጴዛዋን አዚም አጠላባት፡፡ የጀመረውን ድራፍት የጨረሰ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ሂሳቡን ከፍሎ ውልቅ፡፡ ‹‹አሆ ለኔ፣ ጀግና ነህ ለኔ…!›› የሚለውን ዘፈን በእልልታ አጅበን እንድንጨፍርለት ጠብቆን ይሆን? እላለሁ አንዳንዴ እያሰብኩት፡፡ ጠብቆን ከነበረ ይገርመኛል፡፡
ወይስ ‹‹ሲለላ›› መሆኑ ነው? Reaction-ናችንን ለማጥናት? ያም ቢሆን፣ ከመሀላችን ማን መሰለልን ይፈራል? ተሰልለን አልቀን የለ እንዴ፡፡ ምን የሚሰለል ነገር አለንና?! ወይ ለከፋ ይሆናል እንጂ! በየሱስ ስም! በወሳኝ ሰዓት መጥቶ፣ በአጉል ወሬው! የሞቀ ጠረጴዛችንን ደወከው!
አንድ የምወዳቸው የሰፈሬ የኔ-ብጤ አሉ፡፡ በጧት ማልደው በንግድ ባንኩ ትይዩ፣ የታክሲ ሰልፉ የሚጀመርበት አካባቢ ይቀመጣሉ፡፡ ማንንም አይወተውቱም፡፡ ስትመጸውታቸው ግን «አውሎ ያግባህ ልጄ!» ነው ምርቃታቸው፡፡ ከቤቱ ወጥቶ እስኪመለስ – መነጀስን፣ መደወክን፣ መሸቀብን የሚወድ ማንም የለም፡፡ በዚህ ነጃሳዎች በሞሉበት ዘመን፣ ሠላም አውሎ ያግባህ መባል ትልቅ ምርቃት ነው፡፡ ሰልፈኛው ያለውን ይሰጣቸዋል፡፡ እሳቸውም ሲመርቁት ያረፍዳሉ፡፡ የጎደለህን ይሰጡሃል፡፡ የጎደላቸውን ትሰጣቸዋለህ፡፡
አንዳንዴ ደስ ይበልህ፡፡ ህይወት ጎደሎ መሆኗ፡፡ ብዙ ጊዜ የጎደለች ህይወትህ ምሉዕ የምትሆነው በትልቁ የሎተሪ ዕጣ አማካይነት አይደለም፡፡ በእንደዚህ ያሉት በየሰዓቱ በሚያጋጥሙህ ሽርፍራፊ የማስተዛዘኛ ገጸበረከቶች ውስጥ ስትመላለስ ነው፡፡ «አውሎ ያግባህ ልጄ!»፡፡ ብዙ ጊዜ ትመጣብኛለች፡፡ ይቺ ምርቃት፡፡ በተለይ በእንደዚህ ያለው ለካፊ ምሽት፡፡ በተለይ እንዲህ እንደ ኮሎኔሉ ያለ ነጃሽ ሰው የተከበረች የድራፍት ማዕድህን ሲደውክብህ፡፡
ግሮሠሪ ውስጥ ሌላው ሰው የማያውቀው የታወቀ የአተሚክ ፊዚክስ ክስተት አለ፡፡ ንጀሳ እንደ ቼይን-ሪአክሽን (nuclear fission) ከአንድ ቦታ ተነስቶ ይሰፋል፡፡ አንዱ ሌላውን እየለኮሰ ያቀጣጥላል፡፡ አንተ ስትነጀስ – አንተም ሌላውን ትነጅሳለህ፡፡ ያኛውም ሌላውን ይነጅሳል፡፡ እና ትልቅ የንጀሳ ፍንዳታ ይፈጠራል፡፡ ለትንሿ ንጀሳ ፊት ከሰጠህ፣ ሀገር ምድሩን ትነጅሰዋለህ፡፡ «በጥንቃቄ ያሽከርክሩ!» የሚሠራው ለመኪና ብቻ አይደለም፡፡ ለግሮሠሪም ነው፡፡ «በጥንቃቄ ይጠጡ!»
አሁን ኮሎኔሉ ነጅሶሃል፡፡ አንተም አሳላፊውን ትነጅሳለህ፡፡ «ዛሬ ደሞ የጎዶሎ ነው እንዴ ቀኑ!?» ትጠይቃለህ በስጨት ብለህ፡፡ የበርጭቆውን ነጭ የአረፋ ጥምጣም በጣትህ እየደነቆልክ፡፡ «ኧረ አይደለም! ማሽኑ ነው! ከአዲስ በርሜል ቀድቼልህ ነው! ይሞላ?» ይልሃል ደንገጥ ብሎ፡፡ ደንገጥ ማለት ደስ የምትል አርት ነች፡፡ ብዙውን ሰው ታበርዳለች፡፡ የድራፍት ብርጭቆ ሞላ አልሞላ፣ ምን ያስደነግጣል? የአባይ ግድብ አይደለም፡፡ እሱስ ቢሆን?! አንዳንድ ነገረኛ ሰው፣ ከግድብ ጋ ራሱ ያላትምሃል፡፡ ያ ለካፊ ነው ተላካፊ ያደረገኝ ዛሬ፡፡ ተበላሁ! ነገ ግን አያመልጡኝም! እኚያ አባት! «አውሎ ያግባህ ልጄ!»፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ያው ኮሎኔል ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ ድንገት ዘው አለ፡፡ የኛ ነገር አልሆንለት ብሏል፡፡ ሰዉ ሁሉ ግን ስትከለክለው የሚብስበት፣ ወጥ ካንተ ጋር እልህ የሚያያዘው ነገር አለ መሰለኝ አንዳንዴ፡፡ እና ዘው ብሎ ገባ ወደ ተከበረችው ጠረጰዛችን፡፡ አልረሳውም የሁሉንም ፊት፡፡ ለእሱ ግን ደንታ የሰጠው አይመስልም የኛ ፊት መጎማዘዝ፡፡
እንደልማዱ ቢራዋን ግማሽ ካደረሰ በኋላ ሊያበስረን የፈለገውን የዕለቱን የነጃሳ ምሥጢር ተነፈሰ፡፡ ‹‹ዛሬ ከማን ጋር እንደዋልኩ ታውቃላችሁ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ማንም መልስ አልሰጠውም፡፡ የሁሉም ዓይኖች ግን በእሱ ላይ አርፈዋል፡፡ በእፎይታ አንዴ ቢራውን ጎንጨት ካለ በኋላ እንዲህ አለን፡- ‹‹አንዳርጋቸው ጽጌን ኢንተሮጌት ሳደርግ ውዬ ነው የመጣሁት!››፡፡ የዚያን ሰሞን አንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔ ደህንነቶች ከየመን ታፍኖ መጥቶ የመታሠሩ ዜና ከተማዋን ሞልቶት ነበር፡፡
እሰይ ሰይጣን! ይል ነበር አንድ የድሮ ጓደኛዬ፡፡ እሰይ ኮሎኔል! በዶ/ር መረራ ጀምሮ፣ በአንዳርጋቸው ጽጌ ገላገለን፡፡ የኢንተሮጌሽን ጀብዱ፡፡ በተሰቀለው! አሁንስ አበዛው ይሄ ሰውዬ! የምር መረረኝ! የሆነ ነገር ልናገረው? ማንም የመለሰለት የለም፡፡ አሁንም ድጋሚ እርስበርሳችን ተያየን፡፡
አንዱ ወዳጃችን ግን ወሬውን በሚያቃልል ተራ አነጋገር ረጋ ብሎ፡- ‹‹So what?››… ‹‹እና ምን ይጠበስ?››… ‹‹ያንተ ኢንተሮጌሽን ለኛ ምን ያደርግልናል?›› አለው፡፡ ኮሎኔሉ በንዴት ከንፈሩ ተንቀጠቀጠ፡፡ ቃላት ግን አላወጣም፡፡ ሽጉጥም አልመዘዘም፡፡ የከፈተውን ቢራ ይዞ ተመንጥቆ ወደ ሌላ ጥግ ወዳለ ጠረጴዛ ሄደና ብቻውን ተቀመጠ፡፡
እኛም የዚያኑ ዕለት ወሰንን፡፡ የጠረጴዛችን ጉባዔተኛ አመረረ፡፡ ይህ ሰው እጅግ አደገኛ ሰው ነው – አለ አንደኛው፡፡ ቃሉ ሁላችንንም አሳቀን፡፡ ክፉ ሰይጣን ነው እንጂ – አለ ሌላኛው፡፡ አሁንም ሳቅ አጫረ፡፡ በመጨረሻ አንዱ – ይሄማ ደዋኪ ነው እንጂ – ሁለተኛ ቀን ነጀሰን እኮ – ነጃሳ! – አለው፡፡ ይሄኛው ቃል በጉባዔተኛው አድናቆት ተቸረው! ነጃሳ! ብዙም ሳይቆይ ነጃሳው ሁለተኛ ወደ ጠረጴዛችን እንዳይመጣብን ለባለግሮሰሪው ወዳጃችን – ከዝርዝር መረጃ ጋር አጠናቅረን – አስጠነቀቅን፡፡ ለነጃሳው ተነገረው፡፡
ሁለተኛ አይደርስም አጠገባችን ብለን አስበን ነበር፡፡ ግን ተሳስተናል፡፡ ሌላ ቀንም መጣ፡፡ ይቅርታ ሊጠይቀን፡፡ ወንበር ስቦ ግን አልተቀመጠም፡፡ ቆሞ ይቅርታ ጠየቀን፡፡ እኛም ቁጭ ባልንበት ‹‹አፎይቲሊላሂ!›› አልነው፡፡ ይቅርታ ተባባልን፡፡ እህል ውሃችን አለቀ፡፡ መሄድ ነበረበት፡፡
ችግሩ እዚያው በዚያው ቢራ ካልመጣላችሁ ብሎ ደሞ ድርቅ፡፡ ብዙ ለመነ፡፡ ሁሉም አመረረበት፡፡ ሁሉም ድርቅ አለ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ነበር የምሩን ጥርቅም አድርጎ የዘጋን፡፡ እና በአሪፍ እንግሊዝኛ ‹‹ዊ ዳን ኒድ ቱ ሳልዩት ኢቻዘ›› ብሎ ዘግቶን የገባው፡፡ እና በሳቅ የገደለን፡፡
«በስምንተኛው ሺ … ሲመሽ ተወልጄ፣
ጅቡን ጋሼ እላለሁ … ተኩላውን ‘ወዳጄ’»
ነጻነት ግሮሰሪ፡፡ የማታሳየን የማታሰማን ጉድ አልነበረም፡፡ መሸታ ቤት እንዲህ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ትያትረኛ ዓለም፡፡ አንዳንዱ በሳቅ ይገድልሃል፡፡ አንዳንዱ ሽጉጥ ይመዝዝብሃል፡፡ በረባ ባልረባው ሀሳብ ትማዘዝበታለህ፡፡ ትግባባበታለህ፡፡ ትፋታበታለህ፡፡ ብዙ ጊዜ ትስቃለህ፣ ትሳሳቅበታለህ፡፡ ግን ትሳቀቅበታለህ፡፡ ትጨቃጨቅበታለህም፡፡ ሆድ የባሰህስ ቀን? ታንቧቧበታለሃ፡፡ እንባህን፡፡ እንደ ለቅሶ ቤት፡፡
ምን ገዶህ? ይህ ነፃነት በጠርሙስ የሚሸጥበት የወዳጆች ደሴት ነው፡፡ ይህ ደስ የሚል እብደት በብርጭቆ የምትገሽርበት የደስታ ምኩራብህ ነው፡፡ ይህ ከበህ ፓርላማውን የምታስቀናበት ዝጉብኝ የሀሳብ ፍልሚያ ግሮሰሪህ ነው፡፡ ይህ የሰፊው ሕዝብ የነጻነት መስክ ነው፡፡
. . . / ክፍል-2 ይቀጥላል…
Filed in: Amharic