ነጻነት ግሮሠሪና የጠረጴዛዋ አሚናዎች!
(እውነተኛ ታሪክ)
ክፍል ፫ አሰፋ ሀይሉ)
ገርሞኝ አላባራ አልኩ። ደነቀኝ፡፡ እጅግ በጣም። የህወሃቱ የቀድሞ ታጋይ ወዳጃችን የነገረን ጥናት፡፡ «ኢህአዴግ ገና 50 ዓመት ይቆያል»፡፡ በግሌ ብዙ ለመነታረክ የሚያበቃ ቅርበት አልነበረኝም፡፡ «ጥናቱን» በሳቅ ተቀብዬ ዝም አልኩ። የጠረጴዛዋ ማህበርተኞች ግን መጀመሪያ ጆሯቸውን፣ ቀስ በቀስ ደሞ ምላሳቸውን አሰሉ፡፡ ይሄን ‹‹ፍርምባ›› የሆነ የጨዋታ እንዲሁ በዋዛ ረግጦ ማለፍ አልቻሉም፡፡
እና ለዚያች ምሽት የመረጥነው የጠረጴዛዋ አፈጉባዔ፣ በህወሃቱ ሰው በተነገረው በኢህአዴግ የ50 ዓመት በሥልጣን የመቆየት ‹‹በጥናት የተረጋገጠ›› የሥልጣን ራዕይ ላይ፣ የእኛን የጉባዔተኞቹን አስተያየት ጠየቀ፡፡ የሚያናድደው ከእኔ ጀመረ፡፡ ይህ ሰው ኢህአዴግ የሀገረ ሜክሲኮውን አንድ ክፍለዘመን ያስቆጠረ ፒ.አር.አይ. ፓርቲ ለመተካት ማስባቸውን ነገሮናል፡፡
ከዚህ በኋላ 50 ዓመት የሚቆይ ፓርቲ፣ እስከዛሬ ከቆየው ጋር ሲደማመር ያው 80 ዐመት ለመቆየት አስቧል ማለት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ፡፡ 80ኛው ዓመቱ ሲቃረብ ደሞ ሌላ ጥናት ያስጠናና 20 ዓመቷን ደፍኜ 100 ላድርጋት ይላል፡፡ እንዲህ እያሉ የላቲኑን ዘለዓለማዊ አብዮታዊ ፓርቲ በአፍሪካ ኢትዮጵያችን ውስጥ ለመተካት ያደረባቸው ያልተገራ ምኞት በበኩሌ ግልጽ ነው፡፡
ቢሆንም ምኞታቸውን ውጉዝ ከመአርዮስ በማለት በዚያች ምሽት ጨዋታ ተርቦ ጠረጴዛችንን የተጎራበተውን እንግዳችንን ማስቀየም አልፈለግኩም፡፡ የውጪው የታክሲ ሰልፍ ጋብ ሳይል በአጉል መነቋቆር የጠረጴዛችንን መንፈስ ማደፍረስ አዋጪ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ሰውየው (እና ፓርቲው) የገቡበት ለከት የሌለው ድንዛዜ ፍጹም ይቅር የማይባል ዓይነት ሆነብኝ፡፡ ሊነገረው ይገባል፡፡ በትህትና፡፡
ሀሳቤን በትህትና ለመናገር ቃላትን ለመምረጥ እየታገልኩ እንዲህ አልኩ (የኢህአዴጉን ሰው ዓይን ዓይኑን በለበጣ እያየሁ)፡-
«ወንድሜ፣ በበኩሌ ስለናንተ ጥናት አንተ ከመንገርህ በፊት የማውቀው ነገር የለም፣ (እዚህ ላይ ዋሸሁ!) ማን እንዳጠናላችሁም አላውቅም (እውነቴን ነው!)፣ ስለ ሀገሪቱ
ሕዝብ በእናንተ መንገፍገፍ፣ እና በሕዝቡ ልብ ውስጥ ስለተቀጣጠለው ከባድ ቁጣ ግን አሳምሬ አውቃለሁ! በዚህ ሀገራዊ ቁጣ መሐል ሆናችሁ ከዚህ በኋላ 50 ዓመት
እንቆያለን ብላችሁ ካሰባችሁ፣ ምን እንደምልአላውቅም…! ወይ ከእውነታው completely ተፋታችኋል ማለት ነው! ወይ ደሞ ይህን እንዳታዩ ዓይናችሁን የጋረደባችሁ የሆነ
አፍዝ-አደንግዝ ይዟችኋል ማለት ነው! እንጂ… በጤነኛ አዕምሮ ሆናችሁ ብታስቡ በዚህ ወቅት ላይ ሆናችሁ ተጨማሪ 50 ዓመት በሥልጣን እንቆያለን ብላችሁ የምራችሁን የምታስቡ አይመስለኝም!!!”
ብዬ ጨረስኩ ሀሳቤን፡፡ ለሁሉም ጉባዔተኛ በሚሰማ ግልጽ ቋንቋ፡፡ ሀሳብን እንዳንዴ እንዲህ ሲተነፍሱት ደስ ሲል!? ያውም ተመሳሳይ ዲሉዥን ውስጥ ገብተው ስለነበሩት ስለናዚዎች ላነሳ ምላሴ ጫፍ አድርሼ ነው የመለስኩት፡፡ ያ ዓይነቱ ንጽጽር ጥላቻ ያሳደርኩ ያስመስላል፡፡ ከወዳጃችን አልፎ ሌሎችንም የጠረጴዛዋን ጉባዔተኞች ሊያስቀይምብኝ ይችላል፡፡ ለምታልፍ አንዲት ምሽት፣ የማያልፍ ቃል ለምን ልናገር? ላሁኑ ይቆየኝ ብዬ ተውኩት፡፡ የጀርመኑን ብሔራዊ ሶሻሊስት ፓርቲ (ናዚን) እና ኢህአዴግን በዲሉዥናል ዝንባሌያቸው ማነጻጸሩን፡፡ ከኖርን፡፡ ሌላ ጊዜ ይደረስበታል፡፡
ΩΩ ΩΩ ΩΩ ΩΩ ΩΩ
ሀሳብን ከመተንፈሱ በላይ፣ የሌላውን ሰው ሀሳብም መስማት ይበልጥ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ያለኝ፣ ሁሉም የግሮሠሪዋ ጉባዔተኛ፣ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት ይቆያል? በሚለው ትንበያ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ፣ በአውራው ፓርቲ የ50 ዓመት ህልም ላይ የተስማማ አንድም የጠረጴዛዋ ታዳሚ አልነበረም፡፡ ከራሱ ከወሬ አምጪው በስተቀር፡፡ ይህን ሳይ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፡፡
የሰውየውን የዋህነት አይተው – ለማፅናናት የፈለጉ የጠረጴዛዋ አንዳንድ ታዳሚዎች ግን አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ የኢህአዴግን የሥልጣን ዕድሜ እስከ 15 ዓመት ከፍ አድርገው ገመቱለት፡፡ መሸጫውን የነገርኩት እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም፡፡ ኢህአዴጎችን ባጠቃላይ ‹‹ዲሉዥናል›› አድርጌ ማቅረቤም የሰውዬአችን ቆሽት እንዳሳረረው ነው፡፡ ጥቂት ቢራ ተጎነጨና፣ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ፊቱን ወደ እኔ አዙሮ እንደምንም እየፈገገ እንዲህ አለኝ፡-
«‹እናንተ ጤነኞች አይደላችሁም!› ነው ያልከን አስፋ?» (ስሜን በትክክል አይያዝለትም፣ አሣፍ በማለት ፋንታ አሥፋ ብሎ ነው የሚጠራኝ)፡፡
«አሥፋ አንተ እኮ… ስንት ሚሊዮን አባላት ያሉትን ሀገር የሚመራ ትልቅ ፓርቲ… ቀውሷል፣ ዲሉዥናል ሆኗል.. ነው እያልክ ያለኸው?»
ይሄ ሰውዬ ሊላቀቀኝ አልፈለገም፡፡ እኔም ደግሞ ደረቅ ነኝ፡፡ አንዴ ሀሳብ ከጀመርኩ ግፋ በለው ነው፡፡ ወዲህ ወዲያ ማለት አልወድም፡፡ ወይ ሀሳቤን የሚያስቀይረኝ ምክንያት መምጣት አለበት፣ ወይ ሌላ ሀሳብ መምጣት አለበት፡፡ ሰው እዚያው ሀሳብ ላይ ባመነቸክኸኝ ቁጥር፣ እኔም በሀሳቤ እያከረርኩ እሄዳለሁ፡፡ የኖረ ጠባዬ ነው፡፡ ምንም ላደርገው ያልቻልኩት፡፡
«ከዚህ በኋላ 50 ዓመት እንቆያለን ብላችሁ ካሰባችሁ… በደንብ እንጂ!! ወይ እናንተ ጤነኞች አይደላችሁም…! ወይ ደሞ በጥናት አረጋጬላችኋለው ያሏችሁ ሰዎች ጤነኛ አይደሉም…! ማለት ነው..! እንጂ ሌላ ምን ተብሎ ሊጠራ ይችላል ይሄ?!»
በአባባሌ ሁሉም በሳቅ አሽካኩ። የህወኀቱ ወዳጃችን ግን የኢህአዴግን ቀውስነት ስላረጋገጥኩለት በጣም በሸቀብኝ። ስለዚህ ይበልጥ አናዳጅ ወደሆነ ትንበያ ውስጥ መግባት አልፈለግኩም፡፡ ድራፍቴን እየተጎነጨሁ ሰዉ ሲስቅ አብሬ ስቄ ዝም አልኩ፡፡ ሳቁ ጋብ ሲል ግን የህወሃቱ ሰው ራሱ አስታውሶ ጠመደኝ፦
«የ50 ዓመቱን ትንተና ተቃወምክ! እሺ ይሁንልህ 50 ዓመት ድረስ አንቆይም ይባል! … ቆይ እሺ አንተስ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ለስንት ዓመት በሥልጣን ላይ ይቆያል ነው የምትለው?»
አንዳንዴ የድፍረት ድምዳሜ ያስተዛዝባል፡፡ ግምቴን ለመናገር ትንሽ አቅማማሁ፡፡
«ወንድሜ! ይህ ራሱን የቻለ ሰፊና ገለልተኛ ጥናት ያስፈልገዋል! ዝም ብዬ ብገምት ምን ያደረጋል ብለህ ነው?»
«ኖኖኖ…! ይሄኮ ሀገራዊ ኮንፈረንስ አይደለም! በኛ መሐል ነው አይደል እንዴ! የመሰለህን ግምት በነጻነት መናገር ትችላለህኮ እነሱ እንደተናገሩት፣፣፣ እና አንተ ኢህአዴግ ሥንት ዓመት ይቆያል ነው የምትለው?»
አሁን አላቅማማሁም፡፡
«ኦኬ! በእኔ ግምት… ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ እንደ ምንም ብሎ 2 ዓመት ራሱ ከደፈነ፣ ዕድሜ-ልኬን ሲገርመኝ ይኖራል! በእኔ ምልከታ… ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ አንድ ዓመትም ራሱ የሚቆይ አይመስለኝም!»
አልኩት ቆፍጠን ብዬ። አሁንም ጠረጴዛችንን ሌላ ዙር ሳቅ ዋጣት፡፡ አሁን የህወሃቱ ሰው ራሱ በሳቁ ተደመረ፡፡ ብዙ ሳቅ። እና የቀልድ ቺርሶች፡፡ ‹ምኞትህን ተናገር እኮ አልተባልክም አሴ፣ ግምትህን እኮ ነው የተባልከው!›፡፡ ‹የዕድሜ ገመዱን እኮ ነው በጥሶ የጣለው›፡፡ ‹አንተ ግን ኢህአዴግ ምን አርጎሃል? እንዲህ የጨከንክበት?›፡፡
«አሴ ዛሬ የጠጣሽው መመርመር አለበት! የኮሶ አረቄ ነው እንዴ? ወይስ የግብጦው ነው እንዲህ የሚያስሟርተው?››
ያለኝም ነበር፡፡ ሌላ ዙር ሳቅ፡፡ እና ሌላ ዙር ድራፍት።
ΩΩ ΩΩ ΩΩ ΩΩ ΩΩ
አሁን ላይ ሆኜ ያን እሰጥ-አገባችንን ወደኋላ ዞር ብዬ እያሰብኩ፣ የ50 ዓመቱን ኢህአዴጋዊ የሥልጣን ዕድሜ ትንበያ፣ ወሽመጡን ቆርጬ ወደ 2 እና 1 ዓመት ዘጭ ሳደርግበት፣ በእዚያ የህወሃት ሰው ፊት ላይ፣ ከንዴት ይልቅ ትልቅ ድንጋጤ ሲነዛበት እንዳየሁ፣ አሁን ላይ፣ ድንግዝግዙን የግሮሰሪዋን ብርሃን አልፎ ይታየኛል፡፡
በሳቅ የተሸፈነውን ያንን የህወሃቱን ሰው ድንጋጤ ያኔም አይቼዋለሁ፡፡ ሳቁም ከዚያ ያለፈ በርዕሱ ዙሪያ እንካ ሠላንቲያ ይበቃል የሚል የሠላም አቋም መግለጫም ዓይነት ነበር፡፡ በኋላ ሲነገረኝ ሆነ ብዬ እሱን ለመነጀስ እንደሰነዘርኩት የስድብ ቃልም ቆጥሮብኝ ነበር፡፡
በጠረጴዛ ዙሪያ ሀሳብን መሰንዘር እንዴት «ሰደበኝ» ለሚል ስሞታ ይዳርጋል? እንዴት በሀሳብ አለመስማማት ከመሰዳደብ እኩል ይቆጠራል? ቢያውቀውኮ እንዲህ እንደኛ ሀሳብን በጠረጴዛ ዙሪያ በሠላም ቁጭ ብሎ እየተጨዋወቱ መለዋወጥ መቻል እኮ ስድብ ሳይሆን፣ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ጸጋ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው?
«እንግዲህ እስከዚያ ያቆይህና ሁላችንም አብረን እናየዋለን!»
የምትል ነበረች፡፡ በመጨረሻ ከዚያ የህወሃት ሹም አንደበት የወጣችው ሐረግ፡፡ ያን ብሎ ከጠረጴዛዋ ተነስቶ ወደ ባኞ ሄደ፡፡ ይሄ ሰው እስከዚያ አትቆይም እንጂ… ማለቱ ይሆን? (ትርጉም በስለሺ ዳቢ!)፡፡ ወይስ… ጊዜ ያሳየናል፣ ጊዜ መስታወት እያለኝ ነው? አዎ፡፡ መሆን አለበት፡፡ እውነት ብሏል፡፡ ሁሉም የፈለገውን ቢራኮት፣ የመጨረሻው እውነተኛ ፈራጅ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጊዜ ለሁሉም መልስ አለው፡፡ መስታወት ነው፡፡ ያሳየናል፡፡
ኢህአዴጉ ከሄደበት የባኞ ዕረፍት ተመለሰ። ‹‹ኖር ኖር›› ብዬ በጨዋ ደንብ ተነስቼ ወደ መቀመጫው አሳለፍኩት፡፡ በጓደኝነት መንፈስ፡፡ የባጥ የቆጡ እየተነሳ ስንቧልት ቆየን፡፡ በመሐል ማዕድም ቀርቦልን ሳንቋደስ አልቀረንም፡፡ መሰለኝ፡፡ ሆድ ይረሳል፡፡ ነገር አይረሳም፡፡ የኛ ነገር፡፡
ጨዋታ የማይጠገብ ምግባችን ነበር፡፡ ግን ጊዜ የሚባል አሳላፊ አለ፡፡ የሰዓት ነገር ሆነብንና ተነሳን፡፡ እንቆያለን ያሉትን ተሰናብተን ወጣን፡፡ ጨዋታችንን እያውጠነጠንን፡፡ ወደየቤታችን ልንደርስ። እና በማግስቱ ጧት ምንም ያላየ፣ ያልሰማ፣ ያልቀመሰ፣ ያላጤሰ፣ ያልተጢያጢያሰ ፍጹም ጤነኛ ሰው መስለን… ወደየሥራችን ልንነጉድ፡፡ እና ማታ ደግሞ… ጨለማን ተገን አድርገን… መልሰን ወደ ነጻነት ግሮሰሪያችን ልንመለስ፡፡
አንዳንዴ ከዛሬ አስከ ነገ ማታ ማሰብ ራሱ እኮ ረዥም ነው፡፡ ከአንድ ቀን በላይ አርቆ ማሰብ ያስጠላል፡፡ በተለይ እንደ ኢህአዴግ፡፡ ለሥልጣኑ 50 ዓመት አርቆ የሚያስብ ሲያጋጥመኝ፡፡ እታወካለሁ፡፡ ነገ ደሞ.. «ህወሃት እኮ 2 ዓመት እንደማይቆይ ቢያውቀው ኖሮ… ከኦነጎች ጋር ተደራድሮ… የኦሮሚያን ሪፈረንደም ይፈቅድላቸው ነበር… እና ትንሽ ዕድሜ ለመግዛት ይችል ነበር…! ዲሉዥናል መሆኑ… የዕድሜ ገመዱ እያጠረ እንደሆነ አለማወቁ በጀን እንጂ!!» የሚል ትኩስ ክርክር ይዤ ወደ ምሽቷ የነጻነት ግሮሠሪ ጠረጴዛችን ለመድረስ አስቤያለሁ፡፡
«ግንኮ ያ የኢህአዴግ የ50 ዓመት የሥልጣን ትንቤ ጥናት እኮ ልክ ሳይሆን አይቀርም! ይኸው ቀጥሏልኮ በሥልጣኑ…!» እንደገና እነዚያኑ የዛሬ 3 ዓመት ያደረግናቸውን ክርክሮች አጠናክሮ እንደ አዲስ ማፋፋም! Welcome to the past! «እንኳን ወዳለፈው በሠላም መጣህ!» ሲል የሰማሁት ማንን ነበር? «ዲሉዥናል» ያልኩትስ ማንን ነበር? «ዲዝኢሉዥንድ» ሆኛለሁ፡፡ እስቲ ፉጄ! ፉጀጋ! እዚህ ጋ! ጃምቦውን ድገመኝ! የሳንጃውን! አዎ!! ልበይክ!!! የነጻነት ግሮሠሪ፡፡ ቅዝቅዝ ያለ «ዲሉዥን»፡፡ እንዴት ደስ ይላል?!!
ቸር ያሰንብተን፡፡