>
5:13 pm - Saturday April 19, 0842

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ (ክፍል ፫ - በአንዱ ዓለም ተፈራ)

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ

(ክፍል )

 

ፃ አስተያየት፤ በአንዱ ዓለም ተፈራ


በትንንሽ ጎጆዎች ተኮልኩለን፤ በአንድ ትልቅ ቤት እየኖርን ነው ልንል አንችልም።

 

አገራችንን ካለችበት አዘቅት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሻግር ራዕይ፤ በአሁኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የለም። በአገራችን የነገሠው፤ ፍርሃት፣ ነፃ ሆኖ በአገሪቱ የትም ቦታ መንቀሳቀስ አለመቻል፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ታጥቀው የፈለጉትን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉና እያሠሩ ያለበት ሀቅ፣ የዋጋ ግሽበት የየዕለቱ እውነታ የሆነበትና በየመንደራችን ባሉ ጎጆዎቻችን ተኮፍሰን፤ እኔ ከበላሁ ምን ቸገረኝ! ያልንበት ሀቅ ነው። መንግሥት የሕልውናችን ምሰሶ፣ ሕግን አስከባሪ፣ ገበያውን አረጋጊ፣ ዘበኛ ሆኖ የሚጠብቀን ያንገት ማተባችን አድርገን እኖር ነበር። የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ከተጠየቀ ወዲህ፤ ትክክለኛ የሕዝብ አስተዳደር በቦታው ስላልተከሰተ፤ መንግሥትን የኔ ብሎ መቀበልና፤ “ያንተ አሽከር፣ ያንተ ቡችላ!” ብሎ መፎከር፤ ቦታውን ለቅቋል። በአንጻሩ ደግሞ፤ ከመንግሥት አኳያ አማራጭ ሆኖ የቆመ ተፎካካሪ ባለመገኘቱ፤ መንግሥቱንም ንቆ ተፎካካሪውንም አጥቶ፤ ሕዝቡ ወደራሱ ማተኮር ያዘ። ራስን ለማበልጠግና ውሎ ለማደር ብቻ ሆነ ዘመቻው። ሰው ጭንቀቱንና ብሶቱን አምቆ፤ የ“ውዬ ልደር!” ካባውን የኔ ብሎ ተያይዞታል። ለዚህ ነው የኢትዮጵያዊነታችን ማሰሪያ ውሉ የተበጠሰብን። አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገደል ቀርቶ ሲበደል የምንጮኸው፤ ዛሬ፤ “እኔን እስካልነካ!” በሚል ዘዬ እያለፍነው ነው። ሰዎች ተገሉ ሲባል፤ “ሰዎቹ ጥፋተኛ ቢሆኑ ነው!” የሚል ውንጀላ እያከልንበት ነው። ለሰዎች ሞት ተቆርቋሪነታችን ከኛ ርቋል። ዛሬ አገር አድን ጥሪ ባለበት ሁኔታ፤ ለምንድን ነው ስለውስጥ አገዛዝ የማነሳው? ላስረዳ፤

ከሺ ዘጠኝ መቶ ስድስ ስድስት ዓመተ ምህረት ዋዜማ ጀምሮ፤ ከፊታችን ባለው ሀቅ ብቻ ተጠምደን፤ ነገ ሊከተል ስለሚችለውና ሊከተል ስለምንፈልገው ምንም ቦታ ሳንሠጠው፤ ሙሉ ርብርባችንን በ“ዛሬ!”ው እያደረግን ከርመናል። የንጉሠ ነገሥቱን መውደቅ እንጂ፤ ከዚያ በኋላ መከተል ስላለበት ሳንዘጋጅ፤ ክፍተት ተፈጠረና፤ ደርግ ሰተት ብሎ ወንበሩን ተደላደለበት። የመንግሥቱ ኃይለማርያምን አረመኔ አገዛዝ በመጥላት፤ እሱን ለማስወገድ በተደረገው ርብርብ፤ ክፍተት ተፈጠረና፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሰተት ብሎ ገባ። ዛሬም ዘረኛውንና ፀረ-ኢትዮጵያዊውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መደምሰስ ፈልገን ስንቋምጥ፤ ያው ራሱ ኢሕአዴግ፤ ስሙን ብቻ ብልፅግና ብሎ ቀጥሏል። ታዲያ ይህ የሚከተለው ምርጫ፤ ብልፅግናን ሕጋዊነት ከመለገስ ያለፈ፤ ምን ሊያስከትል ይችላል? ለዚህ ነው ወይ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው? ስለነገ ማሰብ አለብን። ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ትኩረት። ያለንበትን እንመርምርና ለነገ እንዘጋጅ።

መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አደባባይ ሲመጡ፤ አገራችን በሙሉ ከጫፍ እስከጫፍ በደስታ ተሞላ። ያለ የሌለ ክብርና ድጋፉን ሠጣቸው። ቀስ በቀስ ከነበረው ስርዓት ጋር ያላቸው ትስስር፤ የማይላቀቁት ወይንም ሊላቀቁት የማይፈልጉት መሆናቸውን ተረዳን። ሕገ-መንግሥቱን ማስከበር፣ የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር፣ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መደምሰስና አማራውን ማስጨረስ ዋና ተግባራቸው ሆነ። “ትዕግስት ይኑረን!” “ጊዜ ስጡት!” የሚለው አባባል አዲስ አይደለም። የእንዳልካቸው መኮንን ጊዜያዊ ካቢኔ ጠይቆ ነበር። አልተሠጠውም። ደርግ ሲጀምር ጠይቆ ነበር። ተሠጠው። የተጠየቀውን መመለስ ሳይሆን ራሱን በአምባገነንነት አሳደገበት። እንግዲህ ሁሉን የምርጫ መንገዶች ከነውጤታቸው አዳርሰናል። የት እንደወሰዱንም አይተናል። የሁለቱንም የምርጫ መንገዶች ሂደት ብንመለከት፤ በሁለቱም ወገን ቅን፣ አገር ወዳድና አዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩባቸው። በዚያውም ልክ እጠቀም ባዮች፣ ነበሩባቸው። አሁን በቦታው ላለነው ያለው ጥያቄ፤ ምን ትምህርት? ወሰድን ነው። እንደ መንግሥቱ እስኪጠናከር ዝም እንበል ወይንስ እንደ እንዳልካቸው አይሆንም እንበል! ይህ ነው የተወጠርንበት። “ምርጫው ይደረግ እንጂ፤ ዴሞክራሲ ባገራችን ይሰፍናል!” ባዮች አሉ። ምርጫ ዴሞክራሲን አይስከትልም። ለዚህ ምስክር አንሻም። በደርግም ሆነ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጊዜ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ምን ዓይነት ምርጫ እንደነበሩ ነጋሪ አይስፈልገንም።

ዴሞክራሲኮ፤ የትም ቦታና በማናቸውም ጊዜ ቢሆን፤ አንዱ ሠጪ ሌላው ተቀባይ የሚሆንበት ሂደት አይደለም። ዴሞክራሲ የጠማቸው በትግል የሚነጥቁትና የሚላበሱት ሂደት ነው። እስኪ እንመርምረው! ማነው ዴሞክራሲን ፈላጊ፤ ማነው ዴሞክራሲን ሠጪ? ይመጣል ብሎ መጠበቁ፤ “ላም አለኝ በሰማይ!” ነው። ሠጪ የሆነ አካል፤ ለምን ብሎ ዴሞክራሲን ይሠጣል? አገራችን የአንድ ፓርቲ መንግሥትና የውሸት ምርጫ ዳስ እንዳትሆን ሠግቻለሁ።

እስከ ዛሬ የነበረውን የፖለቲካ ሂደት እንዳልነበረ ወይንም እንደማያገባን አድርገን መውሰዱ ዕዳ ይከተናል። ከፊታችን የተደቀነው ምርጫ፤ የወደፊቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት አቅጣጫ ተናጋሪ ነው። አሁን በተያዘው አቅጣጫ ከተጓዝን፤ ባለንበት መርገጣችንን እናረጋግጣለን። ይሄን ትተን፤ በክፍል አንድና ሁለት ባሰፈርኩት መሠረት፤ ከምርጫው በፊት መደረግ ያለባቸውን ዝግጅቶች አሟልተን፣ ሕገ-መንግሥቱ ተስተካክሎ፣ የሕዝብ ቆጠራው ተካሄዶ፣ ነፃና አድልዖ የሌለበት ምርጫው ተከናውኖ፣ ትክክለኛው የየቦታው ተወካዮች ተመርጠውና ወደ ፓርላማው ገብተው፣ እያንዳንዱ ከተማ የየራሱን የከተማ ወኪሎችና ከንቲባ ከመረጠ፣ አዲስ በር ተከፈተ ማለት እንችላለን። በርግጥ የተደገሰለት ምርጫ በተዓምርም አይቀርም። ይደረጋል። የዚህ ጽሑፍ መልዕክት፤ ምርጫው ቢደረግም፤ ትምህርት እንውሰድበትና ማስተካከያ እናድርግለት ነው። ያን ካደረግን፤ ወደ ተቃውሞና ወደ አላስፈላጊ የትጥቅ ትግል የሚመራው በር፤ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል። ሰላም፣ ልማትና ዕፎይታ በአገራችን ይነግሣሉ። “አማራው ከኛ ቦታ ይውጣ!” ብሎ፤ ሰዎችን ያስገደለና ንብረት ያስወደመ ግንዛቤ፤ ነገ በኦሮሞ ክልል፤ “እኔ በምንፈልገው መጠን ኦሮሞ አልሆንክም!” ብሎ፤ የራሱን ኦሮሞም እንደሚገድል ጥርጥር ሊኖረን አይገባም። የተያዘው የዘር አገዛዝ ወለሉ ግለሰብ ነው። አጠቃላይ የሚባል ግንዛቤ የለም። አይኖርምም! የግለሰብ ፈራጅ ቆራጭነትና ወሳኝነት ነው ወለሉ! አደጋውን ሊሄድ ከሚችልበት ግቡ አንጻር መመልከት አለብን።

ለውጥ እያልን ስንጮህ፤ ይሄው ሃምሳ ዓመታት አሳልፈናል። ብዙዎች መስዋዕትን ከፍለዋል። ውድ ሕይወታቸውን ሠጥተዋል። ባሁኑ ሰዓት ያለው ጭላንጭል የነፃነት ፍንጣቂ፤ ትንሽ ቆይቶ እንደሚጠፋ ማሰብ አለብን። የውጪ አገራትና ኃይላት ድንፋት ይበርዳል። የየግል ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ነውና ሾፌራቸው፤ ዛሬ ጠላት የሆኑት ነገ ሲበርድላቸው ዋና ወዳጅ ሆነው ይሰለፋሉ። ሁሉን ገዥ የሆነው እውነታ፡ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል፤ ቋሚ ጠላትነትና ቋሚ ወዳጅነት አለመኖሩ ነው። አሁን እንዳለችው ጭላንጭል ነፃነት፤ ደርግም ለጥቂት ጊዜ ፍቃድ ሠጥቶ ነበር። ዛሬ ሕግ አክባሪዎችን ያሰረ መንግሥት፤ ነገ ደግሞ ትናንት እንዲህ አድርጋችኋል! ብሎ ተቃዋሚዎቹን ለቃቅሞ ድራሻቸውን የሚያጠፋቸውን እየመዘገበ ነው። ነገ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚባል አይታሰብም። እንደ ደርግ ጊዜው፤ በየቦታው መግደልና ምክንያት መደረቱ ይቀጥላል። በአገራችን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትና ማደግ የሚሆኑ ተቋማት አልተገነቡም። ሁላችንም አንጋጠን፤ “መንግሥት በፈቃዱ ይሄንን ወይንም ያንን ያደርጋል!” እያልን ነው። ያ ሁሉን ኃላፊነት ለመንግሥት መሥጠቱ፤ ነገ የት እንደሚያደርሰን ከወዲሁ ተገንዝበን፤ ዛሬ መደረግ ያለበትን ካላደረግን፤ ነገ የሕዝብ መንግሥት አይኖርም። ባገር ግን ተስፋ አይቆረጥም።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ልክፍት ከመንግሥቱ ሂደት አልፎ፤ ከኔ ቢጤ ኢትዮጵያዊያን እስከ አዋቂዎች ድረስ ሠርጿል። ልለምደው ባልቻልኩትና፣ ስሠማው ጆሮዬን ቆንጥጦ ሰውነቴን በሚሰቀጥጠው ቃል ልጀምር። ቃላት በግንዛቤያችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አላቸው። ለፖለቲካ ዓላማ ሲባል የሚቀመሙ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች፤ የሰዎችን አመለካከት ይመራሉ። ቃሉ፤ “ሕዝቦች” የሚለው ነው። እኔ እስከማውቀው፤ ሕዝብ ማለት፤ በአንድ ሰፈር፣ በአንድ ወቅት የተገኘ የሰዎች ስብስብ ነው። የገበያው ሕዝብ፣ ለለቅሶ የመጣው ሕዝብ፣ ኳስ ጨዋታውን የሚመለከተው ሕዝብ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንላለን። ከእንድብር ይምጣ ከናዝሬት፣ ከደብረ ብርሃን ይምጣ ከሐረር፤ መርካቶ የሚገኘው ሻጪና ሸማች፤ የመርካቶ ሕዝብ ይባላል። ከአባይ ወንዝ የተቀዳ ውሃ፣ ከዋቢሸበሌ የተቀዳ ውሃ፣ ከኦሞ የተቀዳ ውሃ ባንድ ላይ ቢገኝ፤ ውሃ ይባላል እንጂ፤ ውሃዎች አይባልም። የአዳማ ነጭ ጤፍ፣ የጎጃም ነጭ ጤፍ፣ የሲዳማ ነጭ ጤፍ ባንድ ላይ ቢገኝ፤ ነጭ ጤፍ ይባላል እንጂ፤ ነጭ ጤፎች አንልም። “ሕዝቦች!” የፖለቲካ ግባቸውን በመከፋፈል ብቻ ሲገፉ የሚችሉት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች የቀመሩት የመስሪ አገዛዝ ደባቸው ማስፈጸሚያ ቃል ነው። በሚቀጥለው ጽሑፌ ቃላትን በሚመለከት፤ አራሚ አጥተው ንግግሮቻችንን ያጨቀዩትን በሚመለከት አሰፍራለሁ። ላሁኑ መዝጊያ እንዲሆነኝ፤ የሚከተለውን አቀርባለሁ። በንግግራችን መካከል የውጪ ቋንቋ ቃላትን መደንጎሩ፤ የአዋቂነት መለኪያ ሳይሆን፤ የራስን ቋንቋ ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመነጭ የተናጋሪዎች ማፈሪያ ነው። “የሰው ወርቅ አያደምቅ!” ብለዋል ቀደምቶቻችን።

Filed in: Amharic