>

የአክሱም ክንፎች የት ወደቁ? (አሰፋ ሀይሉ)

የአክሱም ክንፎች የት ወደቁ?

አሰፋ ሀይሉ

 

*…. በቅርቡ ደግሞ «አክሱም» የሚለው ቃል የመጣው «አከ» እና «ሱማ» ከሚሉ ሁለት የኦሮምኛ ቃላት መሆኑ ታወቀ የሚል የሰሚ ሰሚ ወሬ ደርሶኛል፡፡ የአክሱምን ስም ያወቀው ማን እንደሆነ አላወቅኩም፡፡ ግን ይህንንም በእርግጠኝነት ለመናገር ይከብዳል፡፡ እንደተባለው አክሱም የሚለው መጠሪያ ከኦሮምኛ ቃል ከመነጨ፣ የምንኮራበት ቀደምት ታሪካችንን ‹‹እድፍ›› ብለው በብሔራዊ መዝሙራቸው ያካተቱት ጠባቦች፣ ቢያንስ አከ-ሱማ ላይ አሻራቸው እንዳለበት አውቀው፣ ታሪካችንን አክ-እንትፍ ማለት ይተዉልን ነበር፡፡ እና በጊዜ ይጠናልን! (ይጠናስ ቢባል ኢሱ ይፈቅድ ይሆን? – አንድዬ ይወቅ!)    
*    *    *
እያንዳንዱ የአክሱም ሀውልት ከአንድ ወጥ የተራራ አለት ተፈልፍሎ የወጣ ነው፡፡ የሀውልቶቱ ድንጋዮች ዓይነት፣ ሀውልቶቹ ከቆሙበት ምድር የድንጋይ ዓይነቶች ጋር ሲተያዩ ግን ድንጋዮቹ ከብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ካሉ ተራሮች ላይ ተጠርበውና እንደ ሳሙና ተቆርጠው የወጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ግን የዛሬ 1,500 ዓመት ወደ ኋላ ተጉዘን የነበረውን ውሱን ቴክኖሎጂ እናስበው፡፡
እና ያን ሁሉ ኪሎሜትር መንገድ አቆራርጦ እንዴት ሀውልቶቹ መጥተው አክሱም ላይ ሊተከሉ በቁ? እንዴትስ ባለ ዘዴ፣ ትልቁ 13 ፎቅ ህንጻ የሚያህል ርዝመት ያለው (ባለ 33 ሜትር) ድንጋይ እንዴት ያለ ድጋፍ ቀጥ ብሎ ሊቆምላቸው ቻለ?
የአክሱምን ሀውልት አጠናን ያሉ የጀርመን አርኪኦሎጂስቶች፣ እና የንድፍና ምህንድስና ሳይንቲስቶችን ያካተተ ቡድን ይዞ የመጣው ሃሳብ አክሱማውያኑ ሀውልቱን በተራራው ማህጸን እንዳለ ወቅረው (ጠርበው) ከጨረሱ በኋላ፣ በዚህ መልኩ በዝሆኖችና በአንዴ እስከ 30ሺህ በሚደርሱ ባሮች አምዶቹን እንደጎማ በሚያገለግሉ ግንዶች ላይ እየጎተቱ አሁን ያሉበት ሥፍራ ላይ አምጥተው ተከሏቸው የሚል ነው፡፡
ይሄ ግን በተለያዩ ምክንያቶች አያሳምንም፡፡ ለምሳሌ በእነዚያ አቀበትና ቁልቁለት ባልተለያቸው የተራራ ሰንሰለቶች ላይ ክንፍ ካላወጣህ በስተቀር በምን ተዓምር ነው መሬት ለመሬት እንደ ህጻናት መኪና እያንከባለልክ ደህንነቱን ጠብቀህ የምታወጣውና የምታወርደው? የማይሆን ነገር ነው፡፡
እዚህ ላይ የበዕውቀቱ ስዩም «አባት እና ልጅ» የምትል አጭሬ ግጥም መጣብችብኝ፡-
«’ጎዳናው ድንግል ነው፣ አሻራም የለበት
ከቀደሙት ወገን ማንም አልሄደበት’
ይላል አመንትቶ፣
አባቱ ባለክንፍ፣ መሆኑን ዘንግቶ።»
በእርግጥ በአክሱም ዘመን የነበረን ኋላቀር የሜካኒካል ቴክኖሎጂ ብቻ ነበር ወይ? እነዚያን የአክሱማውያን ሚስቲክ ኮምፖዚሽንስ ፍካሬያዊ የቅርጽ ንድፎች አስደናቂ ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ በአሁን ዘመን የተወለዱ ድህረ-ዘመናዊ ወይም «ፖስት ሞደርን» የምንላቸውን እጅግ የተቃለሉና በአያዎ የተሞሉ እጅግ ረቂቅና ዘመናዊ የሚባሉትን የቅርጻ ቅርጽ ንድፎች የሚያስንቁት እነዚያ በአክሱሞች ላይ የምናገኛቸው ንድፎችና ትዕምርቶችስ?
እነሱንስ ምን ልንላቸው ነው? የወቅቱ ሰው ገና ከከርሱ ያልተላቀቀ ህዝብ ባይሆንስ ኖሮ፣ ወደ እንደዚህ ዓይነቶቹ የተራቀቁና የሰውን ልጅ ለማስደነቅ ሆነ ተብለው ወደሚሠሩ የጥበብ ሥራዎች ለመሠማራት አይደለም፣ ለማሰብ ራሱ እንዴት ጊዜ አገኘ?
ብዙው ነገር ቤት አይመታም፡፡ አሁን ዘመን ላይ ያለው በተለይ የምሥራቅ አፍሪካችን አካባቢ ሰፋም ሲል ደቡብ አረቢያን ካርቲዥንና መካከለኛውን ምስራቅ ጨምሮ፣ በጥንት ዘመን ላይ የአሁኑን ዘመን የሚተካከልና (ምናልባትም በአሁኑ ዘመን ሊደረስበት ስላልቻለ) ከአሁኑም በእጅጉ የመጠቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀሙ እንደነበረ፣ ብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶች አንዳንድ ፍንጮችን እያወጡ ነው፡፡
ይህ ከሆነ፣ እኛ ያሁን ዘመኖቹ በጊዜ የኋለኞቹ ስለሆንን ራሳችንን ከኖርንበት ጊዜ አንጻር ‹‹ዘመነኞች›› ብለን ለመጥራት ብንችልም፣ በይዘትና የሥልጣኔ ደረጃ ከተመዘንን ግን ከጥንቶቹ ዘመናዊ ዝርዮቻችን በቴክኖሎጂም፣ በጥበባዊ ከፍታና የፈጠራ አቅማችንም እጅግ የወረድን ኋላቀር ዘመናውያን መሆናችንን አምነን መቀበል ሊኖርብን ነው ማለት ነው፡፡
በእነዚህን መሰል በተለይ በግብጽ ፒራሚዶችና በላቲን እጅግ አስደናቂ መሰል አምዶችና ፒራሚዶች ላይ በርከት ያሉ ባለሙያዎችን በማሰማራት ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ ቢያንስ እኔ የማውቃቸው ሶስት መጽሐፎችን ያሳተመው ግራሃም ሃንኩክ በበኩሉ፣ በአክሱም ዘመን ብቻ ሳይሆን ከዚያም 2ሺህ ዓመት አስቀድሞ በምስራቅ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና እስያ ውስጥ ጭምር የኖሩ የሰው ልጆች፣ ከአሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂ የሚስተካከል የተራቀቀ ኮምፒውቴሽናል (መግባቢያው ሁሉ በስሌቶች የተሞላ) እና በቴክኖሎጂ የቀደመ ማህበረሰብ ነበራቸው – በማለት ይደመድማል፡፡
ከግራሃም ሃንኩክ መጽሐፎች ሁለቱ ‹‹ፊንገርፕሪንትስ ኦፍ ዘ ጋድስ›› እና ‹‹ማጂሺያንስ ኦፍ ዘ ጋድስ›› የሚሉት ሁለት መጽሐፎች አሉኝ፡፡ ረዥም ጊዜ ወስጄ አንብቤያቸዋለሁ፡፡ እጅግ የሚያስደንቁ ጥናቶች ናቸው፡፡ ወደፊት ራሳቸውን ችዬ እመለስባቸዋለሁ፡፡ በእነዚህ  መጽሐፍት የተገለጹ አንዳንድ አስደናቂ የፒራሚዶቹ ቅስቶች ልኬቶችን እናገኛለን፡፡ እጅግ በጣም የረቀቁና፣ ከምድርም ክስተቶች አልፈው ከአስትሮኖሚካል ክንውኖችና ልኬቶች ጋር ሁሉ በማይክሮ ማይክሮ ሜትር ርቀት ደረጃ እኩል የሚመጡ ልኬቶችን የያዙ የሰው ልጅ ይሰራቸዋል ተብለው የማይጠበቁ እጅግ የረቀቁ ሥራዎች ናቸው፡፡
እያንዳንዳቸው ከ2-15 ቶን የሚመዝኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ግዙፍ ድንጋዮች እንዴት አድርገው የአፍሪካና የላቲን ፒራሚዶችን ለማነጽ በዚያ ከፍታ ላይ ተጓጓዙ? አንድ ቶን ክብደት – አንድ ቤቢ ፊያት መኪና ማለት ነች፡፡ አስር ኩንታል፡፡ ወይም አንድ ሺህ ኪሎግራም፡፡ እንግዲህ ይህን ያህል ክብደት ያላቸውን ግዙፍ ጡቦች ይዘው በፒራሚድ ከፍታዎች ላይ እንደልባቸው ይዘው የሚመላለሱት የዚያን ዘመን ቀደምቶቻችን በመጽሐፈ ሄኖክ ተገልጠው የምናገኛቸው ‹‹ኔፍሊምስ›› ወይም ከአሁኑ ሰው እጅግ ግዙፋን የሆኑ ሰዎች ይሆኑ ወይ? ወይስ ክንፋሞች ይሆኑ ወይ?
ይህን ከሰው ልጆች የተለዩ እጅግ የመጠቁና ለሰው ልጅ ሥልጣኔን አጋርተው ወደመጡበት መመለስ የፈለጉ እጅግ የመጠቁ ግዙፋን ሰዎች እነዚህን የተራቀቁ የሰው ልጅ ጥበቦች የመሥራታቸውን ነገር በተለያዩ አሳማኝ ማስረጃዎች እያዳበረ እንደ አንድ ጠንካራ መላምት አስቀምጦት አልፎ እናገኘዋለን ግራሃም ሃንኩክን – ከአምስት ወይም ስድስት ዓመት በፊት ማለት ነው፡፡
ሰሞኑን አንድ ፈረንሳዊ ፕሮፌሰር በጊዜ ፒራሚዶች አካባቢ እጅግ የሚያስደነግጥ ብዛት ያለው የእንስሶች አጥንት በቁፋሮ ማግኘቱን ሲያስታውቅ፣ የብዙ ሪሰርቸሮችን ፍላጎት ስቦ ነበር፡፡ ፒራሚዶቹን የሚገነቡት ጥንታውያን አርክቴክቶችና መሃንዲሶች እጅግ ብዛት ያለው ምግብ ተመግበው ከነበረ፣ ምናልባት ግዙፋን ፍጡራን (ኔፍሊምስ) ሊሆኑ ይችላሉ በሚል፡፡ ፕሮፌሰሩ በዚህም በኩል እያጣሩት መሆኑን፣ ነገር ግን እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች መሠማራታቸውን የሚያመለክት ሊሆንም እንደሚችል ጠቁመው፣ ጥናታቸውን ሲያጠናቅቁ ግኝታቸውን ለዓለም ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ግራሃም ሃንኩክ በጁዳይዝም ዘመን የተጻፈውን የብሉይ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ያጠናዋል ለምርምሬ ከረዳኝ ብሎ፡፡ እና ሲናገር የሰሎሞን ቤተመቅደስ እንዴት እንደተሰራ በመጽሐፍ ቅዱስ ተዘርዝሮ የምናገኛቸው እጅግ አሰልቺና ዝርዝር የቁጥርና የመስፈሪያ ስሌቶችን ተመልከታቸው ይለናል፡፡ እያንዳንዱን ነገር በመስፈሪያና በልኬት እየመጠኑ ነው የሚናገሩት ነብያቱ ሁሉ በባይብል ላይ፡፡ ቋንቋውንና ዘዬውን ከየትም አላመጡትም፡፡ ከሚኖሩበት ማህበረሰብ የተገኘ ነው፡፡ ስለዚህም በብሉይ ዘመን ይኖሩ የነበሩት እነዚያ ሰዎች፣ አሁን ላይ ከምንኖረውና ሂሳብና ስሌት ከሚያነስረን ብዙዎቻችን የዘመኑ ሰዎች ይልቅ ሁለነገራቸው በሂሳብ ስሌትና መስፈሪያ የተሞላ ማህበረሰቦች ወይም ‹‹ኮምፒዩቴሽነል ሶሳየቲስ›› ነበሩ ማለት ነው፡፡
ግራሃም ሃንኩክና የጥናት ቡድኖቹ ታዲያ ያ ሁሉ ሥልጣኔና የሠለጠነ ማህበረሰብ ወደየት ገብቶ ነው እንደ እኛ አይነት ደናቁርት ትውልድ የመጣው? ለሚለው መልስ አላጣም፡፡ በብዙ እጅግ በሚያስደንቁና ጭንቅላትን በሚፈታተኑ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችና አሳምፕሽንስ እየተመራ – ምድሪቱ ልክ ከዛሬ 13ሺህ ዓመት በፊት እንደሆነው ሁሉ፣ ከፒራሚዶቹ (ስለዚህም እኛም ከአክሱሞቹ ብለን እንወስደዋለን) ዘመን በኋላ፣ በመሃል ምድራችን ከነህዝቦቿ በኖህ እንደሆነው በውሃ ተጠራርጋ ጠፍታ እንደነበረ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም የሚነገረን፡፡ ወደ ሃያ ዲግሪ የኬክሮስ (የምድር ወገብ) መስመሮች እኩሌታ የሚሆን ‹‹አንግል›› ገደማ ምድሪቱ ወደ ደቡብ ንፍቀ ክበብ ዘማለች፡፡ ይህም ማለት – በእነ ግራሃም ሃንኮክ ስሌት ከተመራን – ለምሳሌ ግብጾች ከነፒራሚዶቻቸውና የሰሜን አፍሪካ ማግሪቦች፣ ካርቲዥያኖች፣ ወዘተ በተፈጠረው ምድራዊ ክስተት ወደ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ባያዘምሙ (ቲልትድ ባይሆኑ) ኖሮ፣ ትክከለኛ ጂኦግራፊያዊ መገኛቸው የሚሆነው፣ ወይ አውሮፓ ወይ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ይሆን ነበር እንደ ማለት ነው፡፡
እኛስ? እኛ ደግሞ የታችኛው የሞያሌ ቦረና ድንበራችን ከምድር ወገብ 3 ዲግሪ ላይ የምንገኘው፣ ወደ ላይ ከፍ ብለን ወደ 23 ዲግሪና ከዚያ በላይ ከፍ ብለን ምናልባትም ሜዲትራኒያንን ተጎራብተን ልንገኝ ነው ማለት ነው፡፡ እና ግራሃም ሃንኮክና የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ፣ የላቲንንና የአፍሪካን ታላቅ የቀደሙ አባቶቻችንን ዘመናዊ የጥበብ ሥራዎች እንደምንም ብሎ ጎትቶ ከምድር ወገብ በላይ ወደሚገኙት ወደ ሰሜን አሜሪካና ወደ አውሮፓ ሜዲትራኒያን ቻይና አስገባቸው ማለት ነው፡፡ ይሄ ቅዠታም!! ሀሀሀሀ!! ለምን ከቻለ እንደ ፋሺስት ጣሊያን፣ ሀውልቶቻችንንና ፒራሚዶቻችንን ከነነፍሳቸው ነቅሎ አይወስዳቸውም? ወደ ደቡብ ወደ ሰሜን እያለ አሰቃየን እኮ በገብርኤል?!!
በበኩሌ አንድ ደጋግሜ የማነሳው ጥያቄ ግን አለ፡፡ እውነት ገጣሚው በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው፣ የቀደሙት አክሱምንና ሌሎችንም ታላላቅ አፍሪካዊ የሰውን ልጅ የሥልጣኔ ጫፍ የረገጡ በኩር የጥበብ ሥራዎችን አንጸውልን ያለፉት አባቶቻችን ክንፋም አባቶች ሳይሆኑ ይቀራሉ ወይ? ከክንፋሞች ተወልደን እንዴት ክንፈ ሰባራዎችና ክንፍ ሰባሪዎች ልንሆን ቻልን ታዲያ?
አባቶቻችን ታላቅን ጥበብ ሊከስቱልን የእጅ ሥራዎቻቸውን በተከሉባቸው መስኮች ላይ፣ ዛሬ እኛ ምን እየሠራን ነው? ጥበብን እየተጠበብን? ወይስ ጠባቦችን እያስጠበብን? ወይስ መጥበባችንን ለዓለም ከፍ አድርገን እያወጅን? – ህሊናችን ይፍረደን! ወይም ይፍረድብን፡፡ ቀድሞ ነገር ዓይኖቻችን ራሳችን ላይ ናቸው ወይ? ራሳችን ራሳችንን አጥንተነዋል ወይ? ራሳችን ራሳችንን እናውቀዋለን ወይ? እንተዋወቃለን ወይ ከራሳችን ጋር? በእርግጠኝነት ለመናገር ይከብዳል፡፡
በቅርቡ ደግሞ «አክሱም» የሚለው ቃል የመጣው «አከ» እና «ሱማ» ከሚሉ ሁለት የኦሮምኛ ቃላት መሆኑ ታወቀ የሚል የሰሚ ሰሚ ወሬ ደርሶኛል፡፡ የአክሱምን ስም ያወቀው ማን እንደሆነ አላወቅኩም፡፡ ግን ይህንንም በእርግጠኝነት ለመናገር ይከብዳል፡፡ እንደተባለው አክሱም የሚለው መጠሪያ ከኦሮምኛ ቃል ከመነጨ፣ የምንኮራበት ቀደምት ታሪካችንን ‹‹እድፍ›› ብለው በብሔራዊ መዝሙራቸው ያካተቱት ጠባቦች፣ ቢያንስ አከ-ሱማ ላይ አሻራቸው እንዳለበት አውቀው፣ ታሪካችንን አክ-እንትፍ ማለት ይተዉልን ነበር፡፡ እና በጊዜ ይጠናልን! (ይጠናስ ቢባል ኢሱ ይፈቅድ ይሆን? – አንድዬ ይወቅ!)
አንዱ ወጣት አጠገቡ የተቀመጡትን አዛውንት «ሀገርዎ ምን ያበቅላል?» ይላቸዋል መንገዱን የሚያዛልቅ ጨዋታ ለመክፈት አስቦ፡፡ እርሳቸው ደግሞ መንገዱ እየናጠ ሁለመናቸውን አዝሏቸዋልና ጨዋታ አልፈለጉም፡፡ እና ባጭሩ «ሁሉን!» ብለው ይመልሱለታል፡፡ ወጣቱ ግን አልለቃቸው አለ፡፡ «ባቄላም?» ይላቸዋል፡፡ «አዎ ልጄ!»፡፡ «ሽንብራም?»፡፡ «አዎ!»፡፡ «ዘንጋዳም?»፡፡ «አዎን!»፡፡ «ግብጦም?»፡፡ «አዎ!»፡፡ «ማሽላም?»፡፡ «እሱንም አዎ!»፡፡ «ዳጉሳም?»፡፡ «አዎ!»፡፡ «ኑግም?»…. ያለ የሌለ አዝርዕት በላያቸው እየደፋ በ«አዎ!» አሰቃያቸው፡፡
/ይሄን ስናገር የፕ/ር ኃይሌ ገሪማ ‹‹ጤዛ›› የሚል ፊልም ላይ ዋናው ተዋናይ በህልሙ ጎተራ ውስጥ ገብቶ መተንፈስ አቅቶት እስኪቃትት ድረስ እህል በላዩ ላይ እየፈሰሰ የሚያሰቃየው ኦርጂናሌ የአዝርዕት ሆረር (ቅዠት) ትዕይንት ትዝ አለኝና የራሴን በአዝርዕት የሚሰቃዩ አዛውንት ረስቼ ፈገግ አልኩ!/
ወጣቱ የእህል ዓይነት እየጠራ ሲያሰቃያቸው አዛውንቱ መጨረሻ እንዲህ ይሉታል፡፡ «አይ ልጄ! ሁሉንም ያልኩህ ከዚህ ለመገላገልም አልነበር?»፡፡ አፍሮ በሴይቼንቶው መስኮት ዘልሎ እንዳይወድቅ ስጋት ገባኝ፡፡ ጠላታችን ኩም ይበል፡፡ ኩም ብሎ ቀረ፡፡ እኔም አሁን ለራሴ «ሁሉን» ብዬ አበቃሁ፡፡ አለበለዚያ ስንቱን ነገር አንስቼ አውርቼ ጽፌ እዘልቀዋለሁ? ለሃሳብም እኮ ግፍ አለው!!! ምን በወጣኝ?!! ሀሀሀሀሀ…!!
ስሰናበት የሚበቃኝን ያህል ፈጣሪን አመስግኜ መሰናበት አማረኝ፡፡ መሻታችንን ሁሉ በጥበቡ የሚባርክ አምላክ፣ ስሙ እስከ ልጅ ልጅ ሁሉ ብሩክ ይሁን፡፡ የሻትነውን አይንሳን ፈጣሪ አምላክ፡፡ ማስተዋልና ጥበብ ያድርብን ዘንድ ሁላችንን ይርዳን እግዚአብሔር! ሳናውቅ በስህተት፣ አውቀን በድፍረት የሰበርናቸውን የአባቶቻችንን የጥበብ ክንፎች፣ የጠፉብንን የከፍታ ቅስቶች ያመልክተን ፈጣሪ አምላካችን፡፡ የዓለም መድኃኒት – መድኃኔዓለም – የሠላም አምላክ – አዕምሮን የሚያልፍ ሠላሙን ይስጠን፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው!
የጥበብ ምድር ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 
Filed in: Amharic