>

የጠ/ሚው ግራ አጋቢ ባሕርያትና ድርጊቶች (ይነጋል በላቸው)

የጠ/ሚው ግራ አጋቢ ባሕርያትና ድርጊቶች

ይነጋል በላቸው

ጠ/ሚኒስትር አቢይን የሚቀርቧቸው ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትን የመሰሉ ወዳጆቻቸውና አማካሪዎቻቸው አሁን እዚህ የምለውን አንብበው ለጠሚያችን ሊያካፍሏቸው ቢችሉ እጅግ በወደድኩና ራሴን እንደትልቅ ዕድለኛ በቆጠርኩ፡፡ ጠ/ሚንስትሩ ከሚያከናውኗቸው አንዳንድ ተግባራትና ከሚያሳዩዋቸው ተለዋዋጭነት የሚንጸባረቅባቸው ባሕርያት አኳያ ሰውዬው ያለመብሰል ጠባይ (Immaturity) እንደሚታይባቸው ብዙ ሰዎች ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ እኔም የነዚህ ሰዎች ተደማሪ ነኝ፡፡ ጠሚው ግራ አጋቢ ጠባይ ሞልቶ የሚፈስባቸው ሰው ናቸው፡፡ ለምሣሌ ሰሞኑን ዳግማዊ አላሙዲን አቶ ወርቁ አይተነው የሸለሟቸውን ወርቅ ለማንትስ አንዷለም ሰጥተዋል አሉ፡፡ ከዚህ በፊትም የሆነ ሽልማት ለለማ መገርሣ አስተላልፈዋል፡፡ ሸላሚዎችም አያርማቸውምና እንደማይቀበሏቸውና እንደሚያራክሱባቸው እያወቁ መሸለማቸውን ቀጥለዋል – “ከኛ ይውጣ እንጂ ቢጥሉትስ ምን አገባን” ከሚል የተለጠጠ ቸርነት በመነሳት ይመስላል፡፡ ግን በምንም ምክንያት ይሁን ሽልማትን እስከዚህ ማራከስ ነውር መሆኑን በጨዋ ደምብ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ ለማንኛውም በተጨባጭ ከሚስተዋሉባቸው የማልወድላቸው መጥፎ ተግባሮቻቸውና ጠባዮቻቸው በጣም የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

  1. ከዚህ በላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በማንም ያላየሁት አንድን ለራስ የተሰጠ ሽልማት በተመሳሳይ መድረክ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ፡፡ ይህ ነገራቸው ጭራሽ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሌሎች ተሸላሚዎች የተሸለሙትን ነገር በፍቅር ተቀብለው ሲወስዱና ለላንቲካነት በክብር ቦታ እቤታቸው ሲያስቀምጡት እንጂ እንዳልባሌ ዕቃ ለሚወዱት ሁሉ ሲረጩት ወይ ሲበትኑት አይቼ አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው – አንዳንድ ሰዎች ሲያረጁና ሽልማቱ ከሀገር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን ለመንግሥት ሙዚየሞች በስጦታነት ሲያበረክቱ አልፎ አልፎ አያለሁ – በተለይ ወራሽ ቤተሰብ መኖሩ ሲያሳስባቸው፡፡ ሽልማትን በዚህ ጠሚው በተያያዙት መንገድ ማባከን ማለት ግን ለኔ የሚሰጠኝ ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡-
    1. ተሸላሚው ሸላሚውን አይወደውም ወይም ይንቀዋል፡፡
    2. ተሸላሚው ሽልማቱ እንደማይመጥነው አምኖ ያፍርበታል ወይም በተሸለመው ነገር ምክንያት ሌላ ሦስተኛ ወገን እንዳያኮርፍበትና “የኔ አይደለህም፤ ከጠላቴ ተሸልመሃል –  እኔንም አዋርደሃል” በሚል የማግለል እርምጃ እንዳይወስድበት መጠንቀቅ ፈልጓል፡፡
    3. የሽልማትን ትርጉም ከናካቴው የማያውቅ ሞኝ ነው (ይህ ለጠሚው አይሠራም)፡፡
  2. ሰውን በአደባባይ በማዋረድ የራስን ከፍታ በተዛዋሪ መግለጽ፡፡ ጠሚው አዘውትሮ ከሚያሳያቸው መጥፎ ጠባያት አንዱ ሌሎችን በአደባባይ መዝለፍና በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ማዋረድ ነው፡፡ ለአብነት እኚሁ ዳግማዊ አላሙዲን ‹በትምህርት ስድስተኛ ክፍል ሆነው ሳለ የከብት ጭራ መከተል ሲገባቸው እንዲህ ቱጃር ሆነዋል› ማለታቸው የተማሩትንም ያልተማሩትንም በአንድ ጥይት የሚመታ በሁለት ወገን እጅግ የተሣለ ሠይፍ ነው፡፡ ይህ ጠባያቸው በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ ከዚህ በፊትም ተማሩ የተባሉትን ዜጎች በስድብ የሞለጩበት አጋጣሚ አለ፡፡ ለራስ ክብር ለማግኘት በቅድሚያ ሌሎችን ማክበር እንደሚቀድም ይነገራቸው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ አንድን ትልቅ የሥልጣን ቦታ ያገኘ ሰው ከሁሉም ዜጎች የላቀ ዕውቀትና ችሎታ አለው ማለት እንዳልሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ ለነገሩ “ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት” መባሉ ቀርቶ የተገላቢጦሽ ዘመን በመሆኑ እምባጮና ደደሆ ታቦት በሚሆኑበት ዘመን ለዜጋው ተገቢውን ክብር የማይሰጥ ተሳዳቢና አንጓጣጭ የሀገር መሪ ቢታይ አይገርምም፡፡ ዕድል ነው፡፡ በተለይ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ጥሩና ጨዋ የሚባል መሪ አላገኘንም፡፡

ዜጎች ሲታረዱ አዘኔታንና የሁሉም ወገን መሪነትን አለማሳየት፡፡ እርሳቸው እወክለዋለሁ ብለው ከሚያምኑት ዘውግ አንድ ታዋቂም ሆነ ተራ ዜጋ ሲሞት ያዘኑ መምሰላቸውን ለመግለጽ የማይሄዱበት ርቀት የለም፤ “ሟቹ የረጂም ዘመን ጓደኛየ ነበር” በማለት የዕድሜና የሥራ መስክ ልዩነታቸውን ጭምር ለትዝብት ክፍት አድርገው ያለ አንዳች ሀፍረት በአደባባይ የዓዞ ዕንባ ሲያነቡ ይታያሉ፡፡ ይህንንም መጥፎ ጠባይ በሃጫሉ ሁንዴሣ ሞት አይተን ተገርመናል፡፡ ሌሎች ወገኖች በማንነታቸው ምክንያት በብዛት ሲገደሉና ከተማቸው ሲወድም ያዘኑ መስሎ ለመታየት ይቅርና ገዳይ ወገኖችን ለማስደሰት በሚመስል አኳኋን ነጫጭ ለብሰው የመናፈሻ ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ሲመርቁ ይታያሉ፡፡ ይህን ግፍ ፈጣሪ አይመለከትም ብለው ካሰቡ እጅግ ተሳስተዋል፡፡ ምክንያቱም  ፈጣሪ ሰው አድርጎ ፈጠረ እንጂ እንደጠሚው ሸፋፋ አተያይ ኦሮሞና አማራ ወይ ትግሬና ሶማሌ አድርጎ አልፈጠረም፡፡ አስመሳይነታቸውና የውሸት ትርክት መድብላቸው ደግሞ ብዙ ያናግር ነበር፡፡ ለአሁኑ ግን ይብቃኝ፡፡ ሰሚ ከተገኘ ይህም ከበቂ በላይ ነው፤ ዋናው ነገር ደግሞ እግዜር ይስማኝ፡፡ 

Filed in: Amharic