ዛሬ፤ የፖለቲካ ዓለም ማዕከሉ ኃይል ሳይሆን፤ ዕውቀት ነው።
ነፃ አስተያየት፤ በአንዱ ዓለም ተፈራ
አምባገነኖች የሥልጣን ጊዜያቸውን የሚያራዝሙት ሕዝቡን በማደንቆር ነው።
እኛ በምንኖርበት ዘመን፤ አዋቂዎች ለአምባገነንነት አይመቹም። የራስን ጥቅም ከሌሎች ላይ ለማግኘት፤ ቅኝ ግዛቶችን በማስፋፋትና የወረሩትን አካባቢ ጨቁኖ ለመግዛት፤ ምዕራባዊያን ለዘመናት ኃይል ተጠቅመዋል። ውሎ አድሮ፤ የተጨቆነው ክፍል ዕውቀት ሲያገባ፤ አምፆ ነፃነቱን አግኝቷል። የዚህ ሂደት አንዱ ክፍል፤ የምሥራቁ ዓለም መነሳት ነው። በምሥራቁ ዓለም ጎላ ያለውን ቦታ ይዘው የሚገኙት ሩስያና ቻይና ናቸው። እኒህ ደግሞ በአስተዳደራቸው፤ ከምዕራባዊያኑ አገዛዝ አንጻር፤ ልዩ ርዕዩተ ዓለም አዝለው ተነሱ። በዚህ የምሥራቅና ምዕራብ ጉንተላና የቅኝ ግዛቶች ግብግብ ዘመን ነው ማዖ ዜዱንግ፤ “የፖለቲካ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ይመነደጋል!” የሚል መፈክር የፈነቀሉት [Political power … comes from … the barrel of a gun (Mao Zedong – 毛泽东)]። ይሄ አባባል፤ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ፤ እስካሁን ድረስ በየቦታው የሚጠቀስና፤ በተለይም ግራ ቀመስ በሆነው የፖለቲካ ቅኝት፤ ከፍተኛ ግምት የተሠጠው ነው። አሁን ላለንበት ዘመን ግን፤ ይሄ አይሠራም። ዛሬ፤ የፖለቲካ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን፤ ከሕዝቡ ዕውቀት ማነሳ ወይንም ማደግ ጋር የተቆራኘ ነው። አዋቂዎች የአምባገነኖች ዋና ጠላት ናቸው። አዋቂዎች፤ የዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚያደላድሉ ተቋማትን በማበጀት፤ ለአምባገነንነት ማነቆ ሠርተው፤ መቆሚያ መደላድል ይነሱታል። እናም አዋቂዎች ለአምባገነኖች ዕንቅፋት ናቸው። አምባገነኖች የሥልጣን ጊዜያቸውን የሚያራዝሙት፤ ሕዝቡን በማደንቆርና፤ በዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ ነው። ሕዝቡ ዋና ዋና በሆኑ አገር ተኮር ጉዳዮች ላይ እንዳይጠመድ፤ ርስ በርሱ በማናከስና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንዲገዛ በማድረግ፤ እነሱ የተደላደለ ዘመን ያገኛሉ።
ይሄን ከጠቆምኩ በኋላ፤ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደ ሆነኝ ልመለስ። “የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ (ክፍል ፫ )” በሚለው ጽሁፌ ላይ፤ የፖለቲካ አመለካከትን ለመለወጥ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ “ሕዝቦች” የሚለውን ቃል እንዴት እንዳንሸዋረረው አስፍሬ ነበር። ዕውቀትና ድንቁርና ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር ያላቸውን ዝርዝር ትስስር፤ እዚህ ላይ አላቀርብም። ማድረግ የፈለግሁት፤ አሁን ባገራችን፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከድህረ ምርቃት መምህራን እስከ ቤተ ክህነት አባቶች፣ ከመንደር አባወራዎች እስከ ከፍተኛ የአገር መሪዎች ድረስ፤ በፀያፍ ብዜት የተለከፉበትን፤ ባደባባይ ማዋል ነው። ቃላት በመካከላችን ባለው ግንኙነት ውስጥ ምሰሷዊ ቦታ አላቸው። እናም የምንጠቀምባቸው ቃላታ፤ የኛን ዕውቀትና የኅብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ይገልጣሉ። አንዳችን አንድ ነገር ስንናገር ሌላችን የምንረዳው፤ ሁላችን የምንግባባበት የአገርኛ ቋንቋችን ሰዋሰው ስላለው ነው። እያንዳንዳችን እንደፈለግነው ቋንቋውን ልናሽከረክረው አንችልም። ያ ከሆነ መግባባቱ ጥሎን ይጠፋል።
አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ፤ በአገርኛ የሰዋሰው ትምህርት፤ በስም ውስጥ፤ ፀያፍ አበዛዝ የሚል ክፍል ነበረው። ቃል፤ ነጠላ ወይንም ብዙ ይሆናል። ትክክለኛ ያልሆነ ደግሞ፤ “ፀያፍ” የተባለ ብዜት አለው። ይሄ ብዜት ፀያፍ፣ ነውር፣ ተገቢ ያልሆነ ነው። የትምህርቱ ጥራት ይሁን አራሚ ባለመገኘቱ፤ ይህ ስህተት ባሁኑ ሰዓት፣ በየቦታው፣ በሰዎች ንግግር ውስጥ ተደላድሎ ቤቱን ሠርቷል። ዝርዝሩ ግልጥ ስለሆነ፤ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ በማስቀመጥ አሳያለሁ።
ነጠላ ቃል ብዙ ፀያፍ
ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊያኖች
ኢትዮጵያዊት ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊያኖች
አገር አገራት አገራቶች
ሕግ ሕግጋት ሕግጋቶች
ተግባር ተግባራት ተግባራቶች
ቃል ቃላት ቃላቶች
ሊቅ ሊቃውንት ሊቃውንቶች
ምሁር ምሁራን ምሁራኖች
ርእስ/ አርእስት አርእስት አርዕስቶች
አርብቶ አደር አርብቶ አደራት አርብቶ አደራቶች
ቤተ ክርስትያን ቤተ ክርስትያናት ቤተ ክርስትያናቶች ወ. ዘ. ተ.
ይሄ የሆነው፤ የግዕዝ ቃል አበዛዝን ከአገርኛው አበዛዝ ጋር በመዳበል፤ የሁለቶችን አበዛዝ ባንድ ቃል ላይ በመደንጎር ነው። በአገርኛው፤ ኢትዮጵያዊ የሚለውን ቃል፤ የተባዕቶችን ስብስብ ብቻ ለመግለጥ፤ ኢትዮጵያዊዎች ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያዊት የሚለውን ቃል፤ የእንስቶችን ስብስብ ብቻ ለመግለጥ፤ ኢትዮጵያዊቶች ማለት ይቻላል። ለኔ ግን፤ ኢትዮጵያዊያን የሚለው፤ የተባዕትን ስብስብ ሆነ የእንስትን ስብስብ፤ ብሎም የዝንቅ ስብስብን ለመግለጥ ስለሚያገለግል፤ ይሄኑ መጠቀም እወዳለሁ። ይሄ ትምህርት፤ በሊቃውንቱ በነዶክተር ጌታቸው ኃይሌ እና ዶክተር ዘሪሁን አስፋው ቢሆን ደስ ይለኛል። ነገር ግን፤ ማንኛውም ግለሰብ፤ ስህተትን እስከተገነዘበ ድረስ፤ ከማረም ተጠያቂነት ስለማይድን፤ እኔም ኃላፊነቴን ለማወራረድ ነው። አርእስት የሚለው የአማርኛ ቃል ብዛት የለውም።
“ባላዋቂ ቤት እንግዳ ናኘበት” እንዲሉ፤ የእኛን አነጋገር በትክክል መቅዳት ያልቻሉ የውጪ አገር ሰዎች ያሉትን መልሰን እኛው ቀጂ ሆነን የተገኘንበትን ላመላክት። ራስ ደጀን በጎንደር፤ ስሜን ውስጥ የሚገኘው ያገራችን ቁንጮ ተራራ ነው። እናም ራስ የሚለው መግለጫ ተሠጥቶታል። ደጀንነቱ ደግሞ ከግዝፈቱ ጋር የተያያዘ ነው። ደጀን፣ ደጃዝማች፣ ደጀኔ እንዲሉ። ታዲያ ራስ ዳሸን ማለት ምን ማለት ነው! ለምንስ ነው የውጪ ሰዎች ማለት ስላልቻሉበት፤ የነሱን ድንቁርና እኛ የምንቀዳው!
ጠለቅ ብለን ብንመረምረው፤ ይህ የሚያሳየው፤ ለራሳችን ያለን የማንነት ግምትና፤ የራሳችን የሆነን ነገር ምን ያህል እንደምናከብር ነው። በመጀመሪያ ራሱን የማያከብር ሌሎችን ሊያከብር ችሎታው ይጎድለዋል። ራሱን ከሌሎች ዝቅ አድርጎ ያስቀመጠ፤ በራስ መተማመን የለውም። ማሳየት የፍለግሁት፤ ወደ ራሳችን እንድንመለስ ነው።