>
5:33 pm - Tuesday December 6, 1070

አንቲ-ቫይረስ፣ ሶሻል-ፊልተሪንግ፣ እና ፊልቴር-ጠላ! (አሰፋ ሀይሉ)

አንቲ-ቫይረስ፣ ሶሻል-ፊልተሪንግ፣ እና ፊልቴር-ጠላ!

አሰፋ ሀይሉ

 

*…. ይህ ፖለቲካዊ ሶሻል-ፊልተሪንግ እንደ አንቲ-ቫይረስ ሶፍትዌሮች ሲስተሙን ስካን አድርጎ ለሲስተሙ ጤንነት አደገኛ የሆኑ ቫይረሶችን ሲያገኝ፣ የግድ ኳራንታይን በመክተትና በመግደል ብቻ አይደለም ቫይረሶቹን የሚያመክናቸው፡፡  ቫይረስ ወደሌላው አፕሊኬሽን እንዳይዛመት እንደሚደረገው፣ መንግሥቶችም ተቋሞቻቸውን በማብዛትና አሠራራቸውንና የሚንቀሳቀሱበትን መስክ ለየብቻ በመነጣጠል፣ አንዱ ቦታ የተቀሰቀሰው አመጽ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዛመት ጠንክረው ይሰራሉ፡፡ 
 
፩. አንቲ-ቫይረስ፡-
አንቲ-ቫይረስ የሚባሉት ሶፍትዌሮች አገልግሎታቸው ምንድነው? – የሲስተሙን መደበኛ አሠራር (ስቴብሊቲ) የሚያውኩ ፕሮግራሞችን (ወይም ቫይረሶችን) ከኮምፒውተሩ ውስጥ ‹‹ስካን›› እያደረገ ወይም እያሰሰ ማግኘት ነው፡፡ ቫይረሶቹን ሲያገኛቸው ምን ያደርጋቸዋል? አንድ የቫይረሶቹን ማንነትና ብዛት ከነባህርያቸው ይመዘግባል፡፡ ሁለት በቫይረሶቹ የተጠቁ የሲስተሙ ክፍሎች የትኞቹ እንሆኑ ይጠቁማል፡፡ ሶስት ቫይረሶቹን ይገድላል ወይም ያስወግዳል፡፡ አራት ቫይረሶቹን ሲገድል ከቫይረሶቹ ጋር የተጣበቁ የሲስተሙን ፕሮግራሞችና መረጃዎች አብሮ ሊገድል የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር – ቫይረሶቹ ቢገደሉ ሲስተሙ መረጋጋት አይችልም፡፡ ስለዚህ አራተኛ ተግባሩ ቫይረሶቹ እስኪጠሩ ወደሚከረቸሙበት የሲስተሙ ‹‹ኳራንታይን›› (የሲስተሙ ማዕከላዊ እሰርቤት) መክተት ነው፡፡
፪. ሶሻል-ፊልተሪንግ፡-
ሶሻል-ፊልተሪንግ የሚባለው ጽንሰ-ሀሳብ (አሠራር) ምንድነው? ‹‹ሶሻል-ፊልተሪንግ›› ከዝግመተ-ለውጥ ፅንሰ-ሀሳብ የዘር ሀረጉን የሚመዝ ለማህበረሰብ ህልውና አስጊ የሆኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ቀስ በቀስ በማህበረሰቡ ሥርዓት አማካይነት እንደ እንክርዳድ እየተንገዋለሉና እየተለቀሙ ከኮሙኒቲው የሚወገዱበት ተፈጥሯዊ ሂደት ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት በዓለማችን የሠለጠኑ መንግሥታት ለፖለቲካ ዓላማ ጥቅም ላይ ከዋለ በርካታ ክፍለዘመኖች ተቆጥረዋል፡፡ ሶሻል-ፊልተሪንግ በመንግሥታዊ ፖሊሲ የማይፈለጉ የህብረተሰብ ባህርዮችንና አመለካከቶችን ወይም እነዚህን የተላበሱ ግሰለቦችንና ቡድኖችን ከማህበረሰቡ መሐል በማጥለያ አጥልሎ በማውጣት፣ የሚወገዱበት መንገድ ነው፡፡
ሶሻል ፊልተሪንግን ለመተግበር መንግሥቶች ሰላዮችን በህዝቡ መሐል ያሰማራሉ፡፡ በሥርዓቱ ላይ የሚያምፁና የሚያሳምፁትን ከማህበረሰቡ መሐል ለማስወገድ (ለብቻቸው በከርቸሌ በማሰር፣ ወይም በመግደል) ህግ ያወጣሉ፡፡ ፍርድቤት ያቋቁማሉ፡፡ ለሥርዓቱ መረጋጋት ጠቃሚ የሆኑ ሐይማኖታዊና ዓለማዊ ተቋማትን ያበረታሉ፡፡ በትምህርት ካሪኩለምና ተቋማት ተጠቅመው ለሥርዓቱ ታዛዥና ተስማሚ ዜጋ በብዛት ያመርታሉ፡፡
ልክ አንቲ-ቫይረስ ሶፍትዌሮች ሲስተሙን ‹‹አንስቴብል›› የሚያደርጉትን ቫይረሶች ፈልጎ አግኝቶ በመመዝገብ ኳራንታይን እንደሚከታቸው ወይ እንደሚገድላቸው፣ ሶሻል-ፊልተሪንግ ቱሎች (መሣሪያዎችም) ለመንግሥታዊ ሥርዓቱ አደገኛ የሆኑ ቫይረሶችን (ለውጥ-ፈላጊ አመጸኞችንና አመፅ-ቀስቃሾችን) እያሰሰ፣ ማንነታቸውንና የሚንቀሳቀሱበትን ሥፍራ እየመዘገበ፣ በአመፅ አስተሳሰባቸው የለከፉትንና ያልለከፉትን እያጣራ፣ ወይ ከማንም ወደማይገናኙበት ወደ ከርቸሌ ይከትታቸዋል፣ አሊያም ይገድላቸዋል፡፡
ይህ ፖለቲካዊ ሶሻል-ፊልተሪንግ እንደ አንቲ-ቫይረስ ሶፍትዌሮች ሲስተሙን ስካን አድርጎ ለሲስተሙ ጤንነት አደገኛ የሆኑ ቫይረሶችን ሲያገኝ፣ የግድ ኳራንታይን በመክተትና በመግደል ብቻ አይደለም ቫይረሶቹን የሚያመክናቸው፡፡ ቫይረሶቹ (አማፂዎቹ) እርስ በእርስ እንዳይገናኙ ያደርጋል፡፡ ልክ በኮምፒውተር ፕሮግራሞች ላይ እያንዳንዱ አፕሊኬሽን ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ – አንዱን አፕሊኬሽን ያጠቃው ቫይረስ ወደሌላው አፕሊኬሽን እንዳይዛመት እንደሚደረገው፣ መንግሥቶችም ተቋሞቻቸውን በማብዛትና አሠራራቸውንና የሚንቀሳቀሱበትን መስክ ለየብቻ በመነጣጠል፣ አንዱ ቦታ የተቀሰቀሰው አመጽ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይዛመት ጠንክረው ይሰራሉ፡፡
ሌላው ሶሻል-ፊልተሪንግ ሜካኒዝም – ፖለቲካል ከንዲሽኒንግ ነው፡፡ ይህ ዘዴ ለመንግሥታዊ ሥርዓቱ ቀጣይነት አደገኛ ሆነው የሚገኙ ሰዎችንና ቡድኖችን ከማንኛውም ዓይነት ጥቅም፣ ሥልጣን፣ የኑሮ አቅምና ማህበራዊ ቅቡልነት ውጪ ማድረግ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ለመንግሥታዊ ሥርዓቱ ተረጋግቶ መቀጠል በጎ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ወይም ሥርዓቱን የሚያገለግሉ የሥርዓቱን ታዛዦች የጥቅም፣ የሀብትና የሥልጣን ተካፋይ አድርጎ፣ ማህበራዊ ቅቡልነትና ስኬት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሪዎርድ-ፐኒሽመንት ዘዴ – መንግሥቶች ማህበረሰባቸውን ለመንግሥታዊ ሲስተሙ በሚመች መንገድ ይቀርጹታል ወይም ይመሩታል፡፡ እነዚህም እጅግ በረቀቁ እና እጅግ ዘርፈ-ብዙ በሆኑ መንገዶች የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
፫. ፊልቴር ጠላ፡-
ፊልቴር ጠላ የሚባለው እንኩሮው በቀጥታ በማሰሮው ውስጥ መከተቱ ቀርቶ፣ በማሰሮው አንገት ላይ በገመድ ታሥሮ ወደ ማሰሮው ሆድ በገባ ጆንያ አማካይነት እህሉ፣ ጌሾው፣ ቂጣው፣ ወዘተ ይነኮርና ከዚያ እየጠለለ የሚንጠባጠበው ፈሳሽ በማሰሮው ይጠራቀማል፡፡ ሲጠጣ የጠለለ (ፊልቴር የተደረገ) ጠላ ነው፡፡ ገፈት አይኖረውም፡፡ ዝቃጭ አይኖረውም፡፡ ሲጠጣ እንደልብ በነጻነት ይጠጣል፡፡ በደንብ ተብላልቶ ስለጠለለም ሀይሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከደጋገሙት ጥሩ አድርጎ ያሰክራል፡፡
፬. አንቲ-ቫይረስ፣ ሶሻል-ፊልተሪንግ፣ እና ፊልቴር-ጠላ!
አንቲ ቫይረስ ለኮምፒውተር-ነክ ፕሮግራሞች የተገጠመ የፊልቴር ጆንያ ነው፡፡ ሶሻል-ፊልተሪንግ ለፖለቲካዊ ሥርዓቶች (ለመንግሥቶች) የተገጠመ የፊልቴር ጆንያ ነው፡፡ አሁን ይህን ጽሑፍ ስጽፍ ዘመናውያኑ ሀያላን መንግሥታት ‹‹ለቶውት ኮንትሮል›› ወይም ‹‹ሶሻል ፊልተሪንግ›› የሚጠቀሙበት ፌስቡክ – የምንጽፈውን ጽሑፍ ይዘት፣ ለእነማን እና ለምን ያህል ሰዎች መድረስ እንዳለበት፣ የሚነቀፍ (ፊልተር የሚደረግ) ነገር እንዳለውና እንደሌለው – ያለማቋረጥ እያጠለለና እየመዘገበ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው እጅግ ግዙፍ የሆኑ መረጃዎችን ወደ ጆንያቸው ከትተው እያብላሉ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው፣ ለስካር ምቹ የሆነ ማለፊያ ጠላ ማምረት የሚችሉ ሜጋ ኮምፒውተሮቻቸውን እየተጠቀመ ነው፡፡
በየመንግሥታቱና በየተቋማቱ ያሉ ቃል-አቀባዮች ወይም የህዝብ-ግንኙነት ክፍሎች፣ ጋዜጠኞች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ፖሊሶች፣ ሹመኞች፣ መምህሮች፣ ሰባኪዎች፣ ድምጻዊዎች፣ ነጋዴዎች፣ አትሌቶች፣ አርቲስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ መሃንዲሶች፣ ሃኪሞች፣ ወዘተ. ወዘተ. ሁሉ አውቀውትም ሆነ ባለማወቅ በብዛት የምናገኛቸው የዚሁ ሶሻል-ፊልተሪንግ አስፈጻሚ አካሎች ናቸው፡፡ ሁሉም አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር እየተጋገዙ – ‹‹ጤነኛ›› ዜጋ በማፍራት ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ለትውልዱ ‹‹አርዓያ›› እየሆኑ ነው፡፡ በየተሠማሩባቸው ዘርፎች ጠንካራ ‹‹ዲሲፕሊን›› እያነፁ ነው፡፡
እንግዲህ በፖለቲካል-ፊልተሪንግ ቋንቋ – ‹‹ጤነኛ›› ዜጋ ማለት ከአመጽ አስተሳሰብ ቫይረሶች የነጻ፣ ወይም በሥርዓቱ ቀጣይነት ላይ አደጋ የማይፈጥር ዜጋ ማለት ነው፡፡ ‹‹አርዓያ›› የሚሆን ዜጋ ማለት በሥርዓቱ ላይ አመጽ በማያስነሳ የህይወት መስክ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ዜጋ ማለት ነው፡፡ በ‹‹ዲሲፕሊን›› የታነፀ ዜጋ ማለት – ለሥርዓቱ ዕድሜና ጤና ሲባል በጥንቃቄ የተዘረጋለትን የሥርዓቱን ደንቦችና መንገዶች አክብሮ የሚንቀሳቀስ፣ ታዛዥ፣ ህግ አክባሪ፣ እግዜርን ፈሪ፣ ባለሥልጣንን ፈሪ፣ እና ለባርነት ፍጹም ራሱን ያመቻቸ ዜጋ ማለት ማለት ነው፡፡
በዚህ ሶሻልፈ-ፊልተሪንግ ጽንሰ-ሀሳብ በተለመደ ሀሳባችን ተቃራኒ የሚመስሉን ነገሮች ሁሉ እኩል መንግሥታዊ ቅቡልነት ተሰጥቷቸው በአርአያነት ይቀነቀናሉ፡፡ ለምሳሌ ቢሊየነሮች ወይም ሞጃዎች – ሰዎች ጠንክረው ከሰሩ፣ ከነገዱ፣ በመንግሥት አታድርጉ የተባሉትን (ወንጀሎች) ካልሰሩ፣ ከሌሎች የሥርዓቱ አርዓያዎች ጋር መልካም ግንኙነት ከፈጠሩ፣ የሚመኙትን ሁሉ ማግኘት እንደሚችሉ የሚያሳዩ የሶሻል-ከንዲሽኒንጉ አሪፍ ሶሻል-ሞዴሎች ናቸው፡፡
ግን መናጢዎችስ? የሚገርመው ባለሀብቶችን ሶሻል-ሞዴል አድርጎ የሚያቀነቅነው የመንግሥታት ሲስተም – የኔቢጤ ለማኞችንም ደግሞ ማህበረሰባዊ አርዓያ አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ ለምን? የኔቢጤው ሲቸግረው ለምን በዚህች ሀገር እኩል ተፈጥሬ ጾሜን አድራለሁ? ብሎ የማይጠይቅ፣ እየዞረ የሰውን አንጀት እየበላ በልመና የሚኖር ነው፡፡ አርዓያ ያለው ሙያ ነው፡፡ የቱንም ያህል ቁሳዊ ችግር ቢገጥማቸው ዜጎች መብታቸውን በሀይልና በአመጽ ተግባር ከማስከበር ይልቅ በልመናና በማሳዘን እያገኙ መኖር እንደሚችሉ ህያው ማስረጃ ወይም ‹‹አርዓያ›› ነው፡፡
በዚህ አንጻር ስንዘረዝረው ሌላ ቀርቶ ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚሰብከው፣ ሎተሪ እያዞረ የሚሸጠው፣ ዋናዋ መንግሥት ከምድር ወዲያ ያለችው ነች ለዚች ጊዜያዊ ድንኳን አትጨነቁ የሚለው፣ በሰላሳ ዓመት ከበለፀጉ ሀያላን ሀገራት ተርታ አሰልፋችኋለሁ የሚለው፣ ፈጣሪ ከዓለም ሀብት ሁሉ በላይ የሆነውን ጤንነትን የመሰለ ሀብት ሰጥቷችሁ ሌላ ነገር ካልሰጠኸን እያላችሁ ለምን ታማርራላችሁ? የሚለው፣ እና በውጊያና በጦርነት ሳይሆን በሩውዝ (በሩጫ፣ ውርወራና ዝላይ) የወጣልህ ሚሊየነር መሆን ትችላለህ፣ እኔን ተከተለኝና፣ ጧት ጧት ዳገቱን በሶምሶማ እየወቃህ ወደ እንጦጦ መናፈሻ ሩጥ የሚልህ – እነዚህና ሌሎች ሚሊየኖች ዓይነት ድምጾች – በዘመናዊው ሶሻል-ፊልተሪንግ የተፈጠሩልህ – ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ …. አንቲ-ቫይረሶች ናቸው፡፡
ዘመናችን እዚህ ደርሷል! የምናገረው ሣይንስ ነው፡፡ የምጽፈው ሀቅ ነው፡፡ ራስህን ፈልግ፡፡ አካባቢህን ተረዳ፡፡ ሚናህን ወስን፡፡ አበቃሁ፡፡
ደብል ፊልቴር ጠላ አማረኝ!
ቸር እንሰንብት!
________________________________________
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አቻ የአማርኛ ቃል የሚገኝላቸውን፣ ወይም ትክክለኛ ፍቺ ሊቸራቸው የሚገቡ የእንግሊዝኛ ቃላትን እንደወረዱ ተጠቅሜባቸዋለሁ፡፡ ከይቅርታ ጋር፣ አንባቢው የራሱን ማጥለያ (ፊልቴር) ተጠቅሞ እንዲያነብ አደራ እላለሁ፡፡
Filed in: Amharic