>

ግብጽ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ጐዳና...!!! ክፍል  ሁለት (ቢኒያም መስፍን)

ግብጽ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ጐዳና…!!!

ቢኒያም መስፍን. ክፍል  ሁለት

 

የመካከለኛው ዘመን ግንኙነት
ግብፆች ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ ፍሰትን እንዳታሰናክል እና አቅጣጫውን እንዳታስቀይር የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክን ገፀ በረከት በማስያዝ ለምልጃ ወደ ኢትዮጵያ ነገስታት ይልኩ እንደነበር ይገለፃል:: የአባይ ወንዝን በማስፈራሪያነት በመጠቀም በግብፅ እና በእስልምና ሀይማኖት ላይ ጫና ለማሳደር የሚያስፈራሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበረም:: 
ይህን በተመለከተ አቶ ሀይሉ በመጽሃፋቸው “ከአስራ አራተኛው ምዕተ አመት አጋማሽ ጀምሮ አውሮፓውያን ክርስቲያኖች ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የጀመሩትን ትግል ለማሳካት የዝነኛው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ፕሪስተር ጆን /በውል ማንነቱ ያልታወቀውን/ እርዳታ እና ድጋፍ መጠየቃቸውን በመካከለኛው ዘመን ላይ የተፃፈ ዜና መዋእል ያወሳል” ብለው ጽፈዋል::
በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን በግብፅ ውስጥ የነበረ አልናስር ሙሀመድ የተባለ አንድ ሱልጣን የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞችን መግደል እና ቤተክርስቲያኖቻቸውን ማጥፋት ይጀምራል:: ይህ ድርጊት ያስቆጣቸው አፄ አምደ ጽዮን በ1321 ወደ ካይሮ መልእክተኛ ልከው ሱልጣኑ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱትን በደል እንዲያቆሙ ካልሆነ ግን የአባይን አቅጣጫ በማስቀየር የግብፅን ህዝብ ለችግር እንደሚዳርጉ ማስጠንቀቃቸውን ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ የተባሉ የታሪክ ምሁር ፅፈዋል:: 
ቀጥሎም አፄ ዘረያዕቆብ የግብፅ መንግሥት በቁጥር አናሳ በሆኑ የግብፅ ክርስቲያኖች ላይ ያደርስ የነበረውን ግፍና ጭቆና በተደጋጋሚ ይሰማሉ:: በዚህም “የዓባይን ወንዝ የውሃ ፍሰት አቅጣጫ ቀይሬ ወደ ግብፅ እንዳይፈስ አደርጋለሁ” እያሉ የግብፅ መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ንጉሱ ያስጠነቅቁ እንደነበር ጸሐፊው ተርከዋል። 
በግብጽ በኩልም በተመሣሣይ መልኩ አባይን ለመቆጣጠር እና ኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ጫናን ለማሳደር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረጓን የታሪክ መረጃዎች ያመላክታሉ:: አንድሪው ካርልሰን ይህን በተመለከተ “ግብጽ ኢትዮጵያ ውስጥ በሀይማኖት ምክንያት ግጭት እንዲፈጠር እና ኢትዮጵያ አንድትተራመስ ራሳቸውን ኢትዮጵያውያንን ትጠቀም ነበር:: ለዚህም እንደ አብነት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አህመድ ወራሪነት የተከፈተው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ጦርነት የግብፅ እጅ አለበት” በማለት ጠቅሷል::
በአጠቃላይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ሊቃውንትም ሆኑ የመልክዓምድር አጥኚዎች ኢትዮጵያ ግብጽን ከምድረገፅ ለማጥፋት ጥቁር አባይን ወደ ቀይ ባህር ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመጥለፍ ትችላለች የሚል አስተሳሰብን ያራምዱ ነበር:: ነገር ግን የዲፕሎማቲክ ተልዕኮን ይዞ በ1540 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የነበረው አልባሬዝ እና በ1618 ዓ.ም በሚያዚያ ወር አባይ ምንጭ ድረስ ዘልቀው የነበሩት ጀስዊቶች የአባይን አቅጣጫ የማስቀየር ሃሳብ በዘመኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ቴክኖሎጂ የማይቻል መሆኑን ገልጸው ነበር::
የግብጽ ቀጥተኛ ትንኮሳ
ግብፅ ፣ቱርክ እና ጣሊያን “ኢትዮጵያ ተዳክማለች፤ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻዎች አይለዋል” ያሉባቸውን ጊዜያት እየመረጡ ወረራ ለመፈፀም ከሞከሩ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ:: በመሳፍንቱ መካከል አልፎ አልፎ እርስ በርስ ሽኩቻ ቢፈጠርም ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያዊነት ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ለሁሉም የጋራ ትውፊታዊ ሀብታቸው የሆነች ሀገራቸውን በኃይል ለመቆጣጠር የመጣውን የባዕድ ወራሪ ኃይል በአንድነት በመመከት ጠላቷ ወደ ውስጥ እንዳይዘልቅ አድርገዋል።
በቅድሚያ ቱርክ ነበረች ሀገራችንን ለመውረር አሰፍስፋ የመጣችው:: የኦቶማን ቱርክ ስረወ መንግስት ለረጅም ጊዚያት በመካከለኛው ምሥራቅ (በባልካን አገሮች) እንዲሁም በሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ከነበራቸው የበላይነት በተጨማሪ ቀይ ባህርን ለመቆጣጠርና ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ በቅኝ ግዛት ሥር ለማድረግ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ ተሰናክሏል። 
የቱርኮችን እግር ተከትለው ወደ አገራችን ድንበሮች የተጠጉት ደግሞ ግብፆች ነበሩ። ግብፆች ምኞታቸው ከፍ ያለና የአባይን ምንጭ ጨምሮ ቀይ ባህርንና ሜዲትራኒያን እስከ ህንድ ውቅያኖስ ያለውን የብስና ባህር ለመቆጣጠር ነበር:: ይህ የቆየ ምኞት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ከሱዳን ጋር ቀላቅሎ ለመግዛት ፅኑ ምኞትና ህልም አሳድሮባቸዋል፣ በዚህም ግባቸውን እውን ለማድረግ ማሰብና ሙከራ ማድረግን ከቱርኮች ተማሩ።
ጉንደት እና ጉራ
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ እስማኤል ፓሻ በተሰኘው የግብፅ መሪ ተነድፎ በአዲስና በተጠናከረ መልክ በእንግሊዝ እና ሌሎች ቅኝ ገዥ ሀገራት ወታደራዊ ሙያተኞች በመታገዝ ሀገራችን ላይ ወረራ ተፈጽሟል። ለዚህም ደግሞ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት በየአካባቢው ባላባት ተከፋፍላ እና በእርስ በርስ ግጭት መቆየቷ ትልቁን አስተዋጽኦ ተጫውቷል::
በዚህም ግልፅ ወረራ ለማድረግ ወደ ምፅዋ የገባውን ጦር ሙንሲንጀር የተባለ የስዊስ ተወላጅ ተቀብሏቸውና መርቷቸው ከረንን፣ ሀባብንና መንሳን በ1864 ዓም ወረሩ። በሌላ በኩል ደግሞ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ሥር ያሉትን የጠረፍ ወረዳዎች ማለትም መተማን፣ አብደራፊን፣ ቋራንና ደምቢያን ሌላው የግብፅ ኃይል ከሱዳን ተነስቶ ወረረ።
በዚያው በኤርትራ በኩል ከከረን አካሎ በአሥመራ ከተማና በምፅዋ ወደብ መካከል የሚገኘውን ጊንዳዕን በ1865 ዓ.ም ተቆጣጠሩ። ጊዜውም አፄ ዮሐንስ ሥልጣን የያዙበት አፍላ ወቅት በመሆኑና በንጉሠ ነገሥታዊ ዙፋን ስር ያሉትንና ያመፁ መሳፍንቶችን የማንበርከኩና የማሳመኑ ትግል ራሱ አድካሚ በመሆኑ የግብፅን ግሥጋሴ ለመግታት ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ አልቻሉም ነበር።
አፄ ዮሐንስም ችግሩን ከጦርነት ይልቅ በሠላም ለመፍታት ታላቅ ጥረት አድርገዋል። ለዚህም በጊዜው ኃያልና ተደማጭነት ካሏቸው የአውሮፓ መንግሥታት ጋር ተፃፅፈው፤ በሽምግልና እንዲረዷቸው እየጠየቁ ባሉበት ወቅት በ1867 ዓ.ም ግብጾች በኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ክልል የሚገኘውን ዘይላ የሚባለውን ሌላውን ወደብ ያዙ። ቀጥለውም ከዚያው ተራምደው የሐረርጌን ክፍለ ሀገር ተቆጣጠሩ።
አጼ ዮሐንስ የሰላም ጥያቄያቸው ውድቅ በመደረጉ በ1868 ጥቅምት ወር ጉንደት በተሰኘ ስፍራ ከግብፆች ጋር ገጥመው ድል ተቀዳጅተዋል:: በኤርትራ ጉንደት ላይ በተደረገ ጦርነት ከቱርክ ጋር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የመጡ ግብጻውያን በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተራራ ላይ የገጠማቸውን ቀጭን መንገድ ሲያዩ በድንጋጤ መዋጣቸውን ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤሪክ ተርኮታል:: 
የኢትዮጵያ ጦረኞች ካደፈጡበት በመውጣት ፈጣን ጥቃት ሲሰነዝሩባቸው የሚገቡበት ማጣታቸውን ይኸው ታሪክ ጸሀፊ ያብራራል:: ገዢ መሬት ይዞ ያልታሰበ ጥቃት በመሰንዘር ወታደራዊ የበላይነትን የያዘው የኢትዮጵያ ጦር እንቅስቃሴውን ሲቀጥል የግብፅ ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ ሙሉ በሙሉ መደምሰሱና የዚህ ትልቅ ሽንፈት ዜና በግብፅ ሲሰማ ከፍ ያለ ፍርሃትና ንዴት መፍጠሩም በታሪክ ዘጋቢዎች ተከትቧል::
የተበተነው የግብጽ ጦር ንጉሱ ዳግም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት በሚል መዘናጋታቸውን ጠብቆ ከሰባት ዓመታት በኋላ ወረራ ቢፈጽምም ጉራዕ በተባለ ስፍራ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ዳግም ተበትኗል::
የተጨናገፈውን ወረራ ተከትለው ግብፃውያኑ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ነበር የሞከሩት:: በዚህ ጊዜ ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ይዘው ነበር:: ረቲብ ፓሻ በተባለ የግብጽ መሪ የሚመራ ጦር በምፅዋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ:: ጉራዕ ሸለቆ አቅራቢያ ሁለት ምሽጎችን በጉራዕ እና ከጉራዕ ጥቂት አለፍ ብሎ በሚገኝ ተራራ ላይ ሰራ። 
ረቲብ በጉራዕ ምሽግ ውስጥ ካሉት ሰባት ሺህ 700 ወታደሮች ውስጥ አምስት ሺዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ እንዲገጥሙ ትዕዛዝ ሰጠ:: ይህ የግብፅ ኃይል በራስ አሉላ አባ ነጋ በሚመራ የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈጣን ሁኔታ ተከበበ:: በተወሰደበት ጥቃትም ወዲያው ተበተነ:: ኢትዮጵያውያኑ ባገኙት ድል ሳይኩራሩ ኃይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ጉራዕ በመሸገው ኃይል ላይ ሁለተኛውን ጥቃት ሰነዘሩ:: ግብፆች መከቱ:: በሚቀጥለው ቀን የኢትዮጵያ ጦር ምሽጉን ደረመሰው:: የግብፅ ጦር ብዙም ሳይቆይ ሸሸ።
በአፋር በኩል የዘለቀው የግብፅ ጦር እንዲሁ በኢትዮጵያዊያን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል:: በርከት ያሉ የውጭ ዜጎች በዚህ ጦርነት ተሳትፈዋል:: አዶልፍ አረንድረፕ እና የስዊስ አሳሽ የነበረው ወርነር ሙዚንገር በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው:: ሙንዚገር የግብጽን ጦር እየመራ ኢትዮጵያን ለመውጋት በታዳጁራ (ጂቡቲ) በኩል ወደ መሀል ሀገር ዘልቆ ለመግባት ጉዞ ጀመረ:: ነገር ግን ይህ የሙዚንገር ሠራዊት የአውሳው ሱልጣን በነበሩት በሙሐመድ ኢብን ሃንፍሬ ጦር ተሸነፈ:: ሙዚንገርም በዚሁ ጦርነት ተገደለ::
ይሁንና ኢትዮጵያ በጉንደትና ጉራዕ ወታደራዊ ድልን እንጂ ዘላቂ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድልን አላገኘችም። ይልቁንም ተጨማሪ ጠላቶች በኢትዮጵያ ዙሪያ እንዲያሰፈስፉ እና በሉዓላዊነቷ እንዲሁም የገዛ ሀብቷን በመጠቀም ላይ የተደቀኑ ችግሮች ተያይዘው መጡ:: በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የተደረጉ የአንድ ወገንም ሆነ የሴራ ውሎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል በማለት የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ያስረዳሉ::
ይቀጥላል
Filed in: Amharic