>

የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!  (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!

 ዶ/ርበድሉ ዋቅጅራ

የሰበብ ምንጭ አይደርቅም! 
ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት! 
.
ዛሬ በጠዋት አንዲት ባልንጀራዬ ከባህር ማዶ ደውላ፣ ‹‹የዶክተሩን የምርጫ ቅስቀሳ አየኸው?›› አለችኝ፡፡ ‹‹አስደናቂውን ዘጋቢ ፊልም ማለትሽ እንዳይሆን፤›› ስላት፣ ‹‹የሚያስደንቀውስ አለማፈሩ፤ ሀገሪቱ እዚህ ችግር ውስጥ እያለች . . .›› አላስጨረስኳትም፡፡ ቀኔን በመጥፎ መንፈስ መጀመር አልፈለግኩም፡፡ እሷ ‹የምርጫ ቅስቀሳ› ያለችው ዘጋቢ ፊልም ከፈጠረብኝ በጎ ስሜት ጋር ነው ክንቅልፌ የነቃሁት፤ ከዚሁ ስሜት ጋር ማረፋፈድ እፈልጋለሁ፡፡
.
ቆይ ግን ለምርጫ ቅስቀሳ ቢጠቀምበትስ? መሪዎቻችን በ‹ኢንተርሀሙዌይ› እያሸበሩ፣ በ‹‹እኛ ከሌለን ሀገር አትኖርም›› እየስፈራሩ አልነበረም እንዴ ምርጫ የሚቀሰቅሱት!
.
ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት፡፡
.
ኢትዮጵያን እንደሀገር ያገለገልኳት፣ ያፈቀርኳት በ1970ዎቹ መጨረሻ (1976-79) ባለው ጊዜ ነበር፤ በመጀመሪያው ዙር የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመኔ፡፡ ከትምህርት ቤት በግዴታ ታፍሼ የገባሁበት የብሄራዊ ውትድርና ከሀገሬ ጋር ልብ ለልብ አስተዋወቀኝ፤ አፈቀርኳት፡፡
.
ግዳጄን ፈጽሜ፣ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ፣ በ1983 አ.ም. ወደ ስራ ስሰማራ ኢትዮጵያን አጣኋት፡፡ በብሄር ፖለቲካ ሴራ የተካኑ፣ ስሟን መጥራ የሚዘገንናቸው መሪዎች እጅ ወድቃለች፡፡ ለጎሳና ቋንቋ ድንበር ከልላ፣ ባንዲራ ሰቅላ እሷ ፈዝዛለች፡፡ . . . ለብሄረሰቦችና ለቋንቋዎች እኩልነትና ለሰብአዊ መብት መከበር ዝም ብዬ አላውቅም፤ እሟገታለሁ፡፡ ባንዲራቸው ሲከልላት፣ ምትተነፍሰው አየር ሲያጥራት፣ ኢትዮጵያን ሲረሷት ግን አዝናለሁ፤ያመኛል፡፡.
.
ከረዥም ጊዜ በኋላ በትላንትናው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት፡፡ ዘመንን መስላ፣ ተስፋ አዝላ አነበብኳት፡፡ በሶስት አመት፣ ያለጥላቻና ግጭት ዜና ነግቶ በማይመሽበት ሀገር፣ ‹የእኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገሬ ትበተን› በሚል ጽንፍ ረገጥ ፖለቲካዊ መርገምት ውስጥ፣ እንኳን በልእልና መስራት በትክክል ማሰብስ ይቻላል ወይ? ያውም ይህ ሁሉ ሀላፊነት ለተጫነበት መሪ!
.
የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!
.
አዎ፣ ሀገራችን የብሄር ፖለቲካው ካጣባት ደዌ አልተፈወሰችም፡፡ አዎ አሜሪካ ማእቀብ ጥላብናለች፡፡ አዎ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ መሬታችንን ይዛለች፡፡ አዎ የትግራይ ወገኞቻችን በከፍተኛ ሰብአዊ ችግር ላይ ናቸው፡፡ አዎ የኤርትራ ወታደሮች ከሀገራችን ጨርሶ አልወጡም፡፡ አዎ ሸኔና የጁንታው ርዝራዦች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው፡፡ አዎ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል፡፡ . . . ሀገራችን በርካታ ችግሮች፣ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡
.
እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ እነዚህ አስደናቂ ፕሮጀክቶች መሰራታቸው አግባብ አይደለም በማለት ሰዎች ለጥላቻቸው የሰበብ ድር ያዳውራሉ፡፡ እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መሰራት መቻላቸው ነው፡፡
.
መሰራት የነበረበት ያልተሰራ አለ፡፡ ካልተሰራው የበለጠ የተሰራው የወደፊት መንገዳችንን ያሳያል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገሪቱ ባጀት ሳይነካ፣ የተሸለመውን የግል ገንዘብ ሳይሰስት፣ ወዳጆቹን ለምኖ በሶስት አመት፣ ጥላቻና ዘለፋን ቁብ ሳይል ይህንን ሰራ፡፡ ባለቤቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁ ከሀያ በላይ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ቀበሌዎች ገነባች፡፡ ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች የማናደንቀው ከነማን ጋር እያወዳደርናቸው ነው? እንኳን በሶስት አመት፣ በሶስት አስርታት ውስጥ የዚህን ግማሽ የሰራ መሪ ኖሮን ያውቃል?
.
እንደመሪ እነሱ ይህን ሰሩ፤ ያልመለሷቸው ችግሮችም አሉ፡፡ እኛስ! እንደ ዜጋ ባለፉት ሶስት አመታት ምን ሰራን? እኛ እንደዜጋ ያለነው የት ነው? የሰሩት በጎ ተግባር ወይስ ያልመለሷቸው ችግሮች አካል ነን? በዋናነት የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው፡፡ ሀገራችን በውስጥና ውጭ ችግር ተተብትባለች፤ ፈተና ላይ እንደሆነችም እናውቃለን፡፡ ዋናው፣ እያንዳንዳችን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ሀገራችንን የተበተባት ችግር፣ የተጋረጠባት ፈተና አካል አለመሆናችንን ነው፡፡ እና እንጠይቅ! እንደዜጋ የቆምነው የት ነው?!
Filed in: Amharic