እወቋቸው…!!!
ሙሉአለም ገብረመድህን
“ጠላቶቻችን ጽንፈኛ ሙስሊሞች የሊቢያ ጠላቶች ብቻ አይደሉም። በየቦታው ተበትነዋል። ብቸኛ ግባቸው መግደል፣ ማረድና ማውደም ነው። ቀውስ ከመፍጠር የዘለለ ሌላ ተልዕኮ የላቸውም”
ይህን የተናገረው መቀመጫውን ቤንጋዚ ያደረገውና ዛሬ ላይ የሊቢያን 2/3ኛ ግዛት የተቆጣጠረው ሌተናል ጀኔራል ኸሊፋ ኻፍተር (L.General Khalifa Hafter) ነው። ንግግሩን የሊቢያ የሽግግር መንግሥት በመመስረት ሂደት ላይ ነበር የተናገረው። ከዚያ በኋላ የሆነው ታሪክ ነውና የሊቢያን የለውጥ ተስፋ ያጨለመው የቀውሱ አስኳል በዓለም ታሪክ ውስጥ በጥቁር መዝገብ ሰፍሯል።
~~***~~
ከዚህ በላይ የተመለከተውን የመግቢያ ሃሳብ በዚህ ጽሁፍ መውጫ ላይ ካለው ፍሬ ነገር ጋር አዛምዳችሁ እንዳታነቡ እየመከርኩ የሚከተለውን ትንታኔ ጋብዣቻችኋለሁ!
የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም አልባነት፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም ‹የእየሩሳሌም ግዛት ይገባኛልነት› መተራመስ ከጀመረ ሦስት ትውልዶችን ተሻግሯል። ከድኀረ-ቀዛቃው ጦርነት ማብቂያ በኋላ ግን፣ በሁለቱ ኃይሎች ፍጥጫ ላይ ሌላ የግጭት መስመር ተወልዷል።
ይህ በጠርዘኛ የፖለቲካ እስልምና የሚበየነው ዐዲስ እስልምናዊ መነቃቃት፣ ለደም-አፋሳሽ ግብሩ ሃይማኖታዊ መደላድልና ከምዕራቡ ጋር ለጀመረው አውዳሚ ግብ-ግቡ ርዕዮተ-ዓለማዊ ማብራሪያ ፍለጋ ወደኋላ ሦስት መቶ ዐመታትን ተንሸራቷል። በዚያም መሐመድ ኢብን አብድ አል-ዋሃብ ተብሎ የሚጠራ፣ ቅዱስ ቁራዕንን በዐሥር ዐመቱ በቃሉ ስለመወጣቱ የተነገረለትንና ሃይማኖቱን በዐዲስ ትርጓሜ ያፍታታውን መምህር አግኝቷል።
የሰውየው አስተምህሮት በስሙ ተቀፅላ “ዋሃቢዝም” ተብሎ ይጠራል። በርግጥም፣ የፖለቲካዊ እስልምናን ክሮች ፈልጎ ለማግኘት. ይህን መስመር መከተሉ ድካምን ይቀንሳል፡፡…በ1703 ግድም፣ ከሌሎቹ የሳዑዲ ቤተሰብ አባላት ባልተናነሰ የወደፊቷን ሳዑዲ-ዐረቢያ ምንነት የሚወስን ሰው “ኡያኢና” ተብላ በምትጠራ አካባቢ ተወለደ። የ”SAUDI ARABIA” መጽሐፍ ጸሐፊ ጀምስ ዋይነብራንደት እንደሚለው፣ መሐመድ ኢብን አበድ አል-ዋሃብ አያቱ በዘመኑ የተከበሩ የሥነ-መለኮት መምህር ሲሆኑ፤ አባቱ አብዱላሓ ኢቢን ሙማር ደግሞ በ1726 በካሃረፊሽ የተባረረ ዳኛ ነበሩ። ከመካ እስከ መዲና እና ባስራ እየተዟዟረ በጊዜው ከነበሩ ጉምቱ የሃይማኖቱ ሊቃውንት ቅዱስ ቁራዕንን የተማረው አል-ዋሃብ፣ በሙስሊሙ ማኀበረሰብ በታዩት ለውጦች በመበሳጫት፣ ‹ተዋሂድ› ወይም ‹ከፈጣሪ ጋር አንድ መሆን› ተብሎ የተጠራ አማራጭ የእስልምና መስመርን አስተዋወቀ።
በዋይነብራንደት ቃል “አል-ወሃብ፣ ሱፊዝም ላይ የማይመቻመች ተፃራሪ አቋም ይዞ መጣ። ‹ሁሉም የፈጠራ ሥራዎች ወደ ነባሩ እስልምና ለመመለስ እንቅፋቶች ናቸው› ሲል ፀረ-ሥልጣኔ አቋሙን ሰበከ።” የሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ መምህሩ አክባር አህመድ “Journey into Islam” በሚለው ድርሳኑ፣ “እንደ ሰውዮው አስተምህሮ ራስን ማጥፋት ቅዱስ ቁዕራን በግልጽ ቢከለክልም፣ [ከአስተምህሮቱ ውጭ ያሉ]፤ ሰላማዊ ሰዎችን ጭምር መፍጀት ምክነያታዊ ነው።” ይህ አክራሪ አንጃ ስያሜውን ያገኘው በ1740 ነጅድ ከምትባል በዛሬዋ ሳዑዲ መካከለኛ ክፍል ከምትገኝ ቦታ ከተነሳው ይህ ሰው ነበር።
የአብድ አል- ወሃብን አስተሳሰብ መከተል የጀመሩት የተለያዮ ጎሳዎች አባላት፣ “ወሃቢያውያን” በመባል ተጠሩ። ዛሬ ከዚህ ስም ለመራቅ በመሞከር “ሰለፊ (ወደ ምንጩ ተመላሾች) ነን” የሚለውን ስም መጠሪያቸው ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ወሃቢ በስፋት የሚታወቁበት ሆኗል። የተሀድሶ ንቅናቄ መሪው አብዱል ወሃብ፣ “እስልምና ብዙ ባህላዊና ባዕዳዊ ነገሮች ገብተውበታል። በእነዚህም ተጠፍንጎና ተተብትቦ ተይዟል። በመሆኑም ተሀድሶ ያስፈልገዋል። ‹እኛ ሙስሊም ነን፤ እምነታችንም እስልምና ነው› የሚሉም እንደ ዐዲስ ‹ሸሀዳቸውን› ሊወስዱና መስመሬንም ሊከተሉ ግድ ይላል። ያንን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነ የዐረብ ጎሳም ሆነ አባላቱ ሰይፋችንን ያያሉ፤” የሚል ኃይለ-ቃል ሰብኳል። ከስብክትም አልፎ፣ በተሃድሶ ስም በሙስሊሞች ላይ ሰይፉን እስከመምዘዝ ደፍሯል።
በሃይማኖቱ ላይ ውጊያውን ሲጀምር ምክንያቱ ‹መስመሬን ተከተሉ› የሚል ነበር። ጊዜው ደግሞ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የአካባቢውን ሕዝቦች በማነሳሳት የኦቶማንን ግዛተ-ዐፄን ለመገርሰስና ዛሬ “መካከለኛው ምስራቅ” የሚባለውን አካባቢ ከእጃቸው ለመንጠቅ ውስጥ ውስጡን መጠነ-ሰፊ ዘመቻ የጀመሩበት በመሆኑ፣ ድጋፍ አስገኝቶለታል። ከዚህ በኋላ ነው፣ በእንግሊዝ አጋዥነት በርካታ ጎሳዎችን ማስገበር ከመቻሉም በዘለለ፤ ለኦቶማን ጦርና አገዛዝ ስጋት እየሆነ የመጣው። በዚህ መልኩ ዐቅሙን ያደራጀው አብድ አል-ወሃብ፣ የወሃቢዝምን እምነተ-ክፍል ማስፋፋቱን አጠናክሮ ቀጠለ።
በአገሪቱ ሌላኛው ጫፍ ደግሞ፣ በእንግሊዞች ሙሉ ድጋፍ የሚንቀሳቀስና አብዛኛውን የአካባቢውን ጎሳዎች በማስገበር ኦቶማንን የሚዋጋ መሐመድ ኢብን ሳዑድ የተባለ (ወደኋላ የትውልድ አገሩ በስሙ “ሳዑዲ ተብላ የተጠራችለትና የአሁኖቹ የሳዑድ-ዐረቢያ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ቅድመ-አያት) የሽምቅ ተዋጊ ቡድን መሪ ነበር። እነዚህ ሁለት አንጃዎች በእንግሊዝ አደራዳሪነት መዋሀዳቸው፣ በአካባቢው ምናልባትም ለኦቶማን መዳከም ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ይታመናል።መሐመድ አብድ አል-ወሃብ አስተምህሮቱ እንዲስፋፋለትና በሌሎች ላይ በግድ ለመጫን በመፈለግ ያደርግ የነበረው የሽብር ሰበካና ትግል፣ በሥልጣን-ጥም ፖለቲካዊ መስመር ይዞ ይዋጋ ለነበረው ዐማጺ መሪ መሐመድ አል ሳዑድ ትልቁን በር ከፈተለት።
አል ሳዑድ ከአል-ወሃብ ጋር መዋሀዱ በአጎራባች ጎሳዎች ላይ ለሚያደርገው ጦርነት በ‹ጅሀድ› ስም ሃይማኖታዊ ሽፋን መስጠት እንደሚያስችለው አምኖ ነበር። ይህንን ‹ጅሀድ›ም ለሥልጣን መያዣው ሰበብ በማድረግ፣ በስመ-ሃይማኖት አገር አሸብሮበታል። የሁለቱ ጥምረትም ዓለማችን ላስተናገደቻቸው በርካታ እልቂቶችና ጦርነቶች ሰበብ የሆነውን ‹ፖለቲካዊ እስልምና›ን አዋልዷል።
ኢትዮጵያን ያያችሁ…?
በኢትዮጵያ የታዩት ኢኽዋን አል ሙስሊሙም (በዲን ስም ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴም) ሆነ የመንግሥትን ተቋማትን ህልውና ባለመቀበል፣ ግብር ባለመክፈልና ወደ መንግሥት ተቋማት ባለመሄድ ራሱን አጥሮ በመቀመጥ የራሱን ‹ካሊፌት› የመመስረት ፍላጎት ያለው ከሱዳን ተሻግሮ ሰርጎ የገባው “ተክፊር” (ተክፊር ዋል ሂጅራ) መሰረቱ ራሱን ከዓለማዊ መንግሥት የማላመድ ተፈጥሯዊ ችግር ያለበት ወሀቢይዝም ነው፡፡
በጣሊያን ወረራ ዘመን በፋሽስቱ ባርኮት ወደ አገር እንደገባ የሚታመነው ወሃቢይዝም፣ ከሰማንያ ዐመት ቆይታው ይልቅ፤ ባለፉት ሠላሳ ዐመታት ቀላል ግምት ሊሰጠው በማይችል ሁኔታ አድማሱን አስፍቷል፡፡ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ዜጎች የትኛውም ዐይነት ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዳላቸው ቢደነገግም፤ የትኛውም ሃይማኖታዊ አተገባበር የሌሎቹን ሃይማኖቶችንም ሆነ የአገሪቷን ነባር ተቋማት ህልውና መቀበልን ያስገድዳል። ይህም ሆኖ፣ የአገዛዙ ከፋፋይ ባህሪና የፔትሮ ዶላር መንግሥታት የህቡዕ ድጋፎች፣ አመለካከቱን የአገር ቤት አፈር ቆንጥጦ እንዲይዝ አበርትተውታል።
በሌሎች አገራት እንደታየው፣ በባህሪው የአስተሳሰቡን የበላይነት ለማረጋገጥ በሚሄድበት የዐመጻ መንገድ ሁሉንም ነባር ዓዕማዶች ማፍረስ ግድ ስለሚለው፤ የአንድን አገር ታሪክ፣ እሴት፣ ባህል፣ ወግና ልማድ ንዶ፣ ከዜሮ መጀመርን ይመርጣል። የቀደሙ አሻራዎችን ለማጥፋት በድፍረትና በግላጭ ይንቀሳቀሳል፡፡ “መስቀል አደባባይ”ን፣ “ኢድ ዐደባባይ” ብሎ እስከመጥራት መድረሱን ማስታወሱ የቡድኑን የጠርዘኝነት ደረጃ ያመላክታል፡፡
በነባሩ እስልምናም ሆነ በሌሎች ሃይማኖቶች የሚከወኑ ኹነቶችና ነባር አሻራዎችን የበላይነቱን እንዳያነብር የተደቀኑ እንቅፋቶች አድርጎ ስለሚያያቸው፣ የማጠልሸት ዘመቻ ይከፍትባቸዋል፡፡ ታሊባን በአፍጋኒስታን፣ አልቃይዳና አይ.ኤስ በኢራቅ በርካታ ሺሕ ዐመታትን ያስቆጠሩ የቡዲሂዝም እምነት ሐውልቶችን ማፍረሳቸው በማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። ለዚህም ነው፣ አስተሳሰቡ እንኳንስ ብዝሃ-ሃይማኖት ባለባቸው ኢትዮጵያን የመሰሉ አገራት ቀርቶ፤ ሙሉ እስላማዊ አገር በሆኑ የዓለማችን ክፍሎች እንዳሻው ለመራመድ ሲቸግረው የታየው። በኢትዮጵያ እያቆጠቆጠ ያለው ሃይማኖታዊ የግጭት መስመር መሰረቱ ከዚህ አስተሳሰብ ጋር ይያያዛል፡፡
የአብያተ-ክርስቲያናት ውድመትና የአማኞች መታረድ ሥረ-ምክንያቱን እዚህ ጋ ፈልገን አናጣውም፡፡ በኃይል መስጂድን እና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶችን መቆጣጠር፣ የአገሪቷን መሰረታዊ ተቋማት መጠምዘዝ… የእግር መትከያ ባህሪያቱ ናቸው። አደገኛ አመለካከት ያላቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች፣ ውለው-ሲያድሩ የከፋ አደጋ ሊያመጡ እንደሚችሉ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ህያው ምስክር ነው።
የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የከረሙ የመብት ጥያቄዎችን በመጥለፍ፣ ራሳቸውን ወደ እስላማዊ ገዢ-መደብነት ለመቀየር የተጠቀሙበት አካላት፣ ለዘመናት የዘለቀው እውነተኛው የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ላይ ውሃ ሲቸልሱበት ታዝበናል። ዛሬም፣ ሃይማኖቱን የሀብት ምንጫቸው ያደረጉ አካላት፣ እውነተኞቹን ከእስልምና ክበብ እያስወጡ፣ ፅንፈኛ አስተሳሰባቸውን ለመጫን ይተጋሉ። አንዳንዶች ራሳቸውን ከጽንፈኛው የኦሮሞ ብሔረተኝነት መስመር ጋር በማዛመድ፣ አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየገፏት ነው፡፡
የምናብ “ከሊፋ”ውን ጨምሮ፣ በዋናነት በስም የሚታወቁ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ የአስተሳሰቡ ወራሾች በሚያራምዱት ፖለቲካዊ እስልምና ሃይማኖታዊ ግጭት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ግልጽ ስጋት ሆኗል፡፡ ይህ አደገኛ መስመር በዝምታ መታየት ከቀጠለ ኢትዮጵያን ወደ ገደሉ ጫፍ እንደሚገፋት አትጠራጠሩ።
መዘንጋት የሌለበት አንድ እውነታ፣ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት” መሆኗ የታሪክ ትውስታ እንጂ፤ በአሁኑ አገራዊ ቁመና ሊገለጥ የማይችል መሆኑ ነው። ያ ጊዜ ላይመለስ አልፏል።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር ተጋግዘው የአገር-ግንባታው አካል ይሆኑ ዘንድ፣ ቅድሚያ በውስጣቸው የመሸጉ፣ ከማንነታቸው ተዛምዶ የሌላቸውን ነቀልተኛ አስተሳሰቦች የተሸከሙ ኃይሎችን ከመስመር ማስዋጣቱ ለእምነቱም ሆነ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ህለውና ይጠቅማል። በዳይን በማፍቀር የ’ስቶኮልም ሲንድረም’ የተጠቃውና ምክንያት እየፈጠረ “ጁንታው ይሻላል” በሚል መንጋ ታጅቦ የታየው የዚያው ሰሞን ፖለቲካዊ እስልምና ንቅናቄ መዳረሻው፣ ኢትዮጵያን በደም-ከማጨቅየት የዘለለ፤ ለነባሩ እስልምና የሚፈይደው ነገር የለም፡፡