>

ገብር ሄር ፡ መክሊቱን አትራፊው ሊቀ ሊቃውንት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (ዶ/ር)

ገብር ሄር ፡ መክሊቱን አትራፊው ሊቀ ሊቃውንት
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (ዶ/ር)
ጸሐፊ/ደራሲ፣ ተመራማሪ፣ የግእዝ ሥነ ልሳን ሊቅ፣ … 
(በ መ/ር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል )

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (ዶ/ር) የተወለዱት በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ኀገር በሸንኮራ አውራጃ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግንቦት ወር 1924 ዓመተ ምኅረት ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአደጉበት አካባቢ በአጥቢያ የሚሰጠውን የንባብና የግብረ ድቁና ትምህርት ቀጥሎም አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በወቅቱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ወደ ኮሌጅነት አድጎ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ የትምህርት ፋከልቲዎች አንዱ አልሆነም ነበር፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ብቻ ያስተምር ስለነበር ጌታቸው ኃይሌ ለተከታታይ ስድስት ዓመታት በመንፈሳዊ ትምሀርት ቤቱ ሚሰጡትን መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርቶች ተከታትለዋል፡፡
ጌታቸው ኃይሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ግብጽ ተልከው በካይሮ የኮፕቲክ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በካይሮ የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ለአምስት ዓመታት የሚሰጠውን የቴዎሎጅ (ነገረ መለኮት) ትምህርት በቅድመ ምረቃ (ባችለር) ዲግሪ ደረጃ በአረብኛና በእንግሊዛኛ ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡
የጌታቸው ኃይሌ ሴማዊ ባህልና ቋንቋ ጥናት ችሎታ በዋናነት የተመሠረተው በዚህ ትምህርት ቤት ካገኙት የአረብኛ ቋንቋ ዕውቀት በኋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጌታቸው ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና በልጅነት ባደጉበት አካባቢ ካገኙት ሁለት ቋንቋ በተጨማሪ አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የግእዝ ቋንቋን በብቃት ተምረዋል፤ ካይሮ ሲሄዱ አረብኛን በረጅም ጊዜ የዘመናዊ ትምህት ካዳበሩት የእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ ብዝኀ ልሳን እንዲሆኑ አድርጓዋል፡፡
የካይሮ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ጃንሆይ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ በ1950 ዓ/ም ማብቂያ ላይ ወደ ጀርመን ተጉዘው በኤበርሃርድ ካርልስ ቱበንጀን ዩኒቨርስቲ (Eberhard-Karls-Universität Tübingena) በሴማዊ የሥነ ልሳን ጥናት (Semitic Philology) የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በጀርመን ቋንቋ “Das Verbalsystem im Äthiopischen: Ein orphologischer Vergleich mit den orientalischen semitischen Sprachen” በሚል ርዕስ ወይም በእንግሊዝኛ ሲተረጎም “The verbal system in Ethiopia: an morphological comparison with the oriental Semitic languages” በመሥራት ተመርቀዋል፡፡
ከዚህ ሁሉ የትምህርት፣ የጥናትና የምርምር ጉዞ በኋላ ጌታቸው ኃይሌ በአማርኛ፣ በግእዝ፣ በአረብኛ፣ በእብራይስጥ፣ በላቲን፣ በግሪክ፣ በጀርመንና በኮፕቲክ ቋንቋች ጥናትና ምርምር የሚየደርጉ ታላቅ ሊቅ በመሆን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በቀድሞው የቀዳማዊ የኃይለ ሥላሴ ዪኒቨርስቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል Department of Ethiopian Languages and Literature በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ተቀጥረው አማርኛ ቋንቋቋ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ግእዝ ሰዋስው፣ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ፣ አረብኛ ሰዋስው፣ አረብኛ ቋንቋና አረብኛ ሥነ ጽሑፍ እንዲሁም የሴማዊ ቋንቋዎች ጥናትን የተመለከቱ ትምህርቶችን ማስተማር ጀመሩ፡፡ ከማስተማሩ ጎን ለጎን በተጨማሪ የComité de lecture of Analecta Bollandiana (Journal of Christian Hagiography), Ethiopian Journal of Education, Journal of Ethiopian Studies, Northeast African Studies, (1994-2001), and Acta Aethiopica የተባሉ ዓለም አቀፍ የትምህርትና የምርምር መጽቶች አማካሪና አርታኢ፣ እንዲሁም ጸሐፊ በመሆን መሥራት ጀመሩ፡፡
በርካታ ትርጉምና ወጥ ሥራዎችን፣ ቁጥራቸው የበዛ እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ አስደናቂ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል፡፡ በርካታ የማስተማሪያ መጻፍትን አዘጋጅተዋል ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ተሸልመዋል፡፡ በዚሁ በሴማዊ ጥናት ውስጥ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ በሥነ ልሳን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይ ያተኮሩ ዕውቅ ምሁራን የጌታቸውን ሥራዎች በከፍተኛ አድናቆት ያከብራሉ፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከአካዳሚክ አገልግሎታቸው በተጨማሪ ከልጅነት ጀምሮ ባሳደገቻቸውና ባስተማረቻቸው የኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰፊ አገልግሎት ፈጽመዋል፤ በሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶች፣ በውጭ ግንኑነት ተወካይነት፣ ሰፊ ሥራ ሠርተዋል፡፡ የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ኮሚቴ በመሆንም ከአራት ያላነሱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ተሳትፈዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ ባለትዳር የልጆች አባት ነበሩ።  ባለቤታቸው ከወ/ር ምሥራቅ አማረ ይባላሉ፡፡  ከልጆቻቸው በተጨማሪ የልጅ ልጆችንም ለማየት ታድለዋል፡፡
በ1966 ዓ/ም የተከሰውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ዶ/ር ጌታቸው የደርግ መንግሥትን ፓርላማ በግልጽ በመቃወማቸው በመንግሥት ትእዛዝ አንዲያዙ አብዮት ጥበቃዎች ወደቤታቸው ተልከው በተፈጠረው ከፍተኛ ተኮስ የተሞላበት ግርግር በጥይት ተመተው በጀርባ አጥንታቸው ላይ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ለሕክምና ወደለንደን ተጉዘው ባደረጉት ክትትል ሕይወታቸው ተርፎ እስከ አሁን በተሸከርካሪ ወንበር በመሆን ዓለምን የሚየስደምሙ በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በእግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ ቋንቋዎች ሥነ ጽሑፎችን ለማምረት በቅተዋል፡፡
ከሀገራቸው ከወጡ እና ጤንነታቸው ከተመለሰላቸው በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ላለፉት ዓርባ እና ከዚያ በላይ ዓመታት በሰሜን አሜሪካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሜኖሶታ ጠቅላይ ግዛት ፣ኮሌጅ ቪል ሒል የቅዱስ ዮሐንስ ዪኒቨርስቲ Professor Emeritus of Medieval Studies የግእዝ እና ሴማዊ ቋንቋች የተጻፉ ጽሑፎችን በማደረጀት፣ ካታሎግ በመሥራት፣ በማጥናት፣ በመተርጎም፣ በማስተማር፣ በማማከር፣ እና በመመርመር ሰፊውን ሕይወታቸውን አሳልፈዋል፡፡ እስከ አሁንም ከአምስት ሽህ በላይ የግእዝ ሥነ ጽሑፎችን እና በርካታ የቅብጥ (ኮፕቲክ)፣ አረብኛ፣ ጽሑፎችን ማደራጀት ችለዋል፡፡ በአማርኛ፣ በግእዝ፣ በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ፣ በጀርመን ቋንቋዎች ማሳተም ችለዋል፡፡
1. የታተሙ መጻሕፍት (በአውሮፓ አቆጣጠር የተጻፉ)
i. የፒኤዲ ጽሑፍ የታተመ 1962
ii. የአማርኛ ማስተማሪያ ለመምህራን 1964
iii. አማርኛ መመሪያ ለጎልማሶች 1964
iv. ከጀርመን ቋንቋ የተተረጎመ – ማርክ ቴቫን ደብዳቤ ከምድር 1968
v. የግእዝ ብራና መጻሕፍት ካታሎግ፡ ብዛት ስምንት ቅጽ
vi. የነግሥ ስብስብ 1983
vii. የቅብዓት እምነት 1990
viii. ጦማረ ትስብዕት የንጉሠ ነገሥት ዓፄ ዘርዓያዕቆብ 1991
ix. ሥነ ፍጥረት ከምሥራቅ አማረ ጋር (1991
x. የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ስለ ነገረ ማርያም (እንግሊዝኛ) 1992
xi. ባህረ ሐሳብ 2000
xii. አባ ባህርይ 2002
xiii. ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ 2004
xiv. ገድለ አባ እስጢፋኖስ (2006)
xv. አንድአፍታ ላውጋችሁ (2008)
xvi. የመጀመሪያው እስጢፋኖስአውያን መንኵሴ (2011)
xvii. ገድለ አቡነ በርተሎሜዎስ የደብረ ዘመዶ 2013
xviii. መጽሐፈ ብርሃን 2013
xix. ግእዝ በቀላሉ
xx. የግእዝ መጻሕፍት
…..
2. ጥናትና ምርምሮች
i. በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት የታተሙ
ii. በኮርፐስ ስክሪፕቶሪየም ክርስቲያን ኦሬንት የታተሙ
iii. በሰሜን አሜሪካ አፍሪካ ጥናት መጽሔቶች ታተሙ
iv. እና በሌሎችም የጥናትና ምርምር ሥራዎች ታተሙ በብዙ መቶዎች ሚቆጠሩ
3. የጋዜጣና የመጽሔት ጽሑፎች፡ ፕሮፊሰር ጌታቸው ኃይሌ ለመጻፍ ወደ ኋላ አይሉም፣ ለአንዳንድ ሕዝባና የሃይማኖት በዓላት የሚበተኑ በራሪ እና አስተማሪ ጽሑፎች ሳይቀር በበጎ ፈቃድ ያዘጋጃሉ፤ በሀገራዊና በዓለም አቀፍ መጽሔቶች ሳይቀር በመቶዎች የሚቆጠሩ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በሥነ ጥበብ፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በመዛግብት ጥናት፣ አጫጭር ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡
4. የማስተማሪያ መጽሐፎች
i. የግእዝ ቋንቋ
ii. የአማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያዎችን በዩኒቨርስቲ ደረጃ አዘጋጃተዋል (በአዲስ አበባ ኒቨርስና በኮተቢ መምህራን ማሰልጠኛ እስከ አሁን ማስተማሪያ ናቸው፡፡
5. ሽልማቶች፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በርካታ ሽልማቶችን ተቀብለዋል ተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል
i. በንጉሠ በነገሥቱ ዘመን መጨረሻ የሸዋ ጠቅላይ ግዛትን በመወከል ፓርላማ አባል
ii. የማክ አርተር ፍሎሽፕ አዋርድ
iii. የብሪቲሽ አካዳሚ አዋርድ
iv. የሴማዊ ጥናት የኤድዋርድ ዑሌንዶርፍ አዋርድ
v. የቢል ክሊንተን ሽልማት
vi. አበባ ብቂላ ሕይወት ዘመን ተሸላሚ የመሳሰሉት
6. አጠቃላይ
በአጠቃላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በግእዝ፣ በአረብኛ፣ በጀርመን፣ በኮፕቲክ፣ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ በርካታ ሥነጽሑፎችን ያበረከቱ፤ የታሪላዊና፣ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ምሁር አርኣያ ናቸው፡፡
ትውልዱ ያላየውን ዘመን፣ የማያውቀውን ታሪክ በሥነ ጽሑፍ መነጽር ያስቃኙ፣ አይነኬ ታሪኮችን የዳሰሱ፣ የተዳፈኑትን ያጎሉ፣ እጃቸው ከጽሑፍ ሕሊናቸውም ከምርምር ያላረፈ ከሀገራቸው ወጥተው ለሀገራቸው በየቀኑ እና በየሰዓቱ የኖሩ ታላቅ ሊቅ ናቸው፡፡
በባህርያቸው ለተጠየቁት መልስ ለመስጠት የማይነፍጉ፣ ሰው አክባሪና ትሑት፣ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ከጥንቃቄ ጋር ወደኋላ የማይሉ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የኃላፊነት ስሜት ያላቸው፣ ሀገርና ሰው ወዳድ አርበኛ፣ የሃይማኖትን ምሥጢር የጠነቀቁ፣ ትጉህ ሰው መሆናቸውን የማይመሰክር የለም፡፡
የሊቃውንት አምላክ በዘለዓለማዊ መንግሥቱ  በክብር ይቀበልልን።
Filed in: Amharic