>

‹‹ይህ ሰው ማን ነበረ ቢሉህ ‹ዕውቀት እንደጠማው እድሜው ያለቀበት!› ብለህ ንገርልኝ!››   (ዝክረ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ )

 
‹‹ይህ ሰው ማን ነበረ ቢሉህ ‹ዕውቀት እንደጠማው እድሜው ያለቀበት!› ብለህ ንገርልኝ!››
 
ዝክረ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (፩)
በአማን ነጸረ

#ማስታወሻ፡- ግንኙነታችን የጸሐፊና የአንባቢ ነው፡፡ እርሳቸው ሻል ያለ ሰው አድርገው ያስቡኛል፡፡ ግን አይደለሁም! ቃሌ ዝርዝር ሳያስፈልገው ሊታመን የሚገባ ቃል ነው! ፕሮፌሰር የተጓዙበትን በማየትና ሥራዎቻቸውን በማንበብ ከመደነቅ የዘለለ አቅምም ምኞትም የለኝም! ምናልባት ከሆነልኝ አንዲት የመጣጠፍ መድብል እንጂ ከዚህ በኋላ ወጥ መጽሐፍ የመጻፍ ፍላጎትም የለኝም! ይኸንን ለእርሳቸውም ነግሬያቸዋለሁ፡፡ እንዲህ መዘብዘቤ በምለጠፋቸው ልውውጦች ቅጽል ሲያበዙልኝ ቢታይ የእኔን ቁመና ሳይሆን የእርሳቸውን ትሕትና እንደሚያመልክት ለማስታወስ ነው፡፡ ድኩምነቴን እየነገርኳቸው ሆን ብለው ይረሱልኛል፡፡
#ትውውቃችን፡- በ2009 ዓ.ም. የእርሳቸው ደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍ ላይ መደነቅን ከቅሬታ ያጣመረች ‹‹ወልታ ጽድቅ›› የተሰኘች ክታብ በደመ ፍል ደብተራ ስሜት ከረተስኩ፡፡ ጽሑፏ በደጉ ወንድማችን ብርሃኑ አድማስ በኩል ደርሳቸው በፌስቡክ ጥቂት አወራን፡፡ በኋላ በፌስቡክ ሱታፌያቸው የሚያስቀይማቸው በዛና መጻጻፉ በኢሜይል ይሁን በማለታቸው በ2009 ዓ.ም. የተጀመረው ተዋሥኦ መልአከ ሞት መካከላችን ከመግባቱ 16 ቀናት በፊት እስካሉት ጊዜያት ቀጠለ፡፡ እግረ መንገድ መጻሕፍቶቻቸው ብልጭ እያሉ ከሚጠፉ ወንድማችን አማረ አበበ (#ብራና_መጻሕፍት) የመልአከ ብርሃን አድማሱንና አለቃ አያሌውን ሥራዎች እንደ ፕሮጀክት ሥራዬ ብሎ እንደሠራቸው የእርሳቸውንም እንዲሠራ ተነጋግረን መስመር ያዘልን፡፡ ለእኔም እግረ መንገድ መገናኛ ሆነኝ፡፡ ትሑቱ አባት ግን ሰው ስለሚናፍቃቸውም ይመስለኛል ‹‹በመጻጻፋችን የምጠትቀም አንተ ሳይሆን እኔን ነኝ›› ይሉኝ ነበረ፡፡ በእነዚያ መጻጻፎች (ወደ መጨረሻ ላይ ጽሑፋቸውን በፋይል ነበር የሚልኩልኝ) ጊዜያትና ከሥራዎቻቸው ከሩብ ያነሡትን እንዳነበበ ወገኛ ተማሪ ሰዎች ቢያውቁላቸው የምለውን ላካፍል፡፡
ሰዎች ቢያውቁላቸው፡-
(1) ስለ ነገረ ሃይማኖት ሲጽፉ ስለ እኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ስለ አኃት አብያተ ክርስቲያን ጭምር በማሰብ ነውና ደግሞም ግብፅን በትምህርት፣ ሶርያን በመምህርነትና በጥናት ያውቋታልና ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሲሉ›› ይህን አንድነት እያሰቡ ነው፡፡
(2) ሥራዎቻቸው ዘመናዊውን /አካዳሚክ/ ማኅበረሰብእ ማዕከል ያደረጉ ናቸውና ማስረጃን ይከተላሉ፡፡  ፕ/ር ጌታቸው ዕውቀት ዓለም አቀፋዊ ነው የሚል እምነታቸው ጽኑዕ ነው! ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚለውን ቅጽል ሁሉ ‹‹ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው›› ብለው ነው የሚረዱት፡፡
(3) ተደራሲዎቻቸው ለረጅም ጊዜ – በተለይ በእንግሊዝኛ ሥራዎቻቸው- ምዕራባውያን ስለሆኑ የሁለቱን ንፍቀ ክበብ ሃይማኖታዊና ሥነ ጽሑፋዊ እይታ እየበለቱ በማስረዳት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እኛም ስናነብ ይኸን ከግምት ውስጥ ብናስገባ ካልተገባ ሐሜት እንድናለን፡፡ እንደ ሰባኪ ሳይሆን እንደ አጥኚ ነው የሚጽፉት፡፡ የሚያነባቸው ሰውም የጥናት መሠረታውያንን ይረዳል ያውቃል ብለው ይገምታሉ፡፡
(4) የፕሮፌሰር አንባቢ ሥራቸውን ከግል እምነታቸው እንዲለይ ይጠበቅበታል፡፡ ስለ ቅብዓት ቢጽፉ ቅብዓትን ደግፈው አይደለም፣ ስለ ሐሳዊው ዘክርስቶስ ቢጽፉልን እሱን ደግፈው አይደለም፣ ስለ ደቂቀ እስጢፋኖስ ሲጽፉልን እነርሱ በሚያደርጉት ሁሉ ተስማምተው አይደለም፣ … ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ሥነ ጽሑፍ በውስጣዊ ዕይታ የማቅረብ ጥረት ስለሚያደርጉ የዚያ ጥረታቸው አካል ነው፡፡ ‹‹መጽሐፍ የያዘውን ማጽናት ልማዱ ነው›› እንዲሉ አበው የያዙትን ርእስ ለማድማት ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ በጽሑፋቸው የሚገልጡት ባለታሪክ ደጋፊ እንዳይመስሉን ማስተዋል ያሻል፡፡
(5)ራሳቸውን እንደ ተራ ሰው ነው የሚያዩት፡፡ ሰብእናቸውን ራሳቸውም በአንዳፍታ ላውጋችሁ የመጀመሪያ ገጾች በመጠኑ ገልጠውታልና ከዚያ ማመሳከር ይቻላል፡፡ አንድ ጊዜ፤ ‹‹ይህ ሰው ማን ነበረ ቢሉህ ‹ዕውቀት እንደጠማው እድሜው ያለቀበት› ብለህ ንገርልኝ›› ያሉኝ በውስጤ ታትሞ ይኖራል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሥራዎቻቸውን ታላቅነት ለመግለጥ ብንደፋደፍ ‹‹አለመሰደቤ ይበቃኛል!›› ብለውኛል፡፡
(6) ፕ/ር ከኢትዮጵያውያን ምሁራን በተለየ አድናቆታቸውን አይሰሱትም፤ እጅጉን አመስጋኝ ናቸው፡፡ ከእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የመንፈስ ልጆቼ እስከሚሏቸው እስከነ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለጻፉ ሁሉ ክብር አላቸው፡፡ በቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ላይ የጣሉትን ተስፋና ለዲ/ዳንኤል የመዛግብት ኀሠሣ ያላቸውን አድናቆት ሲሰስቱ አላየሁም፡፡ የስደትና የአካላዊ ጉዳት ምክንያት ለሆኗቸው አቡነ ቴዎፍሎስ ያላቸው ክብርና አድናቆት የማይደበቅ ነው፡፡ ግዕዝ በቀላሉ የተሰኘውን መጽሐፋቸውንም መታሰቢያ አድርገውላቸዋል፡፡
(7)የቤተ ሰብእ ሰው መሆናቸውን በየኢሜይሉ ልውውጥ ምክንያት ሳይኖር እንኳ ስለባለቤታቸውና ልጆቻቸው ከሚያነሡበት መንገድ ታዝቤያለሁ፡፡ የተረጋጋ ቤተ ሰብእ መገንባታቸው ጉዞአቸውን እንዳሳመረላቸው ዕድሜ እንደ ቀጠለላቸው አምናለሁ፡፡ ‹‹ናሁ ከመዝ ይትባረክ ብእሲ ዘይፈርሆ ለእግዚአብሔር›› ቢባልላቸው ስለሚገባቸው ነው! የተባረከ ቤተ ሰብእ አላቸው! የአባታቸው ፍቅር ሳይወጣላቸው ተቀላቅለዋቸዋል! አባቱን ባሰበ ቁጥር ሰቀቀኑ የማይወጣለት ልጅ ነኝና የአባታቸው ናፍቆት እየተጋባብኝ እቸገራለሁ!
(8)ፕሮፌሰር እጅግ ምልስና ድንጉፅ አባት ናቸው፡፡ በጻፉት ጽሑፍ የሰው ስሜት ሲጐዳ ካዩ ያዝናሉ፡፡ ጽሑፋቸውን እንደ ገና ይመረምራሉ፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስና በአባ ባሕርይ ዙሪያ አዳዲስ ጽሑፍ በወጣ ቁጥር በተደጋጋሚ መመላለሳቸው ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የደቂቀ እስጢፋኖስን መሪ አባ እስጢፋኖስን ቢያደንቁና በቅድስና ቢጠሩም እንቅስቃሴው በፕሮቴስታንታውያን ወገኖች ያልግባብ ተለጥጦ በመወሰዱ እጅጉን ከማዘን አልፈው አቋማቸውን የሚያጠራም የሚያፀናም ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገደው ነበረ፡፡ አንዳንድ ጽሑፎቻቸው በሙስሊምና አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መፍጠራቸውን እንደሚገነዘቡ በአንዳፍታ ላውጋችሁ ጠቆም ያደርጋሉ፡፡ በምሥራቅ ጎጃሙ የቆጋ ድርጊት እንዳዘኑ ነው ያለፉ፡፡ የቅብዓትን አስተምህሮ አጥንተው የአስተምህሮው መሪዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በማየት ቢደነቁበትም እንደ አማኝ በቅርብ ጊዜው ድርጊት አዝነዋል (በዚህ ርእስ ዙሪያ የተለዋወጥናቸውን መልእክቶች ለብቻ አቀርባለሁ፡፡)፡፡
(9) ክርስቲያን ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ዶግማ ታማኝ ናቸው፡፡ ከላይ እንዳልነው በግብፅ ኮፕት ከጳጳሳት ውጭ ያሉ ዘመደ ካህናትና ምዕመናን በቅዱስ ሲኖዶስ ሲሳተፉ አይተዋልና የእኛ ቅ/ሲኖዶስም ይህን እንዲያደርግ በመመኘት ትችት ይሠነዝራሉ፡፡ አፍራሽ የውጭ ትችት እንጂ የውስጥማ ጠጋኝ ነው ብለው ስለሚያምኑ እንደኔ ያሉ ድንጉጦች በርገግ እስኪሉ ድረስ ሊደረግና ሊታረም ይገባል ያሉትን ይጽፋሉ፡፡
(10) ፕሮፌሰር ጌታቸው በአጻጻፍ ዘይቤ የተለየ የራሳቸው መለያ ቀለም አላቸው፡፡ ዐረፍተ ነገሮቻቸው ብዙ ጊዜ አጫጭሮችና ነጠላ ሰረዝ ያለባቸው በመሆናቸው ‹‹ችብስ›› የመብላት ምቾት ዓይነት አላቸው፡፡ አንድን የግእዝ ቃል ወደ አማርኛ ሲመልሱ ከዐውዱ ባለማውጣትና ወደረኛውን ቃል በማኖር ሊተካከሏቸው የሚችሉት የዘመነ አክሱምና የመካከለኛው ዘመን መተርጕማን ናቸው፡፡ ዐረብኛን፣ ግሪክንና አማርኛን በዘዬ ጭምር ያውቁታል፡፡ ከቃል ዘር ሲያወጡ ወጥ አካሄድን ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹ገለበጠ›› የሚለው ቃል (በ‹ሀ› ግእዝ: ‹ሁ› ካዕብ አነጋገር) ከአራት የግእዝ ፊደላት የተዋቀረ ነው፤ ዘር ሲወጣለት ‹‹ግልበጣ›› ይባላል፡፡ በዚህ አምሳል ‹‹መሰከረ›› የሚል ግስ ቢኖር ፕ/ር ዘር ሲያወጡለት ‹‹ምስክርነት›› ብለው አይደለም፤ ‹‹ምስከራ›› ይሉታል እንጂ፡፡ ቀለም አላቸው! ከአማርኛዎቻቸው ለማስታወስ፡-  መሻማትን ለመግለጥ ‹‹መመሳጥ››፣ ይዘት ለማለት ‹‹ይዞት››፣ ተሞክሮ ለማለት ‹‹ተመክሮ››፣ አብያተ ክርስቲያናት ለማለት ‹‹አብያተ ክርስቲያን››፣ ዐረብ አደረጓቸው ለማለት ‹‹አሳረቧቸው››፣ ጳጳስ አደርገው ሾሟቸው ለማለት ‹‹አጰጰሷቸው››፣ … የመሳሰሉ መገለጫዎች አሏቸው፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው በአማርኛ በኩል የብላቴን ጌታ ኅሩይ አድናቂ መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍሰ ሣህለ ማርያም ያድኅና እመዐተ ወልዳ፡፡
Filed in: Amharic