>

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን በበዙበት አገር ውስጥ በግል እጩ ሆኖ ለመወዳደር ለምን ፈለገ?  (መታሰቢያ ካሳዬ)

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን በበዙበት አገር ውስጥ በግል እጩ ሆኖ ለመወዳደር ለምን ፈለገ? 
መታሰቢያ ካሳዬ

መንፈሳዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን አጣምሮ ማህበረሰቡን ለመለወጥ የሚተጋውና በሃይማኖት መምህርነቱና በደራሲነቱ የሚታወቀው ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በመጪው ስድስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግሉ ለመወዳደር እጩ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ክልል 28 የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9,10,11,12,13, 14, እና በአዲሱ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ደግሞ ወረዳ 2,3,4,5, እና 10 ውስጥ በሚገኙ 151 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚወዳደረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
 ለምን የግል  እጩ ሆኖ ለመቅረብ ፈለገ?
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን በበዙበት አገር ውስጥ በግል እጩ ሆኖ ለመወዳደር የፈለገባቸውን ሦስት አበይት ምክንያቶች  ሲገልፅ፡-
‹‹ቀዳሚው የአገር ልዕልና ከሁሉ በላይ በሃሳቦች ልዕልና የሚመጣ ነው ብዬ በማመኔ ነው››  ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ፓርቲ ፕሮግራም መዋቅርና አሰራር የሚሰፋ በመሆኑ በፓርቲ ጥላ ስር መከለሉ ምቹ አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ #የሃሳቤ ምንጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምዕራብ ወይም ከምስራቁ አለም እንደሚቀዷቸው ርዕዮቶች ውጫዊ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያውያን እምነት ባህልና ትውፊት ውስጥ የሚቀዱ ናቸው፡፡ በታሪኮቻችን በተረቶቻችን፣ በግጥሞቻችን፣ በባህላዊ ትምህርቶቻችን፣ በፍርድ ስርዓታችን፣ በሃይማኖት ትምህርትና በነባር ጥበቦቻችን ውስጥ የሚገኙ ሃሳቦችን፣ መርሆዎችንና እሴቶችን ገምግመን እኛው ለእኛው በሰራናቸው መፍትሔዎች እንደ ሃገር የገጠመንን ፈተና ድል መንሳት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡; ይላል ዲያቆን ዳንኤል፡፡
“በፓርቲዎች ፖለቲካ ትኩረት የተነፈጋቸው ኢትዮጵያዊ ሃሳቦች፣ መርሆዎችንና እሴቶችን ከፓርቲ ወጣ ብሎ ወደ  ገዢው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ወደ ህጎችም ሆነ ወደ አሰራሮች ማዝለቅ የሚያስችል ዕድል የሚሰጠኝና ከነባር አገራዊ ዕውቀቶች የተቀዱ ኢትዮጵያዊ ሃሳቦች፣ በፖሊሲ ቀረፃዎች፣ በህጎችና አሠራሮች ውስጥ የተመጣጠነ ቦታ እንዲያገኙ ግፊት ለማድረግ የሚያስችለኝ በግል እጩ ሆኜ መወዳደሬ ነው” ሲልም ያስረዳል፡፡
ሁለተኛው በግል እጩ መሆንን ያስመረጠው ምክንያት ደግሞ የፓርቲ ተመራጮች በሚበዙበት ፓርላማ ውስጥ ከፓርቲ ውግንና እና  አጥር ነፃ የሆነ አቀራረብ ሊኖር ይገባል ብሎ ማመኑ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ፉክክርን ብቻ ሳይሆን መተባበርንም የሚፈልግ በመሆኑ በፓርላማ የሚነሱ የተሻሉ ሃሳቦች ተቀባይነት ለማግኘት የሚችሉበትን ዕድል  ለመወሰን ከፓርቲዎች ይልቅ ለግል ተመራጩ የተሻለ ነፃነት ይሰጣል ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዲ/ዳንኤል ክብረት በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የመታቀፍ ፍላጎት የለውም፡፡ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ታቅፎ በእጩነት እንዲወዳደር የቀረበለትን ጥያቄም ያልተቀበለው ከበፊት ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የመታቀፍ ፍላጎት ስላልነበረው እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ፖለቲከኝነት የንቁ ዜጋም ስልጡን እንቅስቃሴ እንጂ በፓርቲ አባልነት ብቻ የተወሰነ አይደለም የሚለው  ዲያቆን ዳንኤል፤ በግል እጩ ሆኖ ለመወዳደር መወሰኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያሳውቅ ጠንክሮ እንዲገፋበት እንዳበረታቱት ይናገራል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል በኢትዮጵያ ባህላቸውን፣ መልካቸውንና እሴታቸውን ያደረጁ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ተቋማት እንዲፈጠሩ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ ወደፊትም በምርጫው ቢያሸንፍ ምኞቱ እነዚህኑ ጉዳዮች አጠናክሮ መቀጠል እንደሆነም ይገልፃል፡፡ 6ኛው አገራዊ ምርጫና ከምርጫው በኋላ የሚኖረው የኢትዮጵያ ጉዞ በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር በጣም መሰረታዊ ለውጦች የሚታዩበት ይሆናል የሚል ግምት እንዳለው የሚናገረው ዲያቆን ዳንኤል፤ በመጪው  ወሳኝ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ በከፍተኛው ህግ አውጭ አካል ዘንድ ከነባር አገራዊ እውቀቶች የተቀዱ ኢትዮጵያዊ ሐሳቦች በፖሊሲዎቻችን ህጎቻችንና አሰራሮቻችን ውስጥ ቦታ እንዲያገኙ የማድረግ ዓላማን ማንገቡን ያስረዳል፡፡
“ኢትዮጵያዊነት በርቱዓዊነት” የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የምርጫ ዘመቻ መሪ ቃል ነው፡፡ ርቱዓዊ አሥተምህሮ በሸፍጥና በሴራ  የተሞላውን  የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያቃናዋል የሚል እምነት እንዳለው ይናገራል፡፡
“ርቱዓዊነት ከህግም በላይ በእውነት፣ በእምነትና በሞራል ልኬት ስለሌላው ማሰብና ለሌላው በጎ ሲሉ መሠዋትን የሚመለከት ነው፡፡; ይላል ዲያቆን ዳንኤል። ርቱዓዊነት ወንድማማችነትን በተጨባጭ ለማሳካት የሚቻልበት የአእምሮና የልብ መንገድ መሆኑንም ያሰምርበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሐሰትና ግፍ የሌለበትን የቀናና የተስተካከለ የፖለቲካ አመራር፣ የህዝብ አስተዳደር፣ የማህበረሰብ ልማት፣ የተቋም አሰራርና የዳኝነት ስርዓትን ሊቀዳጁ የሚችሉት በርቱዓዊነት እንደሆነም ያምናል።  ይህ ሁሉ ዕቅድና ዓላማ በተለምዶ የፓርቲ መስመር ሲከተል በኖረ ምክር ቤት ውስጥ በግል ተወዳድሮ ለገባ ተወካይ ምን ያህል ፈታኝ ይሆን? የግል ተሳትፎስ ምን ያህል ዋጋ ይኖረው ይሆን? ዳንኤል ለዚህ ጥያቄም ምላሽ አለው፡፡ “በፓርቲዎች መካከል ፍትጊያ በሚበዛበት ምክር ቤት ውስጥ ለማንም ፓርቲ ሳይወግኑ ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለአገራቸው የሚበጀውን እንዲሰሩ የሚያደርግ ሐሳብና ገለልተኛ ሰው ያስፈልጋል፡፡” የሚለው ዳንኤል፤ ድምፅ ለሌላቸው ሃሳቦችና ወገኖች ሁሉ ድምጽ የመሆን ዓላማ እንዳለውም ይናገራል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል  ምርጫውን ቢያሸንፍ ለማድረግ ቃል የገባቸው ጉዳዮች ከዚህ ቀደም በአገራችን ፖለቲካ እምብዛም ያልተለመዱ ይመስላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በምርጫ  ክልሉ ፅ/ቤት መክፈትና የህብረተሰቡን ችግር በመቀበል ለመፍታት ጥረት ማድረግ፣ በፌደራል መንግስቱ፣ በከተማው አስተዳደር፣ በክፍለ ከተማውና በወረዳዎች መካከል የመልካም አስተዳደር ድልድይ ሆኖ ማገልገልና የተወሰነ ጊዜ በምርጫ ክልሉ ህዝብ መሀል በመገኘት በአካባቢውና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከር ይገኙባቸዋል፡፡
“መፍራት ያለብን ፈጣሪን ሕሊናንና እውነትን ብቻ ነው፡፡ መናገር ባለብኝ  ጊዜ ሁሉ እናገራለሁ፡፡ መስራት ባለብኝ ጊዜ እሰራለሁ፡፡ ዝም ማለት በሚኖርብኝ ጊዜ  ደግሞ ዝም እላለሁ፡፡ ወሳኙ ጉዳይ የነዚህን የሶስቱ ነገሮች ትክክለኛ ጊዜ ከማወቁ ላይ ነው፡፡ ሁሉም በንግግር ብቻ፣ ሁሉም በስራ ብቻ፣ ሁሉም ደግሞ በዝምታ ብቻ እንደማይፈታም አምናለሁ፤ ይላል ዲያቆን ዳንኤል፡፡ መጪው ፓርላማ ሁሉም አይነት ሃሳቦች ተወክለውበት፤ ክርክር የሚካሄድበትና ብልጫ ያለው ሃሳብ የሚያሸንፍበት፣ የሐሳብ የበላይነት የሚከበርበት ስፍራ እንዲሆንም ይመኛል። ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ተከብሮ፣ ህዝቦቿ በእኩልነትና በመከባበር አብረው የሚኖሩባት አገር እንድትሆንም እንደሚሻ፣ ለዚህም አጥብቆ እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያን በተሻለ ሃሣብ ወደሚመጥናት ደረጃ ለማሻገር እሰራለሁ” የሚለው ዲያቆን ዳንኤል፤ የምርጫ ምልክቱን መሻገርን አመላካች የሆነውን ፊደል #ሐ;  አድርጓል፡፡ “ፊደል ሐ ሶስት እግሮች በአንድ ራስ የተያያዙበት ነው፡፡ ይኸውም ህግ አውጪው ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈጻሚው አካላት ናቸው፡፡ ምልክቱ እነዚህ ሶስቱ ለአንድ አገር ህልውና በርቱዓዊነት መስራት እንዳለባቸው ያሳያል። ፊደል ሐ ለገበሬው ደግሞ  መንሽ ነው፤ ምርቱን ከገለባው የሚለይበት መሳሪያው፡፡ እናም ዛሬ በአገሬ በየአቅጣጫው በርክተው የሚታዩትንና ለርቱዕ ኢትዮጵያዊነት ፈተና የሆኑትን ሐሰተኛ ትርክቶች ከእውነተኞቹ፣ በእውቀትና በሐቅ መለየት አለባቸው ብዬ ስለማስብም ነው የምርጫ ምልክቴ እንዲሆን የመረጥኩት” በማለት ያብራራል፤ዲያቆን ዳንኤል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀይማኖት መምህርነቱ በስፋት የሚታወቀው ዲያቆን ዳንኤል፤ 32 የነገረ ሃይማኖት መጻህፍትን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡  ተናግሮ የሚያሳምን አንደበተ ርዕቱም እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ በሌላ በኩል በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ወጎችና መጣጥፎችን አሳትሟል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- “የሁለት ሐውልቶች ወግ”፣ “ጠጠሮቹ”፣ “የኔ ጀግና”፣ “ስማችሁ የለም”፣ “እኛ የመጨረሻዎቹ”፣ “የሚከራዩ አማት”፣ “የሰርቆ አደሮች ስብሰባ” እና “ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት” ይጠቀሳሉ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል በቤተ ክህነት ብቻ ሳይሆን በቤተ-ኪነት ምኩራቦችም አዘወትሮ እየተገኘ መልዕክት አዘል ቁምነገሮችን ለታዳሚው ለማድረስ ይታወቃል፡፡ በየመገናኛ ብዙኃኑ ሃሳቦቹን በትውልዱ ውስጥ የሚዘራ አትክልተኛ ነው ይሉታል፤ ብዙዎች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከዓመታት በፊት በመሰረተውና እስካሁንም በዘለቀው ዓመታዊ “የበጎ ሰው ሽልማት” ይበልጥ ስሙንና አሻራውን አሳርፏል፡፡ የተለያዩ የሽልማት ድርጅቶች በየጊዜው እየተቋቋሙ ከዓመት በላይ በማይዘልቁበት አገራችን፣ “የበጎ ሰው ሽልማት” የስምንት ዓመታት ዕድሜ ማስቆጠሩ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትና ከብርን አስገኝቶለታል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በግል እጩነት በመወዳደር ያልተሄደበትን መንገድ የመረጠ ይመስላል። ያልተሄደበት መንገድ ደግሞ ፈተና ይበዛዋል። ይወጣው ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
Filed in: Amharic