በኢትዮጵያ «ዲሞክራሲያዊ ምርጫ» ሊደረግ ይችላል? – ነፃ ምርጫ አለን? ኖሮንስ ያውቃል…???
አሰፋ ሀይሉ
ላለፉት 30 ዓመታት ስሙንና ቅርጹን እየቀያየረ የመንግሥትነትን የሥልጣን መንበር የሙጥኝ ብሎ የቆየው ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ነው? ወይስ በታጣፊ ክላሽና በታንክ አፈሙዝ? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ የወጣው በምርጫ ተወዳድሮ አይደለም፡፡ በጥይት አረር በልጦ ነው፡፡ በመግደል ሀይል በርትቶ ሥልጣን የያዘ ጦረኛ ድርጅት ነው ኢህአዴግ፡፡
ስለሆነም ነው ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ባህል የሌለው፡፡ እንዲኖረውም መጠበቅ የበዛ የዋህነት የሚሆነው፡፡ ኢህአዴግ ላለፉት 30 ዓመታት ሥልጣኑን አስነክቶ የማያውቅም ጠቅላይ ቡድን ነው፡፡ ጠብመንጃንና ምርጫ-ቦርድን አንግቦ በመንቀሳቀስ ኢትዮጵያውያንን ለ30 ዓመታት ሰጥ-ለጥ አድርጎ የገዛና፣ ወደፊትም ሀይልና ጉልበቱን አጠናክሮ ለመግዛት በቻለው አቅም ሁሉ እየታገለና እየተጋደለ ያለ የለየለት አፋኝና በዓለም በሰብዓዊ መብት ረገጣው የተመሠከረለት አምባገነን መንግሥት ነው፡፡
እንግዲህ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊባል የሚበቃ «ነጻ» ምርጫ ሊካሄድ ይችላል ወይ? የሚለውን ስናስብ በቅድሚያ የሚመጡልን ግልጽ እውነቶ ናቸው እነዚህ፡፡ ከእነዚህ የተለመዱ ኢህአዴጋዊ (ማለትም ብልጽግናዊ) ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ልምዶች በተጨማሪ፣ በአሁን ወቅት ሀገሪቱ የገባችበት የእርስ-በርስ ደም መፋሰስ፣ አጠቃላይ ሥርዓት አልበኝነት፣ ጠርዝ የረገጠ ጎሰኝነት፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሲታከሉበት የወትሮው ኢህአዴጋዊ የጨረባ ምርጫ ከወትሮውም በላይ ሳንካ የሞላበት ሆኗል፡፡
የዘመናዊና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችና ተቋማት ከጥቅም ውጪ መሆን፣ የዲሞክራሲ ጅምሮች ሁሉ መጨንገፍና የዲሞክራሲ ተቋማት መቀንጨር፣ የሠላማዊ ዜጎች ሠላም ማጣት፣ ጭፍጨፋ፣ ግድያና መፈናቀል፣ እንዲሁም አብዛኛው የሀገሪቱ ግዛት ነዋሪ ከምርጫ ሂደት ውጭ መሆን ሲደማመሩ – የአሁኑን የኢህአዴግ «ምርጫ»፣ ከምንጊዜውም የተለመዱ ኮሮጆ-ግልበጣ የሚበዛባቸው የኢህአዴግ ያለፉ ምርጫዎች ሁሉ በባሰ ሁኔታ – ፍጹም የማይታመን፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ፣ ኢ-ፍትሃዊና፣ መሠረታዊ የሚባሉ የምርጫ መስፈርቶችን እንኳ ያላሟላ ከይስሙላም የከፋ፣ ዓይን ያወጣ «የይስሙላ» ምርጫ ያደርገዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ስለሚካሄደው የኢህአዴግ ምርጫ (ወይም «ምርጫ» ስለተባለው ጉዳይ) በተመለከተ ጠቅለል ባለ መልኩ ያፈጠጠውን እውነታ ካስቀመጥን፣ እስቲ ደግሞ በዓለማቀፍ ደረጃ በታወቁ መሠረታዊ የሚባሉ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርቶች አንጻር የኢህአዴግን የዘንድሮ ምርጫ እንመዝነው፡፡ እና ፍርዱን ለራሳችን እንስጥ፡፡
1) አጠቃላይ የሀገሪቱን ህዝብ አሳታፊነት
(Effective Participation – Adequate and equal opportunities of citizens)
የሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ የመሳተፍ ዕድሉ የተከበረበት ሠላማዊ የምርጫ ውድድር ለአንድ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መኖር የግድ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት፣ መንግሥት ህጉን አውጥቶ የሚያስፈጽመው በአጠቃላይ ያገሪቱ ዜጎች ላይ ስለሆነ ነው፡፡ የሀገር ዜጎች ለሚገዙበት ህግ ስምምነታቸውን የሰጡ፣ በሂደቱ የተሳተፉና የማይፈልጉትን ህግና ተግባር ያመጡባቸው ወኪሎቻቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉበት (ከሥልጣን የሚያወርዱበትና በሌላ የሚተኩበት) ሥርዓት መኖርን ነው የዲሞክራሲ መኖር የምንለው፡፡ ይህን እውን ማድረጊያው መንገድ ደግሞ ምርጫ ነው፡፡ የኢህአዴግን የቀደመ የምርጫ ባህርይ የምናውቀው ስለሆነ፣ እነዚያን ትተን በአሁኑ የኢህአዴግ ምርጫ ላይ እናተኩርና ራሳችንን እንጠይቅ፡፡
የአሁኑ የኢህአዴግ ምርጫ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የመምረጥ ዕድሉን የሰጠ ነው ወይ? – በትግራይ ክልል ምርጫ አይደረግም፡፡ ስለሆነም 6,000,000 ከሚገመተው የትግራይ ህዝብ መሐል ለምርጫ ብቁ የሆኑ መራጮች በሀገራዊው ምርጫ የመሳተፍ መብታቸው ታግዷል ማለት ነው፡፡
በተመሣሣይ መንገድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በብዛት የአማራ ተወላጆች የሚኖሩበት የመተከል አካባቢም ከምርጫ ውጪ መደረጉ ተነግሯል፡፡ ይህ ማለት በቁጥር ከ500,000 (ከግማሽ ሚሊዮን) ህዝብ በላይ እንደሆነ ከሚገመት የሀገሪቱ ዜጋ መሐል ለመምረጥ መብት ያላቸው ዜጎች መብታቸውን ተነጥቀዋል ማለት ነው፡፡ የቀረውም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምርጫና መራጭ ሕዝብ በአሻድሊ ሀሰንና (በአጎራባቹ ሽመልስ አብዲሳ) ኢህአዴጋዊ የክልል አፈና መዋቅሮች ቁጥጥር ሥር የዋለ ነው፡፡
በሶማሊ ክልል የሚደረገውም ምርጫ እንደተራዘመ ተነግሯል፡፡ የሶማሊ ክልል ህዝብ ቁጥር እስከ 6,000,000 እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ መካከል ለመምረጥ የሚችሉ ዜጎች መብታቸው ለጊዜውም ቢሆን ተገድቧል ማለት ነው፡፡
በእንዲህ ያለ መልክ የአንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የምርጫ ክልል ነዋሪዎች ሌላው የሀገሬው መራጭ ከመረጠና ውጤቱ ከተገመተ ወይም ከታወቀ በኋላ እንዲመርጥ መደረጉ፣ አሊያም በእኩል ጊዜ እንዲመርጥ ቢደረግ ኖሮ ሊኖር ከሚችለው ውጤት ጋር ሲነጻጸር በመራጮች ስነልቦናና የምርጫ ውጤታቸው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ግዙፍ እንደሆነ በዓለም ዙሪያ በተከሰቱ መሰል የምርጫ አጋጣሚዎችና ድጋሚ ምርጫዎች በጉልህ የተስተዋለ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙው መራጭ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ እንደተሸነፈ ለተነገረለት ቡድን የምርጫ ድምጹን ለመስጠት የሚነሳሳበትን ምክንያት እንደሚያጣ ግልጽ ነው፡፡
በመላው ኦሮሚያ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በኢህአዴግ በሚደረግብን ግድያ፣ አፈናና እስር ምክንያት በነጻ ለመወዳደር እንችልም በማለት ከምርጫ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ክልሉ አለኝ ከሚለው 35,000,000 ህዝብ መሐል ለምርጫ ከደረሱት ዜጎች ውስጥ ከገሚስ በላይ የሚሆነው ህዝብ ራሳቸውን ከምርጫ ካገለሉትና ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ከሚታወቁት የኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል ጋር አብሮ ከምርጫው ውጪ የሚሆን ነው፡፡
ኢህአዴግ በኦሮሚያ የሚወዳደረው ከራሱ ከኢህአዴግ ጋር ነው፡፡ ማለትም ቀጄልቻ የተባለው የኢህአዴግ ወኪል፣ ጉርሜሳ የሚባለውን የኢህአዴግ ወኪል አሸንፎ ኢህአዴግን ለመወከል ነው የምርጫው ፉክክር፡፡ እንጂ ከኢህአዴግ ጋር የሚፎካከር ተወዳዳሪ የለም፡፡ በኦሮሚያ ብቻውን ተወዳድሮ የሚያሸንፈው ኢህአዴግ ያለምንም ተቀናቃኝ 178 የፓርላማ ወንበር በእጄ አስገባሁ ብሎ እስኪያውጅ እየተጠበቀ ነው፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ ለየነገዱ (ብሔር ብሔረሰቡ) ተሸንሽነው በየተሰጡት የሀገሪቱ የአስተዳደር ክልሎች ውስጥ ያሉ፣ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች – የራሳቸው ብሔር የሆኑ ተዋካዮችን የመምረጥ መብታቸው መገደቡንም ሳንረሳ ነው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ከ10,000,000 በላይ የአማራ ተወላጆች እንደሚገኙ በተደጋጋሚ የሚነገር አኀዝ ነው፡፡ የእነዚህ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት በኢህጋዊ መንገድ በስልታዊ አሠራር ተገድቦባቸዋል ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ከክልሉ ውጪ የሚኖረውን ጉራጌ፣ ከክልሉ ውጪ የሚኖረውን ስልጤ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ፣ አፋር፣ ሶማሊ፣ ወዘተ እንቁጠረው፡፡ በሚሊየን የሚቆጠሩ እነዚህ ዜጎች በኢህአዴግ የጎሳ ሥርዓት አወቃቀር የተነሳ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ ናቸው፡፡ ከክልላቸው ውጪ ሆነው እንዲመርጡ ከተፈቀደላቸው ከአደሬዎች በስተቀር፡፡
ሌሎችንም ብዙ የኢትዮጵያን አካባቢዎች ህዝቦች መናገር ይቻላል፡፡ በተለይ አሁን ሀገሪቱ ካለችበት የጸጥታ እጦትና የመንግሥት የሀገሪቱን ሕዝብ ደህንነት ከታጠቁ የፖለቲካ ጎራዎች ጥቃት ለመታደግ ካሳየው እጅግ ኢምንት ፍላጎት አንጻር፣ በብዛት ከከተሞች ወጣ ብሎ የሚኖረው ማህበረሰብ ደፍሮ የፈለገውን ለመምረጥ የሚያስችለው የህይወት ዋስትና ያላገኘና፣ ስለሆነም የማይመርጥ ሕዝብ ነው፡፡ እና ሌላውን ሁሉ ዓለማቀፍ የምርጫ መስፈርት ትተን፣ የአሁኑ የኢህአዴግ ምርጫ የኢትዮጵያውያንን መራጮች የመምረጥና የመመረጥ መብት ያከበረ ምርጫ ነው ወይ? ብለን እንጠይቅ፡፡ መልሱ ግልጽ መሰለኝ፡፡
2) የበቂ አማራጮች መኖር
(Availability of Choice – Political diversity)
የኢህአዴግ የፖለቲካ ሥርዓት በብዛት በኮሚኒስታዊ መንገድ የተቃኘ፣ እና ነጻ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመምሰል ደግሞ በዓለም የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ የተረጋገጡ የሰው ልጅ መብቶችን አጭቆ የያዘ፣ እና እጅግ ኋላቀር የሆነ የራሱን ዓይነት የተለየ የብሔር-ብሔረሰብ አወቃቀር፣ በዘር ሽንሸና ላይ ከተመሠረተ የክልልና ዞን አደረጃጀት ጋር ቀላቅሎ የያዘ (tribal politics mixed with racial segregation) የፖለቲካ ሴኮንዶ-ሚስቶ የመሰለ – በተግባር እጅግ ኋላቀርና ደፍጣጭ – በመልክ ደግሞ የዘመነና ዲሞክራሲያዊ ቀለም የተቀባ፣ በአንድ የታጠቀ የኢህአዴግ አውራ ቡድን የተጻፈም፣ የሚመራም የሚጠበቅም የለየለት አምባገነናዊ ሥርዓት ነው፡፡
ይህን በመሰለ ሥርዓት ውስጥ፣ ከሥርዓቱ የተቃረኑ ዜጎች ሁሉ «ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ» ተንቀሳቅሳችኋል ተብለው የሚፈረጁበትና በታጠቁ ወታደሮች የሚገደሉበት፣ የሚሳደዱበትና በእስር የሚንገላቱበት ሥርዓት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ያው የራሱን ኋላቀር የዘር ፖለቲካ የአጠቃላይ ሀገሪቱ ሥርዓት መዋቅር አድርጎ በቀጠለ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሆነው ነው ሌሎች ተቀናቃኞች ኢህአዴግን የሚወዳደሩት፡፡ ወይም እንዲወዳደሩ የሚታሰቡት፡፡
ዓሳ እና ዓሳነባሪው በአንድ ገበታ ቀርበው «ብሉ» እየተባሉ፣ እንዴት ውድድር ሊኖር ይችላል? በኢትዮጵያ ውስጥ በቂ በሀሳብ ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ አማራጮች ለህዝቡ ይቀርባሉ ወይ? ሥርዓቱስ ያንን ይፈቅዳል ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የፖለቲካ አማራጮች ሊኖር ቀርቶ፣ ተመሳሳይ የዘር ሽንሸና ፖለቲካውን የሚቀበሉ የፖለቲካ ቡድኖች መሪዎችና ተከታዮች ራሳቸው ዛሬ እስርቤት ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ የቀሩትም ተገድለዋል፡፡ አሊያም በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ተዘምቶባቸው እየታደኑ የሚገኙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የፖለቲካ አማራጮች የሉም፡፡ አሁን ባለው የኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥም ሊኖሩ አይታሰቡም፡፡
3) ለምርጫ መብት አስፈላጊ የሆኑ የዜጎች መብቶችስ ተከብረዋል?
(Freedom of Citizens – Freedom from fear, and other corollary freedoms of speech, association, assembly, demonstration, etc)
በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ኢህአዴግ እጅና እግር የሌለው የጠብመንጃ አፈሙዝ አገዛዝ ነው ያሰፈነው፡፡ ይህ ግማሹ በፀጥታ ሰበብ፣ ግማሹ በወያኔ፣ ግማሹ በኮሮና ወረርሽኝ፣ ግማሹ በብሔሮች ግጭት፣ ግማሹ በአቅም ውሱንነት፣ ግማሹ በሌላ ሺህ ምክንያቶች እየተሳበበ፣ ብዙዎቹ በዓለም የታወቁ የዜጎች የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ከኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በጠራራ ጸሐይ ተገፍፈዋል፡፡
በአሁኑ ከኢህአዴግ ዘመኖች ሁሉ በከፋው የሥልጣን ዘመኑ፣ ዜጎች ከፍርሃት ነጻ አይደሉም፡፡ አይደሉም ብቻ አይበቃም፡፡ በጠራራ ፀሐይ በመንግሥት ታጣቂዎችና፣ በሌሎች የታጠቁ የጎሳ ሀይሎች በትብብርና በፈረቃ ይታረዳሉ፣ በጥይት ይረሸናሉ፣ ተገድደው ይደፈራሉ፣ እርጉዞች ይተለተላሉ፣ ህጻናት በቤታቸው እንዳሉ በእሳት እየተለኮሰባቸው ይንጨረጨራሉ፡፡ በመቶ ሺህዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለሀገር ውስጥና ለሀገርውጭ ስደት ተዳርገዋል፡፡
ኢትዮጵያችን በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ቀዳሚ የስደተኞች ተቀባይ ሀገር ተብላ ከ900,000 እስከ 1,000,000 የሚገመቱ የአካባቢውን ሀገራት ስደተኞች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎቿ የምታኖር፣ የራሷ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ግን ለከፋ ስደትና መፈናቀል የተዳረጉባት ለሰብዓዊ ትንተናም ሆነ ድምዳሜ የማትመች የዜጎች ሲኦልነቷን እያስመሰከረች ያለች የኢህአዴግ የዘር ሽንሸና ጦስ ያነደዳት ምድራዊ የጎሰኞች ቤተሙከራ ሆናለች፡፡
እንኳን ስም የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ይቅርና የታወቁ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስብሰባ ይከለከላሉ፣ ሆቴሎች የስብሰባ ቦታ ከፈቀዱ የበቀል እርምጃ ይጠብቃቸዋል፣ ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ በብዙ መንገዶች የተከለከለና ለህይወት የሚያሰጋ ነው፡፡ በመናገር ነጻነት በኩል በአንድ ወቅት የኡጋንዳው አምባገነን ኢዲ አሚን እንዳለው ሆናለች የኢህአዴጓ ኢትዮጵያ፡፡ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ – የመናገር ነጻነት አለ፣ ነገር ግን ከተናገርክ በኋላ ከሥራህ ትባረራለህ፣ መሬትህን ትነጠቃለህ፣ እስርቤት ልትወረወር፣ ልትታረድና፣ ልትረሸንም ትችላለህ! እንግዲህ እነዚህ መብቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ ነው የምርጫ መብቶች እንዲከበሩ የሚጠበቀው? በመልሱ ከዚህ በላይ ራሴን አላደክምም፡፡
4) ነጻና ገለልተኛ ፍርድቤት
(Independent Court and Judicial Remedy)
በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ዳኞቹና ፍርድቤቶቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንግሥቱንና ባጀቱን በተቆጣጠረው በኢህአዴግ መዳፍ ውስጥ የዋሉ ናቸው፡፡ ዝርዝሩ ለወደፊቱ የሚቆየን ሆኖ፣ ለአሁኑ ግን ለጥያቄው ያህል በኢህአዴግ ዘመን የፍርድቤቶች አደረጃጀት ውስጥ የሚታዩትን እውነታዎች በአምስት ዋና ዋና መንገድ ልንገልጻቸው እንችላለን፡፡
በኢህአዴግ ዘመን ፍርድቤቶች መዋቅራዊ ነጻነት አላቸው ወይ? – በፍጹም የላቸውም፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከሚባለው ጀምሮ፣ እስደ ዳኞች ሹመትና ሽረት ሁሉም ነገር በኢህአዴግ መልካም ፈቃድና ቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጎ የተቀረጸ መዋቅር ነው የምናገኘው፡፡
ፍርድቤቶች የውሳኔ ነጻነትስ አላቸው ወይ? ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ለማንኛው ዳኛ እንደሚመሩ፣ በየትኛው ችሎት እንደሚወሰኑ፣ ዳኞቹ በማን እንደሚመረጡ፣ በምን መልክ ጉዳዮቹ በችሎት እንደሚመሩ ግልጽ ነው፡፡ ነጻነት የላቸውም፡፡
የአሠራር ነጻነትስ አላቸው? የላቸውም፡፡ ከአንድ ኢህአዴግ ቤት በጥቅሻ የሚግባቡ ካድሬዎች ግማሾቹ ፍርድቤቶች፣ ግማሾቹ ጠቅላይ አቃቤ ህጎች ሆነው በሚሰሩበት ከፓርቲ ያልተለየ የመንግሥት ሥልጣን በሚዘወርበት ሀገር አንዱ ከአንዱ ተለይቶ የአሠራር ነጻነት የሚዘረጋበት ዕድልም ቅንጦትም የለውም፡፡
በኢህአዴግ ዘመን የዳኝነቱ አካል የበጀት ነጻነትስ አለው ወይ? በኢህአዴግ ዘመን ያውም ፍርድቤቶች በዳኝነት ክፍያና በቅጣት ክፍያዎች፣ በቴምብሮች ወዘተ የተለያዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገቢዎችን ከዜጎች ላይ የሚሰበስቡ ተቋማት ሆነውም እንኳ ሳለ፣ ነገር ግን በኢህአዴግ ቁጥጥር ሥር የዋለው ፓርላማ (በባንኩም በታንኩም) ጥገኛ ናቸው፡፡ የፍርድቤቶቻችን በጀት ከቤተመንግሥት ግቢ በጀት ጋር የሚቀራረብ እጅግ አስቂኝ ባጀት ነው፡፡ እሱም ቢሆን በኢህአዴግ በኩል ለኢህአዴግ ሹመኞች የሚተላለፍ የእንካ ለእንካ ባጀት ነው፡፡ እና ሌላ ቀርቶ ከተፈቀደለት ዳኛ በላይ ለመቅጠር በኢህአዴግ የበጀት ጥገኛ የሆነ ተቋም – ከበጀት ነጻ ሊሆን አይችልም፡፡ ብ
ዙዎቹ ዳኞች የፍርድቤቱን ባጀት አያወቁትም፡፡ የዳኝነት አካሉ አስተዳደራዊ አሰራሮች ከዳኞች የተሰወሩና በካድሬዎች እጅ የሚዘወሩ ናቸው፡፡ ዳኞች በስብሰባና በመሳለጥ መከራቸውን ይቀበላሉ፣ ከሥርዓቱ ያፈነገጠ ብድራቱን እዚያው ያገኛታል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ዳኞች ደመወዝ በአፍሪካችን፣ ሀገር ከሌላት ከሶማሊያና ከሚጢጢዎቹ አፍሪካዊ ሀገራት ከእነ ሌሶቶና ሞሪሺየስ ጋር ራሱ ሲወዳደር እጅጉን አናሳውና አሸማቃቂው የወረደ ክፍያ የሚከፈላቸው ናቸው! ለአንድ ግለሰብ ብሎ አዋጅ የሚያጸድቀው ኢህአዴግ ለህግ ያለውን የወረደ ክብር በተለያዩ መንገዶች ማየት ይቻላል፡፡
ከድራማውና የምርጫ ችሎቶች ተቋቁመዋል ከሚለው ሸፍጠኛ ማሽቃበጦች አልፈን፣ እንዲህ ዓይነት የዳኝነት አካሎችን ተሸክመን በምንጓዝበት የኢህአዴግ አገዛዝ ሥር – ፍትሃዊ ምርጫ ይገኛል፣ ፍትህን የሚያስከብሩ የዳኝነት አካላት ይኖራሉ ብሎ መጠበቅ እጅግ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በየፍርድቤቱ መቋቋማቸው የተነገረላቸው ልዩ የምርጫ ችሎቶች የተባሉትን በተመለከተ፣ የአሁኑ ኢህአዴግ ከበፊቱም ተሞክሮው ብሶ ዓይን በማውጣት፣ በምርጫ ጉዳይ የሚነሱ ክርክሮችን በመደበኛ ችሎቶች እንዲታዩ ከማየት ይልቅ፣ የሚፈልጋቸውን ካድሬ ዳኞች ሰግስጎ ድራማውን የሚተውንባቸውን የምርጫ ጉዳይ ብቻ የሚያስተናግዱ ችሎቶች መክፈቱ ከፍ ባለ ጥርጣሬ ውስጥ የሚወድቅ፣ እና የበፊቱን ህቡዕ ኢህአዴጋዊ ሸፍጦች በፊት ለፊት አዛኝ-ቅቤ-አንጓቻዊ ያደባባይ ሸፍጦች ለመተካት የቻለበት፣ የዳኝነት ነጻነትንም እኩልነትንም የሚጻረር፣ እና ፍርድቤቶችን በተላላኪነት ለማሰማራት እጅጉን የቀለለ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
5) ነጻ ሚዲያና የፕሬስ መብቶች
(Freedom of the Press Impartial Media – Free flow vs. control of agenda)
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ባቀረብኩት ጽሑፍ በኢትዮጵያችን የሚዲያ ነጻነት እንደሌለ በዝርዝር አመልክቼያለሁ፡፡ ይህንኑ ከሚከተለው የፌስቡክ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላልና የገፁን አድራሻ አስቀምጬ አልፈዋለሁ፡-
6) በፓርቲዎች ውስጥና ከፓርቲዎች ውጪ ያሉ ነጻነቶች መረጋገጥ
(Freedom of Political Parties – External and internal)
የፖለቲካ ምርጫዎች ነጻ መሆናቸው ከሚረጋገጥባቸው መለኪያዎች አንዱ የፓርቲዎች ውጫዊ የመንቀሳቀስ መብቶች የመረጋገጣቸው ጉዳይ፣ እና የፓርቲዎች ውስጣዊ ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች የተረጋገጡበት መጠን ነው፡፡ በቀድሞውም ሆነ በአሁኑ ኢህአዴግ የፓርቲ ውስጥ አሠራር «ዲሞክራሲ» የሚባለው ነገር ከቃል ባለፈ በተግባር የሚታወቅ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ አይታወቅም፡፡ አይተገበርምም፡፡
በሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ በኢህአዴግ ህዋሶች መካከል በሚካሄዱ የውስጥ ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር – ከኢህአዴግ መርሆችና መመሪያዎች ያፈነገጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ስማቸው እየተጠራ – እንደ 60ዎቹ የአብዮት ዘመን «እገሌ ይመታ የምትሉ!» «እገሌ ትመታ ወይስ አትመታ?» እየተባለ፣ በአመለካከት የተለየን ዜጋ በጣት ማውጣት በሚወሰን ድምጽ ድብቅ የሚመታበትና አፈርድሜ የሚግጥበት ሥርዓት ነው፡፡ የኢህአዴግ አባላት እንኳን በአመለካከት ከድርጅቱ ዛሮችና ማዕከላዊ ጉልተኞች መመሪያ ሊያፈነግጡ ይቅርና፣ ከኢህአዴግ አመለካከት የተለየ አመለካከት ከያዘ ግለሰብ ጋር አብረው መታየትን እንደ ጦር የሚፈሩ ናቸው፡፡
የኢህአዴግ በታንክና በታጣፊ ክላሽ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው የ60ዎቹ የመግደልና የመሞት – የጠላትና የአጋር ፖለቲካ – አሁንም በኢህአዴግ ዘመን ሁሉ – እስካሁኑም ድረስ ኢህአዴግ በተቆጣጠራቸውና እጁን ባስገባባቸው የህይወት መስኮች ሁሉ ውስጥ ቀጥለዋል፡፡ በዚህ በኩል ኢህአዴግ የሀሳብ ልዩነት ኖሮህ ሊያኖርህ የማይችል እኩይና አረመኔ ኮሚኒስት ነው፡፡ ድንገት መስሚያ ጆሮ ይኖራቸዋል የሚባሉ የፓርቲውን ከፍ ያሉ ሰዎች ብትጠይቅ የሚሰጥህ ምላሽ፣ «አባሎቻችንን ጠላትና ወዳጅ ብለን ካላሰለፍን የፓርቲያችንን ህልውና ጠብቀን መቀጠል አንችልም፣ ኢህአዴግ ከውስጥ ይሸረሸርብናል!» የሚል ፍርሃታቸውን ይነግሩሃል፡፡ ኢህአዴግ እንዳይሸረሸር የአባላቱ መብት ይሸረሸራል፡፡
ሌሎች የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከኢህአዴግ አፈናና የጠላትነት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ብዙ ነገራቸው በሸፍጥና በህቡዕ ግንኙነቶች የተሞላ ሊሆን በቅቷል፡፡ ኢህአዴግ ጠላት ብሎ እያሳደደው፣ ወዳጄ ነው ብሎ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ አባላትን የሚያፈራ ነጻ የፖለቲካ ፓርቲ ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ ብዙዎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በስብስቴ ዘመን በጉልተኝነት በተሰየሙ የፖለቲካ መሪዎች የሚዘወሩ ናቸው፡፡ የዕድሜ ልክ ሥልጣንን ይዞ ታማኞችን እያፈሩ መቀጠል፣ ከኢህአዴግ ቤትም አልፎ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችንም የመታ የዲሞክራሲ ዋግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ስለውጪያዊ የፓርቲዎች ነጻነት ስናወራ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያክል በመላ የኢትዮጵያ ግዛቶች አባሎቻቸው፣ ደጋፊዎቻቸውና እንቅስቃሴያቸው ባጠቃላይ ከኢህአዴጋዊ ሥልጣናትና ከታጠቁ ጎሰኛ አሸማቂ ሀይሎች ጥቃትና ማሸማቀቅ ነጻ ነው? የሚለውንም ጨምረን ማየት ይኖርብናል፡፡ በዚህ በኩል ከታየ፣ የኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲዎች – ከራሱ ከኢህአዴግ በስተቀር – በሀገሪቱ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው፣ አባላቱና ደጋፊዎቻቸው በሰላምና ያለስጋት ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሥራቸውን ሊያከናውኑ የሚችሉበት የፖለቲካ አየርም፣ ፀጥታውም፣ የኢህአዴግ ፍላጎትም የለም! ስለሆነም የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለጸጥታ ምቹ መሆናቸው በተመሰከረላቸው የደሩ ከተሞች ብቻ ላይ የተወሰነ ሊሆን ግድ ብሏል፡፡
በአንዳንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች በኩል ለኢህአዴግ ከበሮ ለመደለቅ ካልሆነ በቀር፣ እንደ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ያልረገጥነው የኢትዮጵያ ግዛት የለም ብሎ መደስኮር ለትዝብት ከማጋለጥና ሸፍጥን ከማስጣጣት በቀር የሚያመጣው ፋይዳ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ባጠቃላይ በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ራሱንም ኢህአዴግንም ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው ነጻነታቸው አልተረጋገጠም!
7) በነጻ የመቀስቀስ ነጻነት
(Freedom to Campaign Freely)
ይሄንንም ነጥብ ከላይ ካነሳሁት ርዕስ ጋር በተገናኘ ያነሳሁት ስለሆነ አልፈዋለሁ፡፡ ለመሆኑ መኢአድ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ በወለጋ ነቀምት ወይም በጉሙዝ አቢ ደንጎሮ ላይ ወይም ሌሎች የባሌ ተራሮች ላይ ሄዶ በነጻነት መቀስቀስ ይችላል ወይ? አሸባሪዎችን በሀይለቃል ማውገዝ – በኦሮሚያ የሚኖሩ ንጹሃን የአማራ ተወላጆችን ማስጨረስ ነው እየተባለ በአማራ ክልል መሪዎች በሚመከርበት ዘመን ላይ እንዴት ባለ ተዓምር ነው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚባሉት አካባቢዎች ከደህንነት ሥጋት ነጻ ሆነው የቅስቀሳ ስራ የሚያካሂዱት?
በጠራራ ጸሐይ የኦነግ ሠራዊት መጥቶ እንደ አንበጣ መንጋ ተግትጎ እንደሚጨርሳቸው እያወቁ፣ ምን ዓይነት ደፋር ነሆለሎች ናቸው ለአንድ ቀን መጥቶ የሚጠፋን የተቃውሞ ፖለቲከኛ ‹‹እንኳን መጣህልን›› ብለው ከጎኑ የሚቆሙት? ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ በተለይ በአሁኑ የኢህአዴግ ምርጫ፣ በህይወትህ ተወራርደህ መሆን አለበት ወደሆነ ቦታ ሄደህ የምትቀሰቅሰው፡፡ በመሐል ከተማ የምርጫ ተወዳዳሪዎች በጥይት ሲቀደነደቡ እየታዩ፣ ማነው በዚህ የጮሌ ዘመን፣ እና መንግሥት አለ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር በማይቻልበት ዘመን ለጥቃት በተጋለጡ አካባቢዎች ሄዶ በነጻነት መቀስቀስ የሚደፍረው? – ይህን ብዬ ባበቃ ይሻላል፡፡
8) የምርጫ ተወዳዳሪዎች፣ የመራጮች፣ እና የምርጫ ጣቢያዎች ከደህንነት ሥጋት ነጻ መሆን
(Electoral Safety – Safety of candidates, electorates, and ballot stations)
ይህንንም ነጥብ ከላይ ያነሳሁት ነጥብ በቀላሉ የሚመልሰው ነው፡፡ ከተሞች በታጣቂዎች ቁጥጥር በሚውሉበት፣ መንገዶች በኢህአዴግ ወሮበሎችና በቄሮ ወጣቶች በሚዘጉበት ሀገር ላይ – እንዴት ነው የምርጫ ጣቢያዎችንና የተወዳዳሪዎችን – እና በተለይም የመራጩን ደህንነት ያስጠበቀ ከሥጋት-ነጻ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው? – ‹‹ልብ እንቅርት ይመኛል›› ካልሆነ በቀር!?
9) በሲቪልና የመንግሥታዊ አገልግሎት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች ያላቸው የፖለቲካ ነጻነት
(Extent of Political Liberalization – Right of dissent inside and outside public institutions)
ይህንንም ጥያቄ ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች መልሰውታል፡፡ በየትኛውም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከፖለቲካ አርበኝነትና አድሏዊነት ወጥቶ ለሁሉም ዜጎች እኩል አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ በዛሬውም ሆነ በትናንትናው ኢህአዴግ መዳፍ በምትመራው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የትኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋም በኢህአዴግ ካድሬዎችና የስለላ ሰንሰለት ቁጥጥር ሥር የዋለ ነው፡፡
ከኢህአዴግ አፈና ውጪ የሆነ ተቋም የለም ማለት ምን ማለት ነው? ዛሬ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የውልና ማስረጃ ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ሃላፊ ወይም ሠራተኛ በቴሌቪዥን ላይ ወጥቶ፡- «ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እያካሄዱ ያሉት የኦሮሙማ አካሄድ ለሀገሪቱ ሠላም ጠንቅ መሆኑን አምናለሁ!» የሚል የግል አስተያየቱን ቢሰጥ ሰውየው ምን ሊገጥመው ይችላል? አንድም ከሰዓታት ያላለፈ ፈጣን እስር! ሁለትም ፈጣን የመሥሪያቤት ግምገማ! ሶስትም ፈጣን ሹም-ሽር! አራት ፈጣን ከሥራ መሰናበት! አምስት ፈጣን የግል ኑሮ መሰቃየት! ስድስት ድብደባ፣ ዛቻ፣ እንግልትና ከማንኛውም የብዙሃን መገናኛ አውታር እርም መባል ያጋጥመዋል!
ይህ ሁሉ በትንሹ ነው! ዓላማውና የብሔር ጀርባው ደግሞ እንደጉድ ተጠንቶ ሲያበቃ፣ የሚጠብቀውም ከፍ ያለ በትር ይኖራል! ይህ የሀሳብ ምሳሌ አይደለም፡፡ ይህን የመሰሉ ብዙ እልፍ እውነተኛ ክስተቶች አሉ፡፡ እንግዲህ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ያለ ሠራተኛ እንዴት ብሎ የውጭ ጉዳይን ፖሊሲዎች ተቃውሞ መናገር ይችላል? በመከላከያ ውስጥ ያለ አባል እንዴት ብሎ ብርሃኑ ጁላ የተናገረውን ተችቶ ይናገራል? የማዘጋጃ ቤት የጽዳት ሠራተኛ እንዴት ብትደፍር ነው የአዳነች አቤቤን የዘረኝነት አካሄድ የምትቃወመው?
ይህ በኢህአዴጓ ኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች የታወቀ የተቃዋሚ ፖለቲከኛን የፌስቡክ ገጽ «ላይክ» ለማድረግ የሚሳቀቁ ናቸው፡፡ በተገኘው ክፍት የሥራ ቦታ እንደንብ ተንጋግቶ ለማመልከትና ለመቀጠር የሚጠባበቅን ተጠባባቂ ሥራአጥ ግብረሀይል («Industrial reserve army») በከፍተኛ ቁጥር ከየኮሌጁ የሚያመርተው ኢህአዴግ በህይወት እያለ መቼም፣ ብዙ ሰዎች አሰፍስፈው የሚጠባበቁትን ሥራውን ለመልቀቅ ያልተዘጋጀ ሰው፣ አንዲትም ሀባ የተቃውሞ ሀሳብ መተንፈስን አያስበውም!
ከቦልሼቪኮቹ የኬጂቢ የአፈና መዋቅር፣ እና ከናዚ ኤስ ኤስ አፋኝ ጓዶች ያልተናነሰ አፋኝ ግብረሀይል በየተቋማቱ ያሰማራው ኢህአዴግ በህይወት እስካለ ድረስ፣ በየተቋማቱ ተቀጥረው በኢህአዴግ በምትቆረጥላቸው ደመወዝ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች፣ የሀሳብም፣ የፖለቲካም፣ የዲሞክራሲ መብቶችና ነጻነቶችም ባለቤቶች ሊሆኑ አይችሉም!
10) የምርጫ ውጤትን ይፋ የሚያደርገው አካል (ምርጫ ቦርድ) ነጻነት
(Machinery Determining Electoral Results)
ይህ ብዙ ጥናት ተሰርቶበታል፡፡ ብዙ ወቅታዊ ጥናትም ያሻዋል፡፡ ሆኖም ብዙው ነገር ከህዝብ ዕውቀት የተሰወረና ጥልቅ ምርምር የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የይስሙላ ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ነው፡፡ እስከዛሬ ነጻ አልነበረም፡፡ አሁንም ብዙዎች እምነት የሚጥሉባትን የቀድሞ የፍርድቤት ዳኛና በእስራት የቆየች የተቃዋሚ ፖለቲከኛ የምርጫ ቦርዱ ሀላፊ አድርጎ ከመሾም ባለፈ – ኢህአዴግ ምርጫ ቦርዱን የሚያሽመደምድባቸውና ጠፍሮ የሚይዝባቸው በርካታ መንገዶች በእጁ ላይ ናቸው፡፡ ነጻነት በተቋማዊ ቁመና አስካልተገነባ ድረስ የምርጫ ቦርዱን በወጣና በወረደ የግለሰብ ሰብዕና አንጻር ብቻ እየለኩ «ነጻ ነው» እና «ነጻ አይደለም» ብሎ መደምደም ላልተፈለገ ስህተት የሚዳርግ ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ምርጫ ቦርዱ በአስፈጻሚው አካል ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ የበጀትና የሰው ሀይል ጥገኛ ነው፡፡ የምርጫ ቦርዱ አቅም በእጅጉ የኢህአዴግ መንግሥት በሚለግሰው ትብብር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ካስፈለገም ኢህአዴግ በፓርላማ ሰብሰብ ብሎ፣ ወይም በአብይ አህመድ በኩል በማንኛውም ሰዓት የምርጫ ቦርዱን ሀላፊ ከሥልጣኑ ማባረር የሚከለክለው ህግ የለም፡፡ ህጉን ራሱ እየጻፈው፣ ተቋማቱን ራሱ ለራሱ እየፈጠረ እንዴት ኢህአዴግን የሚከለክል ህግ ይታሰባል?!
እስካሁን ያየናቸው የተሟላና ተቀባይነተ ያለው ምርጫ መደረጉን የሚያመለክቱ 10 (አስር) ዓለማቀፍ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርቶችን ነው፡፡ ሌሎችም ይህንኑ ያህል ቁጥር ያላቸው መስፈርቶች አሉ፡፡ ብዙዎቹ እርስ-በርስ የተያያዙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የምርጫን ሂደት ብቻ ሳይሆን የሀገሮችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውነተኛ ቁመናና ውስጣዊ ገጽታ በተግባር ለማወቅ የሚረዱም ማነጻጸሪያ ነጥቦች ናቸው፡፡
እነዚህ ነጥቦች ለብዙ ተቋማዊ ጉዳዮቻችን እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከዚህ የይስሙላ ምርጫ ሂደትም አልፈን ጠለቅ ብለን ብንመረምራቸው፣ በዙሪያችን የሚከናወነውን ነገር ብንመረምርባቸው፣ ኢህአዴጋዊ ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል በራሳችን ለመመዘን ብንገለገልባቸው እናተርፋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከጊዜና ከቦታ አንጻር – የቀሩትን የምርጫ ሥርዓት መመዘኛ ነጥቦች ሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ፡፡ ለዛሬ ዝም ብዬ ቁጥር ሰጥቼ ዘርዝሬ ብቻ እሰናበታለሁ፡-
11) የመንግሥት አካሎች ህገመንግሥቱን ቢጥሱ ስለጉዳዩ የሚወስነው ተቋም ብቃትና ነጻነቱ አለው ወይ?
(Machinery Determining Constitutionality of State Actions and Judicial Review)
12) በመንግሥት የሥልጣን አካሎች መካከል እውነተኛ የሥልጣን ክፍፍልና አንዱ የሌላውን የሥልጣን መተላለፍ ሊቆጣጠር የሚችልበት እውነታ አለ ወይ?
(Checks and Balances – Accountability for executive infringements)
13) በሀገሪቱ የተቋቋሙ የምርጫ ክልሎች (የምርጫ ወረዳዎች) ብዛትና ሀገራዊ ስርጭት፣ የሀገሪቱን ህዝብ በትክክል የሚገልጽ፣ መብቱን ያከበረና የህዝቡን ፍላጎት ፍትሃዊ በሆነ መልክ የሚወክል ነው ወይ?
(Electoral College Distribution – Fairness, proportionality and representativeness)
14) በሀገሪቱ ውስጥ በሠላማዊ ምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣውን ኃይል ማውረድ ይቻላል የሚል እምነት በዜጎች ዘንድ አለ? በሀገሪቱ ከዚህ በፊት ሥልጣን የያዘው አካል በምርጫ ካርድ ውጤት መሠረት ከመንግሥት ሥልጣኑ ወርዶ ያውቃል? ወይስ መንግሥትን የተቆጣጠረው ፓርቲ ነው የምርጫ ኮሮጆዎችን እየገለበጠ የምርጫውን ውጤት አሃዞች የሚወስነው? የዲሞክራሲ ባህል ምን ያህል በሀገሪቱ ሰርጿል? ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ለመጠበቅ ምን ያህል አርበኝነት ያሳያል?
(Democratic Culture – Has there ever been a system for choosing and replacing government officials through election? Or is it the government that “fixes” elections? Is there and enlightened and understanding electorate?)
15) የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝና አከባበር ደረጃ እንደምን ያለ ነው?
(Protection of Human Rights for All)
16) የህግ የበላይነት አለ? ህጉ በመንግሥት ባለሥልጣናቱም ላይ፣ በዜጎችም ላይ በእኩል የሚፈጸም ነው? ህጉ ለሁሉም ይሠራል? ነገሮች የሚመሩት በህግና በህጉ መሠረት ነው? ሀጎች የሁሉንም ዜጋ መብትና ፍላጎት ያማከሉ ናቸው? ወይስ የጉልበተኛው ፓርቲ መጨቆኛ መሳሪያዎች?
(Rule of Law)
17) የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎችና የሀገሪቱ ህዝብ ምን ያህል አንዱ ሌላውን የመቀበልና በጋራ ተቀራርበው የሚያስማማቸውን አስታራቂ ነጥብ የመፈለግ ልምዱና ዝንባሌው አላቸው?
(Acceptance of Compromise)
18) የሀገሪቱ የፖለቲካ አየር የተረጋጋ ነው? ሠላም አለ? ህዝቡ ከሥጋት ዳመና ውጪ ነው? ምርጫው የፈለገ ዓይነት ውጤት ቢኖረውም የመንግሥትና የህዝብ ተቋማት መደበኛ ተግባራቸውን የመቀጠል አቅም አላቸው? ሥልጣን በሚይዙ አካሎች መፈራረቅ የተነሳ የሚፈራ ሀገራዊ ቀውስ አለ? ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግርን የሚያስተናግድ ህግና ልማድ አለ በሀገሩ ላይ?
(Political Stability)
19) የዲሞክራሲ ተቋማት ምን ያህል ነጻ ሆነው ይንቀሳቀሳሉ? የእምባ ጠባቂ ተቋማት በነጻነት ለዜጎች መብት መከበር ይሠራሉ? የሰብዓዊ መብት ተቋማት የዜጋውን መብት ይቆማሉ? ፍርድቤቶችስ የዜጋን መብት ያስከብራሉ? የዜጋውን መብት የጣሰ መንግሥት ሊጠየቅ የሚችልበት አቅምና ሥልጣን ያለው ተቋም አለ በሀገሪቱ ውሰጥ? የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ከመንግሥትና ከጉልበተኛ ፓርቲዎች አፈናና ጣልቃገብነት ምን ያክል የተላቀቁ ናቸው?
(Freedom of Democratic Institutions)
20) የዜጎች ማህበራት፣ የሴቶች መብት አስጠባቂ ማህበራት፣ የህጻናት መብት ተቆርቋሪ ማህበራት፣ የመምህራን መብት አስጠባቂ ማህበሮች፣ የሀኪሞች መብት ተከላካይ ማህበሮች፣ የጠበቆች ማህበሮች፣ የሾፌሮች ማህበሮች፣ የምርት ተጠቃሚዎች ማህበራት፣ የፋብሪካ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽኖች፣ የሙያ ማህበሮች፣ የእምነት ማህበሮች፣ የኢኮኖሚያዊ መረዳጃ ማህበሮች፣ ዕድሮች፣ የነጋዴ ማህበሮች፣ የተፈጥሮ ተቆርቋሪ ማህበሮች፣ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ህብረተሰብ አንቂ ማህበሮች፣ እና ሌሎችም የሲቪሉ ማህበረሰብን የሚወክሉ ማህበሮችና፣ ራሱስ የሀገሬው ህዝባና የተለያየ ማህበረሰብ – ፍላጎቶቹንና ጥቅሞቹን በሠላማዊ መንገድ የሚያስጠብቅበትና የሚያስከበርበት፣ ከመንግሥታዊና ድርጅታዊ ጥቃቶች የሚከላከልበት፣ ስለመብቶቹና ጥቅሞቹ የሚደራደርበት ነጻ ማህበሮች አሉት? ነጻነቱ አለው ህዝቡ በሠላማዊ መልክ ተደራጅቶ በሠላም ስለመብቶቹ አበክሮ ለመስራት?
(Freedom of Civil Society)
እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት በአጠቃላይ 20 የሚሆኑ መሠረታዊ ነጥቦች – የማንኛውም በዓለም ላይ ያለ ሀገር ሥርዓት ዲሞክራሲያዊነት የሚለካባቸው እጅግ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡ እነዚህ 20 ነጥቦች የአንድ ሀገር የፖለቲካ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መሆንና አለመሆኑን በትክክል ማሳየት የሚችሉ በዓለም የታመነባቸው መስፈርቶች ናቸው፡፡ በአጋጣሚ በዘርፉ ለጥናት ያንዣበብኩ በመሆኔ ብዙዎቹን ከያሉበት አሰባስቤ በአንድ ላይ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡ እነዚህን ብንጠቀምባቸው፣ ከሚያልፈው ኢህአዴጋዊ ምርጫም ተሻግረን፣ የማያልፍ ቋሚ ተቋማዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመፍጠር እንደ ማንጸሪያ ያገለግሉናል፡፡ እያልኩ ረዥሙን ጽሑፌን በዚሁ አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
የነጻነት ምድር በሆንነው መጠን፣ የነጻነት ምኩራባችንን ጠባቂዎች ያድርገን፡፡ ለነጻነታችን ቀናዒዎችና አርበኞች ያድርገን የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
«ምርጫ» አለ ብለው ለሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ መልካም ምርጫን እመኝላቸዋለሁ፡፡
በኢትዮጵያችን «እውነተኛ ምርጫ» የሚደረግበትን ቀን በተስፋ ለምንጠብቀው ደግሞ ፈጣሪ ልብና ጥበቡን አብዝቶ ይስጠን፡፡
— ተጻፈ በአሣፍ ኃይሉ
ከዋተርሉ፣ ኦንቴሪዮ፣ ካናዳ
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም