ድንቄም ምርጫ! “ልመርጥ” ሄጄ ሳልመርጥ ተመለስኩ
ግርማ በላይ
እኔም ተጨምሬበት ሃሳባችንን ልክ እንደዚህ በጽሑፍ የምንገልጽ ሰዎች የምንጽፈውን ሁሉ በአንደኛ ደረጃ የመረጃ አሰባሰብ እናገኛለን ማለት አይደለም፡፡ ከምንሰማውና ከምናየው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከሰሙትና ካዩት ወይም ከደረሰባቸው ጭምር በመስማትና ከሰሙትም በመቅዳት እንጽፋለን – በዚያም ሂደት አንዳንዴ ልንሳሳት ብንችል ሰው ነንና ይቅርታና ምሕረት ይገባናል፤ የስህተታችን መንስኤ ተንኮልና ሸር ሳይሆን የመረጃና የማስረጃ ዕጥረት ነውና፡፡ መሳሳት ደግሞ ሰውኛ ነው፡፡ አሁን የምጽፈው ግን በራሴ የደረሰና ራሴው የታዘብኩት ነው፡፡
ከምርጫ ጣቢያ አሁን መመለሴ ነው፡፡ “ለደኅነነቴ” ሲባል የምርጫ ጣቢያውን ስምና አድራሻ አልናገርም፡፡ ግን እዚሁ አዲስ አበባ ማለትም ፊንፊኔ ውስጥ ነው፡፡ ፊንፊኔዎች በዋዛ አልያዙንም ጎበዝ! እጅጉን አምርረዋል፡፡
አክራሪ ኦሮሞዎች በያዙት ያረጀና ያፈጀ የዘር መድሎንም ማዕከሉ ባደረገ የተረኝነት መንገድ የትም ሊደርሱ እንደማይችሉ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ምርጫ ጣቢያው ከሄድኩ ጀምሬ ስስቅበት የዋልኩበትን ነገር ነው የምነግራችሁ፡፡ አሁን ሰዓቱን ለማስታወስ ያህል ዕለቱ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ነው – መጻፍ ስጀምር፡፡ (አሁን በዚህች ቅጽበት የመጨረሻውን አርትዖት ሳደርግ ደግሞ 4፡30 ሆኗል፡፡)
- የትዳር አጋሬና ሁለት ይሁኑ ሦስት ጓደኞቿ 150 ሜትር ያህል ከቤታችን ወደሚርቀው ምርጫ ጣቢያ ተጠራርተው የሄዱት – የተጀመረው ቡና እንኳን ሳያከትም – ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ከተጠራሩት ሴቶች የሁለቱ ባሎች 11 ሰዓት ገደማ ወደዚያው ሄድን፡፡ ለምርጫ የተሰለፈው ሕዝብ ከግቢው ተርፎ የኮብልስቶኑን አውራ መንገድ 50 ሜትር ያህል ሸፍኗል፡፡ ተገረምን፡፡ የተመዘገበው ሰው 1500 ከሆነና “ምርጫው” 12 ሰዓት ጧት ከጀመረ ይህንን ሕዝብ አስተናግዶ ለመጨረስ ግማሽ ቀንም ከበቂ በላይ ነው – ቀናነት፣ ሥርዓታዊነትና ሸፍጠኝነት የሌለበት ሃቀኛ አሠራር ቢኖር ማለቴ ነው፡፡ እኛ ስንደርስ ከጧት ጀምሮ እዚያው የዋለው ሕዝብ መምረጥ ባለመቻሉ መንግሥትን እየወቀሰ በምሬት ይተራመሳል፡፡ ምን እየተሠራ እንደሆነ ማንም አያውቅም፡፡ እኔና ጓደኛየ “ሚስቶቻችን ወረፋ ይዘውልን አሁን ጠርተውን ነው” በሚልና በፀጉራችንም ንጣት ታዝኖልን እንድንገባ ተፈቀደልን፡፡ የውጩን ሰልፍ በዚህ መልክ ብንሸውደውም የውስጡን ግን አልቻልንም፡፡ ሁለት ሰዓት ለሚጠጋ ጊዜ አለመላው ተጎልተን ወንበር ካሞቅን በኋላ ተናደን ትተነው ወጣን፡፡ ልንመርጥ ሄደን ሳንመርጥ ተመለስን፡፡ ሚስቶቻችን ግን እዚያው ትተናቸው እንደወጣን አሁንም እስከምሽቱ 2፡30 አልተመለሱም – እግዜር ከሌላ ነገር ይጠብቅልን፡፡ አሃ፣ ኋላ ሰዶ ማሳደድ ነዋ ሞኜ! የውሻሸቱ ምርጫ ጥንቅር ይበል እንጂ በነርሱማ ቀልድ የለም፡፡ (ቀልዴን ነው አንተ!)
- ምርጫ አስተባባሪዎቹ፣ ሰልፍ አስያዡ፣ ሻይና ምግብ በሽያጭ መልክ ለመራጮችና ሠራተኞች እንዲያቀርቡ የተፈቀደላቸው … ምን አለፋችሁ የምርጫው አዛዥ ናዛዥ በአብዛኛውና በወሳኝነት ሚና ላይ የተመደቡት ኦሮሞዎች ናቸው – ይህን መሰል ትያትር ከሦስት ዓመታት በፊት በነበረው ተረኛ በሚገባ ስለማውቀው አለቃ ገ/ሃና “በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ” ያሉትን የጎመን ይሁን የሽሮ ወጥ ታሪክ በማስታወስ አስፈግጎኛል፡፡ ዘረኝነት እንዴት እንደሚያሣውር አጥንቴ ድረስ ዘልቆ የገባኝ ዛሬ ነው – ሊያውም በለበጣ እያሳቀኝ፡፡ በዘረኝነት ወያኔን የሚያስከነዳ ሌላ ዘረኛ በዓለም ውስጥ ለዚያውም በሀገራችንና በዚህ ዘመን ይፈጠራል ብዬ በጭራሽ ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ እነዚህ ደግሞ የባሰባቸው ናቸው፡፡ “ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ አይመሰገንም” መባሉ እውነት ነው፡፡ ወያኔዎች እኮ ቢያንስ ማስመሰልም ይችሉ ነበር – (ሆ! እነሱንም በበጎ ማንሳት ልጀምር? ወይ ጊዜ! አዎ፣ Give the devil its due! ይላሉ ፈረንጆች)፡፡ እነዚህ “ሰዎች” የጅልነታቸው ብዛት የ80+ ነገዶችን ከተማ በስሟ እንኳን ለመጥራት እየቀፈፋቸው “ፊንፊኔ” ነው የሚሏት – ሊያውም ኦሮምኛ ባልሆነ ቃል፤ የቃሉ አመጣጥ onomatopoeic (ድምፀ-ኩረጃ) ሲሆን “ፊን” ከሚል ምንጭ ሲመነጭ ከሚሰጠው ድምፅ የተወሰደ ነው – “ደሙ ከግንባሩ ፊን አለ” የሚል ዐረፍተ ነገር ሰምቶ የማያውቅ ካለም አሁን ይስማ፡፡ … እንግዴህ ስሟን ለመጥራት እየተጠየፍክ እንዴት ነው ነዋሪዎቿን ላስተዳድር ብለህ የሥልጣን ቦታዎችን ሁሉ ካለይሉኝታና ካላንዳች ሀፍረት ከዘበኛ እስከ ከንቲባ የምትቆጣጠረው? ለዚህ ለዚህማ ወያኔዎችስ ምን አጠፉ? ለዚህ ነው የነዚህ ሰዎች ዕድሜ በአጭር እንደሚቀጭ ጠንቋይ መቀለብ ሳያስፈልግ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻል ከልቤ የማምነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርቃቱ ዳተኛ ቢሆን እንጂ እርግማኑ በመብረቃዊ የማጥቃት ሥልቱ ይታወቃል – ይህን ሁሉም ወገን ሊረዳ ይገባል፡፡ እንጦርጦስ ነው የሚያወርድ፡፡ ማንም ሳይነካቸው እንደጪስ በነውና እንደጤዛ ረግፈው ድንገት ሳያስቡት ከታሪክ ባቡር በመውረድ ዚምባብዌና ደደቢት በረሃ የተወተፉትን ደርግንና ወያኔን አስታውስ፡፡
- ማጭበርበር ወሰን አለው፤ መጃጃል ገደብ አለው፡፡ ለሁሉም ዓይነት ሸርና ተንኮል ለከት አለው፡፡ እነዚህ የዚህ ዙር ምርጫ መሃንዲሶች የለየላቸው ነፈዞች ናቸው፡፡ የሥልጣንና የተረኝነት ስሜት ናላን ሲያዞር ምን ሊፈጥር እንደሚችል ለመገንዘብ ይህን “ምርጫ” ማየት ብቻውን በቂ ነው፡፡ እነአቢይ እስከዚህ ድረስ የሚበሻቀጡት ምን ያህል ቢንቁን እንደሆነ በበኩሌ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ አንድን ሰው የምታታልልበት መንገድ ራስህንም ትዝብት ውስጥ እስኪከትህ ድረስ እጅግ የወረደ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንዴ smart መሆንና የምታታልለው ሰው ሳይቀር እስኪገረምብህ ድረስ ለማታለል መሞከር ቢያንስ በብልጠትህ በሰዎች ዘንድ እንድትደነቅ ያደርጋል – መደነቁ ባይጠቅምህም፡፡ አንድ ነገር ላስታውስህ – ማርካቶ ውስጥ ነው፡- በማጭበርበርና በማታለል ችሎታ ከገገማው የበሻሻ ቁማርተኛ እጅግ የሚበልጡ ሁለት አራዶች ሁለት ፈረንጆችን ይዛ የቆመች መኪና ያያሉ፡፡ አንድ የስርቆት ሥልት በፍጥነት ይቀይሱና ወደተግባር ይገባሉ፡፡ አንደኛው ሲጋራ ያወጣና ቀይ በበራው የኋላ ፍሬቻ መብራት ተጠግቶ ሊለኩስ ይሞክራል፡፡ ፈረንጁ ሹፌር በልጁ እሳትን ከመብራት ያለመለየት ችሎታና በአፍሪካዊ “ኋላቀርነት” ተደንቆ ወጥቶ ፎቶ እያነሳ ይዝናና ጀመር፡፡ ልጁ ግን ሲጋራውን መለኮሱን እንደተያያዘ ነው፡፡ በጋቢና የነበረውም ፈረንጅ በጓደኛው ጋባዥነት ወጥቶ ሆዱን ይዞ በሣቅ እየተንፈራፈረ ነው – በ“ኢትዮጵያውያን ማይምነት” እየተደነቀ፡፡ ሣቁን ጨርሰው ምናልባትም ፍራንክ ቢጤ ለልጁ ወርውረው ወደ ጋቢናቸው ሲመለሱ አንድም ቦርሣና ሻንጣ የለም፡፡ ወደሲጋራ ለኳሹ ሲመለሱም ፈሱ የለም፡፡ እያነቡ እስክስታ አትሉልኝም? የዚህ ዓይነት ቁጭ በሉ እያዝናና ያስለቅሳል፡፡ መሰረቅህ ያናድድሃል፤ አሰራረቁ ግን ያስደንቅሃል፡፡ የነአቢይ ዓይነቱ ግግም ያለ ቁጭ በሉ ግን በውነት ከነሱ ጋር እኩል ሰው ሆኜ መፈጠሬን ሳይቀር እንድጠላው ነው ያደረገኝ፡፡
- ለነገሩ አንዳንዴ ከኔ አይቅር ከሚል የምትሞክራቸው ነገሮች መኖራቸውን ለማጠየቅ እንጂ ምርጫው ዋጋ አለው ብዬ አልነበረም የሄድኩት፡፡ ረጋ-ሠራሽ ትያትሩን በነፃ ለማየት ነበር እንደመዝናኛ ቆጥሬ ወደ‹ምርጫ›ው ሥፍራ ያዘገምኩት፡፡ ግን እንዲህ ዓይነት ቀሽም ድራማ መመልከት ያናድዳል፡፡ ያን የመሰለ ትርምስ መፍጠር የተፈለገው በአንድ ቀን 1500 ሰው ማስተናገድ ከባድ ሆኖ ሳይሆን የሆነ ሤራ ኖሮ ያንን እውን ማድረግ እንዲቻል የሽፋን ተኩስ ለመስጠት መሆን አለበት፡፡ የማይማንና የሆዳሞች ድራማ ደግሞ መቼም ቢሆን ሰምሮ አያውቅም፡፡
- ይህን መሰል ድራማ በዚህ ወረዳ ካደረጉ በሌላውና በገጠሩማ ከዚህ በባሰ በግልጽና በማንአለብኝነት ምን ዓይነት የወረደ ተግባር እንደሚፈጽሙ ከግምት ባለፈ ማወቅ አይከብድም፡፡ ከዚህ ቁጭ በሉ በተያያዘ ሌላው የሚያናድደው ነገር ለዚህ ድራማ ሲባል የሚከሰከሰው የድሆች ገንዘብ (እሱም የኛው ነውና)፣ አላግባብ የሚባክነው ጊዜና ጉልበት ነው፡፡ ይህ እየራበንና እየጠማን አለውድ በግዳችን የምንነጠቀው ገንዘብ ለሌላ ዓላማ ቢውል ኖሮ ስንትና ስንት ባተረፍንበት ነበር፡፡ ሆድ እንጂ ጭንቅላት ቤተ መንግሥት አልገባ ብሎን ብዙ ተቸገርን፡፡ ፖለቲካችን የሥራ አጦችና የማይማን ቦዘኔዎች ጎረኖ ሆነና ሀገራችን መቅኖ አጥታ በኤሎሄ ላይ ትገኛለች፡፡ እግዜር በቶሎ ይጎብኘን – ለዚህም በርትተን እንጸልይ፤ ልባዊ ጸሎት የዕዳ ደብዳቤን የመቅደድ ልዩ ኃይል አለው፡፡ ለሀገራችን እጅግ የተወሳሰበ ችግር ዋናው መፍትሔ ደግሞ ከክፋት ርቀን ከፈጣሪ ጋር ያለንን ኔትወርክ ማጥበቅ ነው፡፡
- ሰሜን ኮርያና ኤርትራ በዚህ ረገድ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ለውዳቂ ትያትር በቢሊዮኖች የሚገመት ብር ከሚፈስ ጥሩ አምባገነን መሪ – እንደመንግሥቱ ኃ/ማርያም ያለ ግን ወደ አቅሉ የተመለሰ እኩል ገዳይና እኩል ጨቋኝ መሪ – ቢኖረን ኖሮ ምርጫው ቀርቶብን በዚያ ገንዘብ ስንትና ስንት መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ ሀኪም ቤት ወዘተ. መገንባት በተቻለ ነበር፡፡ የኛ “ሲያጌጡ ይመላለጡ ዓይነት” ነው፡፡ የዕድላችን ጠማማነት ከዚህ አኳያ ሲታይ ወደር የለውም፡፡ በባዶ እግሩ ከሚሄድ ገበሬ የተሰበሰበን ግብር በዚህ መልክ በሀሰተኛ ምርጫ ሲያባክኑትና በሚሊዮኖች በሚገዛ የቅንጦት መኪና ሲዘባነኑበት ማየት የሰዎቹን ቅል-ራስነት በግልጽ ያሳያል፡፡
- አሁን ባለቤቴ ደወለችልኝ፡፡ “ሰው ቀንሷልና ኑ” አለችን፡፡ ከምሽቱ 2፡40 ነው፡፡ ስመለስ ልቀጥል፡፡
- … ተመለስኩ፡፡ አሁን ሰዓቱ ከምሽቱ 4፡15 ነው፡፡ መረጥኩ፤ ደስ አለኝ፡፡ “አረረም መረረም ማመሬን ተወጣሁ” ብላለች አንዷ ማመርተኛ ( የጽዋ ማኅበር ተረኛ ከፋይ)፡፡ እኔም ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ኅሊናየን ግን ቀለለኝ፡፡ “ምንም ይሁን ምን” ስል ግን ብልጽግና ከእግዜር ዱላ ውጪ በምርጫ ይሸነፋል ከሚል ቂልነት ተነስቼ እንዳልሆነ መጠቆም እፈልጋለሁ – ለአባባል ያህል ነው፡፡ እንጂ አጥንት የያዘን ውሻ ከሚግጠው አጥንት የሚለየው ውኃ እማያሰኝ ሽመል ብቻ መሆኑን አጥቼው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ደግሞ አብዛኞቹ ከውሻም ያንሳሉ፡፡