>

የሁለቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች ፍጥጫ መቼ ያበቃ ይሆን...??? (ሲሳይ መንግስቱ)

የሁለቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች ፍጥጫ መቼ ያበቃ ይሆን…???

ሲሳይ መንግስቱ

 

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የአንድ ትውልድ ሰዎች ሲሆኑ ሁለቱም ረዥሙን ዘመናቸውን ፓርቲ እየቀያየሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቢያሳልፉም በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳቸውም አልተሳካላቸውም።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ የፖለቲካ ተሳትፎውን ሀ ብሎ የጀመረው በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ
(ኢሕአፓ) ሲሆን ፕሮፌሰር መረራ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ነው።
እንደሚታወቀው ሁለቱ ድርድጅቶች ገና ከጅምሩ በባላንጣነት ይተያዩ ስለነበረ አንዱ ሌላኛውን አጥቅተውና አስጠቅተው በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማስጨረስ ጭምር ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጭ ለመሆን በቅተዋል። በዚህም ወጣቱ ብርሀኑ ለስደት ሲዳረግ መረራ ወደ እስር ቤት ተወረወረ። ይህም ሆኖ ሁለቱም ወጣቶች እድለኞች ሆነው ብርሀኑ በስደት ሆኖ መረራ በዋነኛነት አገሩን
ሳይለቅ በትምህርታቸው ቢገፉም በፖለቲካው ግን አልቀናቸውም።
በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ሲደረግ ሁለቱም ወደ ፖለቲካው መግባታቸው አልቀረም፣ መረራ ቀደም ብሎ የገባ ሲሆን በወጣትነቱ ጊዜ የነበረውን አቋም በመቀየር በብሔር ላይ የተመሰረተ ድርጅት በማቋቋም በመሪነት ብቅ ማለት ቻለ።
ብርሀኑ ደግሞ ዘግየት ብሎ ወደ ፖለቲካው አለም ቢገባም አቋሙን ሳይቀይር ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር በመሆን ሀገራዊ ፓርቲ በመመስረት መታገልን
መረጠ።
በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ላይ ባይሳካላቸውም ብርሀኑ ቅንጅትን መረራ ደግሞ መድረክን ወክለው በመቅረባቸው በንቃት መሳተፍ ችለዋል። ሆኖም ብርሀኑ በግሉ በዛ ምርጫ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉና
ፓርላማ ገብቶ እንዲታገልለት የመረጠውን ህዝብ መልሶ ምክር ቤት እንግባ ወይስ አንግባ የሚል የሞኝ ጥያቄ አንስቶ ሲዋልልና ወጣቱን ሲያነሳሳ ተገኝቶ ለእስር ተዳረገ፣ በተቃራኒው መረራ ዝምታን በመምረጡ ከመታሰር ዳነ።
ባለፉት 16 አመታት ፕሮፌሰር ብርሀኑ የትጥቅ ትግልን መርጦ ወደ ኤርትራ በረሀ በመግባት ጭምር በትህነግ የበላይነት ይመራ የነበረውን ኢህአዴግ
ሲፋለም፣ ፕሮፌሰር መረራ ሰላማዊ ትግል ይሻላል በማለት አዲስ አበባን ሳይለቅ በየጊዜው በተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ መሳተፍን መርጧል። በዘንድሮው
ምርጫ ግን መረራ አለመሳተፍን ሲመርጥ ብርሀኑ በምርጫው ተሳትፎ የጠበቀውን ሳያገኝ ቀርቷል።
እንግዲህ ከላይ በምሳሌነት ያነሳናቸውን እውነታዎች በጥሞና ስንመለከት ፕሮፌሰር መረራ እና ፕሮፌሰር ብርሀኑ አንድም ጊዜ የሚያግባባ ፖለቲካዊ ሁኔታ
ውስጥ ተገኝተው አያውቁም። ይልቁንም ሁል ጊዜ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በተቃራኒ ቦታ ላይ ሆነው እንደሁኔታው ሲፋለሙ ተመልክተናል። ሁለቱም ሰዎች ባለፉት 46 አመታት ማለትም ሁለት ትውልድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት የተሳትፉ ቢሆንም በጎ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ይኸ ነው የሚባል
ጉልህ ለውጥ አላመጡም፣ የረባ ስልጣንም አላገኙም።
ይህም የሆነው አንድም የሚከተሉት የፖለቲካ መስመር ብዙሀኑን ኢትዮጵያዊ ማሳመን ባለመቻሉ፣ ሁለትም ሁለቱም ሰዎች የሚሰጧቸው መግለጫዎችና የሚያሰሟቸው ንግግሮች ምቾት የማይሰጡ በመሆናቸው እንደሆነ ይታመናል።
ስለሆነም ይህ ወቅት ሁለቱም ጉምቱ ፖለቲከኞች ጡረታ ወጥተው ራሳቸውን ከፖለቲካው አለም በማግለል ወጣቶችን ወደ መሪነት ቢያመጡና አዲስ
አስተሳሰብ የበላይነት የሚያገኝበትን ሁኔታ ቢያመቻቹ ክብር ያገኛሉ።
Filed in: Amharic