>
5:29 pm - Wednesday October 11, 5815

ኻብ ዳላክ  /ዳኽላክ/ ...!!!  ታታ አፍሮ (ነፃ ብዕር)

ኻብ ዳላክ  /ዳኽላክ/ …!!!

 ታታ አፍሮ (ነፃ ብዕር)

የኔ ብዕር /ነፃ ብዕር/ በማንም ለማንም ያልተገዛችው ብዕሬ የጦመረችው ጦማር ነው። ዘፈን ኃጢያት ነው። ዘፈን ኃጢያትም አይደለም። ቁረጠው ፍለጠው ስትል ኃጢያት ነው። እንዋደድ እንፋቀር ስትል ግን የጽድቅ ቃል ነውና ኃጢያት አይሆንብህም። ኃጢያት ከኃሳብ ጀምሮ እስከ ተግባር ያለው ሂደት ነው። ኃሳብህ በግራ የሚያስቆምህ ከሆነ መዝፈንህ ሀጢያት ነው። ያንን ሀሳብ መደገፍህም እንዲሁ!
ኻብ ዳላክ..! ብዙ ሰዎች በ1997 ዓ.ም ከተለቀቀው የቴዲ አፍሮ አልበም ውስጥ ያስተሰርያል የሚለውን ሙዚቃ ትልቅ የፖለቲካ መቃወሚያ ሙዚቃ አድርገው ቆጥረውታል። በእርግጥም ኃያል ነው። እኔ ግን ሁሌም የምደነቅበትና እንዴት ባለ የወኔ መመላት ቢመላ ነው እንዴትስ ባለው የጀግንነት መንፈስ ቢደራጅ እንደምንስ ያለ የመንፈስ ብርኃን ቢመላው! ኻብ ዳላክን አዜመው ስል ዘወትር አስባለሁ! “አትሰብ” /አታስብ/ ባይ ቢኖር በጅ ባልኩ ነበር። ምክንያቱም የወኔ ሙላቱን የጀግንነት መንፈስ አደረጃጀቱን ሊነግረኝ የደፈረ ቢኖር ነውና አትሰብ ማለቱ! የመንፈስ ምልአቱን ለኔ ተወው! /ይኼን ሙዚቃ ቡና መጠጫ ጋ ቁጭ ብዬ እየሰማሁ በኃሳብ ነጉጄ ኖሯል ለካ የላሊበላዋ ተወላጅ የቡና መጠጫው ቤት አስተናባሪዋ ፈገግ ብላ “አንተ ታታ አትሰብ እንጂ…” አለችኝ አታስብ እንደሆነ ስለገባኝ ፈገግ አልኩላት!
ዘፈኑ ላይ የግጥሙ ጸኃፊና የዜማው ደራሲ ከኢትዮጵያ በሁለቱ መሪዎች አለመግባባት ወደ ኤርትራ የሚወዳትን ሚስትና ልጁን ጥሎ የተሰደደ ሆኖ ነው የሚያንጎራጉረው! ሙዚቃ ፍጹም ጥበብ ነችና በግርድፉ ብቻ ባንቀበለው መልካም ነው። የመጀመሪያው አዝማች ላይ ቤተሰቦቹን ያለ ውዱ ጥሎ የተሰደደ ኤርትራዊ አባ ወራ ዳኽላክ ላይ ቤቱን ቀልሶ ይኼ ክፉቀን እንዳለያየን ጥሩ ቀን ይመጣና ያገናኘናል እስከዚያው ግን የምነት ቃልሽ /ቀለበቱ/ ከእጄ አይወጣም አንቺንም በዚያ አይሻለሁ እያለ በደብዳቤው ያትታል። ደግሞ ናፍቆቱ ሲያይል ጠረናቸው ሲናፍቀው የባለቤቱ ደብዳቤ ሲደርሰው አቅሙ እየዛለ እኒያ ዝሆኖች ድንበሩን ሰብረውት መምጫ አጣሁ እንጂ ዐይንሽን አይቼው ባረፍኩ እያለ አቅም በሚነሳ ዜማ ያንጎራጉራል። ይኼው የግጥም አዝማች ሌላ መንፈሳዊ ትርጉም ይሰጠኛል። እሱም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለመባረክ በአባቶች ጸሎትና በጻድቃን ልመና እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አገራችን ሊመልስ ቢፈልግም ግፈኞች ግን አሁንም በደላቸውን ቀጥለዋል። እግዚአብሔር ደግሞ በግፈኞች መኃል ቁጣውን እንጂ በረከቱን አያወርድም። እስቲ ግጥሙን እንየው።
“ዳላክ ላይ ልስራ ቤቴን
ቁርጥ ሆኗል መለየቴ
ነጠለኝ ክፉ ዘመን ከምወዳት ባለቤቴ
ቀን ብሎ እስክንገናኝ ያረግሽልኝ የምነት ቃልሽ
አይወጣም ለዘለዓለም ከጣቴ ላይ ቀለበትሽ
ካለሁበት ቦታ ሲደርሰኝ ደብዳቤ
ይረበሽ ጀመረ ቅር እያለው ልቤ
ወይ አልመጣ ነገር አቋርጬ ዱሩን
ዝሆኖች ተጣልተው ሰበሩት ድንበሩን”
ከኢትዮጵያ የተባረረው ወዲ ኃጎስ በዝሆን ፀብ ሲጎዳ ሳሩ ዝም አይልም ያያል እግዜሩ እኔ ግን ሺ ዘመን ቢቆጠርም ላልከዳሽ ቃል አለኝ ሲል ቀጣዩን አዝማች ይጀምራል። ወዲያ ደሞ ተኝቶ ወርቅ የሆነ ህልም ያያል። ያ ህልም ለኔ እጅጉን ድንቅ ህልም ነው። አዎ የበረከት ህልም። የመልካም ትንቢት መፈጸምን የሚያበስር ኃያል ህልም። ህልሙ እንዲህ ነው። ወዲ ኃጎስ ዳኽላክ ደሴቱ ላይ አንዲት መርከብ ማዕበል ሲያናውጣት ወጀብ ሲያስጨንቃት ያያል። በመርከቢቱ ያለች የልጅ እናት ህጻን ልጇን ታቅፋ እመርከቡ ላይ ቆሞ ወደ አምላኳ ስትጮኽ ወጀቡ ሁሉ ጸጥ ይላል። ዛዲያ አጅሬ ጥበበኛው ወዲያው በይ እንዲህ ነው ህልሜ ሲፈታ ብሎ ይኼን ይላታል  ለህጻን ልጅ ይራራል ጌታ ያለ ኃጢያቱ እንዳይሞት ሲል ለመርከቢቷ መዳን ሆነላት። ወጀቡ ፀጥ ያለው በጸሎት ነው! ህጻን ልጅ /ንጹህ ልብ/ ይዞ ጸሎት መከራን ያርቃል። እያለ እየመከረን ባልሆነ..?
የጠቢብ ነገር ቅኔን በቅኔ ነው… ና እኔ ደግሞ የገባኝን ልተርጉምልህ መርከቧ ኢትዮጵያ ነች! ወጀብና ማዕበሎቹ ደግሞ ሁለቱ ሁከት ፈጣሪዎች! በሴት እና በህጻን የተመሰሉት ህዝቦቿ ናቸው። እኒያ አገር ወዳዶች እንደ እናት የሚወደዱ እኒያ ቂም የማያውቁ ያገሬ ልጆች በልባቸው እንደ ህጻን የሆኑ ሩሩህ እና ለጋሶቹ ናቸው። ሌላም በእግዚአብሔር እጅ ያለች አገር ያ ሁሉ መከራ ሲፈጸምባት ልቧን እንደ ታቀፈችው ህጻን ንጹህ ያደረገች አንዲት ጻዲቅ እናት ብቻዋን ቆማ ወደ አምላኳ ድምጿን ስታሰማ የመከራው ወጀብ የስቃዩ ማዕበል ፀጥ ይላል ማለት ነው። በመርከቧ ሌላ ሰው ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። የሌላ ሰው ጨኸትም የለም ማለት አይደለም። ቀዛፊው እና ሌሎች ተጓዦችም የሉም ማለት አይደለም። ግን እግዚአብሔር የአንዲት ንጹህ ነፍስን ጨኸት እንደሚሰማም ለማመላከት ታስቦ እንጂ።
በዘፈኑ የቃልኪዳን ቀለበት እያለ የሚያነሳው ጣት ላይ የሚታሰረውን የወርቅ ፈርጥ አልያም ውድ እንቁ አይምሰልህ። እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የገባላትን ቃልኪዳን ሲያወሳ እንጂ! አዎ በመከራ እንዳትኖር በጠላቶቿም ሴራ ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ እግዚአብሔርም እንዳይተዋት ቃልኪዳን አለው። ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ መሪዎቿ ከእርሱ ርቀዋል ህዝቦቿም ፊታቸውን አዙረዋል። ለዚህም ይመስለኛል ዜመኛው
“እንዳልከዳሽ ቃል አለብኝ እንዳልከዳሽ
እንዳልመጣ እርቀሽ እንዳልመጣ እሩቅ ነሽ” እያለ የሚያንጎራጉረው።
በሙዚቃው የህልሙ ክፍል ላይ ያ ህጻን ልጅ ቂም ካልተማረ በቀል ይበጀኛል ካላለ እኔና አንቺ በቀጣይ ትውልድ በእሱ ጊዜ እንገናኛለን። እያለ ያሳስባታል። ኢትዮጵያም ኤርትራም ግን ልጆቻቸውን ከቂም ሰውረው አላሳደጉም። ቀን ቆጥረው ለበቀል ተሰናዱ። ታዲያ መዝጊያውን እንዳልመጣ እርቀሽ እያለ ቋጨው… ቂም እኮ ያራርቃል። በቀል እኮ ያጨካክናል! እንዴት ብሎ ቃልኪዳኑን ይፈጽም? እንዴት ብለን የአባቶቻችንን በረከት እንቀበል? አሁንም እኮ ቂም አለ! አሁንም እኮ ዝሆኑ ሳሩን እየረገጠ ነው! አሁንም እኮ እንደ ዝሆን የገዘፈ መከራ በህዝባችን ላይ እየጣልን ነው! አሁንም እኮ ወገኖቻችንን ከመሰደድ አልታደግናቸውም። አሁንም እኮ ምስኪን እናቶቻችን ደም እንባ እያነቡ ነው። አሁንም እኮ አሰህቶቻችን እየደፈሩ ነው። አሁንም እኪ ኢ ሰብዓዊ በደሎች እየተፈጸሙ ነው። ስለዚህ በጥበባዊ ቋንቋ የተነገረንን እንፈጽም። በወጀቡ ላይ ቆመን ልባችንን እንደ ህጻን ልብ አንጽተን “በንተ ማርያም” ብለን እንለምነው። ያኔ ቃልኪደኑ ይፈጽማል።
Filed in: Amharic