>
5:33 pm - Wednesday December 5, 1906

'ትግሉ ይቀጥላል...!!!' (ጌጥዬ ያለው)

‘ትግሉ ይቀጥላል…!!!’

ጌጥዬ ያለው

ባይተዋር ችሎት…
 
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) መሪዎች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከአንድ ወር በኋላ ባለፈው ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ችሎት ተመልሰዋል። ከዚህ በፊት ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር ፍርድ ቤት የቀረቡት። በ29 ቀናት ውስጥ ለውጦች ተከስተዋል። የባይተዋር ችሎቶች ስውር አላማ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ ተካሂዷል። አራቱም የፖለቲካ እስኞች በምርጫው ድርጅታቸውን ወክለው በእጩነት የተሳተፉ ቢሆንም የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ግን ተገርስሶ አልፏል። እንደ ተመራጭ የምርጫ ቅሰሰቀሳ ማድረግ ቀርቶ ራሳቸውን መምረጥ አልቻሉም። በእስክንድር ነጋ ላይ ቀደም ሲል ታስሮበት በነበረው ቃሊቲ ወህኒ ቤት የግድያ ሙከራ ተደርጓል። በምርጫው ዋዜማ የተፈጠረው አካላዊ ትንኮሳ አስደንጋጭ ነበር። የዚህን ዱካ ተከትሎ እስክንድርና ስንታየሁ ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ተወስደዋል። በዚያም የአገዛዙ ሥራ ፈፃሚዎች ጥላቻ ከልክ በላይ ገንፍሎ ጠብቃቸው። ነገሩ የእስር ቤት ውስጥ እስር ሆኖባቸዋል። ዝርዝሩን እመለስበታለሁ።
የፖለቲካ እስረኞች በተረኞች ቁጥጥር ስር ከዋሉ ዛሬ ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ ዓመት ሞላቸው።
የአብይ አሕመድ መንግሥት አምባገነናዊ ሥልጣኑን የሚያስጠብቅባቸው ሁለት አፋኝ መዋቅሮች አሉ። አንደኛው ጠመንጃ አነግቶ የሚዞረው ወታደራዊ ሃይሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ መፅሀፈ ዳዊት ሕገ መንግሥት ተብየውን የጥላቻ ሰነድ በብብቱ ስር ወሽቆ የሚንከራተተው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው። ይህ ቀውላላ ተቋም ሲያሻው ከቴሌኮሙኒኬሽን፤ ሲፈልግ ከስለላ ድርጅቱ ጋር እየተንሾካሾከ በእነ እስክንድር አንገት ላይ ወንጀል ለመጠምጠም ዓመት ሙሉ ቢማስንም አንዳች እድፍ አላገኘም።
የሥረ ነገር ክርክር ሳይጀመር ጉዳዩን ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደ ዝሃ ዘጊ ሲያመላልሰው ባጀ። ምልልሱ በ21 ምስክሮች ጉዳይ ነው። በግልፅ ችሎት ይሰሙ ወይስ በድብቅ የሚል፤ ሰው ይሁኑ ወይም ከብት ሳይታወቁ እንዲመሰክሩለት ወጣ፤ ወረደ። 5ቱ ማንነታቸው ሳይታወቅ እንደ ገጠር ሙሽራ በመጋረጃ ተጋርደው እንዲመሰክሩ፤ 16ቱ ደግሞ ታዳሚያን እና መገናኛ ብዙሃን በሌሉበት በዝግ ችሎት እንዲቀርቡ ጠይቋል። ከዚህም አልፎ ተከሳሾችም ሆኑ ጠበቆቻቸው በሌሉበት እንደ ኮንትሮባንድ ሸቀጥ እማኞችን ለችሎቱ ለማቅረብ ጠይቋል።
ሆኖም  የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት በግልፅ እንዲቀርቡ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ  በድጋሜ ፈረደ። ሀምሌ 8፣9፣14፣15 እና 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ በይኗል። ውሳኔው ገቢራዊ የሚሆን ከሆነ ከአመት በፊት በይኖት እንደነበረው በቀን 4 ምስክሮች ይሰማሉ ማለት ነው። ከአምስቱ ቀናት ውስጥ በአንዱ ብቻ አምስት ምስክሮች ይቀርባሉ።
 በርግጥ ‘መብላቷን ሳታውቅ እጇን ታጠበች’ የሚያሰኝ ጠብደል  ጥያቄ አለ።
“ከታሰርን ከሁለት ቀን በኋላ አንድ ዓመት ይሞላናል። ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም። ከዚህ በኋላ መንገላታት የለብንም። በውሳኔው ላይ አሁንስ ይግባኝ ይጠይቃል ወይ? አቋሙ ምንድን ነው? የዐቃቤ ሕግ አለቃው እዚህ ናቸው፤ ይመልሱልን” በማለት እስክንድር ደጋግሞ ጠይቋል።
እዚህ ላይ ባለፉት ችሎቶች ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ‘በህቡዕ ካልሆነ በቀር በግልፅ የማቀርባቸው ምስክሮች የሉኝም’ ማለቱን ስንዶልበት ተረቱን ወደ ሐቅነት ያምዘገዝገዋል። በአጭሩ የሀምሌ 8 አማራጮች ሁለት ናቸው። ‘ዘጭ ምረጭ አንዱን ምረጭ፤ ዘውድ ወይም ጎፈር!
፩. ከሳሽ  እማኞችን ማቅረብ ስላልቻለ ዶሴውን ለጊዜው አቋርጦ (ምስክር ባገኘ ጊዜ እንደገና መክፈት ይችላል) የፖለቲካ እስረኞችን በዋስ ማሰናበት
፪. ነገሩን አተባትቦ ዳግም ይግባኝ መጠየቅና ወደ ዝሃ ዘጊ ሚናው መመለስ ነው።
ከሁለቱ ውጭ ከሆነ ዘውድም፤ ጎፈርም ሳይሆን ዶሴው በጠርዙ ይቆማል። ይህም ያፈጠጡ፤ ያገጠጡ 21 የሀሰት ምስክሮች በችሎት አደባባይ ይሰየማሉ ማለት ነው። ቀጣዩ ጥያቄ ‘እነኝህ ምስክሮች የሚሰጡት የሀሰት ቃል እንዴት ሊያሸንፍ ይችላል?’ የሚለው ይሆናል። ከሳሽ ባለዕዳ ነው፤ እሾህ ለበዛበት ለአንድ ሰባራ ወንበር ስንት ጊዜ ይዋሻል!? እንዴትስ ይችላል? ምስክሮቹ እውቅ ‘የጉማ አዋርድ’ ተሸላሚ ተዋንያን ካልሆኑ በቀር አንድን ቅጥፈት በ21 ሰዎች አንደበት 21 ጊዜ መድገም በራሱ ዳገት ነው። የጉማን ዋንጫ የጠቀለሉ እንኳን ቢሆኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ተዓምር እንዳያሳልፋቸው እመኛለሁ።
ወደ እስር ቤቱ እስር እንመለስ፤ ቂሊንጦ።  እስክንድር ነጋ እና ስንታየሁ ቸኮል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሦስት ወህኒ ቤቶች ታስረዋል። የመጀመሪያው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚሉት ማገቻ ግቢ ነው። በዚህ ለወራት ከቆዩ በኋላ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተግዘዋል፤ ከዚያም ወደ ቂሊንጦ። አስቴርና አስካለ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ ታግተው ለወራት ከቆዩ በኋላ አሁንም ድረስ ቃሊቲ ይገኛሉ።
ቂሊንጦ የቀለጠ የጭቆና ቤት ነው። በተደጋጋሚ ለመጠየቅ ብንሄድም ከወንድሞቻችን ሊያገናኙን አልፈቀዱም። ገና ‘እስክንድር’ የሚለውን ስም ሲሰሙ ዛር እንዳለበት ፀበልተኛ ፊታቸው ይለዋወጣል። በጥላቻ የሰከሩ ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞችን ስሙ ያስጎራቸዋል ቢባል ኩሸት አይመስለኝም። እኔ በሄድኩበት ጊዜ የስንታየሁ ቸኮል ባለቤት ወ/ሮ ውዴ ስንቄ የቋጠረችውን ምግብ ይዛ ላለመመለስ እያነባች ስትማፀናቸው እንኳን ርህራሔ አልነበራቸውም።
እስክንድር በሰኔ 22ቱ ችሎት በባሕር ማዶ ከሚኖሩት  ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እና ልጁ ናፍቆት እስክንድር ጋር ከዚህ በፊት በቃሊቲ ያደርገው የነበረው የስልክ ግንኙነት በቂሊንጦም እንዲፈቀድለት በአፅንኦት ጠይቋል። “በየሳምንቱ ለ30 ደቂቃ ያህል ከባለቤቴና ከልጄ ጋር በስልክ እንገናኝ ነበር። አሁን ‘ፍርድ ቤቱ በግልፅ አላዘዘም’ በሚል ተከልክያለሁ። በምንገናኝበት ጊዜም የግል ጉዳየን በነፃነት ማውራት ስለምፈልግ ፖሊስ ከጎኔ ቁሞ እንዳይሰማ። በተጨማሪም እኛ በባልደራስ ውስጥ ያለን የሥራ ሓላፊነት እንደተጠበቀ ነው። ከድርጅት አመራሮች ጋር ተገናኝተን አመራር እንድነሰጥ፤ ይህም ድርጅታዊ ምስጢር ስለሆነ ፖሊስ እንዳያዳምጠን ይሁን። እነኝህ ትዕዛዞች በግልፅ ተፅፈው ይሰጡልን” በማለት እስክንድር ችሎቱን ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ ተሰጥቶታል። የወህኒ ቤቱ ሓላፊዎች ከጠባቂ ፖሊሶች ጋር ሰጣ ገባ እንዲፈጥሩ ሆን ብለው እየጋበዟቸው መሆኑንም ተናግሯል። በቃሊቲ የተሞከረበትን አደገኛ ትንኮሳ በቂሊንጦም ለመድገም የኦሮሞና የትግራይ ፅንፈኛ ብሔርተኞች ተቀናጅተው እየሠሩ እንደሆነም የወህኒ ቤቱ የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል። ሰበብ ፈልጎ ወደ ቢሮ የመጥራትና በዚያውም እስክንድርን የመደብደብ እቅድ መነደፉን የሚያረዱ መረጃዎች አሉ። የዚህ መሃንዲሶች ደግሞ በኦነጋዊ የጥላቻ ርዕዮተ ኢትዮጵያ የተገራው የወህኒ ቤቱ ሓላፊ እና እስራኤል ዳና የተባለ እስረኛ ናቸው።
በተመሳሳይ ስንታየሁ ቸኮል ቂሊንጦ ከቃሊቲ የባሰ መጥፎ እስር ቤት መሆኑን በችሎቱ ገልጿል። ወህኒ ቤቱ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ እንደማያከብርም ተናግሯል። “ማረሚያ ቤት የሚለውን ስም አይመጥንም። ሕፃናት ልጆቼ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። ባለፈው እሁድ ልጄ ‘እናትሽ ስለገባች አትገቢም’ ተብላ አልቅሳ ተመልሳለች። በቀን አንድ ሰው ብቻ እንዲጠይቀን ነው የተፈቀደው።  ፀበልና ቅባ ቅዱስ እንዳይገባልን ተከልክለናል” በማለት ቅሬታውን ተናግሯል።
አስቴር ስዩም በበኩሏ ከወትሮው በተለየ መልኩ ከጠያቂ ቤተሰቦቿ ጋር በምትነጋገርበት ፖሊሶች እስከ ሦስት ድረስ  በመሰባሰብ ቤተሰባዊ ምስጢሮቿን እየሰሙ መሆኑን ተናግራለች።
የሰኔ 22ቱ ችሎት በርከት ያሉ ታዳሚያን የተገኙበትና ድጋፋቸውን ያሳዩበትም ነበር።   በችሎቱ ማጠናቀቂያ ላይ እስክንድር የባልደራስ የምርጫ ምልክት የሆነውን የተጨበጠ  ክንዱን ከፍ አድርጎ በማሳየት ለታዳሚያኑ መፈክር አሰምቷል። “ትግሉ ይቀጥላል! ትግሉ ይቀጥላል!” ቀኝ ክንዳቸውን ከፍ አድርገው በአንድ ድንፅ ተቀበሉት። ሦስቱ ዳኞች መጋረጃውን ገልበው ወደ ኋላ ተሰወሩ። ከፊል ፖሊሶች ጋዜጠኞችንና ታዳሚውን እየገፉ ከአዳራሹ አስወጡ። ከፊሎቹ እነ እስክንድርን አጅበው ቆሙ። ሁለቱ ዐቃቢያነ ሕግ በተለመደው የሌባ ኮቴያቸው ሾለኩ። ጠበቆች ሔኖክ አክሊሉና  ሶሎሞን ገዛኸን ጋውን እያወለቁ ጠረንጴዛ ላይ የተጎዘጎዘ ወረቀት ይሰበስባሉ።
Filed in: Amharic