>

የተመድ ቢሮ ቆይታዬ...!!! (አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ)

የተመድ ቢሮ ቆይታዬ…!!!

አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ

*…. ምንም ሆነ ምን የትግራይ ሎቢስቶችንና አክቲቪስቶችን አለማድነቅ ንፉግነት  የመንግስት ሳይድን ሰዎች አለመተቸት ስንፍና መስሎ ነው የሚሰማኝ! በነገራችን ላይ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ሲነሱ በቀጥታ ትግራይ እየተባለ እንጂ የኢትዮጵያ ስም እንኳን አይነሳም ነበር።
በውድቅ ሌሊት የተመድ የቃል አቀባይ ቢሮ ባልደረባ የሆነችው ኤሪ ለጋዜጠኞች የምታደርገውን ፕሬስ ብሪፊንግ በቀጥታ ከ UNTV ላይ እያየሁ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ርእሷ ያው ኢቢሲ ዜና ላይ የለመድነውን አይነት የዩኤን  ሴክሬታሪ ጀነራል የእለት ተእለት ስራን የሚመለከት  ነበረ፡፡ ለጥቃ “ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስናልፍ”  ስትል ጆሮየ  ቀጥ አለ
“የኢትዮጲያ ጉዳይ ቮላታይል  እና የማይገመት ሆኖ ቀጥሏል “ብላ ጀመረች ..
“ዋና ዋና ከተሞች መቀሌን ጨምሮ  አዲግራት አድዋ አክሱም እና ሽሬ  የተረጋጉ ቢሆንም በደቡብ እና በሰሜን ምእራብ ዞኖች ያልተረጋገጡ የግጭት ሪፖርቶች ደርሰውናል፡፡በክልሉ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሚኒኬሽን አቅርቦቶች እንደተቋረጡ ናቸው፡፡ከክልሉ የሚወጣም ሆነ የሚገባ የአየርም ሆነ የየብስ ትራንስፖርት የለም፡፡ይሁን እንጂ የሰብኣዊ እርዳታ ሰራተኞቻችን ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ፡፡ለምሳሌ የተመድ  የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ የውሃ ፓምፕ እና ለምግብ ማብሰያ የሚሆን የማገዶ እንጨት ለመቀሌና ለዙሪያዋ ኗሪዎች እንዲደርስ አድርጓል፡፡በዚህም በርካታ ሺዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ወደ ሽሬ እና መቀሌ እንዲሁም በደቡባዊ ምስራቅ ለምትገኘው ሳምረ ውሃ እና መድሃኒቶችን ማድረስ ተችሏል፡፡ ወደሌሎች ቦታዎች እርዳታ ማድረስ የምንችልበትን  አማራጭም እየፈለግን ሲሆን እዛ የሚገኙ ስታፎቻችን ተጨማሪ የሰው ሃይል በአፋጣኝ እንድዲጨመር እየወተወቱን ነው ” ካለች በኋላ
“ከዚህ ቀጥሎ ወደ ሶሪያ ጉዳይ እናልፋለን” በማለት ልክ እንደኛ ሁሉ አለም ላይ  መከራ ውስጥ ስለወደቁ ሀገራት ስትዘረዝር ቆየች፡፡ስትጨርስ  መድረኩን ለጋዜጠኞች ክፍት አደረገች፡፡
የመጀመሪያ እድል የተሰጣት አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ኤዲ ነበረች፡፡ስለ ድምጿ አትጠይቁኝ፡፡ጆሮ ይቧጥጣል፡፡
“የመጀመሪያ ጥያቄዬ  “ቲግራይን”  ይመለከታል” ብላ ጀመረች፡፡
”  ቃል አቀባይዋ ኤሪ ካነሳቻቸው ከነኛ  ሁሉ የአለም መከራዎች ጋዜጠኞች የኛን አስቀድመው ጠየቁ ማለት ነው!?”  ብዬ እየተገረምኩ በንቃት መከታተሌን ቀጠልኩ፡፡
“ትላንትና ቲግራይ ውስጥ ወሳኝ የሚባል ድልድይ “ቴኬዚ” ወንዝ ላይ ያለ ተሰብሯል እየተባለ ነው፡፡የሰብኣዊ እርዳታ እንዴት ነው የሚደርሰው!? መሰበሩንስ ሰምታችኋል ወይ!?” ተመድ ሌላ ብሪጅ አይሰራም ወይ!?”   መጀመሪያ  ይሄ  ከተመለሰልኝ በኋላ ሌላ ጥያቄ  አለኝ አስከትላለው፡” አለች፡፡
ኤሪ ቀጠለች…” እምም በቀጥታ የደረሰን መረጃ ባይኖርም ስለ ጉዳዩ  ሰምተናል፡፡ እዛ ካሉ አባሎቻችን ፈርዘር እናጣራለን.፡፡”
እሰይ ኤሬዬ ! እንዲህ ኩምሸሽ አድርጊልኝ እንጂ! ብዬ ፈገግ አልኩ፡፡ ኣዛውንቷ ኤዲ ስለ ሜይናማር ሌላ ጥያቄ ቀጠለች፡፡
የሷ ተራ ሲያልቅ ኤሪ እድሉን ለጎልማሳው ጋዜጠኛ ጀምስ ሰጠች፡፡
” የእኔ ጥያቄ ቅድም ኤዲ ካነሳችው ጥያቄ የሚቀጥል ነው፡፡ የተሰበረው ድልድይ ጉዳይ…..” አለና ጀመረ፡፡ድንግጥ አልኩ፡፡ቆይ እኒ ሰዎች ከ TMH(ትግራይ ሚዲያ ሃውስ) ነው እንዴ የተሰባሰቡት አልኩ ለራሴ፡፡
ጀምስ ቀጠለ፡፡”የተሰበረው እኮ ከአራቱ ወሳኝ ድልድዮች አንደኛው እና ዋናው ነው! ይሄ ድልድይ ከተሰበረ በፊትም ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር አሁን እንዴት ነው ታዲያ ነገሮች በጣም አይወሳሰቡም ወይ!?” ተመድ በዚህ ጉዳይ ምን ያህል ተጨንቋል !?” አለና አፈጠጠ
ድምቡሽቡሿ ኤሪ (የቻይና ወይ የኮሪያ ሰው ትመስላለች) ጥያቄው ሲደገምባት ከቅድሙ የበለጠ ትኩረት ሰጥታ መለሰች፡፡
“..በነገራችን ላይ በትግራይ ያለው ሁኔታ በጣም እያሳሰበን ነው፡፡በተደጋጋሚ እያነሳነው የነበረም ጉዳይ ነው፡፡ እዛ ያለው የሰብኣዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በዚህ ላይ እናንተም እንዳነሳችሁት የድልድዩ መሰበር ሲጨመር  እጅግ የሚያሳስበን ነው፡፡” አለችና ምን እንደመለሰች ሳይገባኝ ፡ጥያቄውን በአግባቡ እንደመለሰ ሰው በኩራት ዘና ብላ “እሺ ሌላ ጥያቄ ያለው አለ ?” ብላ እድሉን ወደ ጋዜጠኞች ወረወረች፡፡
ቀጣዩ ጋዜጠኛ ወጣቱ ቶቢ ነበር፡፡ ቶቢ እግዜር ይስጠው “ሰሜን ኮሪያ “ብሎ ጀመረ፡፡ ኡፈይ አልኩ፡፡
በቀጣይ ለአብዱል ሃሚድ የሚባል ጋዜጠኛ እድል ተሰጠው ፡፡ስለ ፓለስታይን ጠየቀ፡፡ ከሪፖርቱም አንጻር አብዱል ሃሚድ የተባለ የአረብ ፌስ ያለው ሰው  ምን እንደሚጠይቅ ገምቼ ነበር ፡፡ስለ እኛ ስላልሆነም ደስ  አለኝ፡፡
 አሁን ጉዳያችን ተረሳሳ ብዬ ፈታ አልኩ፡፡
በስካይፕ የሚጠይቅ ሌላ ጀምስ ራይሞ የሚባል ደግሞ እድል ተሰጠው፡፡
“ጥያቄዬ ስለ ቲግራይ ነው” ብሎ ጀመረ
“ኤጭ አሁንስ በዛ!”  አልኩ፡፡
“የኔ ጥያቄ በፕሌን እንዴት ነው እርዳታ ለማድረስ ያሰባችሁት!? ….. ምናምን  ምናምን …”ብቻ ቀወጠው፡፡
አሁን ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን ኤሪም ሳይመራት አይቀርም፡፡
ምንም ሆነ ምን የትግራይ ሎቢስቶችንና አክቲቪስቶችን አለማድነቅ ንፉግነት  የመንግስት ሳይድን ሰዎች አለመተቸት ስንፍና መስሎ ነው የሚሰማኝ! በነገራችን ላይ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ሲነሱ በቀጥታ ትግራይ እየተባለ እንጂ የኢትዮጵያ ስም እንኳን አይነሳም ነበር።
ኤሪ ትንሽ ሰልቸት ባለ ሁኔታ የቅድሙን መልስ መለሰች ፡፡
ቀጣዩን እድል ደግሞ  ለሌላኛው (ጎልማሳው  ጄምስ ) ሰጠችው፡፡
“እኔ የማነሳው ሁለት ነገር ነው” አለ ጄምስ፡፡ ቁጡ ነገር ነው፡፡”አንደኛው ጥያቄ ሲሆን ሁለተኛው ልመና ነው፡፡ ጥያቄዬ የሚመለከተው ስለ አፍጋኒስታን ነው..ፕረሪሪም ረሪሪሪ አለ(ያው ላሳጥረው ብዬ ነው) ፡፡በሁለተኛ ደረጃ የማነሳው ተማጽኖዬ/ልመናዬ  ግን የሚመለከተው ስለ ትግራይ ነው “አለና በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆኖ ማውራት ጀመረ..”እባካችሁ የናንተ ሰዎች(የተመድ)  ትግራይ  ውስጥ ካሉ  እንድናናግራቸው ፍቀዱልን፡፡ መሬት ላይ ያለውን ነገር በቀጥታ የሚገልጽልን ሰው ማግኘት እንፈልጋለን …” ቀወጠው፡፡
አሁን ኩምሽሽ አልኩኝ፡፡ እሱ የማይመለከተው ሰውዬ ይሄን ያህ የሚያንጨረጭረው ከሆነ እኔም ስለገዛ ወገኖቼ ጉዳይ የበለጠ ለማወቅ ፈለግሁ፡፡
ስልቹዋ ኤሪ አሁን ደግሞ ምን ትል ይሆን አልኩ ለራሴ
አግራሞቷ ከፊቷ ይነበባል፡፡ሁሉም መጠየቅ የሚፈልገው ስለ ትግራይ ነው፡፡ጄምስ መጀመሪያ የጠየቃት ስለ አፍጋኒስታን ቢሆንም ስሜቱን በመረዳት ይመስለኛል ስለ ትግራይ  ከጠየቀው ወይም  እንደሱ አገላለጽ “ካቀረበው ተማጽኖ” ነበር መልስ መስጠት የጀመረችው፡፡
“እኛም እኮ ግራ ገብቶናል !ዋይፋይ የለ! ቪሳት የለ! እንኳንስ ለእናንተ ለኛም ግራውንድ ላይ ያሉ ሰራተኞቻችንን ማግኘት ተስኖናል እኮ!”  ብላ ንግግሯን ትርጉሙ በማይገባ እንደ ሱዛን ራይስ የያኔው የምርጫ ሰሞን ሳቅ የሚመሰል ቀፋፊ ሳቅ አጅባ ወሬውን ለማስቀየስ ሞከረች፡፡
የሷ የፕሬስ ብሪፊንግ  ጊዜ ተጠናቀቀ፡፡
በቀጣይ የጸጥታው ምክርቤት የወቅቱ (የሀምሌ ወር ) ፕሬዘዳንት የሆኑት የፈረንሳዩ አምባሳደር የፕሬስ ብሪፊንግ ተራ ነበር፡፡
አምባሳደሩ ፈረንሳይ የጸጥታው ምክርቤት ፕሬዝዳንት በምትሆንበት የሀምሌ ወር ተራዋ የሚሰሩ ስራዎችን ቀን በቀን ዘርዝረው አስቀመጡ፡፡ዋና ዋና የሀምሌ ስራዎቻችን ብለው ከዘረዘሩት ውስጥ የሶሪያ ፡የሊቢያ ፡የየመን የመካከለኛው ምስራቅ ፡የኮንጎ ፡የማእከላዊ አፍሪካ ጉዳዮች ይነሳሉ በትኩረት ይታያሉ  አሉ፡፡እስከ ሃምሌ 30 በዘረዘሯቸው የስራ እቅዶች ውስጥ የኢትዮጵያ ስም አልተነሳም፡፡
ሀምሌ ጣጣ የለውም! ፈረንሳይዬ ይመችሽ! ብዬ ፈታ አልኩ፡፡
ከዛ በኋላ እድሉ ለጋዜጠኞቸ ተሰጠ፡፡
አዛውንቷ  ኤዲ አንደኛ ነበር እጇን ያወጣችው፡፡ አምባሳደሩ ግን እሷን ትተው ለመልከመልካሟ ወጣት ጋዜጠኛ እድል ሰጡ፡፡ወ/ሮ ኤዲ ቀወጠችው ፡፡አምባሳደሩ ኢንሲስት  አድርው ቆንጅዬዋ ልጅ እንድትቀጥል አደረጉ ፡፡ሁሉም በአምባሳደሩ ተግባር ተሳሳቁ..”አዬ የፈረንሳይ ወንድ!” ያሉ ሁላ  መሰለኝ፡፡
ቆንጆዋ ጋዜጠኛ ስትጨርስ ሁለተኛው እድል ..ያው ለወ/ሮ ኤዲ ተሰጠ፡፡
“ቲግራይ” ብ ላ ጀመረች፡፡ ገራ  ገባችኝ እቺ ሴትዮ፡፡
 እንደውም ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ጸጉራን ተተኩሳ “ኤዲ” የሚል መታወቂያ አሰርታ የመጣች ሁላ ነው የመሰለኝ፡፡
ወ/ሮ ኤዲ (እማማ አደይ ብላት ይቀላል) ቀጠለች
“የጸጥታው ምክርቤት ነገ ሲሰበሰብ ስለ ትግራይ አያወራም ወይ?!  ምን ልታደርጉ አስባችኋል?..ዋናው ትልቁ ድልድይ ተሰብሯል እኮ..!!?” ብላ ጠየቀች፡፡
ሰውዬው መለሱ፡፡
” ስለ ትግራይ ጉዳይ ካባለፈው አመት መጨረሻ ጀምሮ ስንወያይ ነበር፡፡ውይይት እንቀጥላለን፡፡የሰብኣዊ ቀውሱ አስከፊ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ማንም በዚህ ላይ ተቃውሞ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ምናልባት ብንለያይ እንኳን የጸጥታው ምክርቤት ወይም የአፍሪካ ህብረት  ኢንቮልቭመንት በምን መልኩ  ይሁን በሚለው ላይ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በነገራችን ላይ ከሁለት ወይም ከሶስት ቀናት በፊት የተኩስ አቁም ተደርጓል፡፡ይህም  ትልቅ መሻሻል ነው፡፡ከተኩስ አቁሙ በፊት አየርላንድ፡ ዩኬ እና ዩኤስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡በነገራችን ላይ የነገው ስብሰባ ላይ ይሄ አጀንዳ ይነሳ አይነሳ  ገና አልተረጋገጠም ፡፡ግን የሚነሳ ይመስለኛል፡፡የሚነሳ ከሆነ ግን ኢትዮጵያም ቀርባ ሃሳቧን ብትገልጽ ደስ ይለኛል፡፡እኔም እንዲሳተፉ አበረታታለሁ፡፡ግን ያው ይሄ ነገር በስራ አጀንዳችን ላይ ስለአልተያዘ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡” አሉና አምባሳደሩ መለሱ፡፡
ሌላ ጥያቄ የተነሳው  ስለ ክላይሜት ቼንጅ ነበር፡፡ይለፈን፡፡
ሶስተኛ የጥያቄ እድል የተሰጠው ለዛ  ለቅድሙ ጀምስ  ነበር፡፡
“እኔ የገረመኝ !”ብሎ ጀመረ “እኔን የሚገርመኝ ይሄ ስለ ትግራይ የሚደረገው ስብሰባ እርግጠኛ አይደለሁም ያሉት ነገር ነው፡፡ምንድነው ቆይ የሚያጠራጥራችሁ!?…ስብሰባው እንዳይደረግ የሚገፋ አካል አለ እንዴ!?”…ተንጨረጨረ፡፡  “በሌላ በኩል ስለ ብሉናይል ጉዳይስ ምን አስበዋል?! ..ከእርስዎ በፊት የነበረው ፕሬዝዳንት ሲደርሱት የነበሩትን ደብዳቤዎች እርግጠኛ ነኝ ቴብሎት ላይ አይተዋቸዋል፡፡ ግብጽና ሱዳን ለውይይት ሲዘጋጁ ኢትዮጲያ ነች እምቢተኛ እየሆነቸ ያስቸገረችው ..ይባላል፡፡ ይሄ  ነገር አያሳስብችሁም  ወይ?! የጸጥታው  ምክርቤት እንዴት ይሄን ነገር ዝም ይላል?!…የትግራዩ  ስብሰባ ከተደረገስ ለእኛም ኦፕን ነው ወይ የሚሆነው?! ..” በማለት ቁጡው ጀምስ ጥያቄዎቹን አዥጎደጎደ፡፡ በተለይ ስለ ግብጽ ሲያነሳ ስሜቱ ይግላል፡፡ትንሽ ትንሽ የስውየው ኮንሰርን እየገባኝ ነው  አሁን፡፡
አምባሳደሩ ቀጠሉ…”ትግራይን የሚመለከተው ስብሰባ እንዳልኩህ የመካሄድ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ግን አጀንዳችን ላይ የግድ ይካሄዳል  ብለን አልያዝነውም…ከተካሄደ ግን ኦፕን ነው የሚሆነው ፡፡ኢትዮጵያም  እንድትገኝ ለተወካያቸው ነግሬዋለሁ፡፡የአባይ ጉዳይንም ቢሆን በቀጣይ ሳምንት ስብሰባ ይኖራል፡፡ግን ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ አጀንዳችን  ላይ  ስራዬ ብለን  አልያዝነውም፡፡ ያው በራሳቸው በሀገራቱ መካከል ዲስከሽን እየተካሄደበት ስለሆነ  አላሳሰበንም፡፡” አሉና እድሉን ፓሜላ ለምትባል ጋዜጠኛ ሰጡ
ፓሜላ በስካይፕ  ነው ጥያቄ ያቀረበችው
“እንዴት ነው በትግራይ ጉዳይ የጸጥታው ምክርቤት እንኳን ዝም ቢል  ባይሆን ፈረንሳይ  እንኳን ስለ ማእቀብ መጣል ምን አስባለች!?” አለችና  አረፈችው፡፡
የዚች ፈጣጣነት ደግሞ “በዩስስ ስም “ነው ያስባለኝ፡፡ፓሜላን ላየ  አረ ወ/ሮ ኤዲ ይቅር በይኝ! የምታስብል ነቸ፡፡
አምባሳደሩ በአጭሩ “ማእቀብ የሚጣለው ሁሉም ከተስማማ ብቻ ነው! ግን አሁን ላይ ወደዛም የሚያስኬድ  ነገር ያለ አይመስለኝም!” ብሎ ኩም አደረገልኝ፡፡
ቀጣይ እድል ነቢል ለሚባል ግብጻዊ የሚመስል ጋዜጠኛ ተሰጠ፡፡
ያው ጥያቄውን አውቃችሁታል፡፡”ኢትዮጲያ እኮ በዚህ ወር ውሃውን ልትሞላ ቀነ ገደብ አስቀምጣለች! የሆነ ነገር አድርጉ እንጂ!” ብሎ “ጠየቀ”  ከማለት “ብሎ  አለቀሰ” እንበለው
የአምባሳደሩ መልስ አንጀቴን አራሰኝ…
“የግድቡ ወይም የውሃው  ጉዳይ የጸጥታው ምክርቤት መልስ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ፡፡አይመለከተንም፡፡ ማንዴቱም  የለንም፡፡ሶስቱ ሀገራት እንዲነጋገሩ ብቻ ማበረታታት  ብቻ ነው የምንችለው፡፡” ቆፍጠን ብው  መለሱለት
ፈጣሪ  ፈረንሳይን፡ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ፡፡
ሪፖርቱን ያጠናሸርኩላችሁ አንዲ ነኝ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት ኒዎርክ …..ሲተላለፍ ወሎ ሰፈር ሆኜ በቲቪ እንዳየሁት)
መልካም ቀን
Filed in: Amharic