>

ትግራይ፡ የትግራይ ክልል ሁኔታን በተመለከተ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ማን ምን አለ?  ማለዳ ቲቪ

ትግራይ፡ የትግራይ ክልል ሁኔታን በተመለከተ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ማን ምን አለ? 
ማለዳ ቲቪ

የተባባሩት መንግሥት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ያለውን ሁኔታ በማስመልከት ከዚህ በፊት ካደረጋቸው በተለየ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መክሯል።
በጸጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ኬንያ፣ ኖርዌይ፣ ታይዋን እና አየርላንድ ቋሚ አምባሳደሮች በትግራይ ስላለው ሁኔታ የአገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም ውሳኔ የሚደነቅ ነው፣ አስቸኳይ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ይድረስ፣ እንደ ቴሌኮም እና የአሌክትሪክ ኃይል ያሉ አገልግሎቶች ይጀመሩ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት ያስፈልጋል የሚሉት ጉዳዮች በተወካዮቹ በስፋት ተንጸባርቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት ያሉት ሲሆን አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግድ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ናቸው።
ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጂር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ደግሞ አስሩ ተለዋዋጭ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።
ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ኬንያ
“ዛሬ የምንወያይበት ችግር በአንድም ሆነ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም” ያሉት በጸጥታው ምክር ቤት የሩሲያው ተወካይ አምባሳደር ባሲለይ ኔቤንዘያ ናቸው።
የተኩስ አቁሙ አዋጅ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚመራ ነው ካሉ በኋላ፤ መንግሥት በትግራይ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ለዚህም መንግሥት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል ብለዋል የሩሲያው አምባሳደር።
“የትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ በመሆኑ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ችግሩን ለመፍታት የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል” ሲሉም ተደምጠዋል።
በምክር ቤቱ የቻይና ቋሚ ተወካይ ዳኢ ቢንግ ዓለም አቀፉ ማኅብረስብ በትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብር ጠይቀዋል።
አምባሳደር ቢንግ የትግራይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ነው ካሉ በኋላ፤ ኢትዮጵያ የትግራይ ችግር በእራሷ ለመፍታት አቅሙ አላት ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብም ድጋፍ በሚሰጥበት ወቅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ባለቤትነት ባከበረ ሁኔታ መሆን አለበት ብለዋል።
የሕንድ ቋሚ አምባሳደር የሆኑት ቲ. ኤስ. ቲሩሙርቲ የፌደራሉን መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅን አድንቀው፤ ውሳኔው ሰላም ለማስፈን ይረዳል ብለዋል።
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት የተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበው፤ አገራቸው ሕንድ የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ታረጋግጣለችም ብለዋል።
በምክር ቤቱ የኬንያ ቋሚ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ ደግሞ የመንግሥታቸውን ጨምሮ የቱኒዚያ፣ የኒጄር፣ ሴንት የሴንት ንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ መንግሥታትን አቋም በጽሑፍ አቅርበዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያውያንን የዲሞክራሲ ግንባታ ፍላጎታቸውን እንረዳለን በቅርቡም ያካሄዱት ምርጫ ተዓማኒነት ያለው ስለመሆኑ የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ሪፖርቱ ስለማድረጉ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ለተፈጠረው ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የመስጠት አቅሙ አለ ያሉ ሲሆን፤ የጸጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ተደግፎ ኢትዮጵያዊ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጥ እናበረታታለን ብለዋል።
አምባሳደር ማርቲን ኪማኒ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምን ለማስጠበቅ አቅሙ አለው ብለዋል።
አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ፈረንሳይ
በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በቅርቡ መንግሥት የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውሰው፤ በቀጣይ የፌደራሉ መንግሥት ያልተገደብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።
አሜሪካ ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ጋር በመሆኑ ይህ ስብሰባ እንዲካሄድ ጥሪ ያቀረበችው በትግራይ ያለው ሁኔታ መሻሻልን ባለማሳየቱ ነው ብለዋል አምባሳደሯ።
ክፍት ስብሰባ ማድረግ ብቻ በቂ አለመሆኑን ተናግረው በትግራይ ያለው ሁኔታ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ የጸጥታው ምክር ቤት ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ሠራዊት ከመቀለ ለቆ ሲወጣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶችን ቢሮዎች ተዘርፈዋል፤ የግንኙነት መሳሪያዎችም ወድመዋል” ያሉት አምባሳደር ግሪንፊልድ፤ የተዘረፉት ቁሳቁሶች በሙሉ መመለስ አለባቸው ብለዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢያዎች ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው በላይ በአሁኑ ወቅት እርዳታ የሚያሻቸውን መድረስ ከባድ ሆኗል ስለማለታቸው አምባሳደሯ ጠቅሰው፤ ይህ የሚረጋገጥ ከሆነ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ያወጀው የተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው ብለዋል።
የኖርዌይ ተወካይዋ በበኩላቸው “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ረሃብ ሊባል በሚችል ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል” ካሉ በኋላ፤ በትግራይ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶቹ ተቋርጠው ስለሚገኙ በቂ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አውስተዋል።
“ሕዝቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው” ያሉት አምባሳደሯ፤ “አሁንም የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢያዎች ሥራቸውን እንዳይሰሩ እየተከለከሉ ነው። የፌደራሉ መንግሥት ፍቃድ መስጠት አለበት። የተቋረጡ መሠረተ ልማቶች መመለስ አለባቸው። በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ውድመት መቆም አለበት” ብለዋል።
በጸጥታው ምክር ቤት የኖርዌይ ተወካይዋ ጨምረውም የትግራይ ችግር በጦር ኃይል የሚፈታ አይደለም ብለዋል።
የኢስቶኒያው ተወካይ የትግራይ የጸጥታ ችግር ለዓለም ሰላም እና ደኅንነት ስጋት ሰለሆነ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ተደምጠዋል።
የፈረንሳዩ ተወካይ አምባሳደር ኒኮላስ ዲ ሪቪዬራ ደግሞ፤ የትግራይ ኃይሎች መቀለ ከተማን መልሰው መያዛቸው በትግራይ ለተከሰተው ቀውስ የጦርነት አማራጭ መፍትሄ እንደማይሆን ያሳየ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ ጠይቀው፤ ጦሩ ከትግራይ መውጣቱም መረጋገጥ መቻል አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የጦር ኃይሎች አለመረጋጋትን ከሚያስከትሉ ተግባራት እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ጥሪ አቅርበዋል።
Filed in: Amharic