በውሸቶች ማማ፣ የሚወሰወሰው፣ የዘመኔ ሰው… !!!
አሰፋ ሀይሉ
«ቁንጫና አይጥ፣ ጋን ተሸክመው
ነብር ዓይኑ ታውሮ፣ ፍየል ስትመራው
አባይ ውሃ ደርቆ፣ መሬት ሲሰፋው
ይህን አየሁ ይላል፣ የዘመኑ ሰው፡፡»
የዛሬው ዓላማዬ Tower of lies (የውሸት ግንብ) የተሰኘው በፈረንጅ አፍ የተጻፈ ድርሳነ ክለሳ አይደለም፡፡ በመጽሐፉ መነሻነት ልናገረው የግድ የሆነብኝን የራሳችንን አንዳንድ ነገሮች ለማስታወስ ነው፡፡ የራሳችንን ታሪክ፡፡ የራሳችንን ጠባይ፡፡ የራሳችንን ነገር፡፡
ድሮ አንድ ድርቅ ብሎ መከራከር የሚወድ ሰውዬ ነበር አሉ፡፡ አባቶቻችን በታሪክ መልክ የነገሩን ታሪክ ነው፡፡ እና ከርቀት መስኩ ላይ ወዲህ ወዲያ የምትቀነጣጥብ ፍጡር ያያል ከጓደኛው ጋር ጉብታው ላይ ተቀምጠው እያወጉ፡፡ እና እንዲህ ይለዋል ክርክር ሲጀምር፡- ‹‹አየሃት ፍየሏን?! እንደጉድ ትግጠው የለም እንዴ ባክህሷ!››
ጓደኝየው ደሞ ከርቀት የተመለከቱትን ነገር ልብ ብሎ ለማስተዋል ቢሞክር፣ መሬት ላይ ወርዶ ከሣሩ ላይ ያገኘውን ከሚቀነጣጥብ አሞራ በቀር፣ ዝር ያለ የፍየል ዘር ማየት አልቻለምና፡- ‹‹የምን ፍየል ነው የምታወራው?! አሞራውን ነው የምትለኝ?›› ይለዋል፡፡ ፍየል ነች ባዩ ግን ያንኑ ፍጡር እያመለከተ፣ ነገር ግን ፍየል እንጂ አሞራ አይደለችም ብሎ ሞገተ፡፡ አልተስማሙም፡፡ ስለዚህ እንየውና ይለይልን ብለው፣ ወደታየው ነገር ይበልጥ ተጠጉ፡፡
አሁን በመስኩ የሚታየው አሞራ መሆኑ ግልጥ እየሆነ መጣ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ተከራካሪው ፍየል ናት ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ‹‹በሁለት እግር የምትራመድ ፍየል አይተህ ታውቃለህ?›› ቢለው ጓደኛው፣ ‹‹አሻፈረኝ! ፍየል ነች!›› ብሎ ድርቅ አለ፡፡ እንዲህ እየተሟገቱ በጥቂት እርምጃዎች ርቀት ብቻ ርቀው ወደ ነገርዬው ተጠጉ፡፡ አከራካሪው ፍጡርም እመር ብሎ ወደ ሰማይ ክንፎቹን ጆፌ እያማታ በረረ፡፡
ይህን ጊዜ በመገላገልና በአሸናፊነት ስሜት ወደ ጓደኛው ዘወር ብሎ፡- ‹‹አሁንስ አመንክ? አሞራ መሆኑን?›› ይለዋል፣ እሱ ሆዬ ሊያምን? በፍጹም ፍየል ናት ብሎ ድርቅ፡፡ ጓደኛው በብስጭት ቃል፡- ‹‹እየበረረች እያየሃትም?! ፍየል ነች ነው የምትለው!?›› ይለዋል፣ ጓደኝየው አሁንም ዓይኑን በጨው እጥብ አድርጎ ሠማይ ሠማዩን እያየ፡- ‹‹አዎና! ብትበርስ? ብትበርም ፍየል ናት!!››፡፡
(ከዚህ በኋላ ምን እንደተባባሉ አላውቅም፡፡ ሳስበው ግን ጓደኛው ‹‹በ…ል በል ወዳጄ፣ እኔ ደሞ ሰው አገኘሁ ብዬ፣ ተወው ተወው…፣ አዎ የምትበር ፍየል ትሆናለች እንግዲህ! ትሁንልህ ፍየል ናት!›› ብሎት፣ ባለበት ጥሎት የሚሄድና፣ ዳግመኛም ተመልሶ ለቁምነገር ወሬ ዝር የማይል ይመስለኛል፡፡)
ታዲያ አሁን አንዳንድ ሰዎችን ሳይ፣ ነገረ ሥራቸው በሙሉ ልክ ያንን ‹‹ብትበርም ፍየል ናት!›› ያለውን ደረቅ ሰው እየሆነብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ቅድም አንዱን የጽሑፍ መልዕክት ላኩለት፡- ‹‹አየኸው የደብረፅዮንን ንግግር?›› ብዬ፡፡ ምን ብሎ ቢመልስልኝ ጥሩ ነው? ‹‹የትኛውን?›› ብሎ፡፡ ፈጥኜ መለስኩለት፡- ‹‹አሁን ሞተ ከተባለ በኋላ፣ ሽርጥ ባንገቱ አገልድሞ፣ በትግርኛ ያስተላለፈውን ንግግር! አየኸው?›› አልኩት ዘርዘር አድርጌ፡፡ ‹‹አዎ አየኹት፣ አልገባኝም ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› የሚል ጥያቄ ላከልኝ፡፡
እንዴ? ጥያቄው ገረመኝ፡፡ የደብረፅዮን ሞት በመንግሥት አፍ ከተለፈፈ ጀምሮ፣ በቀብሩ ላይ እንደተገኘ ለቀስተኛ ‹‹በእርግጠኝነት ሞቷል!›› እያለ ቁምስቅሌን ሲያሳየኝ ነበራ! ያውም እኮ ‹‹አዎ ሞቶ ሊሆን ይችላል!›› እያልኩትም ጭምር እኮ ነው – ‹‹ለምን በእርግጠኝነት መሞቱን አታምንም!›› እያለ መከራዬን ሲያበላኝ የከረመው፡፡ ታዲያ አሁን እንደ አዲስ ርዕሰ ጉዳይ ምነው እንዳልገባው ሆነ?
አንደኛ ነገር ሰው ሞተ አልሞተ፣ ያን ያህል በሰው ሞት ላይ መከራከሩና መቆመሩ አግባብ ነው የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ እና ባነሳው ቁጥር በቀላሉ ‹‹አዎ ሞቶ ይሆናል፣ እሱን እንተወው›› እያልኩ አልፈዋለሁ፡፡ ይናደዳል፡፡ መዓት ሟቾችን ያጎርፍልኛል፡፡ መዓት የእነ አብይ አህመድን መግለጫዎችና ዜናዎች ያዘንብልኛል፡፡ አሁን በመጨረሻ ሰውየው በሚዲያ ቀርቦ ንግግሩን እያሰማ ነው! እና ‹‹…አልገባኝም ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ማለት ምን ማለት ነው?
አናደደኝ፡- ‹‹በህይወት አለ፣ አየኸው አይደል? አልሞተም ማለት ነዋ፣ አሁንስ አመንክ መኖሩን?›› ብዬ ጻፍኩለት፡፡ የብሽሽቅ አደረግኩት፡፡ እንጂ እኔ ደብረጽዮን ለመኖሩም ሆነ ቢሞትም ኖሮ ለመሞቱ ያደረግኩት ቅንጣት አስተዋፅዖ የለም፣ እና ምን ቤት ነኝ፣ አሁን አክሜ እንዳስነሳሁት ሰው፣ ከሰው ጋር አልሞተም ብዬ ብሽሽቅ ውስጥ የምገባው?
ለማንኛውም መለሰልኝ በፍጥነት ጓደኛዬ፡- ‹‹የቆየ ቪዲዮ ይሆናል፣ ወያኔዎችን አትመን፣ ራሱኑ ቢያቀርቡልኝም አላምንም፣ ለመሆኑ በትግርኛ ምን እንዳወራ ሰምተኸዋል? በማወናበጃ ኢንፎርሜሽን አትሸወድ፣ ሰውየው ሞቷል!››፡፡ ገረመኝ፡፡ ምን እንደምለው አላወቅኩም፡፡ ቀጭን መሴጅ ልኬለት ስልኬን ጠረቀምኩት፡፡ መልዕክቴ እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹ልክ ነህ ደብረፅዮን ሞቷል! ብትበርም ፍየል ናት!››
አንዳንድ ሰው ግን አለ፡፡ ልማደኛ ዋሾ የሚባል፡፡ ወይም ‹‹የውሸት አባት›› የሚል መጽሐፍ ሊጻፍበት የሚገባ፡፡ የምሬን እኮ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በገበያ ላይ የዋለውንና፣ ትራምፕን – የዋሾዎች ቁንጮ አድርጎ የሚያቀርብና፣ ‹‹የውሸቶች ማማ›› የሚል ርዕስ የተሰጠውን መጽሐፍ ከሰሞኑ አግኝቼ እያነበብኩት ነበር፡፡ የትራምፕ ታወርን በገነባችለትና ከትራምፕ ጋር ከ18 ዓመት በላይ በቅርብ ሠርታ የዋሻትን ጉዶች ሁሉ በምትዘከዝክ ሴት የተጻፈውን መጽሐፍ፡፡
የትራምፕን ያልተቋረጡ ውሸቶችና ‹‹አንቺ ግን በጣም ሀቀኛ የመሆን ችግር አለብሽ፣ ይህን ጠባይሽን ማሻሻል አለብሽ!›› የሚል ተግሳጽ የሰጣትን ሁሉ እያነበብኩ ነው፡፡ መዋሸት በነገሠበትና መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባር በሆነበት ሥፍራ ላይ፣ እውነትና እውነተኛነት እንደ ችግር መቆጠራቸው አይቀርም፡፡ ይገርማል፡፡ ያሳዝናልም፡፡
‹‹የውሸቶች ማማ››ን እያነበብኩ፣ በየመሐሉ የሚመጣብኝ ሀሳብ አንድና አንድ ሀሳብ ብቻ ነበር፡፡ በኛ ሀገር ግን፣ እንዲያው ደፍሮ በመጽሐፍ መልክ የሚያሳትም ዜጋ ጠፍቶ ነው እንጂኮ – አንዳንድ ሰውማ አለ – ከእኛም ሀገር መሐል – በስነሥርዓት – ትራምፕን ራሱ ደህና አድርጎ የሚቦንስ ዋሾ – የዋሾዎች ጠቅላይ፣ የውሸቶች ማማ፡፡ የዋሾዎች ቁንጮ ብቻ ሳይሆን፣ የዋሾዎች ጋሜ፣ የዋሾዎች ጎፈሬ! የውሸት ባለሀብት መሆን የሚችል ተስተካካይ መሪ፡፡ የዋሾዎች ማማ ብቻ ሳይሆን፣ መዓት ውሸቶችን ማመንጨት የሚችል የዋሾዎች ግድብ፡፡ አበስኩ ገበርኩ፡፡ እግዚአብሔርን?! ቢቀርስ? ባይበላ! የምሬን እኮ ነው?
ሰዉ ሁሉ በኛ ሀገር ጭፍንነቱ እየበዛብኝ የመጣበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ምክንያት ሲጠፋ ያሰጋኛል፡፡ የመጠፋፋት የመግቢያው ገጽ የምክንያቶች መትነን ነው፡፡ ሰዉ ሁሉ መስማት የሚፈልገውን ነገር እንጂ፣ እውነቱ ይሄ ነው ብሎ የሚሞግተውን ማድመጥ ከተወ ሰነበተ፡፡ ገና ለገና አሳምሮ የሚናገርልኘ አገኘሁ ብሎ፣ አዳሜ ጋሜው መራሁ ሲል ‹‹አደም ቀደመ››፣ ጋሜው እኩል ሆንኩ ሲል ‹‹አደም ታጀበ››፣ ጋሜው ውራ ሲቀር ‹‹አደም ነዳቸው›› ከማለት አልፎ፣ አሁን አሁን ‹‹ሞተ!›› የተባለ ሰው፣ ተነስቶ ሲናገርም፣ የተናገረበትን ቋንቋ በምክንያትነት አቅርቦ ‹‹ቢናገርም ሞቷል!›› የሚልበት ደረጃና አስደንጋጭ ጊዜ ላይ ተደርሶልናል፣ ጎበዝ፡፡
ለማንኛውም ‹‹ብትበርም ፍየል ናት!›› መባባላችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እስቲ የደብረፅዮንን የሠማይቤት መልዕክት ደሞ የሚተረጉምልኝ ባገኝና፣ የተወሰነ ስለ ገሃነም ምንነት የማውቅበት ጭላንጭል እንኳ ቢከፈትልኝ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ግድየለም፣ አልከራከርም፡፡ መሮኛል ሙግት፡፡ ግን እስቲ ግድየለም፣ ከሙታን መናፍስት ጋር ህያዋንን የምታገናኙ፣ ከንፋሳት ላይ የተበተነን ዱቄት አገጣጥማችሁ የምታስነሱ፣ የዚህ መንደር አማኞች – እባካችሁ – የደፂን ቃል በመተርጎም ብትተባሩን? እስቲ እርዱንማ!
«መሰለኝ ልክ ነው፣ ከቶም አይመስለኛል
ስንጥቅ ምላስ ወሬ፣ አለና የለሁም፣ ሁሉም ይመቸኛል
ማዳመጥ ልጀምር፣ ጆሮዬን ብከፍተው
የወያኔ ቅጥፈት፣ በድንገት መረገው ።
ዘመኑ የዋሾ፣ ጊዜውም የገዳይ
አስመሳይ አገር-ወዳድ፣ ባገር ሁሉ ተባይ
ፈልቶ ተጠናክሮ፣ እያፈነን ስቃይ
ዝምታው ለምን-ነው፣ ወድቀን በትቢያ ላይ?»
(ግጥም፡— ሀበሺኛ በአስር፣ በሀማ ቱማ)
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ!
መልካም ጊዜ፡፡