ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የአረቡ ራቢጣ ማህበር የጥላቻ እና ሚዛኑን የሳተ አስተያየት በወፍ በረር ሲቃኝ
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
መንደርደሪያ
የአረቡ ራቢጣ ማህበር መሻሻል ይገበዋል፡፡ በፍትህ ማመን አለበት፡፡ የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ሁኔታ በእኩልነት መንፈስ ስምምነት እንዲደረግበት ወይም ገቢራዊ እንዲሁን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
የዶሃ ኳታር ስብሰባ( summit in Doha, Qatar)
እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር ሰኔ 15 2021 ዶሃ ኳታር ላይ የአረቡ ራቢጣ ማህበር የስብሰባ ውጤት መጨረሻ ድምዳሜ የቅኝ ገዢዎችን መንፈስ የሚያስታውስ ነው፡፡ ይህ የቅኝ አገዛዝ መንፈስ ደግሞ ከአፍሪካ ምድር ከጠፋ ዘለግ ያሉ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ ባሻግር በሁለተኛው የአለም ጦርነት ግዜ አረቦች በቅኝ ገዢዎችነ ስር በነበሩበት ግዜ የጎመራውን የአረብ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴንም ያስታውሰናል፡፡ በነገራችን ላይ የአረቡ ራቢጣ የተመሰረተው ካይሮ ግብጽ ሲሆን በበለጠ ቁጥጥር የሚደረግበት በግብጽ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ግብጽ በበላይነት የምትመራው ማህበር ነው፡፡ ዋነኛ አላማው ደግሞ በፓን አፍሪካኒዝም (በአፍሪካ አንድነት) ፍልስፍና ኪሳራ የፓን አረቢዝም ( የአረብ ሀገራት አንድነት) ፍልስፍናን ማስቀደም ነው፡፡ ምንግዜም ቢሆን የአረቡ ራቢጣ ማህበር ለአፍሪካ አንድነት የሚደማ ልብ የለውም፡፡
በዛሬው ዘመን የአረቡ ራቢጣ ዋነኛ ትከረት ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያን ታርጌት ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር ካለው የዘመናት ምኞት እና ህልም የመነጨ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የእብሪት ውሳኔ በቱርክ ላይ ሊተገብሩ አይቻላቸውም፡፡ ቱርክ ከግዛቷ ተነስተው የሚፈሱ ወንዞችን ልማት ላይ ስታውል ለማስቆም አልሞከሩም ነበር፡፡ ቱርክ በወታደራዊ ሀይል ከአረብ ሀገራት ሁሉ የበላይነት ስላላት እንዲሁም የናቶ አባል ሀገር (is a member of NATO) በመሆኗ ምክንያት የተነሳ ቱርክን በወታደራዊ ሀይል ለማስፈራራት አይሞክሩትም፡፡ ቱርክ የምትገኝበት የአለም ክፍለ አለም አውሮፓንና ኤሽያን የሚያማክል ስትራቴጂክ ቦታ ሲሆን በላይኛው የወንዝ ተፋሰስ የምትገኝም ሀገር ናት፡፡ ከዚህም ባሻግር ቱርክ እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 1980 እሰከ 1990ዎቹ ባሉት አስር አመታት ብቻ በሶሪይና ኢራቅ በሚያዋስናት ድንበሮች አቅጣጫ በኤፍራጥስና ቲግሪስ ወንዞች ላይ ወደ 22 የሚጠጉ ታላላቅ የውሃ ግድቦችን ገንብታ ጥቅም ላይ አውላላች፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በመሃከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የውሃው ተፋሰስ ሀገራት ራሳቸውን ውሃ ከጦርነት አርቀዋል፡፡ የታሪክ እውነታዎች እንደሚያሳዩት በአካባቢው በውሃ ይገባኛል ምክንያት ጦርነት ተካሂዶ የነበረው ከ4,500 አመት በፊት ነበር፡፡
የአካባቢው ወንዙ ተፋሰስ ሀገራት በውሃ ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን የሚፈቱት በሁለትዮሽ እና ከዛም በላይ የሀገራት ንግግርና ስምምነት እንጂ በጦርነት አይደለም፡፡ ሁሉም ሀገራት የህሊና ሚዛናቸውን በመጠቀም እና ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት እንዲሁም በፖለቲካ ግልብ ውሳኔ ሳይሆን ሳይንስና ቴክኒክን መሰረት አድርገው የውሃ ክፍፍል ለማድረግ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ፡፡ ከዚህ እውነት በተቃረነ መልኩ ብዙ ሀገራትን አቋርጦ የሚፈሰው ታላቁ የናይል ወንዝ እንዲህ አይነት የውሃ ክፍፍል ስምምነት አልተደረገበትም፡፡
የናይል ወንዝ ውሃን በእኩልነት ለመጠቀም ስምምነት መድረሻው ግዜው አሁን ነው
ከሰሃራ በታች የሚገኙት 11ዱ አፍሪካ ሀገራትና በናይል ወንዝ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተው የአረብ ሀገራት ሁሉንም ሀገራት ያካተተ በእኩልነት መንፈስ ላይ የተመሰረተ እና ምክንያታዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም ስምምነት የሚያደርጉበት ትክክለኛ ግዜ ላይ የደረሱ ይመስለኛል፡፡ ይህን በገቢርም በነቢብም እውን መሆን የሚቻለው በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እና በአለም አቀፉ ብይነ መንግስታት ልዩ ወኪል ቴክኒካል ድጋፍና በአለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት እገዛ ነው፡፡
አሁን ለተከሰተው ቀውስ ብቸኛው መፍትሔ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም ስምምነት ላይ መድረስ በርካታ የህሊና ምሁራንና ጋዜጠኞች በብዙ መልኩ ያስረዱት ጉዳይ ነው፡፡
የአረቡ ራቢጣ ግጭቶችን እና ጭቅጭቆችን ለመፍጠር ከሚነሳ ለትብብር መንፈሳዊ ወኔ ቢታጠቅ በአፍሪካ ሰላም፣መረጋጋት እና ብልጽግና እውን እንዲሆን አስተዋጽኦው ሁነኛ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ በጤግሪስና ኤፍራትስ ወንዞች ላይ ቱርክ በርካታ ግድቦችን ስትገነባ ውዝግብ ያላስነሳው የአረቡ ረቢጣ ለአፍሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ማደግና መበልጸግ ቀና መንፈስ ማሳደር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሁለቱም ወንዞች ለቱርክም ሆነ ጎረቤት ሀገሮቿ በትብብር መንፈስ ጥቅም ላይ መዋሉ መራር ሀቅ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ግጭትና ብጥብጥ የፓሊስቲንን ጉዳይ መፍታት እንዳላስቻለው ሁሉ የኛይል ተፋሰስ ሀገራት ( በተለይም ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ) በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነት በሰለጠነ እና በእኩልነት መንፈስ እንዲፈቱ መርዳት አለበት እንጂ ከመሰሪዋና አልጠግብ ባይዋ ግብጽ እንዲሁም አቋሟ ለሚለዋወጠው ሱዳን ጭምር ወገንተኛ መሆን የለበትም፡፡ በፔትሮል ዶላር የሰከሩት ሳኡዲ አረቢያ እና የአረብ ኤሜሬትስ ቱጃሮች ወረታቸውን በማፍሰስ ኢትዮጵያንም ሆነ ሁለቱንም ሀገራት የሚጠቅም ኢንቨስትመንት ማፍሰሳቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ስትጀምር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሞዎቹ የአረቡ ረቢጣ አንዳንድ አባል ሀገራት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
በግብጽ የዜሮ ድምር እኩይ ሴራ ተታሎ በጭፍንና ድድብና ግብጽና አጋሯን ሱዳን ለመደገፍ የቆመው የአረቡ ራቢጣ ማህበር አቋሙ ወደ ግጭት የሚወስድ እንጂ ለማንም ሀገር ጥቅም አይሰጥም፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የአረቡ ራቢጣ ማህበር አቋም በዘረኝነት መንፈስ የታጀለ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የአፍሪካ ህብረትን እና የአፍሪካ አንድነትን ድርጅት ሚና የሚቀንስም ነው፡፡ ይህን እኔ ያቀረብኩትን ሃሳብ የሚደግፉ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
ግብጽና ሱዳን ከባድ ጭንቀት ውስጥ በመዶላቸው ምክንያት የተነሳ በታላቁ ህዳሴ ግድብየተነሳውን ውዝግብ በአፍሪካ ህብረት እንዳይዳኝ በርካታ ምክንያቶችን በመደርደር አሁን ድረስ መቋጫ እንዳይበጅለት አድርገዋል፡፡ የአፍሪካን ጉዳይ ለተባበረችው አሜሪካና ለአለም ባንክ አቅረበውም ነበር፡፡ ሄው ሙከራቸው ሲከሽፍ ደግሞ ወደ ብይነመንግስታቱ የጸጥታ ጉዳይ ካውንስል ወስደውትም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የጸጥታው ጉዳይ ካውንስል መልሶ ጉዳዩን ወደ አፍሪካው ህብረት እንደላከው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአረቡ ራቢጣ ማህበር ተመሳሳይ ስህተት ለመስራት ጉዞ የጀመረ ይመስላል፡፡ በእኔ የግል አስተያየት በታላቁ የህዳሴ ግድብ አኳያ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት አፍሪካው ህብረት ህጋዊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሁሉም አሸናፊ (to a win-win outcome ) የሆኑበት ውጤት ማግኘት ለምን አልተቻለም ?
የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ግብጽና ተለዋዋጭ አቋም የምታራምደው ሱዳን ኢትዮጵያ ከግድቡ የምትለቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጥስና ለወደፊትም የተፈጥሮ የውሃ ሀብቷን እንደፈለገችው እንዳትጠቀም በእጅጉ የሚጎዳት ጉዳይ ነው፡፡ የወደፊቱ ትውልድንም በእጅጉ ችግር ውስጥ ሊዶል የሚቻለው ነው፡፡ ለዚህም ነው ይህ አስገዳጅ ውል በኢትዮጵ መንግስት አኳያ ተቀባይነትን ያጣው፡፡
በኢትዮጵያ ስራ ለማግኘት ያለው እድል ጠባብ እንደሆነ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በዚህ ምክንያት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአረብ ሀገራት በተለይም በሰኡዲ አረቢያ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን በሰኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይደፈራል፡፡ ብዙዎችም ወደ ሀገራችው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ጦርነት ባደቀቃት የመን ሳይቀር የኢትዮጵያ ስደተኞች መውጫ ቀዳዳ አጥተው ፍዳቸውን ይቆጥራሉ፡፡
ከዚህ አይነት ብሔራዊ ውርደት ለመገላገል በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር መስፈን ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በሚሊዮን የሚቆጠሩ የስራ እድሎች እውን መሆንም አለባቸው፡፡ የዚህ ውጤቱ ደግሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያፈረጥመዋል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ደግሞ እንዲህ አይነት ስደትን ለመግታት አስተዋጽኦ የትዬሌሌ ነው፡፡
የአረቡ ራቢጣ ማህበር የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ሀብት ለሰኡዲ አረቢያና ለሌሎች የአረቡ ራቢጣ ማህበር አባል ሀገራት የእድገት መሰረት እንደሆነው ሁሉ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውሃ ሀብት የእድገቷ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል መረዳት አልፈለገም፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውሃ ሀብት አልምታ ወደ እድገት ጎዳና እንድትጓዝ አልፈለገም ወይም ውሃ የኢትዮጵያ የልማት መሰረት መሆኑን መገንዘብ ምኞቱ አይደለም፡፡
ለምንድን ነው የአረቡ ራቢጣ ማህበር አቅድ ስህተት የሆነው ?
የአረቡ ራቢጣ ማህበር አባል ሀገር የሆኑት 17 የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በዶሃ ኳታር አድርገውት በነበረው ስብሰባ መቋጫ ላይ የወሰኑት ውሳኔ በግብጽ የተሳሳተ ትርክት ላይ ተመስርተው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በነገራችን ላይ የግብጽ ትርክት የሚያጠነጥነው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ እያስገነባች ያለችው ይህ ግዙፍ ግድብ በሱዳንና ግብጽ ላይ ከባድ ጉዳት ይዶላቸዋል የሚል የሀሰት ትርክት ነው፡፡ ከዚህ የአረቡ ረቢጣ ማህበር አቋም በእኔ በኩል የምረዳው ቁምነገር ቢኖር የረቡ አለም ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለበት ነው፡፡ በአረቡ አለም( በመካከለኛው ምስራቅ) ውሃ የጸጥታ ጉዳይ እንደሆነም ይሰማኛል፡፡ እስቲ አስቡት አይሆንም እንጂ ምናልባት የኢትዮጵያ አቋም የአረቡን አለም ጥቅም ለመጉዳት የታለመ ቢሆንስ ይህ እውነት አይደለም እንጂ ገቢራዊ ቢደረግ ከባድ ጉዳትን የሚጭር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አቅድ ግን ማናቸውንም ሀገራት ለመጉዳት የታለመ አይደለም፡፡
ለአብነት ያህል የኳታሩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱርሃማን አልታኒ ለአለም አቀፍ የዜና አውታሮች በሰጡት ቃለምልልስ ኢትዮጵያ በምታስገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አኳያ የተነሳውን እሰጥ እገባ መፍትሔ ለመስጠት እየተጋን እንገኛለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሽምግልናቸው የአንድ ወገን ጥቅምን ለማስጠበቅ( በተለይም ለግብጽና ሱዳን ጥቅም ያደላ ነበር) የቆመ ነው፡፡
እንደ የውሃ ምህንድስና ጠበብት የጥናት ውጤት ከሆነ ከ90 ፐርሰንት በላይ የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ የሚያከራክር አይደለም( በግድቡ ዙሪያ የነበሩ አብዛኞቹ አለመግባባቶች እልባት ተገኝቶላቸዋል፡፡ ወይም ስምምነት ተደርሶባቸዋል፡፡) የቀሩት ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ይመስሉኛል፡፡ እነኚህም ለወደፊቱ የሚከሰቱ የውሃ ክፍፍል ጭቅጭቆችና በድርቅ ግዜ እንዴት የአባይ ወንዝ ውሃን ማሰራጨት ይቻላል የሚሉት ናቸው፡፡ ( በድርቅ ወራቶች ከአባይ ወንዝ ወደ ሁለቱ ሀገራት የሚፈሰው የውሃ መጠን ቢቀንስ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡) በእነኚህ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሶስቱም ሀገራት ፍትሃዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ መፍትሔው የአፍሪካው ህብረት ዳኝነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡)
የአረቡ ራቢጣ ማህበር ፍጹም የተሳሳተ እና ኢፍትሃዊ ስለመሆኑ በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ምሁራን ካቀረቡት ጥናት እንደሚከተለው ለአንባቢው ግንዛቤ ይሰጣል በሚል አቅርቤዋለሁ፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ እውቅ ኢትዮጵያውያን የተወጣጣው የአካዳሚሻን፣ምሁራን እና ባለሙያዎች ስብስብ አማካሪ ካውንስል በግብጻዊው በሼክ አህመድ አልጣየብ (Sheikh Ahmed Al-Tayeb, Sheikh of Al-Azhar Al-Sharif of Egypt,)፣ የአረቡ ራቢጣ ማህበር ጸሃፊ በሆኑት አህመድ አቡል-ገሂት (Ahmed Abul-Gheit, the Arab League Secretary-General,) እና የተባበረችው አሜሪካ ማእከላዊ እዝ ከፍተኛ የጦር አታሼ የሁኑት ጄኔራል ኬኔት ማካንዚ ( General Kenneth McKenzie, US Central Command (CENTCOM) ) በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አኳያ የሚያሳስት፣ ወገንተኛ እና ፈሩን የለቀቀ አስተያየት በመነሳት የሚከተለውን ምሁራዊና ሚዛናዊ መልስ አቅርቦ ነበር፡፡ ( are outraged by the misguided, biased and unfounded statements made made in reference to the Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD).) በእውነቱ ለመናገር እነኚህ ኢትዮጵያዊ ምሁራን የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ምሁራዊ ድርሻቸውን በመወጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
1.የናይል ወንዝ ( ነጩ ናይል እና ጥቁር ናይል (አባይ) የሚፈሱት በ11 ሀገራት ሲሆኑ (ቡሩንዲ፣የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ግብጽ፣ኤሪትራ፣ኢትዮጵያኬንያ፣ሩዋንዳ፣ደቡብ ሱዳን፣ሱዳን፣ታንዛኒያና ኡጋንዳ በመባል ይታወቀሉ፡፡) ኢትዮጵያ 86 ፐርሰንቱን የናይል ወንዝ ውሃ ታዋጣለች፡፡ ይህንን ጎምዛዛ ሀቅ የአረቡ ራቢጣ ማህበር፣ግብጽና ሱዳን መጋት አለባቸው፡፡
2.ፍትሃዊ ባልሆነው የቅኝ ገዢ ውል ምክንያት 100 ፐርሰንቱን የማይል ወንዝ ውሃ ግብጽና ሱዳን ሲተቀሙ ቆይተዋል፡፡ ሌሎች የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ግን ምንም ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡
- ግብጽ 99 ፐርሰንት ለሚሞላው ህዝቧ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት ያሟላች ሲሆን፣ 65 ፐርሰንቱ ( 65 ሚሊዮን ግድም ) የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መኖር እጣፈንታው ሆኗል
4.ግብጽ 99 በመቶ ለሚሆነው ህዝቧ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ያሟላች ሲሆን፣40 ፐርሰንቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የንጹህ ውሃ አቅርቦት አልተሟላለትም፡፡
- ግብጽ ኑቢያ በሚባለው አካባቢ ከ150,000 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር(150,000 BCM በላይ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት ሲሆን፣ ይህ የተረፈረፈ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የሀገሪቱን እርሻ ለመጪዎች አንድ ሺህ አመት የሚረዳ እንደሆነ በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ወደ 122 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር (122 BCM )የሚጠጋ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት እንዳላት ይገመታል፡፡
6.ግብጽ ጨዋማ የሆነውን የባር ውሃ አጣርቶ ለመጠጥ ወሃነት መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂና በሺዎች ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር በር ያላት ሀገር ስትሆን፣ኢትዮጵያ ግን ቴክኖሎጂውም ሆነ የባህር በር የሌላት ሀገር ናት፡፡
- የግብጽ፣የኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በጥናት እንዳረጋገጠው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሱዳን ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ይቀንሳል፣ ወደ ግብጽና ሱዳን የሚፈሰውን የውሃ መጠን የተመጣጠነ ያደርገዋል፣ በአስዋን ግድብ ላይ ከባድ ተጽእኖ ያለው የውሃን ትነት በእጅጉ ይቀንሰዋል፡፡ ይህም ማለት በከፍተኛ የሙቀት ስፍራ ላይ በተገነባው የአስዋን ግድብ ላይ በውሃ ትነት ምክንያት የሚቀንስውነ የውሃ መጠን ከፍተኛ ሲሆን፣ በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት አካባቢ የሙቀት መጠኑ ዝቅ ስለሚል በውሃ ትነት የሚቀንሰው የውሃ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ የናይል ወንዝ ውሃ መጠን ብክነት ይቀንሳል ማት ነው፡፡
8.በአለም አቀፉ የድንበር አቋራጭ ወንዞች ህግ መሰረት ኢትዮጵያ በግዛቷ በሚገኝ ወንዝ ተጠቅማ ለማደግ ሉአላዊ መብት አላት፡፡ ከዚህ ባሻግር የናይል ተፋሰስ ሀገራት በሙሉ በእኩልነት መንፈስ ወንዛቸውን ቢያለሙ የታችኞቹ አባል ሀገራት ሊጎዱ አይቸላቸውም፡፡
9.እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2010 ላይ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ስምምነትን ሱዳንና ግብጽ አለመፈረማቸው እንደ ስህተት የሚቆጠር ነው፡፡
10.የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት ያለበት በመሆኑ፣የሶስቱ ሀገራት እሰጥ እገባ መፈታት ያለበት በአፍሪካው ህብረት መሆን አለበት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒሰቴር አማካሪ ካውንስል (Advisory Council of the Ministry of Science and Higher Education )ከላይ ከተጠቀሱት እውነታዎች በተጨማሪ ሌሎች ጠቃሚ ሃሳቦችን ለአረቡ ራቢጣ ማህበርና ለግብጽ ዩነቨርስቲዎችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካት ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ምሁራዊ እውነታን እና ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን አንጸባርቆ ነበር፡፡ ይጠቀሙበት ይሆን ? ሁላችንም አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
የትኛዋ ሀገር ናት በድርቅ አመቶች የበለጠ ተጎጂ የምትሆነው ?
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግብጽ የውሃ ሀብት እጥረት የለባትም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ስር የሰደደ ለእኔ ብቻ የሚል የውሃ ፖሊሲ አላት፡፡ ግብጽ ለመካፈልና ለመተባበርም ቢሆን ፍላጎቷ አይደለም፡፡ በጥናት እንደተረጋገጠው ከሆነ ግብጽ ከናይል ወንዝ ባገኘችው ገጸበረከት በገጸ ምድሯ ላይ ባስገነባቸው የአስዋን ግድብ በመጠቀም ወደ 160 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትርስ (160 billion Cubic Meters )(BCM የሚጠጋ የውሃ መጠን ለማከማቸት ችላለች፡፡ ከዚህ ባሻግር ለድርቅና አስከፊ የድርቅ ወራቶች በሚከሰቱበት ክፉ ግዜ ለተለያዩ አገልግሎት ሊጠቅም የሚችል ወደ 15000 ኪዩቢክ ሜትርስ ( 150,000 BCM ) የሚገመት ውሃ አጠራቅማለች፡፡
የኢትዮጵያ የውሃ አማካሪ ካውንስል፣ሳይንቲስቶች፣የውሃ ምሃንዲሶች፣የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና የጸጥታ ኤክስፐርቶች በጥናት እንደደረሱበት ከሆነና አበክረው እንደሚሳስቡት ታላቁ አስዋን ግድብ የያዘው የውሃ መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ ወይም የውሃ መጠኑ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ሌሎች ተጠባቢዎች በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ ግብጽ በኑቢያ ግዛት ከፍተኛ የተፈጥሮ የከርሰ ምድር ውሃ አላት፡፡ ይህ በሊቢያ ግዛት ከሚገኘው የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አንዱ ክፍል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሊቢያ በኮሎኔል መሀመድ የአገዛዝ ዘመን ሰው ሰራሽ ወንዝ የሰራችው ይህን እምቅ የከርሰ ምድር ውሃ ጥቅም ላይ በማዋል ነበር፡፡ በአጭሩ ግብጽ ለ250 አመት የሚበቃ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት እንዳላት ጠበብት ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግብጽ ከ1800 ማይልስ በላይ የባህር በር ላት ሀገር ስትሆን ለወደፊቱ የባህር ውሃን በቴክኖሎጂ በመጠቀም የህዝቧን የውሃ ፍላጎት የማሟላት እድሉ አላት፡፡
የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች በጥናታቸው እንደረሱበት ከሆነ ባለፉት አስር አመታት የባህር ውሃና ጨዋማ የከርሰ ምድር ውሃን ወደ መጠጥ ውሃነት ለመቀየር የሚወጣው ወጪ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ( ወይም የውሃ ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ በመምጣቱ ቴክኖሎጂውን ለማግኘት እየቀለለ መጥቷል፡፡) የግብጽ እና ሌሎች ሀገራት ሳይንቲስቶች በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ከሆነ ግብጽ በምድሯ ላይ በዘረጋችው 40000 ኪሎሜትር ርዝመት ባለው ክፍት ቦይ እና ብዙ የውሃ መጠን የሚያስፈልጋቸው ተክሎች ( ለአብነት ያህል እንደ ጥጥ ያሉት ይጠቀሳሉ) አመሃኝነት ከፍተኛ የውሃ መጠን ታባክናለች፡፡ ግብጽ ከፍተኛ የውሃ መጠን ሚጠቀሙ ተክሎችን በማምረት ትታወቃለች( ለአብነት ያህል ሩዝ፣ሸንኮራ አገዳ፣ እና ሌሎች ይጠቀሳሉ፡፡) ግብጽ ምግብ ለአለም ገበያ የምታቀርብም ሁነኛ ሀገር ናት፡፡ በቅርቡ በካይሮ ዩንቨርስቲ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ሀገሪቱ የእርሻ ዘዴዋን በማሻሻል ብቻ ወደ 40 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን ከብክነት መከላከል ትችላለች፡፡ ይህ የተጠቀሰው የውሃ መጠን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ከሚጠራቀመው የውሃ መጠን የሚወዳደር አይደለም፡፡ ግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች የሚባክንባትን የውሃ መጠን በተለያዩ ዘዴዎች መቀነስ ከሆነላት ከታላቁ የአባይ ግድብ አኳያ የምታነሳውን እስጠ እገባ ታረግባለች ብዬ አስባለሁ፡፡ አልጠግብ ባይነቷን በመተው ወደ ህሊናዋ እንድትመለስ እንማጸናለን፡፡
በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያለችው ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ በርካታ አማራጮች የላትም፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን ብሔራዊ አንድነቷ እንዲናጋ በእጃዙር የምትሸርበው ሴራ መጠነ ሰፊ ነው፡፡ በግብጽ ሁነኛ ሴራ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባር በሯን አጥታለች፡፡ ከዚህ ባሻግር ግብጽ የአለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የሃይል ማመንጫና የመስኖ ልማት ለማካሄድ ድጋፋቸውን ስትጠይቅ የገንዘብ ብድር እንዳይሰጡ የዲፕሎማቲክ ትግል ስታደርግ መቆየቷ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው በአንድ ጥናታዊ ጽፋቸው ላይ ፍንትው አድርገው እንዳስቀመጡት ኢትዮጵያ በግብጽ መሰሪ አካሄድ ምክንያት የተነሳ ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ አጥታለች፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ የደረሰባትን ኪሳራ ታሳቢ በማድረግ ካሳ የመጠየቅ የሞራልና ህጋዊ መብት አላት፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት የሚያስከፍለው ዋጋ ምን ይሆን ?
እንደ ገለልተኛ የምጣኔ ሀብት የጥናት ቡድኖች ውጤት ከሆነ የታላቁ አባይ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 80 ፐርሰንት ለሚሞላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፣ የሀገሪቱን አጠቃላይ የምርት እድገት ከ10 ፐርሰንት በላይ ይቸምራል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ሀገሪቱ በየአመቱ የምታገኘው የተጣራ አጠቃላይ ገቢ ወደ 13.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል፡፡ ስለሆነም ከተጠቀሰው ቁምነገር የምንረዳው ነገር ቢኖር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት የሚያመጣው አሉታዊ ተጽእኖ ሰፊ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ባቀረቡት ጥናታዊ ወረቀታቸው ላይ እንደገለጹት የታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ ለአምስት አመታት በመዘግየቱ ምክንያት ኢትዮጵያ 60 ቢሊየን ዶላር በላይ ከስራለች፡፡ ይህም ማለት ግብጽ ቢያንስ ኢትዮጵያ በየአመቱ ማግኘት የሚገባትን 13 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማጣቷ ዋነኛ ተጠያቂ ናት፡፡
ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የአንበሳውን ድርሻ ይዛ እንድትቀጥል የሚረዳት የትኛው አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ይሆን ?
የአረቡ ራቢጣ ማህበር ግብጽን ደግፎ መነሳቱ ከቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ የሚለይ አይደለም፡፡ የሞራል መሰረትም የለውም፡፡ ምክንያቴን ዝቅ ብዬ ለማብራራት እሞክራለሁኝ፡፡
- የግብጽ መንግስት መሰረታዊ መከራከሪያ አድርጎ የሚያቀርበው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1902 ዳግማዊ አጼ ምኒሊክና የታላቋ ብሪታኒያ መንግስት ያደረጉትን ድንበር ስምምነት በመጥቀስ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ግን የድንበር አከላለንን የሚያሳይ እንጂ የውሃን አጠቃቀም ድርሻ የሚያመላክት አልነበረም፡፡ ከጣና ሀይቅ የሚነሳው የጥቁር አባይ ፣የባሮ ወንዝ ወዘተ ወዘተ ካርቱም ላይ ከነጭ አባይ ጋር እንዳይገናኝ የሚከለክል አልነበረም፡፡ ከዚህ ባሻግር በ1902ቱ ስምምነት ላይ በአለም አቀፍ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ወንዞች እንዳትጠቀም የሚከለክል አንቀጽ አልተቀመጠም ነበር፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና እንዴት አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል የሚያሳየውን ስምምነት ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ ተፈራርመው ተቀብለውት ነበር፡፡ ሃሳቡ ወይም አላማው ግብጽን ወይንም ሱዳንን ለመጉዳት የታለመ አልነበረም፡፡
- ግብጽና ሱዳን ሁለት ስምምነቶችን እንደፈረሙ ይታወቃል፡፡ አንደኛው በታላቋ ብሪታንያ ቅኝ በተገዙበት ግዜ ማለትም አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1929 ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ነጻነታቸውን ካወጁ በኋላ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1959 ላይ ነበር፡፡ በሁለቱም ግዜ ሁለቱም ሀገራት በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛችዋን ኢትዮጵያን አግልለዋት ነበር፡፡ ከዚሁ ባሻግር ሌሎች የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትንም በስምምነታቸው አላካተቱም ነበር፡፡. ይህ ስምምነት ከናይል ወንዝ አጠቃቀም አኳያ ግብጽ አንበሳውን ድርሻ እንድትወስድ የሚፈቅድ ነበር፡፡ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንዲሉ ለናይል ወንዝ 86 ፐርሰንቱን የውሃ መጠን የምታዋጣው ኢትዮጵያ ባይተዋር መሆኗ ሲታሰብ ያሳዝናል፡፡ በዚሁ ምክንያት የናይል ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ግብጽ እኔ ነኝ ወሳኝ በሚል ትምክህት ተቸንክራ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን አግልላ ቆይታለች፡፡
- የአረቡ ረቢጣ ማህበር መረዳት ያለበት ነገር ቢኖር ከላይ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሱትን ስምምነቶች ደጋግማ ህገወጥና አሳሪ አይደሉም በማለት ውድቅ ማድረጓን ነው፡፡ እነኚህ የቅኝ ገዢ ዘመን ስምምነቶች ኢትዮጵያ ገቢራዊ ለምታደርጋቸው የውሃ ፕሮጄክቶች እርባና እንደሌላቸው ነው፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ ለአረቡ ራቢጣ ማህበር ግብጽ አፍጦ የገጠማትን መራር እውነት አስፍረው ነበር፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2019 የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም ‹‹ ግብጽ ያጋጠማት የውሃ ችግር ›› በሚል ርእስ እንደገለጸው ከሆነ ግብጽ በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች የተነሳ የውሃ ችግር ሊያጋጥማት ይችላል፡፡ እነኚህም፡-
ሀ. የግብጽ ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር
ለ.የአየር ንብረት ለውጥ
ሌላው በብዙ የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች ጥናት መሰረት ገብጽ ከናይል ወንዝ የሚገኘውን ውሃ በከፍተኛ ደረጃ ማባከኗ ለውሃ ችግር ሊያጋልጣት ይቻለዋል፡፡
ስለሆነም ግብጽ ለሚያጋጥማት የውሃ ችግር ምክንያት ለሆኑት ሶስቱ ጉዳዮች ኢትዮጵያ መፍትሔ አትሆንም፡፡ ወይም መቆጣጠር አትችልም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያላችው ግብጽ ግን የመፍትሔው አካል መሆን ይቻላታል፡፡ የህዝብ ቁጥሯን ለመቀነሰ መልካም ህዝብ ፖሊሲ ብታወጣ፣ የውሃ ብክነትን ብትቀንስ የሚጋጥማትን የውሃ እጥረት በእጅጉ መቀነስ ይቻላታል፡፡ ከዚህ ባሻግር የአየር ለውጥ ችግርን ለመቀነስ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የትብብር መንፈስ ብታዳብር ውጤት ማምጣት ይቻላታል፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራዎች የደን ልማት ፕሮዤን በገንዘብና ቴክኒክ ብትረዳ ሁለቱም ሀገራት ተተቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግብጽ እንዲህ አይነት የትብብር መንፈስ አልፈጠረባትም፡፡ ግብጽ ምንግዜም ቢሆን የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ የምታሰላ ሀገር ናት፡፡
በመጨረሻም የአረቡ ራቢጣ ማህበር መረዳት ያለበት አቢይ ቀምነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በራሷ ህዝብ የገንዘብና ጉልበት መዋጮ የምታስገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ጉዳይ ግብጽን ሊያስፈራት አይገባም የሚለውን ሁነኛ ቁምነገር ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ የአረቡ ራቢጣ ማህበር ስጋትም ያለቦታው የመጣ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር እስራኤልና ዮርዳኖስ የዮርዳኖስ ወንዝን እንዴት ተስማምተው እንደሚጠቀሙ በቅጡ የሚረዳው ይህ ማህበር፣ ሜክሶኮና ሰሜን አሜሪካ፣ ቱርክ፣ኢራቅና ሶሪያ፣ እንዲሁም የደቡባዊት አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ከጎረቤት ሀገሯ ጋር ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻቸውን እንዴት በሰለጠነ መንገድ ተስማምተው ሀገራቸውን ለማሳደግ እንደቻሉ በግልጽ እየታወቀ የአረቡ ራቢጣ ማህበር የግብጽን አልጠግብ ባይነት ብቻ መደገፉ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድነውም፡፡
እውን ግብጽ የእርሻ አመራረቷን የበለጠ ዘመናዊ ለማድረግ፣ እንዲሁም የውጭ ንግድ ፖሊሲዋን እንደገና ለመፈተሸ መንፈሳዊ ወኔ ትታጠቅ ይሆን ? በታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ምክንያት የናይል ወንዝ ውሃ መጠን ሊቀንስ ይችላል የሚለው የግብጽ መከራከሪያ በቅን ልቦና የሚነሳ ነውን ? በነገራችን ላይ የግድቡ ተገንብቶ መጠናቀቅ የናይል ወንዝ የውሃ መጠንን እንዳማይቀንስ በውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች የተረጋገጠ ነው፡፡ ለምን ይሆን ግብጽ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዳይኖር የምትፈልገው ?መልሱን በተመለከተ ህሊና ያላችሁ ተወያዩበት
በእኔ በኩል የግብጽ ምኞትና የዘመናት ሴራ ግን ለየቅል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የዚች ሀገር ህልምና ሴራ የተዳከመችና አንድነቷ የተናጋ ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ በአለም አደባባይ እንዳትራመድ የግብጽ የሁልግዜ ፍላጎቷ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከሆነላት ግብጽ የኢትዮጵያን የዝናብ እና ውሃ ምንጭ ለመቆጣጠር እረጅም ርቀት ተጉዛለች፡፡ ወይም ጉዞዋ አይቋረጥም፡፡
በነገራችን ላይ የአረቡ ራቢጣ ማህበር የ117 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ለመግፈፍ የሞራል ብቃት የለውም፡፡ የህግም አመክንዮ የለውም፡፡ኢትዮጵያ እና ህዝቧ የተፈጥሮ ጸጋ በረከት የሆኑትን ወንዛቸውን ለማልማትና ከችጋር ለመገላገል ተፈጥሮአዊ መብታቸው ነው፡፡ ማንም ሊሰጣቸው ወይም ሊነፍጋቸው አይቻለውም፡፡
ኢትዮጵያውያን፡-
- የሃይል ፍላጎታቸውን
- የውሃ ደህንነታቸውን እና
- የምግብ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ተፈጥሮአዊ መብት አላቸው፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ( በተለይም የናይል ወንዝ ) ለሱዳንና ግብጽ ብቻ ጥቅም እንዲሰጡ የአረቡ ራቢጣ ማህበር እንዲወስን የብይነ መንግስታቱ የሰጠው መብት እንዳለ የማውቀው ጉዳይ የለም፡፡ በአጭሩ ለመናገር ግን የናይል ወንዝ የግብጽና ሱዳን የተፈጥሮ ሀብት አይደለም፡፡ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት 11 ናቸው፡፡ ከእነኚህ ውስጥ ዘጠኙ (9ኙ) ከሳህራ በታች የሚገኙ ሀገራት እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የአረቡ ራቢጣ ማህበር አባል ሀገራት ግን ከናይል ወንዝ አጠቃቀም አኳያ ትብብር ስለማይፈልጉ ለሱዳንና ግብጽ ብቻ የሚበጅ ፍርደገምድል ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ይህ የማንአህሎተኝነት ውሳኔአቸው ግን ለማንም አይበጅም፡፡ ይህን ኢፍትሃዊ ውሳኔ ከማሳለፍ ፈንታ፣የአረቡ ራቢጣ ማህበር ከትምክህት አስተሳሰብ በመውጣት 11ዱም ሀገራት በፍትህ መሰረት ላይ ቆመው ስምምነት ማድረግ እንዲችሉ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት መንፈሳዊ ወኔ ቢታጠቅ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ገቢራዊ ሲሆን ብቻ ነው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ሊሰፍን የሚቻለው፡፡
እንደ መደምደሚያ
ግብጽና ሱዳን በውስጣዊ የፖለቲካ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚናጡ ሀገራት ስለመሆናቸው ምንም ጥርጣሬ የለውም። ግብጽ ታላላቅ የዲፕሎማቲክ ሰዎች ቢኖሯትም እውነትን ስላላያዘች ለግዜው ታሸንፍ እንደሁ እንጂ በመጨረሻው ሰአት የምታሸንፍ አይመስለኝም፡፡ ለአብነት ያህል ከኢትዮጵያ ዶሮ ወጥ እየተጫነላት ለሚደርሳት ዲጂቡቲ በኢትዮጵያ ላይ ጀርባዋን እንድታዞር የማትፈነቅለው ድንጋይ፣ያልሞከረችው ሸፍጥ ሴራ የለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግብጽ በጅቡቲ በኩል ያላት አማራጮች ተሟጠው ያለቁ ይመስላል፡፡ ዲ
በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በአንፃራዊነት ጥሩ ቢሆንም በሌሎች ተዋንያን መካከል ሚዛኑን ለመጠበቅ የተሰራ ስራ የለም። በተለይም የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ከሱዳን የሲቪል እንቅስቃሴ አዎንታዊ ግንኙነቱን በማስቀጠሉ ሊመሰገን ቢገባውም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሱዳኖች ለግብፅ ላይ ያላቸው አጋርነት አሳንሶ ጥላቻቸው እንዲጨምር አድርጎታል።
አላደረጉትም እንጂ ግድቡ በይፋ መሞላት ከጀመረ በኋላ በግድቡ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ጥቃት በራሱ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል በርካታ ምሁራን የገለጹት ጉዳይ ነው። በግድቡ ላይ ማንኛውም የወታደራዊ ጥቃት ሱዳን ውስጥ በሚገኙ የሱዳን ከተሞች እና መንደሮች መጥለቅለቅን በማስከተል የብዙ ህዝብ ህይወትን ሊያጠፋ የሚችለበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎችም ስጋታቸውን አሰምተዋል። ሆኖም ግን ይሁንና ወታደራዊ ጥቃት እንደማይኖር ብዙ ምልክቶች ታይተዋል፡፡
ወታደራዊ ጥቃት ሊከሰት እንደማይችል የሚጠቁመው ሌላው የግብፅ ወታደራዊ ኃይልን ወደ ሌላ ሃገር ለመላክ ከግብፅ ተወካዮች ምክር ቤት ከረጅም ሂደት በኋላ ፈቃድ ማግኘትን ይጨምራል። ይህ አልተደረገም። ከአለም የመገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው በተመሳሳይ ጉዳይ የግብፅ ወታደራዊ ኃይልን ወደ ሊቢያ ለመላክ ሲባል የግብፅ ተወካዮች ምክር ቤት የፈቀደው በብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነበረ። ይህ ሂደት በኢትዮጵያ ጉዳይ አልተደረገም። ( ወይም ስለመደረጉ ከአለም የመገናኛ ብዙሃን አልተሰማም)
ሌላው ወታደራዊ እርምጃ ማድረግ የሚያመጣው መዘዝ ግብፅ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በተለይም በናይል ተፋሰስ ውስጥ ካሉ አገሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት የምታደርገውን ጥረት ወደ ቂም ይቀየርና ብዙዎቹ ናይል ላይ ግድብ ለመስራት ይነሳሳሉ ብላ ትፈራለች። ከኢትዮጵያ የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ ከአፍሪካውያን ጋር ያላት የረጅም ዘመናት ትስስር፣ ከሱዳን የፖለቲካ ትርምስ፣ በአካባቢው ያሉ ውስብስብ ተግዳሮቶች ተጨምረውበት ግብፅ ወታደራዊ ሃይል መጠቀምን እንደ አማራጭ ከወሰደች ከፊት ለፊቷ ከባድ አለማቀፋዊ የዲፕሎማሲ ችግሮች እንደሚገጥማት ታውቃለች። ደቡብ ሱዳን በናይል ላይ ግድብ ለመስራት ፍላጎት ማሳየቷ ሱዳን በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት እንደምታጠናክር ይመስለኛል። ( ሱዳንን ተለዋዋጭ ባህሪ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡)
ስለዚህ የኢትዮጵያ ትኩረት በይበልጥ ወደ ሰሜን መሆን ያለበት ይመስለኛል። የወልቃይትም ሆነ የራያ ጉዳይ አሁን የአማራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ህልውና ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም በዲፕሎማሲ ጥበብ፣በውይይት በሰለጠነ መንገድ፣ የአካባቢውን ባህል አብነት በማድረግ ለመፍታት በዋነኝነት የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የታሪክ ሃላፊነት አለበት፡፡
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፣ የሱዳን አቻቸው በሌላ በኩል አንድ አይነት አቋም በመያዝ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን በመወከል ዶክተር ስለሺ በቀለ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ለአለሙ የጸጥታው ምክር ቤት የየሃገራቸውን አቋም አሰምተው ነበር፡፡ በተለይም የዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ንግግር ወይም ክርክር ልብ የሚነካ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እጠቅሰዋለሁ፡፡
‹‹ እየገነባን ያለነው የውሀ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም የጸጥታው ምክር ቤት ሀላፊነት ጸጥታን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ መምከር እንጂ የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድብን በሚመለከት መወያየት ባለመሆኑ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ህብረት ሊመለስ ይገባል – (ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ)
በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሊቱን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲመክር የሃገራቸውን የኢትዮጵያን አቋም ያስረዱት ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ምክር ቤቱም ከተመሰረተ ግዜ አንስቶ በግድብ ጉዳይ ሲመክር ይሄ የመጀመሪያው ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ልኡክ መሪ እና ተወካይ ሆነው የቀረቡት ሚኒስትሩ የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በልጆቿ ላብና ደም እየገነባችው ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። እንደ ህዳሴ ግድብ አይነት ፕሮጀክቶችን መገንባት ተሰደው ከሄዱበት ሃገር በባዶ እግራቸው የሚባረሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት የሚቀይርም ነው ብለዋል። ከዚህ ቁምነገር የምንረዳው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጥያቄ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የዳቦ ጥያቄ እንደሆነም ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተሞች ሳይቀሩ በቂ ዳቦ ማግኘት ያልቻሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የሶስቱን ሀገራት ወኪሎች ክርክር የሰማው የጸጥታው ምክር ቤት ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ምንም ሳይል ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት በመምራት የአፍሪካው ህብረት በሽምግልና እንዲፈታው ወስኗል፡፡ ስለሆነም የታላቁ አባይ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካውያን ጉዳይ መሆኑን በመረዳት የአረቡ ራቢጣ ማህበር ከኢትዮጵያ ላይ እጁን እንዲያነሳ በማስታወስ ልሰናበት፡፡