>
5:16 pm - Tuesday May 24, 8912

"እርምጃ ሊወሰድብን ነው ወይም ለሻዕቢያ አሳልፈው ሊሰጡን ነው ብለን ተስፋ ቆረጥን ነበር...!!!"  በእስር የቆዩት ጋዜጠኞች

“እርምጃ ሊወሰድብን ነው ወይም ለሻዕቢያ አሳልፈው ሊሰጡን ነው ብለን ተስፋ ቆረጥን ነበር…!!!”

 በእስር የቆዩት ጋዜጠኞች


*… ሰኔ 23፤2013 እኩለ ቀን አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋሉ የአውሎ ሚዲያ ሰራተኞች ብሎም በቀጣይ ቀናት እና ሰአታት የተያዙ የኢትዮ-ፎረም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች በአዋሽ ሰባት እንደሚገኙ ፖሊስ አስታውቆ ነበር።

እኛ ከገባን በሗላ ባሉ ሁለት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አዋሽ መጥተዋል። ጠዋት ጠዋት ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ተሰልፈው ሲገቡ አይተናቸዋል።  አስፋልቱ ላይ አንበርክከው ሲያንከባልሏቸው እና በዱላ ሲመቷቸው እያየን እናልፋለን። ዞር ብሎ ማየት ወይም የምናውቃቸውን ሰላም ማለት አንችልም ነበር። በባዶ እግር ነው የሚሄዱት፤ ጸጉራቸው ሲላጭ አይተናል። በእንብርክክም ያስኬዷቸዋል።

ለሁለት ቀናት ሜክሲኮ በሚገኛው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ለሁለት ቀናት በእስር ከቆዩ በሗላ «ፖሊስ ጠያቂ ቤተሰቦችን «ተፈተዋል እዚህ የሉም» የሚል መረጃ ከሰጠ በሗላ ያሉበት ሳይታወቅ ሳምንታት አልፈው ነበር።

ከታሰሩ 20 ቀን ቢሞላቸውም ያሉበት ባለመታወቁ ብሎም ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን ተከትሎ ነበር በጠበቃቸው አማካኝነት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ የመሰረቱት።

ይህንን ተከትሎ ነበር ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቦታ ጥበት ምክንያት ወደ አዋሽ ሰባት ወስዶ ማሰሩን ያስታወቀው። በአዋሽ ሰባት ከነበሩት የሚዲያ ሰራተኞች ውስጥ 10ሩ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዋስ ሲለቀቁ ቀሪ ሰባት ሰዎች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በእስር ቆይታቸው ወቅት ስለነበረው አያያዝ ቢቢሲ የአውሎ ሚዲያ ባልደረባ የሆኑትን ከክብሮም ሰለሞን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

እንዴት ታሰራችሁ?

እኔ የታሰርኩት በአውሎ ሚዲያ ስራ በጀመርኩበት በመጀመሪያው ቀን ነው። በፊት ትግራይ ቴሌቪዥን ነበር የምሰራው። በሗላ የአውሎ ሚዲያ ባለቤት የሆነውን አትሌት ገብረ እግዚያብሄርን አናግሬው በማህበራዊ ዘርፍ ተቀጠርኩ። የታሰርን ቀን ገና ሰራተኞቹን አስተዋውቆኝ ቁጭ ማለቴ ነበር።

ፖሊሶች እና ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰራተኞች በድንገት ወደ ቢሮ ገብተው እጅ ወደላይ አሉ እና ስልክ እና ላፕቶፓችንን ወሰዱ። እርስ በእርስ መነጋገር እንኳን አልቻልንም። ከዛም ይዘውን ወደ ሜክሲኮ ወሰዱን። እኛን ሲወስዱን ሁለተኛ ፎቅ ላይ ሆና ፎቶ ያነሳች አንዲት ልጅንም ጨምረው አሰሯት።

በጣም ደንግጠን ነበር። አሻራ ሰጠን ከዛም ፍራሽ አቀረቡልን። ምግብ እንዲገዛልን እዛው ያሉ ታሳሪዎች አደረጉ። አብዛኛው ታሳሪ የትግራይ ተወላጅ ነው። አንድ ወዲ ራያ የሚባል ሰዎችን የሚተባበር ሰው ነበር፤ ራት እርሱ አስመጣልን ከውጪ አስገዝቶ።

ከዛም አርብ ጠዋት አንድ ሰአት ላይ ይዘውን ወጡ። ሃሳባችን ፍርድ ቤት ይወሰዱናል ነበር። ከዛ ወደ ልደታ እንሄዳለን ብለን ስናስብ በአለም ባንክ አድርገው ሲወጡ ቃሊቲ ሊወስዱን ነው ብለን አሰብን። እጃችን በካቴና ታስሯል፤ መነጋገር አንችልም እንዲሁም የት እየወሰዱን እንደሆነ አልነገሩንም። ከቃሊቲ አልፈው ወደ ደብረ ዘይት በድሮ መንገድ ይዘውን ሲያልፉ ዝዋይ ሊወስዱን ነው ብለን አሰብን።

መኪናው በፈጣን መንገድ ገብቶ ከአዳማ ሲወጣ ግን እርምጃ ሊወሰድብን ነው ወይም ለሻዕቢያ አሳልፈው ሊሰጡን ነው ብለን ተስፋ ቆረጥን። ከዛም 220 ኪሎ ሜትር ከሄድን በሗላ አዋሽ ሰባት ኪሎ የፌደራል ፖሊስ የመካከለኛ አመራሮች ማሰልጠኛ አስገቡን።

የቆየነው ብሎክ አስር ውስጥ ነው። ቤቱ ደህና ነው። ሴቶቹ ግን አንድ መስኮት የሌላት ትንሽ ክፍል ውስጥ ለስድስት ነው ታፍገው የቆዩት። የእኛ ክፍል ‘ፋን’ም ነበረው።

ብዙ ግዜ ስለ አዋሽ የማሰልጠኛ ካምፕ አያያዝ አስከፊ ነገር ይሰማል። ባጠቃላይ ስለ አያያዙ ይንገሩን?

እዛ ከገባን በሗላ አንዳንዱ ፖሊስ መጥፎ ቃላት ይናገሩ ነበር። «እናንተን ማንከባለል ነው እዚህ፤ በሽመል ማለት ነው፤ መቀጥቀጥ ነው» እያሉ የሚያስፈራሩን ነበሩ። በአንጻሩ ደግሞ ልክ እንደ አዛዣቸው ያሉ ጥሩ ሰዎች ነበር። ኢንስፔክተር ተስፋዬ የሚባለው አዛዥ የአባትነት ፍቅር ነበረው። በተለይ ሴቶቹን «አይዟችሁ ልጆቼ። እኛ እዚህ ያለነው እናንተን ልንጠብቅ ነው። ምንም አትሆኑም» ይሉ ነበር።

ምግብ ዳቦ ብቻ ነው የሚፈቀደው። ጠዋት ዳቦ ከሻይ ጋር፤ ምሳ ላይ ሁለት ዳቦ ከሆነ ወጥ ከሚመስል ነገር ጋር ነው የሚሰጡን። የሚጠጣ ውሃ አናገኝም። የታሸገ ውሃም መግዛት አይቻልም። የተወሰኑ መልካም ፖሊሶች ከክበብ እየገዙ ያመጡልን ነበር። ከራሳችንም መመገብ አንችልም። ከውጪው አለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለም። ቤተሰባችን የት እንዳለን አያውቅም ነበር።

ቅያሪ ልብስ የያዘ ሰው የለም። በተለይ ለሴቶቹ ይህ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ገላ መታጠብም ሆነ የንጽህና እቃዎች ማግኘት አይችሉም ነበር። በተለይ ሁለት ሴት ፖሊሶች ሲናገሯቸው እንሰማ ነበር። በርግጥ ይህ ሰዎች የግል ባህሪይ ነው።

በማሰልጠኛው ውስጥ ከእናንተ ውጪ ሌሎች የታሰሩ ሰዎች አሉ?

እኛ ከገባን በሗላ ባሉ ሁለት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አዋሽ መጥተዋል። ጠዋት ጠዋት ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ተሰልፈው ሲገቡ አይተናቸዋል። እኛ የምንመገበው ትልቁ አዳራሽ ነበር። ወደ ትንሽ ጎጆ ተሸጋግረን እነሱ ትልቁ አዳራሽ መመገብ ጀመሩ። አስፋልቱ ላይ አንበርክከው ሲያንከባልሏቸው እና በዱላ ሲመቷቸው እያየን እናልፋለን። ዞር ብሎ ማየት ወይም የምናውቃቸውን ሰላም ማለት አንችልም ነበር።

በባዶ እግር ነው የሚሄዱት፤ ጸጉራቸው ሲላጭ አይተናል። በእንብርክክም ያስኬዷቸዋል።

ፖሊስ በፈንታሌ ወረዳ ችሎት አቅርቤ የግዜ ቀጠሮ አሰጥቻለሁ ሲል ለፌደራል ፍርድ ቤት ተናግሮ ነበር። ፍርድ ቤት ተወስዳችሁ ነበር?

ወደ ችሎት የወሰዱን ከታሰርን በሰባተኛው ቀን ነበር። ዳኛዋ ሴት ነበረች እና ሰባት ቀን ሙሉ አላቀረቡንም ብለን ስናስረዳት «መንገድ ሲያጓጉዙ ሊሆን ይችላል፤ ምንም ችግር የለውም» ብላ የ 14 ቀን ግዜ ቀጠሮ ፈቅዳለች።

ቀጥሎ ባለው ቀጠሮ የተሰየመው ዳኛ አዲስ ነበር። «ክሱ አሁን ስለደረሰኝ ምንም አላውቅም፤ የተጠየቀውን 14 ቀን ፈቅጃለሁ» አለ።

ከዛም በቀጣዩ ቀጠሮ ላይ ሴቶቹ በጣም እያለቀሱ ነበር። ሰውነታቸው በጣም ተጎሳቁሎ ነበር። ከዛ ዳኛውበመጀመሪያ ለታሰሩት 10 ቀን ፈቀደ።

በሁለተኛ ዙር ለገባነው ሴቶቹ ሲያለቅሱ ስሜታዊ ሆኖ ሰባት ቀን አለ። የፌደራሉ ፍርድ ቤት አካልን ነጻ የማውጣት ትዕዛዝ የፋኑኤል እህት እዛ ለችሎቱ አቅርባ ነበር።

በሶስቱም ቀጠሮ የቀረበው ክስ ይለያይ ነበር። የመጀመሪያው ክስ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጭት ነው። በሁለተኛው ክስ በአፋር እና በሶማሊ መሃል ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ነው የተከሰስነው።

በአፋር ያሉ ሌሎች ግብረ አበሮችን ለመያዝ እየሰራሁ ነው ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገልጾ ነበር። በሶስተኛው ግዜ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር ተያይዞ ክሱ ተለውጧል።

እንዴት ተፈታችሁ?

የምርመራው ግዜ ሲያልቅ ችሎቱ ማመልከቻ አስገቡ አለን። እኛም የምናሸሸው ማስረጃ የለም ብለን የዋስትና ማመልከቻ ይዘን ልንቀርብ ስንል ቀድመው በመኪና ይዘውን ወጡ።

ክስ ተቋርጦ ይሁን በዋስትና ምንም አልተነገረንም፤ በመኪና ይዘውን «አሁን ወደ ቤታችሁ ሂዱ፤ ሌላ ቀን መጥታችሁ ንብረታችሁን ውሰዱ» አሉን።

የተወሰነ ልብስ ለቀሩት ሰጥተን ነው የወጣነው። ያሉበት ሁኔታ በፊት በነበረበት ሁኔታ ነው። ጠበቃም ሆነ ቤተሰብ ማግኘት አልቻሉም።

በመገናኛ ብዙሃን ስራ ትቆያለህ?

አዎ! ሃቅ እስከሆነ፣ ሕዝቡን የሚበጠብጥ ወይም ወንጀል እስካልሰራን ድረስ በዚሁ ስራ መቆት ነው ፍላጎቴ።

ምንጭ:- መረጃ ዶትኮም

Filed in: Amharic