>

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ!! - ክፍል አራት (ዳንኤል ገዛህኝ)

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ!!

ክፍል አራት
ዳንኤል ገዛህኝ

 

ታምራት ላይኔ በሰረቀው ቡና ንጹሀን ወደ ወህኒ!!

ለቆጠራ አዋክበው እያስወጡን ሳለ በር ላይ ይጠባበቅ የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ተጠመጠመብኝ። ጋዜጠኛ ታምራት ዙማ ነበር። ሲበዛ ግዙፍ ነው ቁመቱ በጣም ረጅም ፈገግታ የማያጣው። ታምራት ዙማ በርካታ ጊዜ ታስሮዋል የታዋቂዋ አትኩሮት ጋዜጣ አሳታሚ ነው።
ታምራት ሰላምታ ከተለዋወጥን በሁዋላ ሳላስበው ከሰልፉ አፈንግጨ ኖሮ ከጀርባዬ የስነ-ስርአት ኮሚቴ ዱላ አረፈብኝ። ፈጠን ብዬ ከሰልፉ ተቀላቀልኩ። ታምራትም ከአካባቢው ራቅ ብሎ በምልክት አነጋገረኝ።
“ስትወጣ እዚሁ እጠብቅሀለሁ” ብሎኝ ከሰልፉ ራቅ ብሎ ይጠብቀኝ ገባ። ታምራት ከታሰረ ወራት ተቆጥሮዋል። የተጠየቀው የዋስትና ገንዘብ ከፍ ያለ ነበር 13.000 አስራ ሶስት ሺህ ብር ። በጊዜው የጋዜጦችም ህትመት አነስተኛ በመሆኑ ከገቢ አንጻር አሳታሚዎች አዘጋጆችን ገንዘብ አስይዘው ማስፈታት ይቸገራሉ። በወቅቱ ከአስራ ሁለት በላይ ጋዜጠኞች የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። በጊዜው የጎህ መጽሄት እና ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ሮቤል ምትኩ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ወቅት በጻፈው “መካሪ የሌለው ንጉስ ያለ አንድ አመት አይነግስ” አርቲክሉ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ገብቶዋል። ሌላው የታሪክ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እዮብ ደመቀ ወደ ከርቸሌ ቢወርድም ነገር ግን እኔ ወደ ከርቸሌ በገባሁበት ቀን ዋስትና አልቆለት ቢፈታም ነገር ግን የመንግስት ደህነቶች ከርቸሌ በር ላይ ጠብቀው ወደሌላ ወረዳ እስር ቤት አፍነው እንደ ወሰዱት ሰምቻለሁ። ሌሎቹ ለአመታት በወህኒ ቤት የቆዩት የኡርጂ ጋዜጣ አዘጋጆች እነ ታምራት ገመዳ፣ ሰለሞን ነመራ ፣ የፈታሽ ጋዜጣ አዘጋጅ ጥላሁን ይግለጡ ናቸው። ወቅቱ ለነጻው ፕሬስ ፈታኝ የፈተና ወቅት ነበር።
ቆጠራችንን አጠናቀን ወደ ውስጥ እንድንገባ ተደረግን። ሻይ በትልቅ ብረት ድስት ከጎኑ ደግሞ በጆንያ የተሞላ ጠቆር ያለ ዳቦ  ደገሎ ይሉታል ተጠቅጥቆ ተቀምጧል።
እዛችው ደቦቃ የተኛሁበት ስፍራ ሄጄ ተቀመጥኩ። የምግብ ኮሚቴው ከአዳዲስ እስረኛዎች ረድፍ በሰልፍ አስነስቶ ወደሻይ እና ዳቦ መቀበያ ስፍራ መራን። በአንዲት አነስተኛ ፕላስቲክ ኩባያ ሻይ ተደረገልኝ አንድ ክብ ጠቆር ያለ ዳቦ ተሰጠኝ። የተሰጠኝን ይዤ ከቦታዬ ተመለስኩ። ሻዩን ቀመስኩት በቂ ስኳር የለውም ግን ቢሆንም አልጠላሁትም። ደጋግሜ ከሻዩ ተጎነጨሁ። ዳቦውን ገና መልኩን ሳየው ለመብላት አፕታይት ሰላላገኘሁበት ከጎኔ ላለው ልጅ ሰጠሁት እጅግ ተደስቶ ተመገበው። ቁርስ በልተን ሳናጠናቅቅ አንድ መመርያ ተላለፈ።በተለይ ለአዲስ እስረኞች። የግዴታ ስራ እንዳለና ወደስራው ስፍራ የሚኬደው በባዶ እግር መሆኑ ተነገረን ።
የዚህን ጊዜ ደነገጥኩ ከስራው ይልቅ በባዶ እግር ያለጫማ መሆኑ አሳሰበኝ። ቢሆንም ግን ለጊዜው ነበር ግራ የተጋባሁት። ሲያወራኝ ያደረው ልጅ ራሱ መፍትሄውን አመጣው። “ስራ መስራት የማትፈልጊ ከሆነ ሰራትኛ መቅጠር ትችያለሽ…”
ሰራተኛ መቅጠር የሚለው አባባል ግራ አጋባኝ እና ማለት እንዴት ነው የሚቀጠረው …
“በአንድ ብር ስው ትቀጥሪያለሽ በቃ አንቺ ስራ አትሰሪም ማለት ነው”
አንድ ብር ከኪሴ አወጣሁ … አንድ ብሩን ከእጄ ላይ መነተፊኝ እና ሙሉ ስሜን ጠየቀኝ። ነገርኩት። ስሜን አስመዝግቦ በኔ ቦታ ሊሰራ ሄደ።
ይሁን እና በቂ የሰው ሀይል ባለመገኘቱ አንዱ የስነ-ስርአት ኮሚቴ “ስራ በፍላጎት… ስራ በፍላጎት” እያለ መጣራት ሲጅምር ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርከት ያሉ ወጣቶች ተግተልትለው ወጡ። ስራ በፍላጎት ምን አይነት ስራ እንደሆነ ከአጠገቤ ያለውን ሌላውን እስረኛ ጠየቅኩት።
” ብዙ ግዜ የጽዳት ስራ ነው ግን የተለያዩ ስራዎች አሉ “
ታዲያ በፍላጎት ማለት ምን ማለት ነው ክፍያ አለው?
“ወይ ክፍያ! ትቀልዳለህ?”
እረ አልቀለድኩም…እንዳው ገርሞኝ ነው
“ዋናው ቁምነገር ለስራ የምትሰማራበት የእስር ቤቱ ስፍራ ውጭውን አሻግሮ ያሳያል ስለዚህ የናፈቀህን ለማየት የጉልበት ስራ ለመስራት በፍላጎት ትሄዳለህ ማለት ነው።
የቁርስ ሰአት አብቅቶ በር ሲከፈት ከእስር ቤቱ ክፍል መውጣት የማይፈቀድላሸው በግብረሰዶም ተግባር የተያዙ ለምግብ እና መጸዳጃ ለመግባት ብቻ የሚፈቱ እጅና እግራቸው በሰንሰለት ከታሰሩ እስረኞች በቀር ሌላው ከአንድ ስታድየም ብዙ ከማይሰፋው የከርቸሌ አጥር ውስጥ ለመንቀሳቀስ በአስሺዎች የሚቆጠር እስረኛ ይተራመስ ገባ እኔም ተቀላቀልኩኝ። ታምራት ከትንሿ ሻይ ቤት ቀጥሮኝ ነበር ወደዝያው አመራሁ ሻይ እየጠጣን ፓስቲ እየበላን የባጥ የቆጡን ስናወራ ቆየን።
የምሳ ሰአት ሲቃረብ ከቤተሰብ ምግብ ተቀበልኩ። መኝታ ከሚካፈሉኝ ጠያቂ የሌላቸው ልጆች ጋር አብሬ ተመገብኩ። ከርቸሌ ውስጥ ሀብታም አለ ደሀ አለ። ሀብታም ቢሉ ሀብታም ብቻ አይደለም። የሚፈልገውን ሁሉ ወደ እስር ቤት ያስገባል። ምንም የሚቀረው ነገር የለም። በታማኝ እስረኝነትም ጠዋት የወጣ እስከ ምሽት አስራ ሁለት ሰአት ድረስ  ወደ ከተማ ወጥቶ ያሻውን ሲያደርግ ያመሽ እና ወደ እስር ቤት ይመለሳል። የገዛ ሰራተኛውን በቅልብ ውሻው አስነክሶ በጥይት ደብድቦ ከገደለ በሁዋላ የተወሰነበትን እስራት በይግባኝ ተቃውሞ ሲከራከር ይበልጥ እስራት የተላለፈበት የጋራድ ባለ ንብረት ለእስረኛው ከርቸሌው ውስጥ መታሰርያ ሰንሰለት እና ቁልፍ ገዝቶ ያቀርባል። እስረኛው በዚህ ሲከፋ በሬ ያርድለታል። ከርቸሌ በየ መታሰርያ አዳራሽ ዙቤር የገዛው ቴሌቭዥን አለ። ነገር ግን ቴሌቭዥን ከሚጀምርበት ከምሽት አስራ ሁለት ሰአት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት የኢቲቪ ስርጭት እስከሚያበቃ ድረስ በወቅቱ የነበረውን ተጨማሪ ቻናል፣ ቻናል አፍሪካን ማየት አይፈቀድም።
ከርቸሌ ሰላይ አለ የመንግስት ወሬ አቀባይ። ከርቸሌ ውስጥ መታሰር አለ መካከለኛ አጥፊ፣ ሌባ፣ ተደባዳቢ ይታሰራል። መጀመርያ ከእስር ክፍል ያለመውጣት። ጥፋቱ ከፍ ካለ ሁለት እጆቹን በሰንሰለት ቁልፍ መታሰር። በጣም አደገኛ አጥፊ ስው ላይ ጥቃት የሚያደርስ የግብረ ሰዶም ተግባርን ይጨምራል እጁም እግሩም በሰንሰለት ይቆለፋል።
በተለይ የግብረ ሰዶም ተግባር ፈጻሚዎች ከርቸሌው በሚገኝበት ወረዳ ፍርድ ቤት በዝግ ችሎት እንደሚዳኙ ሰምቻለሁ። ይሁን እና በከርቸሌ በነበርኩበት ወቅት ከሀያ ሰባት በላይ የግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች በምስክር የተያዙ ያየሁ ሲሆን ሶስት እንደተገደሉ ሰምቻለሁ።
በሶስቱም ተግባር እስረኛው በማዘኑ ሁለቱን ስኳር በጥብጦ ገላቸውን በመቀባት ጸሀይ ላይ በማቆየት አሰቃይተው ደብድበው ገለዋቸዋል። ሶስተኛው የተገደለበት መንገድ በስለት በእንጨት መፈልፈያ እና ቅርጽ ማውጫ ሰውነቱን በአሰቂ ሁኔታ ወጋግተው ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ጥቃት አድራሾች ፊታቸውን በጨርቅ በመሸፈን   ሲሆን ከግብረ ሰዶም ተግባሩ ባሻገር በብዙዎች ላይ የኮሚቴነት ስልጣኑን ተጠቅሞ ስቃይ በማድረሱ ነው።
የሚያሳዝነው ነገር ግብረ ሰዶም የሚፈጸምባቸው ህጻናት መሆናቸው ነው። ለድርጊቱ እንዲጋለጡ የሚያደርጋቸው በቂ ምግብ አለማግኘት፣የሲጋራ ሱስ የማያገኙትን ነገር ለማግኘት ሲሉ አካላቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ።
እስር ቤቱ ውስጥ ይህንን ተግባር መፈጸም ክልክል በመሆኑ የመጸዳጃ ቤት በር በመዝጋት ነበር የሚፈጽሙት በሁዋላ አንድ ሁለት ሰዎች ሲደረስባቸው በግምገማ ፣ በአውጫጭኝ እስከ ሃያ ሰባት ፈጻሚዎች ሲያዙ የመጸዳጃ በሮች ተገንጥለው ክፍት እንዲሆኑ ተደረጉ። ከዚያ ውስጥ የአእምሮ ጉዳት ያለባቸውም አሉ። ይህንን ሁኔታ በማየት ምንም አይነት የሰነ-አእምሮ የምክር አገልግሎት ድጋፍ አይደረግላቸውም። በተለይ ድርጊቱ የሚፈጸባቸው ወጣቶች ምንም ህክምና ድጋፍ አያገኙም ። ህብረተሰቡን ሲቀላቀሉ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ሳይሆን የዚህ አይነት ተግባር እንዲስፋፋ የሚፈልግ አካል እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ከርቸሌ ውስጥ ብዙ ትውልድን የሚጎዱ ተግባሮች ቢኖሩም ጉዳዬ የሚል አካል አልነበረም። እስር ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባሮች በመንግስት የሚደግፉ ናቸው። እርግጥ እስር ቤቱ የሚተዳደረው በመንግስት ይሁን እንጂ ከትልቁ ዋናው የግቢው አጥር ለጥቆ ሁለተኛ አጥር አለ። ከሁለተኛው አጥር በሁዋላ የመንግስት ወታደሮች ወደ እስር ቤቱ አያልፉም ፈላጭ ቆራጮቹ የእስረኛ የስነ-ስርአት ኮሚቴዎች ናቸው። ምግብ ባይስማማኝ፣ ብታመም፣ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙኝ የመንግስትን አቋም የማልደግፍ ሰው ከሆንኩ ጥያቄዬ መልስ የለውም።
ዘውትር ማክሰኞ ትልልቅ ግምገማዎች ይካሄዳሉ። እነዚህ ግምገማዎች የወያኔው አብዮታዊ ዲሞክራሲ እርቃኑን የሚታይበት ነው። ዝርዝሩ ሰፊ ነው ፓለቲካ ማውራት በተለይ መንግስትን መቃወም ብዙ ስቃይ ይጋብዛል።
በሳምንት  እስር ቤቱን ማህበረሰቡን ተላመድኩኝ። ነገር ግን  በእስረኞች ስነ-ስርአት እና የቤት ድልድል ኮሚቴ አሰራር መሰረት አንድ አዲስ እስረኛ ለአስራ አምስት ቀን ከአዳራሹ መሀል ራስ በእግር ተሰባጥሮ መተኛት ግዴታ ነው።
ደቦቃ፣ አስመራ ድርድር ይሉታል። ያ የሌሊት አስተኛኝ አልተመቸኝም። በመጀመርያው ቀን ሁለቱንም ኩላሊቴን ታመምኩኝ። ደረቴን አፍኖ ያዘኝ። ስተነፍስ ጥሩ ያልሆነ ድምጽ ይሰማኛል ፣ ያስለኛል ፣ወደሰማያዊነት የሚያደላ አክታ ካሳለኝ በሁዋላ ከደረቴ ይወጣል ። በወቅቱ የህክምና ኮሚቴ ለነበረው በሁዋላ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ይኖር የነበረው በትረ ጋር ቀርቤ መታመሜን ነገርኩት። ስክሪን ይሉታል። ስክሪን የከርቸሌው ሀኪም ዘንድ ቀርቤ ለመታየት መድሀኒት ለማግኘት ብሞክርም በትረ ግን ለስክሪን ሳያሳልፈኝ ቀረ። ደጋግሜ ሞከርኩ በትረ በመታመሜ ሳያምንበት ቀረ። ከእስር ወጥቼ ከብዙ ጊዜ በሁዋላ በትረን በተደጋጋሚ አገኘው ነበርን
እኔ ግን በጣም ታመምኩ። አብዛኛዎቹ ልጆች እስረኞች ከጎዳና ታፍሰው የመጡ ናቸው አብረን ሳምንት ከረምን። በሳምንቴ ግን እዚያ ደቦቃ ውስጥ እንዳልተኛ የሚያደርግ ክስተት ገና ከማለዳው ጀመረ። የቢቢሲ ፎከስ እን አፍሪካ፣የድምጺ ሀፋሽ ሬድዮ፣ ጀርመን ድምጽ ፣ በስተመጨረሻ ለእንቅልፍ ስንዘጋጅ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞችን እስራት የሚተነትን የታፈሰ ክፍሌ ሰፊ ዘገባ የኔም ስም ተጠቅሶ ተሰራ።
 ዘገባው እንዳለቀ የታሳሪዎችን ቀይ ካርድ ኦራንት የሚይዘው የስነስርአት ኮሚቴ በርካታ ካርዶችን ይዞ ከባልደረቦቹ ጋር ሆነው  ወደተደረደርነው የደቦቃ መኝታ ስፍራ መጡ እና …
“ዳንኤል ገዛኽኝ ማነው ?”
አለኝ አንደኛው…
እኔ ነኝ አልኩት…በጎኔ ደቦቃው ውስጥ ተቀርቅሬ አንገቴን አቅንቼ ላየው እየሞከርኩ…
“አዝናለሁ!…በጣም አዝናለሁ!…ተነስ እስቲ…”
ተነሳሁ እና ቆምኩኝ…
“ሳምንት ሙሉ እዚህ ውስጥ ስትተኛ ለምን ለአንዱ ስነስርአት አልተናገርክም?”
ምንም ሳልናገር አቀቅሬ ቀረሁ።
ኮሚቴዎቹ ተነጋገሩ እና በሁዋላ እንደተረዳሁት አንድ የቀይ ሽብር ተከሳሽ አቶ ታደሰ የሚባሉ ከባሌ የመጡ፣ የኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ጥበቃ አቶ ጸጋዬ እንዲሁም የሜታ ቢራ ዘረፋ ጋር በተያያዘ የተከሰሰው ወጣት ዳዊት እነሱ መሀል ሶስት አራት ፍራሽ ደረርበው ከተኙት አንድ አንድ ተቀንሶ ሶስት ፍራሽ ተደራርቦ ቦታ ተሰጠኝ።
ቀይ መስቀል ለእየ አንዳንዱ እስረኛ ፍራሽ እና ብርድልብስ ይሰጣል ስርአቱ ግን ያስቀረዋል።
ከመተንፈስ ችግር ከህመም ጋር እየታገልኩ አራት ሳምንታት ቆይቼ በመጨረሻው ቀን የእስር ቤቱ ግቢ ይታመስ ገባ። እስረኞችን ከክፍል ክፍል ማቀያየር ። እኔም ጓዜን ይዤ እንድወጣ ተነገረኝ። ጓዜን ይዤ የገባሁበት ቤት ጋደም ብዬ የጀመርኩትን መጽሀፍ እያነበብኩ ሳለ …
“ዳንኤል ገዛኽኝ …እቃህን ይዘህ ውጣ ተባልኩ ከመጽሀፎቼ በቀር ያለኝን ለእስረኞች አከፋፍዬ ወጣሁ።
ከየክፍሉ የወጡ ተፈችዎች ወደተኮለኮሉበት ቢሮ ደጃፍ ደርሼ ተራዬን ስጠባበቅ አስገራሚ ብዙ ጉድ ሰማሁ።የሚዘረዘረው የክስ አይነት ሀገራችን ይህ አለ ? ያሰኛል። ተፈቺው ሲገባ የሰጠውን መረጃ ጫፍ ይሰጠዋል ቀሪውን ይተነትናል። የወላጆች ስም ሲጠራ የአባት እና አያት ስም ይናገራል በስተመጨረሻም የተከሰስክበት ወንጀል ሲባል ብዙዎቹ ለመናገር ሲያንገራግሩ አይቻለሁ። የእኔም ተራ ደርሶ የተጠየቅኩትን መልስ ሰጠሁ በስተመጨረሻም የተከሰስክበት ወንጀል ለሚለው ጥያቄ አቃቤ ህግ በከሰስን መሰረት ሀሰተኛ ወሬ በጋዜጣ ማሰራጨት ብዬ የእስር ሰርተፊኬቴን ተቀብዬ ወህኒ ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ።
ውጭ ከሚጠብቀኝ መፈቻዬን ይዞልኝ ከመጣው ከኤልያስ ጉዲሳ ጋር ተያይዘን በሱ መኪና ወደቤቴ እብስ አልኩኝ። በወቅቱ እሰራበት የነበረው ጋዜጣ አሳታሚ አሁን ስዊድን ሀገር ይገኛል አቶ ሰለሞን ንጉሴ የዋስትናውን ግማሽ ያህል ገንዘብ ከፍሎ ዋስትና አስይዞ እንድፈታ አድርጎኛል። ይሄ ሁሉ ሲሆን ዛሬ ለኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ሊሆን ደፋ ቀና የሚለው የቡና ሌባው ታምራት ላይኔ በወቅቱ እስር ቤት ነበረ። ይኽው ክስ እስከ ምርጫ 97 ዋዜማ በክርክር ቆይቶ ለፍርድ ውሳኔ በተቀጠረበት የመጨረሻ ቀጠሮ ሌሎች ወደ ሰባት የሚደርሱ ለፓሊስ ቃል የሰጠሁባቸው  እንደሌባ አሻራዬን ቃሌን ለፓሊስ የሰጠሁባቸውን፣ ፍሬሽ ክሶች ወደሁዋላ ትቼ ሀገር ለቅቄ የመን ገባሁ።
አበቃሁ።
Filed in: Amharic