>

መዝገቡን ፍለጋ - ጉዞ ወደ መዝገቡ ከተማ!! (ፍስሀ ጌትነት)

መዝገቡን ፍለጋ – ጉዞ ወደ መዝገቡ ከተማ!!

ፍስሀ ጌትነት

 ግራጫ ቃጭሎች:-
ብርዱ አንጀት ድረስ ዘልቆ ይሰማል፡፡ ጧትና ማታ የሚነፍሰው ቀጭን ነፋስ (ለእኔ ቀጭን ይመስለኛል) ቆዳን ሰርስሮ ወደ ውስጥ ይገባል፡፡ ልብስ መደራረብ ግዴታዬ ነው፡፡
በቲሸርት ላይ ሸሚዝ፣ በሸሚዝ ላይ ሹራብ፣ በሹራብ ላይ ጃኬት በዚያ ላይ ደግሞ ጋቢ መደረብ ይኖርብኝ ነበር፡፡ (አብዛኛው ሠው የሚያደርገው እንዲያ ነው) እኔ ግን ጥሎብኝ ብዙ ልብስ መደረብ አልወድም፡፡ ነፋሱን በጀግንነት መጠጣት እመርጣለሁ፡፡
ነፋስ የተወለደው በዚህች ከተማ ነው፡፡ ከተማዋ ስሟን ያገኘችው ከነፋስ ነው፡፡ ነፋስ መውጫ ትባላለች፡፡ የመዝገቡ ከተማ ማለት ይህቺ ናት፡፡ መዝገቡን አወቃችሁት? ካላወቃችሁት ግድ የለም፡፡ አዳም ረታ – በግራጫ ቃጭሎች፣ ገጽ 9 ላይ፣ መዝገቡ ራሱን እንዲህ በማለት ያስተዋውቃችኋል፡-
‹‹ሲወለድ የተረገመ ነው ሲሉኝ እሰማ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ጊዜ ጭር ያለ ሜዳ ላይ የራሴን ስም ከፍ አድርጌ ጠራሁ፡፡
‹መዝገቡ!! መዝገቡ!›
‹‹መ!ዝ!ገ!ቡ!›› የሚገርም ስም ነው፡፡ መዝ-መዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡ መዘዘኛ ለማለት፡፡ ገ-ገጣባ፡፡ ቡ-ቡቃያ፡፡ ሲጠቃለል መዘዘኛ የሆነ ገና ከአሁኑ የተገጠበ ቡቃያ፡፡ ካልጠፋ ስም ይሄን ይሰጡኛል? ሌላ ሌላ ጠፋ እንዴ!? ለምን ‹‹እግዚሃር›› ብለው አይጠሩኝም ነበር? እሱ እንደኔ ተቀምጦ ከማየት ሌላ ምን ሠራ? …››
‹‹…ብዙ ሠዎች የፀሀይን መውጣት ቤታቸው ውስጥ ሆነው ይጠብቃሉ፡፡ በአልጋዎቻቸው አፎት ውስጥ እንደ ሰይፍ ተወሽቀው ዐይኖቻቸውን የንጋት ውጋገን ውስጥ በልጥጠው በሙቀት የሙዋሙዋ ቆዳቸውን እየዳበሱ፣ ወይም የሚስለመለሙ አይኖቻቸውን ጨምድደው ገላቸውን በእርካታ እያከኩ፣ በእነሱ እምነት በመኖር ፍትወት ታስረው … የእንቅልፍ ሰንሰለታቸውን ሰብረው ለመነሳት በሰመመን ሲንደፋደፉ፡፡
‹‹እኔ እጅግ በጠዋት አንድ እድሜ ያነገላት የካኪ ጃኬቴን ደርቤ ከተማዬ መሃል ካለች አንዲት ትንሽ ጉብታ ላይ እተተከለች የስልክ እንጨት ስር ሄጄ እቀመጣለሁ፡፡
‹‹ግራና ቀኝ አይኖቼ ብብት አተር የሚያካክሉ ዓይን አሮች፣ ከአንደኛው የአፌ ጥግ ምናልባት የቀኜ (ፊቴን ወደ መስኮት አዙሬ በቀኝ ጎኔ ስለምተኛ) ወደተዘጋው … ብዙ ነገር መስማት ወዳላማረው ጆሮዬ የሚቃጣ የልጋግ ሰንበር፡፡ ሰፍሳፋ የጠዋት እግሮቼ ሁሉን ነገር በቀስታና በፍርሀት ይረግጣሉ፡፡
‹‹አልጋዬ ውስጥ በቡልኮ የተሟሟቀችውም ቂጤ እዚያ እርጥብ ቀዝቃዛ ሳርና አፈር ላይ ስታርፍ ጮቄው የሚፈጥረው ውጋት በአሰርሳሪዬ አልፎ ማጅራቴን ይሰማኛል፡፡ ግድ ሰጥቶኝ ግን አያውቅም፡፡ መጠበቅ እፈልጋለሁ፡፡ ፀሃይ ስትወጣ ፀዳልዋን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ …›› (ግራጫ ቃጭሎች፣ ገጽ 1)
መዝገቡ ከብዙ በጥቂቱ ይሄ ነው፡፡ መደበኛ ስራው አላፊ አግዳሚውን መታዘብ የሆነ (በትርፍ ጊዜው የእንጀራ እናቱን ዱላ የሚጠጣ)፣ እድሜው አስራ ሶስት አመት የሆነ፣ አንዳንዴ እንደ ፈላስፋ የሚያደርገው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አዕምሮውን የሳተ የሚመስለን፣ በቤተሰቦቹና በነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ እንደ ጅላጅል የሚቆጠር ልጅ ነው – መዝገቡ፡፡
ለኔ ደግሞ መዝገቡ ማለት የአዳም ረታን አስተሳሰብ ከአቅሙ በላይ የተሸከመ የሀሳብ ኩሊ ይመስለኛል፡፡ አንድ ትንሽ ልጅ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚያ ነው ነፋስ መውጫ ከተማን እየዞርኩ ‹‹መዝገቡን ያያችሁ?››  እያልኩ የጮህኩት፡፡
የመዝገቡ ከተማ ነፋስ መውጫ በደቡብ ጎንደር መስተዳደር ዞን ውስጥ ካሉ ከተማዎች መካከል አንዷ ስትሆን፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ደሴ በባህርዳር በኩል የሚሄድ ተጓዥ የወሎን ምድር ከመርገጡ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የሚያገኛት ከተማ ናት፡፡
ነፋስ መውጫ ከአዲስ አበባ ያላት ርቀት ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል (ግምት ነው)፡፡ ከባህርዳር ደግሞ በ170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተመስርታለች፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተለያዩ ታላላቅ ሠዎች ጋር ተያይዞ ስሟ ይነሳል፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ ታማኝ ጄኔራል የሆነውና ከሃያላኖቹ የኢትዮጵያ ጦረኞች መካከል ስሙ የሚጠራው ፊታውራሪ ገብርዬ የዚያ አካባቢ ሰው ነው፡፡ ብርሃኑ ዘሪሁን በጻፈው “የታንጉት ሚስጥር” የተሰኘ ታሪካዊ ልቦለድ ላይ ይሄንን ጠቅሶት አንብቤያለሁ፡፡ ስለ ነፋስ መውጫና አካባቢው ታሪክ የሚያውቁ ሠዎችም ገብርዬ የዚህ አካባቢ ሰው እንደሆነ ነግረውኛል፡፡
የዜማ ፈጣሪው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ካስተማረባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ከነፋስ መውጫ በቅርብ ርቀት የሚገኝና አስገራሚ ቦታ ላይ የተቀመጠው ዙር አምባ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ወደ ዙር አምባ ሲያቀና የዚህችን ከተማ አፈር ረግጦ ነው ያለፈው (ምንም እንኳን ከተማዋ በዚያ ዘመን ባትኖርም)፡፡
ደራሲው አዳም ረታ ስለ ነፋስ መውጫ የሚያውቀው ከሠዎች የሠማውን ነው፡፡ ግራጫ ቃጭሎችን የሚያህል ትልቅ ልቦለድ የጻፈው ሀይለኛ ምናቡንና የሠማቸውን ሽርፍራፊ ሃሳቦች ተጠቅሞ ነው፡፡
ነፋስ መውጫ የምትባል ከተማ ስለመኖሯ የማያውቅ ሰው መጽሐፉን ሲያነብ የአዳም ምናብ የፈጠራት ሃሳባዊ ከተማ ልትመስለው ትችላለች፡፡ ግን አይደለችም፡፡ ነፋስ መውጫ ህያው ናት፡፡
ነፋስ መውጫ በውስጧ ሰው የሚንቀሳቀስባት (አብዛኛው ጋቢ የለበሰ)፣ ወደ ጅቡቲ የሚጓዙና ከጅቡቲ የሚመጡ ትልልቅ መኪናዎች የሚመላለሱባት (በአብዛኛው ነዳጅ የሚጭኑ) ኢንተርናሽናል ከተማ ናት፡፡ መዝገቡ የዚህች አለም አቀፍ ከተማ ነዋሪ ሆኖ የተቀረጸ ገፀ ባህሪ ነው፡፡
የመዝገቡ ከተማ። ነፋስ መውጫ፡፡ መዝገቡ ዱባለ በማትደክም ቂጡ ጉብታው ላይ ተቀምጦ የሚያልፍ የሚያገድመውን የሚታዘብባት ከተማ። “ናና” ከረሜላን በፍቅር ያጣጣመባት ከተማ። ወሰን የለሽን ጨረቃ ላይ አስቀምጦ ያየባት፣ ስለህይወት የተፈላሰፈባት ከተማ፡፡
አሁን፣ ነፋስ መውጫን ስናስብ፣ በጓዳ ጎድጓዳዋ ውስጥ ተመላልሰን መዝገቡ ዱባለን እንፈልጋለን፡፡ የመጀመሪያ ስራችን መዝገቡ ቁጭ ብሎ ይታዘብበት የነበረውን ጉብታ ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡ በግራጫ ቃጭሎች መጽሐፍ መዝገቡ በተቀደደ ሱሪው ቅዝቃዜ ሳይበግረው ተቀምጦ ስለሚውልበት ጉብታ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹እጅግ በጠዋት አንድ እድሜ ያነገላት የካኪ ጃኬቴን ደርቤ ከተማዬ መሃል ካለች እንዲት ትንሽ ጉብታ ላይ ከተተከለች ስልክ እንጨት ስር ሔጄ እቀመጣለሁ…
‹‹ዙሪያዬን የአቡዋራና የድንጋይ ሜዳ ነበር፡፡ የሜዳውን ክፈፍ ከተወለድኩ ጀምሮ ትልቅ እስከምሆን ድረስ ምናቸውም ያልተለወጠ የቆሻሻ ጭቃ ቤቶች ሰልፍ ይዞሩታል፡፡ በአራት ማዕዘን ክትር የተለያዩ አይነት ሱቆች፣ መጠጥ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶች ተደርድረዋል፡፡ በሮቻቸው ሁሉ ወደ መሃል ያፈጠጡ ናቸው፡፡
‹‹በግራ በኩል ያሉት ብዙዎቹ የእህል መሸጫዎች ናቸው፡፡ ከየመሃሉ መደርደሪያቸው በከፊል የተራቆተ የሚሸጡት ግን የማያጡ ሱቆች አሉ፡፡ በስተላይ ቀጭን መንገድ ነበረች፡፡ ወደ ሰሜን ሆቴል የምትወስድ፡ …›› (- ግራጫ ቃጭሎች ገጽ 1-2)።
የመዝገቡን ጉብታ ለማግኘት እንደ ትልቅ ፍንጭ የሚጠቅመኝ ሰሜን ሆቴል ነው፡፡ ይህ ሆቴል ከነፋስ መውጫ የአውቶብስ መናኸሪያ ፊት ለፊት የሚገኝ ዝነኛ ሆቴል ነው፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሆቴል ጣይቱ እንደሆነው ሁሉ፣ በዚህች ከተማ ደግሞ የመጀመሪው ሆቴል ነፋስ መውጫ ሆቴል እንደሆነ ይገመታል፡፡
ይህ ሆቴል ከሰሜን ሆቴል ዝቅ ብሎ የሚገኝ ሲሆን የተገነባው ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ነው ይባላል፡፡ ንብረትነቱም የመንግስት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሆቴልነት ወደ መስሪያቤትነት ተቀይሯል፡፡
ከሰሜን ሆቴል ተነስተን በመጽሐፉ የተጠቀሰውን አቅጣጫ ተከትለን ጥቂት ሜትሮች እንደተጓዝን (ምናልባት 300 ሜትር) ማንን እናገኛለን? ብሶት አደባባይን፡፡ ብሶት አደባባይ! ጉድ እኮ ነው።
ይህ ቦታ የነፋስ መውጫ እምብርት ነው፡፡ የነፋስ መውጫ ፒያሳዋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው የሚታዩት በዚህ ቦታ ነው፡፡ መጠጥ ቤቶች በብዛት ያሉት በዚያ አካባቢ ነበር፡፡ ሰዎች ተሰባስበው ብሶታቸውን እርስ በርሳቸው ይለዋወጣሉ፡፡
በዋናነት ግን ይህ ቦታ “ብሶት አደባባይ” የተባለው የቸገራቸው ሰዎች ጎራ የሚሉበት በመሆኑ ነበር፡፡
አንዲት ወይዘሮ ለበዓል መዋያ ገንዘብ ቢቸግራት መጀመሪያ ወደ አዕምሮዋ ብቅ የሚለው ብሶት አደባባይ ነው፡፡ ቤቷ ያፈራውን ነገር አዘጋጅታ እንጀራና ወጥ ይዛ ወደ ብሶት አደባባይ ትሄዳች፡፡ በዚያ ለዕለት የሚሆን ምግብ የባሳቸውና በርካሽ ዋጋ ምግብ መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች ይጠብቋታል፡፡ የያዘችውን ሽጣ የምትፈልገውን ብር ይዛ ትመለሳለች፡፡
በብሶት አደባባይ የማይሸጥ ነገር የለም፡፡ የተቀቀለ ድንች በሚጥሚጣ፣ ደረቅ እንጀራ፣ የተለያየ አይነት ወጥ፣ ሻይና ዳቦ፣ ቆሎ (በአብዛኛው የገብስና የባቄላ)፣ ወ.ዘ.ተ በብሶት አደባባይ የማይጠፉ ዋና ዋና የምግብ አይነቶች ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ ግን የነበረው ከረዥም አመታት በፊት ነው፡፡
አሁን ወደ ብሶት አደባባይ ሲያቀኑ፣ ጆተኒ እና ቴኒስ የሚጫወቱ ታዳጊዎችን ነው የሚያገኙት፡፡ በርግጥ አልፎ አልፎ ምሽት ላይ ዳቦና ቅቅል ድንች የሚሸጡ ሰዎችን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ስሟ ግን አልጠፋም፡፡ ብሶት አደባባይ!
መዝገቡ ዱባለ ጫማ ባላደረገ እግሩ ከተመላለሰባቸው የነፋስ መውጫ መንገዶች መካከል አንዱ በሆነው ምናልባትም ከጉብታው አቅራቢያ በሚገኘው ብሶት አደባባይ ላይ ብዙ ጩኸቶች ተሰምተዋል፡፡
በግራጫ ቃጭሎች መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸውና መዝገቡ ስማቸውን የዘነጋቸው፣ እንዲሁ በደፈናው ‹የፀሀይ እናት›  እየተባሉ የሚጠሩ ሴት በከተማው አስተዳዳሪ ላይ ጩኸታቸውን ያሰሙት ብሶት አደባባይ ላይ ቁመው ይመስለኛል፡፡
‹‹ንጉሥ ዙፋን እቀርባለሁ፡፡ ንጉሥ ዙፋን ቀርቤ አንድ የነፋስ መውጫ ወደላ አቅሙን ተጠቅሞ የሴት ልጅ ደፈረ ብዬ፡፡ አለቅህ፡፡ እኔም አልወለድኩም፤ አንተም አላበላሸህም፡፡ ከቴም አክብሩኝ፡፡ አክብረናችሁ ስንሰግድ ቀና ከማለታችን ሴት ልጆቻችንን ትነጥቃላችሁ፡፡ ክብርናቸውን ትወስዳላችሁ፡፡ የልጄን ክብር በጉቦ ልስጥ??›› ብለው የከተማውን አስተዳዳሪ አቶ እንግዳን በአደባባይ ይተቻሉ የፀሀይ እናት፡፡ (- ግራጫ ቃጭሎች ገጽ 23)፡፡
የእዮብን ትዕግስት የታደለች ከተማ። የመዝገቡን ጉብታ ማግኘት ያን ያህል ከባድ አልሆነብኝም፡፡ ከሰሜን ሆቴል በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ከፍተኛ ቦታ መምረጥ ብቻ በቂዬ ነበር፡፡ የመዝገቡ ጉብታ ከመናኸሪው ከፍ ብሎ ከአራዳ ገበያው አቅራቢያ ከታዋቂው ሥላሴ ቤተክርስቲያን ብዙም ሳይርቅ ይገኛል፡፡ /ይሄ የኔ ግምት ነው፣ እኔ የምለው ቦታ ላይ ባይሆን እንኳ አካባቢው ከዚህ አያልፍም፡፡/
መዝገቡ ከዚያ ቦታ ላይ ሆኖ ልጅ በመሆኑ ምክንያት ማንም ከቁብ ሳይቆጥረው ማንንም ታዝቧል፡፡ የነፋስ መውጫን ገበና ተመልክቷል፡፡ የፀሐይ እናት የከተማውን አስተዳዳሪ አቶ እንግዳን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሰድቡ ሰምቷቸዋል፡፡ ለምን እንደሚሳደቡና ምሬታቸውን እንደሚያሰሙም ተረድቷል፡፡
መዝገቡ ከዚያች ጉብታው ላይ ሆኖ ማንም ልብ ያላለውን የእንጢቆ ዙፋንን የብሶት ፉጨት ሰምቷል፡፡ የእንጀራ እህቱን ድብቅ የፍቅር ግንኙነት በዓይኑ በብረቱ አይቷል፡፡ የተበደለች ቂጡን (እሱ እንደዚያ ይገልፃታል) ከጉብታው ቅዝቃዜ ጋር አግባብቶ ጠዋትና ማታ ሳያስተጓጉል ንፋስ መውጫን ተመልክቷታል፡፡
ያ ጊዜ ደራሲው አዳም ረታ በፈጠረው ምናባዊ ልብወለድ ውስጥ የሰፈሩትን ሀተታዎች መሠረት አድርገን ስንገምት የአፄ ኃ/ሥላሴ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን አመታት ላይ ይመስላል፡፡  ዛሬ እኔው ራሴ በዚህ ዘመን የመዝገቡ ጉብታ ላይ ቆሜ ነፋስ መውጫን ታዘብኳት፡፡
ዛሬ ላይ ሳያት፣ ነፋስ መውጫ እድሜዋን ባልመጠነ እድገት ላይ ትገኛለች፡፡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ መንገድ በመሃልዋ አቋርጦ ቢያልፍም ያስፋልት መንገድም ሆነ የ24 ሠዓታት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ለረዥም ጊዜ ምድጃ ዳር ቁጭ ብላ ገላዋን በገል እያከከች በእዮብ ትዕግስት ትጠብቃለች፡፡
እንደ በጋ መብረቅ ሳይታሰብ በድንገት የተከሠተውን ‹መረቅ› የተሰኘ መጽሐፉን ለማስመረቅ፣ ደራሲ አዳም ረታ ከሚኖርበት ካናዳ ወደ ትውልድ ሃገሩ ብቅ ባለበት ወቅት፣ እኔን ጨምሮ ወደ ሰላሳ ገደማ የምንሆን አድናቂዎቹ ለሠዓታት ያህል በተለይ ስለ ድርሰቶቹ እየጠየቅነውና እየመለሰ ቆይታ አድርገን ነበር፡፡
በጊዜው ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ በግራጫ ቃጭሎች መጽሐፍ ውስጥ የታሪኩ መውደቂያ ቦታ የሆነችውን ነፋስ መውጫን የተመለከተ ነበር፡፡ ‹‹ለመሆኑ ነፋስ መውጫን ታውቃታለህ?›› ተብሎ ነበር፡፡ መልሱን በአጭሩ ሰጠ፡፡ ‹‹አላውቃትም!››፡፡
መቼም ግራጫ ቃጭሎችን አንብቦ ከመዝገቡ ጋርና በጉያዋ ከተመላለሰባት ነፋስ መውጫ ጋር የተዋወቀ ተደራሲ በአዳም መልስ መደናገጡ አይቀርም፡፡ ባይደነግጥም እንኳ ይደናገራል፡፡ እኔ በርግጥ አዳም ረታ ነፋስ መውጫን እንደማያውቃት ካወቅኩ አመታት አልፈውኛል፡፡ በዚህ ምክንያት የአሁኑ መልስ የተለየ አዲስ ስሜት አልፈጠረብኝም፡፡ የኖረውን ስሜቴን ከመቀስቀስ ውጭ፡፡
ደራሲው ነፋስ መውጫን ሲገልጻት ተወልዶ ያደገባት ያህል የሚያውቃት ይመስለናል፡፡ በተለይ ከተማዋን የሚያውቃት አንባቢ እንደዚያ ቢያስብ አይፈረድበትም፡፡
አዳም እንደሚለው “ነፋስ መውጫ” የሚለው ስም ስለማረከውና ከሠዎች አዕምሮ የማይጠፋ መስሎ ስለተሰማው መዝገቡን ከነ አጃቢዎቹ (እንጀራ እናቱ፣ አባቱ፣ ወሰን፣ እንጀራ እህቱ፣ ሙስጠፋ፣ ወዘተ) እዚያ ወሰደው እንጅ፣ ሌላ የተለየ ምክንያት የለውም፡፡
ተወልዶ እንዳደገባት እናስብ ዘንድ በሚያስገድድ ገለጻ ብሎም በከተማዋ ውስጥ የምናውቃቸው (እንደኔ ላለነው) ትክክለኛ  የቦታ መጠሪያዎች ከነሁኔታዎቻቸው ስለሚያስቀምጥልን አዳም ከነፋስ መውጫ ተነስቶ በመዝገቡ መንገድ አዲስ አበባ የገባ የከተማዋ ዜጋ ይመስለናል፡፡ ይሁንና እሱ መጀመሪያውኑም አዲስ አበቤ ነበር፡፡
ሌላው የመዝገቡን ከተማ አንስቼ ሳልጠቅስ የማላልፈው  “የበላይ ድንጋይ”ን ነው። የበላይ ድንጋይ! ግራጫ ቃጭሎች መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 148 ላይ ስለ በላይ ድንጋይ የሚገልጽ ሃተታ ተጽፏል፡፡ የበላይ ድንጋይ በደራሲው ምናብ ውስጥ የተፈጠረ ፋንታሲ ቢሆንም መሬት ላይ ካለ እውነት ጋር ተዳብሎ በመቅረቡ ለፍለጋ እንወጣ ዘንድ ያስገድደናል፡፡ መጽሐፉ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹በሚሽኑና በከተማው መካከል ሰፊ ሜዳ ነበር፡፡ ለነገሩማ የነፋስ መውጪያ ከተማ መጀመሪያ ከሜዳ ቀጥሎ በተራራ የተከበበች ናት፤ መጀመሪያ የሜዳ ቀጥሎ የተራራ ቀለበት፡፡ ይኸኛው ሜዳ ግን በሚሽኑና በከተማው መሐል ያለው ልክ እንደ መዳመጫ ለስላሳ ነበር፡፡
‹‹ለበጋ ለበጋ የሜዳው ሳር ወርቅ ይመስላል፡፡ ክረምት ክረምት ቀላል ጨፌ ይሆናል፡፡ መስከረም ብቅ ሲልም ጀምሮ አደይ አበባ ይነጠፍበታል፡፡ ‹ወንድ አይወለድብሽ ሜዳ› ወይም በአጭሩ ‹ወንድ ሜዳ› ይሉታል፡፡
‹‹ከሜዳው በስተግራ ከከተማው ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ አንድ ብቻውን የተጎለተ ትልቅ፣ ድቡልቡል ጥቁር ድንጋይ ነበር፡፡ የሚያምር፣ የሚገርም ቅርጽና ውበት አለው፡፡ የዚህ ድንጋይ ስም ‹ወንድ አይወለድብሽ› ይባላል፡፡ በሁዋላ በሁዋላ ‹የበላይ ድንጋይ› ተባለ፡፡
‹‹… እልም ያለ አውላላ ሜዳ ላይ እንዲህ ክብ የሆነ፣ እንዲህ የጠቆረ ድንጋይ መኖሩ የማያስገርመው የለም፡፡ አንዳንድ ሠዎች የግራኝ ድንጋይ ነው ይላሉ፡፡ እንደሚሉት ነፋስ መውጪያ ድሮ ድሮ በማርያም ስም የሚጠራ ታላቅ መቅደስ ነበራት፡፡ እጉና ተራራ ላይ ውጊያ ሆኖ ግራኝ ታች ወርዶ በመዝለቅ የፈለገውን ጥፋት መስራት አለመቻሉ አብሽቆት ያን መቅደስ ለመምታት ድንጋይ አንስቶ ወረወረ ይባላል፡፡ መቅደሱን ሳተውና ድንጋዩ እሜዳው ቀረ ይላሉ፡፡››
ይሄን ታሪክ ተከትለን ፋንታሲነቱን እያመንንም ቢሆን መሬት ላይ የወደቁ እውነቶችን ስንፈልግ የሚከተለውን እናገኛለን፡፡ ነፋስ መውጪያ ከተማ ደራሲው እንደገለጸው በሜዳና በተራራ ቀለበት የተከበበች ናት፡፡ ከተማዋ ካሏት ሜዳዎች መካከል ታዲያ በጣም ሰፊ የሆነና በመጽሐፉ ከተገለጹት ሃሳቦች ጋር የሚዛመደው ወደ ወሎ በሚወስደው መንገድ በከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ነው፡፡
በዚህ ሜዳ ላይ በከተማዋ ስም የተሰየሙት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተጣብቀው ይገኛሉ፡፡ ሚሽን ባይሆንም በዚያው አቅራቢያ የሚገኝ ሀገር በቀል የእርዳታ ድርጅትም አለ፡፡ ‹‹ዋቢ›› የሚል ስያሜ ያለው ድርጅት ሲሆን አቶ ማስቲካ ነጋሽ በተባሉ ሠው የተመሠረተና በተለያየ መንገድ ለችግር ለተጋለጡ ልጆች ድጋፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ስለበላይ ድንጋይና ከግራኝ አህመድ ጋር ተያይዞ በመጽሐፉ ስለተገለጸው ታሪክ ከማውቃቸው ሠዎች ሃሳብ ስጠይቅ ወዳጄ ሙሉቀን ካሳሁን ይሄንን አጫውቶኛል፡-
‹‹ስለ በላይ ዘለቀ ድንጋይ የማውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን ግራኝ አህመድ የወረወረው ስለሚባል ድንጋይ አንድ አፈታሪክ አውቃለሁ፡፡ ከነፋስ መውጫ ከተማ ርቃ የምትገኝ ቤቴልሔም ማርያም የምትባል ቤተክርስቲያን አለች፡፡ በግራኝ አህመድ ወረራ ዘመን ቤቴክርስቲያኗን ለማፍረስ ግራኝ አህመድ አንድ ትልቅ ድንጋይ ወርውሮ ነበር፡፡ ይሁንና ግራኝ ድንጋዩን ሲወረውር ቤተክርስቲያኗ ከዓይኑ ተሰወረች፡፡ ሳይመታትም ቀረ፡፡ አሁን ያ ትልቅ ድንጋይ በስፍራው ይገኛል››፡፡
አዳም ረታ ከላይ የተጠቀሰውን አፈታሪክ ስለማወቅ አለማወቁ መረጃው የለኝም፡፡ ግምቴ ግን ያውቃል የሚል ይሆናል፡፡ ቢያንስ በሌላ ቦታ ስለተወረወረ የግራኝ ድንጋይ መረጃ አለው፡፡ (ታዲያ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ግራኝ አህመድና ድቡልቡሉ ድንጋይ በምን ምስጢር አዳም አዕምሮ ውስጥ ገቡ?)
ስለበላይ ዘለቀ የነገረን ግን ምናብ ወለድ መሆኑን እናምናለን፡፡ ቅልጥ ያለ ፋንታሲ ነው፡፡ (የአጋፋሪ እንደሻው አይነት)፡፡ በላይ ዘለቀ ከመሰቀሉ በፊት በአንድ ሌሊት ከጠባቂዎቹ ጋር በመሆን በእግሩ ነፋስ መውጪያ መሄዱንና እዚያ ድንጋይ ላይ ወጥቶ ፀሎት ካደረገ በኋላ ‹ወንድ አይወለድብሽ› ብሎ መራገሙን እናነባለን፡፡
(ለእርግማን ብሎ በእግሩ ነፋስ መውጫ ድረስ ምን አደከመው? እንጦጦ ላይ ሆኖስ መራገም ይችል አልነበር? ይሄ መቼም ይገርማል!)
የበላይ ድንጋይ ከተሠነጠቀ 8ኛው ሺህ የሚባለው ጊዜ እንደሚገባ የአካባቢው ሠው ያምናል የሚል ሃሳብም በግራጫ ቃጭሎች መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን፡፡ (ጎንደር ከተማ ከፋሲል ቤተመንግስት አቅራቢያ የሚገኘው የጃንተከል ዋርካ መሬት ሲነካ 8ኛው ሺህ ይገባል የሚል አፈታሪክ እንዳለው ሁሉ፤ ከዋርካው ጋር በግጥም የሚባለውን ሌላ አፈታሪክ ግን ሆን ብዬ ዘንግቼዋለሁ)፡፡
በግራጫ ቃጭሎች ውስጥ ስማቸው ከተከተቡት ገፀባህሪዎች መሐል አቶ እንግዳን እናገኛለን። አቶ እንግዳ የከተማዋ አስተዳዳሪ ነው፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ እንደሚነግረን አቶ እንግዳ የተባለው ሠው ስልጣኑን ተጠቅሞ ሴቶችን የሚያባልግ፣ በከተማዋ ነዋሪዎች የሚፈራ ሠው ነው፡፡ የሚደፍሩት የፀሐይ እናት ብቻ ናቸው፡፡
‹ጎልያድና ዳዊት› በሚል ንዑስ ርዕስ ስር የፀሀይ እናት በወንጭፍ ድንጋይ አስተዳዳሪውን ሲመቱት እናነባለን፡፡ ሴትዮዋን ወንጭፍ ያስነሳቸው የሴት ልጃቸው መደፈር ነው፡፡ በነፋስ መውጪያ ታሪክ የተባለው ነገር ስለመፈጸሙ የሰማሁት ነገር ባይኖርም፤ ከአቶ እንግዳ ጋር የሚቀራረብ ታሪክ ያላቸው (በድፍረት ነው ያቀራረብኳቸው) አስተዳዳሪ እንዳሉ ግን ተነግሮኛል፡፡
በእውነታው አለም የነበሩት ሠው አቶ አክሊሉ በላይ ይባላሉ፡፡ በዘመነ ደርግ የነፋስ መውጪያ ከተማን አንቀጥቅጠው ገዝተዋታል፡፡ አስገራሚ ህጎችም ነበሯቸው፡፡ ከነዚያ መካከል አንደኛው የአካባቢውን ገበሬዎች የሚመለከት ነው፡፡ ገበሬዎቹ ከቅዳሜ ውጭ ወደ ንፋስ መውጫ ከተማ መግባት አይችሉም፡፡
በስራ ወቅት ከተማ መሀል የተገኘ ባላገር የአቶ አክሊሉን ዱላ ከመቅመሱ በተጨማሪ ለቀናት የመታሰር እድልም ሊገጥመው ይችላል፡፡ ሰውዬው በዚህ የህግ አፈፃፀማቸው ሂደት ታዲያ የገጠማቸው ነገር ዛሬም ድረስ በነፋስ መውጪያ ከተማ ይወራል፡፡
አንድ ባላገር በሥራ ቀን አህያውን እየነዳ ንፋስ መውጪያ ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡ ያገኙት ደግሞ ራሳቸው አቶ አክሊሉ ነበሩና ከዘራቸውን ላጥ አድርገው ያቀምሱታል፡፡ ማንነታቸውን ያላወቀው ባላገርም ‹ዘራፍ› ብሎ የመልስ ምት ይሰነዝራል፡፡ እንዲያውም ከሳቸው በባሰ ሁኔታ ያንቆራጥጣቸዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የአስተዳዳሪው ጠባቂዎች ባላገሩን ይዘው ሊቀጠቅጡት ሲሉ አቶ አክሊሉ በጀግንነቱ ተደንቀው (የቀመሱት ዱላ ቢያንገበግባቸውም) ምህረት እንዳደረጉለት ይነገራል፡፡ በድጋሚ በስራ ቀን ወደ ከተማ እንዳይመጣ መክረው በሰላም ሸኝተውታል፡፡
በአቶ አክሊሉ ህግ መሰረት የንፋስ መውጪያ ከተማ ነዋሪዎች ከልክ ያለፈ ድግስ መደገስም አይችሉም፡፡ ክርስትና፣ ሠርግና ሌሎች የድግስ ስነሥርዓቶች መጠናቸውን አልፈው ከተገኙ ያንን ያደረጉት ሰዎች ይቀጣሉ፡፡ አቶ አክሊሉን ካነሳን ዘንድ አንድ ታሪክ እንጨምር፡፡
በደርግ ጊዜ ውጊያው በሰሜን በኩል በተፋፋመበት ወቅት ከነፋስ መውጫ ነዋሪዎች መካከል ወደ ጦር ሜዳ የሚሄድ ሰው ቢፈለግም ‹በሥርዓቱ ደስተኛ ስላልነበሩ› ፍቃደኛ የሚሆን ጠፋ፡፡ በሁኔታው በጣም የተደናገጡት አስተዳዳሪው ብዙ ካሰቡ በኋላ አንድ ሀሳብ መጣላቸው፡፡
በተለምዶ ‹አብዮት አደባባይ› በሚባለው ቦታ ላይ የአንበሳ ሀውልት ነበረ፡፡ የአካባቢው ህዝብም ‹አንበሳው ጋይንት› የሚል ቅፅል አውጥቶለት ነበር፡፡ አቶ አክሊሉ የነፋስ መውጪያ ሰዎችን አደባባዩ ላይ ሰብስበው ለዘመቻ ፍቃደኛ የሆኑ ወጣቶች መኖር አለመኖራቸውን ጠየቁ፡፡ ሁሉም ወጣቶች ፍላጎት እንደሌላቸው አሳዩ፡፡ ይሄኔ አቶ አክሊሉ ወደ አንበሳው ሀውልት እያሳዩ ፦ ‹‹ላም ላድርገው?›› ብለው ሕዝቡን በቁጣ ጠየቁ – አሉ፡፡
መዝገቡስ? በነፋስ መውጫ መዝገቡን በአካል አውቀዋለሁ የሚል ሰው አለ ወይ? እግሬ እስኪቀጥን ፈልጌ ያላገኘሁት መዝገቡን ነው፡፡ በተመላለሰባቸው መንገድ እያለፍኩ ሱሪው ቂጡ ላይ የተቀደደበትን፣ በእንጀራ እናቱ የተበደለውን፣ ጉብታ ላይ ተቀምጦ አላፊ አግዳሚውን የሚታዘበውን፣ ናና ከረሜላ በጉንጮቹ ወጥሮ ስለ ቆንጆዋ ወሰን የሚብሰለሰለውን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ሀዘንን ከሳቅ ጋር የቀላቀለብኝን ታዳጊ ልጅ ፈለኩት፡፡ የለም፡፡ ለምን አጣሁት?
መልሱን ያገኘሁት ከንፋስ መውጪያ ከተመለስኩ በኋላ ነበር፡፡ ከደራሲው ጋር በነበረን ቆይታ ከወዳጆቼ አንደበት አንድ ቃል ወጣ፡፡ ‹‹ሁላችንም መዝገቡ ነን!›› የሚል፡፡ ለካ መዝገቡን ያጣሁት አንድ ሠው ስፈልግ ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ግን እኔም መዝገቡ ነኝ፡፡ (እናንተም እንደሆናችሁት ሁሉ)፡፡
በነገራችን ላይ የመዝገቡ ዘመን ንፋስ መውጫ ዛሬ ሌላ ሆናለች፡፡ ግን ዛሬም ቢሆን መዝገቡ ስለ ከተማዋ እንዲህ ሲል ይሰማኛል፡-
‹‹ነፋስ መውጪያ ሆይ!
ምንም ብትሆኚ፣
እንደ ናና ከረሜላ…
እ ወ ድ ሻ ለ ሁ !››
አበቃ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ።
Filed in: Amharic