>

ወደፊት ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው መኪና እንዲኖራት ነው የምሠራው...!!!  (ሺሃብ ሱሌይማን)

ወደፊት ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው መኪና እንዲኖራት ነው የምሠራው…!!!

 ሺሃብ ሱሌይማን

ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው። በአምስት የፈጠራ ሥራዎች ላይ እየሰራ መሆኑን ይናገራል። ከራሱ ባሻገር አገሩን ብሎም አፍሪካን በግንባር ቀደምትነት የማስጠራት ህልም አለው። ሺሃብ ሱሌይማን ይባላል።
ሺሃብ ታይታን (Titan) የተሰኘች እና በልዩ ዲዛይን የተሰራች ባለ አራት እግር መኪና አምርቶ ለአደባባይ አቅርቧል።
መኪናዋ ለተለያየ አገልግሎት እንድትውል ታስባ ነው የተሰራችው።
ስምንት ሰው የመጫን አቅም ያላት ይህች መኪና ለከተማ ትራንስፖርት፣ ለመዝናኛ እንዲሁም ለጉብኝት እንድትመች ሆና በልዩ ዲዛይን መሰራቷን ሺሃብ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ተናግሯል።
የሺሃብ ሱሌይማን መኪና፣ ታይታን፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የምትታይበት ጊዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል።
ከመኪናዋ ቀድሞ ግን የተለያዩ ህልሞቹን ማሳካት የቻለ ወጣት ባለሙያ ነው።
ሺሃብ በአሁኑ ጊዜ አይ ስታር የተሰኘ ኩባንያ በማቋቋም በኃላፊነት እየመራ ይገኛል።
ከዚህ ቀደምም በፈጠራ ሥራው አማካኝነት የተለያዩ ሽልማቶችን ለመቀበል የበቃ ባለሙያ ነው።
በኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በሮቦቲክስ፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በስፔስ እንዲሁም ኢንተርኔት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃ [ስቶቭ] እንደሆነ የሚናገረው ሺሃብ፤ የዳቦ ማሽን፣ በርን በይለፍ ቃል መዝጋት እና መክፈት የሚያስችል ፈጠራ፣ ስማርት ረከቦት ሰርቷል።
በእነዚህ ሥራዎቹ አማካይነትም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ ሽልማት አግኝቷል።
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ወደ ሮቦቲክስ በመግባት እና የራሱን ድርጅት በማቋቋም እስከ ሕንድ ድረስ በመጓዝ ተወዳድሯል።
በማስከተል ደግሞ አንድ ስልክ ዲዛይን በማድረግ እና የሚያስፈልጉትን ክፍሎች ዲዛይን አዘጋጅቶ ወደ ቻይና በመላክ ከተመረተ በኋላ አገር ውስጥ በመገጣጠም ለኢንቬስተሮች ቢያቀርብም ገንዘቡን በእሱ ፈጠራ ላይ ለማፍሰስ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ማግኘት አለመቻሉን ያስታውሳል።
ባለ አራት ጎማዋ ታይታን
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ሺሃብ ሴሌይማን፣ የሰራትን ባለ አራት ጎማ መኪና ሰሞኑን ለዕይታ አብቅቷል።
ይህ ወጣት የሰራት መኪና ስምንት ሰዎችን የመጫን አቅም ያላት ሲሆን፣ በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ አድናቆትን አግኝታለች።
ሺሃብም መኪናውን አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ የመኪናውን ስም ‘ታይታን’ ሲል መሰየሙን ይናገራል።
ታይተን የሳተርን ጨረቃ ስያሜ ነው። ሺሃብ ከፕላኔቶች ሁሉ ለሳተርን የተለየ ፍቅር እንዳለው እና ይህንን ስያሜውንም ከዚያ መውሰዱን ይናገራል።
ይህን ስያሜ የሰጠበትን ምክንያትም ሲያብራራ ለመጥራት ቀላል እና ሥራውም ለውጪ ገበያ በሚቀርብበት ወቅት በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማሰብ መሆኑን ገልጿል።
ይህ ወጣት መኪና የመሥራት የልጅነት ሕልሙ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ አገራችን ኢትዮጵያ “የራሴ የምትለው መኪና እንዲኖራት” እና ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ከሚል እሳቤ በመነሳት መሥራቱን ይናገራል።
“መጀመሪያ አገራችን የሯሷ ስያሜ ያላት መኪና እንዲኖራት በማሰብ ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ከሰራናቸው የተለያዩ ዲዛይኖች መካከል መርጠናል። በዚሁ መሰረት የትኛው ወደ ገበያ ቢወጣ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለውን በማመዛዘን ውሳኔ ላይ ደርሰን ይህንን ለማምረት ቻልን።”
የታይታን መኪናን ለመስራት የሚያስችል ጥሬ እቃ ከየት መጣ?
ሺሃብ ታይታንን ሰርቶ ሲጨርስ ቀለም ተቀብታ ለመነዳት ዝግጁ እንደሆነች፣ መጀመሪያ ያሳፈረው ሰው ወንድሙን እንደሆነ ያስታውሳል።
“መኪናዋ ኢንሹራንስ የላትም” በሚል እየቀለደ ሊያስፈራራው ቢሞክርም ወንድሙ ግን ይተማመንበት እንደነበር እና ከተማ ውስጥ በመዘዋወር በአግባቡ መሥራቷን መፈተሻቸውን ለቢቢ ገልጿል።
ሺሃብ ለሰራት መኪና ሞተሩን በአገር ውስጥ ለማምረት ስላልተቻለ ከውጪ የመጣ ቢሆንም ሻንሲውና ሌላው የአካል ክፍሏ ግን በአገር ውስጥ ከሚገኙ ግብአቶች የተሰራ ነው።
አጠቃላይ መኪናዋን አምርቶ አሁን ካለችበት ይዞታ ለማድረስ ወደ 600 ሺህ ብር እንደወጣ የሚናገረው ሺሃብ፣ ወጪውን በተለያዩ አካላት ድጋፍ መሸፈኑን ይናገራል።
“ታይታን የተሰራችው በአካባቢያችን ከሚገኙ ግብዓቶች ነው፤ አልሙኒየም፣ ፋይበር ማይካ እና ብረት ከዚሁ አገር ውስጥ የተገኙ ናቸው፤ ሻንሲውን እና የመኪናውን አካል በአገር ውስጥ ነው የሰራሁት።”
የመኪናዋ ዲዛይን በባጃጅ እና በትልቅ መኪና መካከል የሚገኝ መሆኑን የሚናገረው ሺሃብ በከተማ ውስጥ ለመዝናናት፣ ለሠርግ እንዲሁም ለትራንስፖርት አገልግሎት እንድትውል ታልማ የተሰራች ናት።
“የታይታንን ዲዛይን ስናዘጋጅ ሦስት ችግሮችን ለመፍታት አስበን ነው” የሚለው ሺሃብ በዋናነት በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት ችግርን መቅረፍ ነው።
ሌላናው ደግሞ በውጪ ምንዛሪ ከባሕር ማዶ የሚገቡትን መኪናዎች በማስቀረት አገሪቱ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ ማዳን ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ “የምናመርታቸውን መኪኖች በአነስተኛ ዋጋ በመቅረብ የሥራ አጥን ቁጥርን በመቀነስ ረገድ የራሳችንን ስተዋጽኦ ለማድረግ ነው” ይላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች የፈጠራ ሥራዎች የሚሰሩ ቢሆንም ተቀናጅተው ወደ ገበያ በማቅረብ ለአገልግሎት በማብቃቱ ረገድ ችግሮች መኖራቸውን የሚናገረው ወጣት ሺሃብ፣ የዚሁ ችግር መነሻው ደግሞ የፈጠራ ሥራዎቹ በሚሰሩበት ጊዜ ከመነሻው አንስቶ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የገበያ ሁኔታ በደንብ ካለማጥናት የተነሳ መሆኑን ይናገራል።
አሁን ባመረቷት ታይታን መኪና ከማኅበረሰቡ አድናቆትን እና ገንቢ አስተያየቶችን እያገኙ መሆኑን እንዲሁም በተሽከርካሪዋ ላይ ያሉትን ውስንነቶች በማሻሻል ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ያስረዳል።
የወደፊት እቅዱን አስመልክቶ ሲናገርም “በአገራችን የራሳችን የምንለውን ብራንድ መኪና እንዲኖረን እፈልጋለሁ፤ እኔ በቴክኖሎጂ እና በአምስት የፈጠራ ሥራዎች ላይ እየሰራሁ ነው። ትልቅ ኢንዱስትሪ በማቋቋም የአገራችን ሕዝቦች እና የውጪው ዓለም እንዲጠቀም እፈልጋለሁ” ይላል።
እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችም ባላቸው ተሰጥኦ የሚወዱትን ነገር በመስራት እና ወደ ቢዝነስ በማሳደግ ለአገራቸው እድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምኞቱ መሆኑን ገልጿል።
Filed in: Amharic