>

ጦርነት ወይስ የርሀብ አድማ...!?! ( ሞገድ እጅጉ)

ጦርነት ወይስ የርሀብ አድማ…!?!

ሞገድ እጅጉ

 

መከላከያን መደገፍ ሲባል በምን እና እንዴት …???

የአብይ አሕመድ መንግስት ያወጀው የጦርነት አዋጅ ብቻ ሳይሆን የርሃብ አዋጅ ጭምር ነው፡፡ መጋቢት 2010 ዓ.ም አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ታይተው የማይታወቁ አሰቃቂ ግፎች ታይተዋል፡፡ የለውጡ ደጋፊዎችም ‹‹በለውጥ ወቅት ያጋጥማል›› በሚል ቀለል አድርገን ማየት እንዳለብን ሲነግሩን ቆይተዋል፡፡
ግጭቱ ግን እየባሰው መጣ፡፡ በተለይም ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ከፍተኛ መፈናቀል ደረሰ፡፡ ይባስ ብሎ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ይፋዊ ጦርነት ታወጀ፡፡ ለስምንት ወራት ያህል የዘለቀ ጦርነት በትግራይ አማጺያን እና በፌዴራሉ መንግስትና በአማራ ልዩ ኃይል ተካሄደ፡፡
የፌዴራሉ መንግስት ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ ‹‹ብቻዬን ተኩስ አቁሚያለሁ›› አለ፡፡ የትግራይ አማጺያን እንደፈለጉ እንዲፈነጩ ተፈቀደላቸው፡፡ በትግራይ ክልል ብቻ ተወስኖ የነበረው ጦርነት፤ መከላከያም የአማራ ልዩ ኃይልም እንዳይንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው አማጺያኑ የፈለጉትን እንድያደርጉ ሆነ፡፡ የትግራይ አማጺያን መሃል አማራ ድረስ ገቡ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የደሴ ከተማ በከፍተኛ የኑሮ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የከተማዋ ጎዳናዎች ከራያ ቆቦ ጀምሮ ካሉ አካባቢዎች በጦርነት ተሰደው በመጡ ሰዎች ተጥለቅልቀዋል፡፡ የደሴ ከተማ ትምህርት ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለስደተኞች መጠለያ ቢሰጡም አሁንም ማዳረስ አልተቻለም፡፡ የቤት ኪራይ በእጥፍ ጨምሯል፣ በስግብግብ ነጋዴዎች ጨካኝነት የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ሳይቀር በእጥፍ እየተሸጠ ነው፡፡
የኢትዮያ መንግስት የርሃብ አዋጅ የጀመረው አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ለሦስት ዓመታት ያህል በፀጥታ ሥጋት ውስጥ ነው የቆየው፡፡ ተረጋግቶ ያረሰ ገበሬ የለም፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የነገደ ነጋዴ የለም፡፡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የቀን ሥራ የሚሰራ የጉልበት ሰራተኛ እንኳን የለም፡፡ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅስ ሰላም አልነበረም፡፡
አርሶ አደሩና ነጋዴው ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ ችግሩ ወደ መንግስት ሰራተኛውም እየሄደ ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ለዚህ መንግስት ድጋፍ በብዙ ሰበቦች ሲበዘበዙ ቆይተዋል፡፡
በዚህ የኑሮ ውድነት የአብይ አህመድ መንግስት የመንግስት ሰራተኞችን እየዘረፈ ነው፡፡ በአሽቃባጭ አመራሮች በጎ ፈቃድ ይሁን በመንግስት ትዕዛዝ ባይታወቅም የምንሰማው ዜና ሁሉ ‹‹የእገሌ መስሪያ ቤት ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሰጡ›› የሚል ነው፡፡
በዚህ የኑሮ ውድነት የአንድ የመንግስት ሰራተኛ ሙሉ የአንድ ወር ደሞዝ መቆረጥ ምን ያህል ቀውስ እንደሚያስከትል ልብ ተብሏል? ይህን የደሞዝ መግቢያን ቀን ጠብቆ የሚኖር ሰራተኛ ኑሮ ማቃወስ የአገር ፍቅር ነውን?
ለመሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ችግር የገንዘብ ነውን? የገንዘብ ከሆነስ መንግስት ደሞዝ ይጨምርለት እንጂ እንዴት የወር ደሞዝ ጠብቆ ከሚኖር የመንግስት ሰራተኛ ላይ የአንድ ወር ሙሉ ደሞዝ ይቆረጣል?
ወታደር ክብር ነው፤ ይሄን ማንም ያምናል፡፡ አህያ የሚሸናበት የኩሬ ውሃ እየጠጣ፣ የደረቀ ብስኩት እየበላ ዳር ድንበር የሚጠበቅ ነው፡፡ መንግስት ግን ማጭበርበር ሲፈልግ ‹‹ወታደር ክብር ነው›› ይላል፡፡ ቅሬታው ያለው ከአመራሩ እንጂ ከታች ካለው ተራው ወታደር አይደለም፡፡
ግደለም የህዝብ ሞራል እንዲያገኝ ለመከላከያ ድጋፍ ይደረግ፡፡ የሰራተኛውም ደሞዝ ይቆረጥ፤ ችግሩ ግን እውነት ለወታደሩ ይደርሰዋል ወይ ነው! አይደርሰውም! ወታደሩ ዛሬም ያንኑ የተጎሳቆለ ኑሮውን ነው የሚኖር፡፡ የሰራተኛው ደሞዝ የሚቆረጠው ለአመራሮች ነው፤ ግልጽ የሆነ ሙስና አለበት፡፡
ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን የአገር ከብት ሲነዳ ነበር፤ የአገር ተቋማት ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር፡፡ የት ደረሰ ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ እነሆ ሁለተኛው ዞር ጦርነት ሲጀመር አሁንም ድጋፍ አድርጉ ተባለ፡፡
ኮቪድ-19 ገና አፍላ በነበረበት ወቅት ብዙ ቢሊዮን (አዎ ቢሊዮን) ብር ተሰብስቧል፡፡ የት እንደደረሰ የጠየቀ የለም፡፡ ምን እንደተደረገ አይታወቅም፡፡ ከብዙ አገራት የተገኘ ድጋፍም ለምን እንደዋለ አይታወቅም፡፡
የመከላከያው ድጋፍም እንደዚሁ ነው፡፡ የሚጎሳቆለው ወታደር አይደርሰውም፡፡ ደረሰው ወይ ብሎ የሚጠይቅ ሚዲያ የለም!
ሚዲያዎች ‹‹የተደረገው ድጋፍ የት ደረሰ?›› ብለው መጠየቅ ሲገባቸው ራሳቸው የሙስናው አካል ሆነዋል፡፡ ከሰራተኞቻቸው ላይ ደሞዝ እየቆረጡ አቀብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሰጡ›› የሚል ዜና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተነግሯል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞችም ይሄንኑ ማድረጋቸውን በድርጅቱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ አይተናል፡፡ በእርግጠኝነት ይህ የሚደረገው በአመራሮች ውሳኔ ነው፡፡ የሚቃወም ሰራተኛ ቢኖር ‹‹የጁንታው ተባባሪ›› በሚል ሊታሰርም ይችላል፡፡
እነዚህ ሁለት አንጋፋ የመንግስት ሚዲያዎች በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ እንደ ሚዲያ ማድረግ የነበረባቸው መረጃ መስጠት እንጂ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ አስፈጻሚ እና የሙስና ተባባሪ መሆን አልነበረም፡፡ በነገራችን ላይ አገሪቱን ለዚህ ቀውስ የዳረጓት የአንድ ግለሰብ ልሳን የሆኑ እነዚህ ሚዲያዎች ናቸው፡፡
ለመሆኑ ግን መከላከያን መደገፍ ሲባል እንዴት ነው?
መንግስት ወታደሩን ‹‹የእገሌ ወታደር ነበርክ›› እያለ ያስራል ይገላል፡፡ በ‹‹ሪፎርም›› ስም የአንድ ብሄር ስብስብ ያደርጋል፡፡ ገለልተኝነቱን ጥላ እሸት ቀብቶ ‹‹በመደመር መንገድ›› እያሉ እንደዘምሩ ያደርጋል፡፡ ይህን እያደረገ ግን ለመከላከያ ድጋፍ በሚል ደግሞ ህዝቡን ይበዘብዛል፡፡ መቼም ይሄ ከየአካባቢው የሚንጋጋ ከብትና ፍየል በገበሬው በራሱ ተነሳሽነት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ለአንድ ገበሬ አንድ በሬ ምኑ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ምናልባት መንግስት በሬዎችን እየገዛ ሊሆን ይችላል፤ ‹‹የምንድንትስ ነዋሪዎች›› እያለ በልሳኖቹ ዜና የሚያስሰራው ግን ድጋፉን ህዝባዊ ለማስመሰል ነው፡፡ የተደረገው ድጋፍም ወታደሩ ጋ አይደርስም፡፡
ለመሆኑ ግን የትግራይ አማጺ ኃይል መሃል ላሊበላ ድረስ የገባው የአብይ ወታደር የስንቅ እጥረት አጋጥሞት ይሆን? ደሞዝ ያንሰኛል አልታዘዝም ብሎ ይሆን? በጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ነው የኖረ›› የተባለው በሬ ካልተሰጠኝ ብሎ ይሆን?
ችግሩ ይሄ ካልሆነ ታዲያ ከድሃ ላይ በሬ መቀማት ለምን አስፈለገ? የወር ደሞዝ ጠብቆ ከሚኖር ሰራተኛ ላይ ሙሉ የአንድ ወር ደሞዝ መውሰድ ለምን አስፈለገ? ከዚህ በፊት የተደረገው ድጋፍ ምን እንደተደረገስ ለምን አይነገርም?
የበለጠ አሳፋሪ የሚያደርገው እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ የሚገባቸው ሚዲያዎች የዚህ ዝርፊያ አካል መሆናቸው ነው፡፡
የአብይ አህመድ መንግስት የረሃብ አዋጅ አውጇል፡፡ የበለጠ የሚያስፈራው ወደፊት ያለው ነው፡፡ በብዙ አካባቢዎች በፀጥታ ሥጋት ምክንያት እርሻ ቆሟል፡፡ 85 በመቶ በግብርና በምትተዳደር አገር ውስጥ እርሻ ቆመ ማለት ምን እንደሚከሰት ግልጽ ነው፡፡ ቀሪው የሥራ ዘርፍም በፀጥታ ሥጋት ምክንያት የተቆራረጠ ነው፡፡ አዲስ አበባ ያለው የኑሮ ውድነት ከዚህ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም ምርቶች ይመጡ የነበሩት ከእነዚህ እርሻ ከቆመባቸው አካባቢዎች ነበር፡፡
የመንግስት ሰራተኛው እንኳን ቤተሰቦቹን እንዳይደግፍ ይሄው በሰበብ አስባቡ ደሞዙን እየተቀማ ነው፡፡ መዋጮ የሚባልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አገራዊ የረሃብ አደጋ ቢከሰት ታዲያ ይሄ መንግስት ነው የሚወጣው?
በአብይ አህመድ መንግስት አንድ የተለመደ ፋሽን አለ፡፡ ይሄ ፋሽን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ እንድሰራበት የተዘረጋ ዘዴ ነው፤ ይሄውም መረጃን ማፈን!
ጭፍን የለውጡ ደጋፊዎች ‹‹አብይዬ አዝግ ስብሰባን የገላገልከን›› ይላሉ፡፡ እርግጥ ነው ስብሰባ አሰልቺ ነው፤ አሰልቺ የሚያደርገው ግን አጀንዳው ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ በአብይ መንግስት የተጀመረው ፋሽን ግን ከሰራተኛው ምንም አይነት ቅሬታና አስተያየት እንዳይነሳ የኮምኒኬሽን መንገዶችን ሁሉ መዝጋት ነው፡፡ ውሳኔዎች የሚመጡት ተወስነው ነው፡፡ ትዕዛዝ ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡ ‹‹ከዚህ ወር ጀምሮ ደሞዛችሁ ይቆረጣል›› ካለ በኋላ በበጎ ፈቃድ የተደረገ አስመስሎ ዜና ያሰራል፡፡
መንግስት የሚሰጣቸውን መግለጫዎች ልብ ማለት እንችላለን፡፡ አብዛኞቹ ጋዜጠኛ በሌለበት ነው የሚላኩት፤ ይሄውም የመንግስት ልሳን ለሆኑት ብቻ በቴሌግራም ይላካል፡፡ ወይም ደግሞ በተደጋጋሚ እንደምናየው በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ማህበራዊ ገጽ ላይ ይለጠፋል፡፡ ጥያቄ የሚባል አይኖርም፡፡
ይሄ ፋሽን ነው እስከ ቀበሌ መስሪያ ቤቶች ድረስ የወረደው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የተመሰቃቀለች አገር የሆነችው፡፡ ከዛሬው የነገረው ያስፈራል!

Filed in: Amharic