>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4524

ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያን ደጋማው ክፍል መቆጣጠር የቅኝ ግዛት ዘመኑ ስትራቴጂ !! አሁንስ ? (ስላባት ማናዬ)


ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያን ደጋማው ክፍል መቆጣጠር የቅኝ ግዛት ዘመኑ ስትራቴጂ !! አሁንስ ?

ስላባት ማናዬ

የቀይ ባህርን አካባቢ ግዛቱ ለማድረግ ና የቀይ ባህርን የማመላለሻ መስመር ለመቆጣጠር የሚመኝ ኃይል ሁሉ ኢትዮጵያን መጓጓቱ የማይቀር ነበር፤ ከኢትዮጵያ በቀር በቀይ ባህር አካባቢ የሚገኙት አገሮች ሁሉ አብዛኛው መሬታቸው ምድረ በዳ ነው፤ሀሩር ነው፤የምግብም ሆነ የውሃ ችግር
አለባቸው፤የኢትዮጵያ ደጋማው ክፍል ግን የምግብና የውሃ ችግር የሌለበት ከመሆኑም ሌላ ቀዝቃዛ ና ለጤንነት የሚስማማ፤ የቀይ ባሕርንም የጉዞ መስመር ለመቆጣጠር የሚያመች ከፍታ ስለአለው ወደ አካባቢው የተጠጋ ቄሣራዊ ኃይል ሁሉ በመጀመሪያ ዓይኑን የሚጥልበት አካባቢ ነው። በጠቅላላው የምዕራባዊያን ኃይሎች ከአሁን በፊት በአፍሪካ ቀንድ ግዛታቸውን ለማስፋፋት የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ሦስት ናቸው።
• አንደኛው በሁሉም ቀላልና ብዙ ወጪ የማያስከትለው ዘዴ ማታለል ነው፤ መሪዎችን በልዩ ልዩ ዓይነት መንገድ እያታለሉ ነፃነታቸውን እየገፈፉ ግዛታቸውን ያስፋፋሉ
• ሁለተኛው በአንድ ሀገር ውስጥ በሕዝብ መካከል ያለውን የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት፤በሥልጣን ተቀናቃኞች መሀከል ያለውንም ውድድርና ትግል ምክንያት እያደረጉ ጠብን በመጫርና ፤ጸጥታን በማደፍረስ እነሱ በቀላሉ የሚገቡበትንና ሥልጣናቸውን የሚዘረጉበትን መንገድ እየፈጠሩ ግዛትን ለማግኘት ይሞክራሉ
• ሦስተኛው ማታለልና ተንኮል ውጤትን የማያስገኙ ሲሆኑባቸው በጉልበትና በጦር ኃይል ግዛታቸውንለማስፋፋትይጥራሉ። ምዕራባዉያን ኃይላት በአፍሪካ ቀንድ ላይ በእነዚህ በሦስቱም ዘዴዎች ተጥቅመዋል። በአፍሪካ ውስጥ ሦስቱንም ዘዴዎች እስከ መጨረሻው ድረስ ያከሸፈች ኢትዮጵያ ብቻ ነች፤ ይህንን ስንል በመሠረቱ ማንም ምዕራባውያን ሃይል የኢትዮጵያን ህልውና ለመደምሰስና የኢትዮጵያን ነፃነት ለመግፈፍ አልቻለም ማለታችን ነው እንጂ የኢትዮጵያን አካል በምዕራባዊያን ኃይሎች አታላይነትና ተንኮል፤ በጦር ኃይላቸውም አልተቆረጠም፣ አልደማም ማለታችን አይደለም ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም (2008ዓ/ም)
 
አሁንስ ?
የኃያላኑ ከአፍሪካ ቀንድ እስከ ታላላቅ ሐይቆች ድረስየአዲስ ካርታ ብወዛ ጅማሮ ወይስ …ኃያላኑ የአፍሪካን ቀንድ በአዲስ መበወዝ የሚቻለው ኦማር ሀሰን አልበሽር አስተዳደር ከተወገደ በኋላ ነው የሚል እምነት ነበራቸው ። ያን የካርታ ብወዛ ቀጣናዊ ስትራቴጂያቸው በአሜሪካው ሀሳብ አፍላቂ መማክርት ለመንግስት ወጋኝ ኩባንያ (Rand Corporation :2000) በኩል ይፋ አድርገውት ነበር ::
ከ11ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2011 ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ አዲስ ሀገር ሆነች ። አሁንም ሰዎቹ ዳርፉር ዳርፉር ማለታቸውን ቀጠሉ …ግን 2019 ደረሱ ሲጠሏቸው የባጁት ፕሬዚዳንት አል በሽር ከሥልጣን ተወገዱ ። ኃያላኑ መንግሥታት ለአካባቢያችን የነደፏቸው ግዛታዊ ማስተካከያዎችም ሆኑ ደህንነታዊ አወቃቀሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ በተለያዩ አቅጣጫ እየጣሩ ይመስላሉ። መጠንቀቁ ሳያስፈልግ አልቀረም ። የአፍሪካ ቀንድ እስከ ታላላቅ ሐይቆች አስፍቶ ታንዛንያን:ሩዋንዳንና ቡርንዲን እንዲያጠቃልል የተነደፈ”የታላቁ ቀንድ”(Great Horn) ህልምም ሆነ ከዛሬ 21ዓመት በፊት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሙስቬኒ የነደፉት ስድስት ሪፐብሊኮች ፕሮጀክተግባራዊነት አሁንም በምዕራባዊያን የጂኦ ፖለቲካ ንሞና ራዳር ውስጥ ነው ።
ይሳካል አይሳካም ጊዜው ይፈቅዳል አይፈቅድም የሚሉ የጥያቄ ጋጋታዎች ሳይዘነጉ ። የልዕለ ኃያላኑ የሱዳን አነባብሮሽ!! የካርቱም የጂኦ ፖለቲካ ሜዳ ከራሺያ እስከ አሜሪካ :ከቻይና እስከ ቱርክ :ከህንድ እስከ ኳታር እያጋፋ ነው ። ወቅታዊው የካርቱም የሽግግር መንግስት በሁለት ገመድ ተወጥሮ በሲቪል እና ወታደራዊ ሹማምንት ጉተታ እያስተናገደ ነው ። በዚህ የኃያላኑ ርኩቻ ካርቱም ራሷንም አድና ከጎረቤቶቿም ተታርቃ ለቀጣናው መረጋጋት ትሰራ ይሆን ወይስ በአሁናዊው ቀልበ ቢስነት ርምጃ ራሷንም ቀጣናውንም ወደ ባጀበት የደህንነት አዙሪት እና ታሪኩ ሆኖ ወደ ተከተበበት የግጭት ቀጣናነት ይዛው ታዘግም ?የግብፅ የባዕዳኑ ተልዕኮ አስፈፃሚ!! ግብፅ በዝነኛው መሪዋ ጋማል አብዱል ናስርዘመንየነበራትን የዲፕሎማሲ ታሪካ ዳግምእየተገበረች ነው ። ያኔ ናስር ተግባር ተኮር የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ይከተሉ ነበር ። በአንድ አመት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን የናስር ሚኒስትሮች ዙረዋል ።
የኢትዮጵያን ፓን አፍሪካ የወቅቱ እንቅስቃሴ ለመገዳደር ። ያኔ በእኛ ተረቱ ። ካለፈው አንድ አመት ጊዜ ጀምሮ የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ከደርዘን በላይ የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት አድርገዋል ። የጉዞአቸው ዋና ዓላማ ያው ግልፅ ነው ። ግብፅ ከአሁን በፊት አፍሪካ ላይ የሰራችውን የዲፕሎማሲ ስህተት መድገም አትሻም ። ከስህተቶቿ መካከል_በአውሮፓውያኑ 1973የአረብ
እስራኤል ጦርነት ወቅት የግብፅ (የአፍሪካመሬት) በእስራኤል በመወረሩ በወቅቱ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ነበር ። ግብፅ ግን ያን ውለታ ከመጤፍ ሳትቆጥር ፊቷን ወደ ወደ ሀብታም ዓረቦች ማዞሯ በአፍሪካ የነበራትን ሚና እና ዝና አውርዶባታል ። ከካምፕ ደቬድ ስምምነት ማግስት ከአፍሪካዊያን ይልቅ አውሮፓ እና አሜሪካን ናፋቂ መሆኗ :ከ1992ቱ የማድሬዱ የሰላም ጉባዔ በኋላ ይዋቀራል የተባለው አዲሱ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ውህደት ውስጥ መታቀፍ የበለጠባት ጊዜም ነበረ።
በዚህ ግርግር ግብፅ በአፍሪካ አህጉር ከተመሠረቱ በርካታ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደቶችን ያነገቡ ቀጣና አባልነትን ሳታገኝ ውጭ ቀርታለች ። ለኢንዱስትሪ ሸቀጦቿ ገበያ ፈላጊ ለሆነችው ካይሮ ይህ በቀላሉ የማይታይ ስህተት ሆኖ አግኝታዋለች ። ካርቱምን ከኢጋድ የማስወጣት የካይሮ ሴራ!! ግብፅ እና የቀድሞው የደህንነት ሹም :ወታደራዊ ኢታማዦር ሹም የአሁኑ ፕሬዚዳንቷ አካሔድ እጅግ ውስብስብ እና ስልታዊ ሆኖ እናገኘዋለን ።
አዲሶቹ ናስሮች ሱዳንን ከኢጋድ ያውም ራሷበሊቀመንበርነት ከምትመራው ለማስወጣት ባጠመዱት ወጥመድ ቀዳሚ ያደረጉት አዲስ ወዳጅነት መመስረት ነው ። ሰሞኑን እንደምናስተውለው ያልተቀደሰ ጋብቻ ። ከዚያ የካርቱም መለዮ ለባሾች አሻፈረኝ ባይነት ከኢጋድ የማስወጣት አካሔድ ይመስላል ። ይህ የካይሮ አካሔድ ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ ታላቁ ቀንድ ምስረታ አዲስ ካርታ ብወዛ ጋር ይገናኝ ይሆን??ሰሞኑን በህዳሴው ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጀመር ምክንያት የግብፅ አክሲዮን ገበያ አሽቆለቆለ የሚል ሀሳዊ ዜና ማጯጯኽ ነገርዮውን ከምዕራባዌያን ኩባንያዎች ጋር የማስተሳሰር ስልት ሆኖ ይታያል። በርካታ የምዕራባዊያን ኮርፖሬት ኩባንያዎች በግብፅ በኩል የአረብ ባህር ሰላጤን አንጡራ ሃብት መቀራመት ይፈልጋሉ እየተቀራመቱትም ነው። የአሜሪካው የአፍሪካ አሜሪካ ሃይል አፍሪኮም ከፍተኛ ወተደራዊ የጦር መኮንን ከቻናል 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ የናይል ጉዳይ የግብፅ ህልውና ነው ማለታቸውም ከላይ የተነሱ ሀሳቦችን የሚያጠናክር ነው።የቀድሞ ባልድረባዬ እና ወዳጄ ጋዜጠኛ እስክንድር ከበደ ነጠብጣቡን ማገጣጠም እንደሚለው ፤ነጠብጣቡን ስናገጣጥመው በኢትዮጵያ ላይ አሁን ከውጭ የተደቀነው የጣልቃ ገብነት አዝማሚያ እና እካሄድ ፤ የቀይ ባህር ፖለቲካን እና የናይል ወንዝን የመቆጣጠር የግብፅ እና የባዕዳኑ ተልዕኮ አንድ አካል ሆኖ እናገኘዋልን።
Filed in: Amharic