የተራድኦ ድርጅቶች ጦርነት በኢትዮጵያ
ኢ.ዜ.አ
ጣሊያናዊት ጋዜጠኛ ፍራንሲስካ ሮንቺን ሰሞኑን “በዝምታና በፕሮፓጋንዳ መካከል” “ETIOPIA The war of the NGOs, between silence and propaganda” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አስነብባለች።
ጋዜጠኛዋ በዘገባዋ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና የሰብዓዊ መብቶች ላይ እንሰራለን በሚሉ ተቋማት ድብቅ ፖለቲካዊ ተልዕኮ እና አጀንዳን የሚያጋልጥ መረጃ ይዛ ወጥታለች።
በዘገባዋ ላይም ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል “ህወሃት ህፃናት ወታደሮችን ስለማሰማራቱ ለምንድነው ሪፖርት የማታወጡት?” የሚል ሞጋች ጥያቄ አቅርባ የነበረ መሆኑን እና ከድርጅቱ ያገኘችው ምላሽ አሳፋሪ እንደነበርም ነው ያስነበበችው።
በወቅቱ በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ተለጥፈው የነበሩት ፎቶዎች አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን በውትድርና ውስጥ ማሰለፉን የሚያሳዩ የነበሩ በመሆናቸው ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ እንደሆነ ሲረዳ ፎቶዎቹን ከጋዜጣው ላይ በፍጥነት ማስወገዱን አስታውሳለች።
ጋዜጠኛዋ ይህንን በተመለከተ በጣሊያን ለሚገኘው የአምንስቲ ቢሮ ቃል-አቀባይ ሪካርዶ ኖውሪ ጥያቄ አቅርባ የነበረ መሆኑን እና ከድርጅቱ ያገኘችውም ምላሽ “ስለሚባለው ነገር መረጃው አለን ነገር ግን በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት በቦታው ተገኝተን የተነገሩ ወቀሳዎችን መመርመር፣ ማጣራት እንዲሁም ማረጋገጥ አልቻልንም” የሚል ነበር፡፡
ጋዜጠኛዋ ምላሹን መነሻ በማድረግም ታዲያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያንን ሁላ የአስገድዶ መደፈር፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የዕርዳታ አቅርቦት መከልከል ሪፖርቶችና ክሶችን እንዴት ርቀቱ ሳይገድባችሁ አዘጋጃችሁ? የሚል ጥያቄ አቅርባ እንደነበርም አስታውሳለች።
በዚህም ሁኔታዎች አመቺ ስላልነበሩ በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለነበሩ ሰዎች በስልክ በተደረገ ቃለ-መጠይቅ መነሻነት ሪፖርቱ ስለመዘጋጀቱ ፍንጭ ማግኘቷን በጽሁፏ ያስነበበችው ጋዜጠኛዋ፤ ይህ ደግሞ ባለፉት ወራት ውስጥ በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ወጣቶች መሆናቸው ተረጋግጧል በማለት እነዚህ ታጣቂዎች ሆን ብለው ቃላቸውን ለአምንስቲ ሰጥተው ቢሆንስ የሚል ጉልህ ጥያቄ አንስታለች፡፡
በመሆኑም መንግስትን ለመክሰስ የዋለውና በአምንስቲ ኢንተርናሽናል የወጣው ሪፖርት በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ እና ያልተጣራ ስለመሆኑም ጨምራ ገልጻለች፡፡
ይህ የአምንስቲ የሴቶች ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሟል የሚለው ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ የተዘጋጀው እና ይፋ የተደረገው ሪፖርት ከዛ በኋላ ለሚወጡ መሰል ባልተረጋገጡ እና ሆን ተብለው ለተቀነባበሩ ዘገባዎች እና ሪፖርቶች ቅቡልነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ማለፉንም አንስታለች።
ለዚህም በነሀሴ ወር መጀመሪያ አካባቢ በሁመራ 50 የሞቱ ሰዎች አስክሬን ተገኙ የሚለውን ዘገባ ታቀርባለች፡፡
በነሃሴ ወር 2013 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ ተቋማት በሁመራ አካባቢ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተፈጸመ ጭፍጨፋ ምክንያት 50 አስክሬኖች ተገኙ የሚል ሪፖርት ማሰማታቸውን አስታውሳ፤ ዘገባው በወጣ በደቂቃዎች ውስጥ መረጃውን የተጋራው የህወሃት አባል እና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም መሆናቸውን፤ ዶክተር ቴድሮስ የተጋሩትን ደግሞ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ ያጋሩት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ሀላፊ ሳማንታ ፓወር እንዲሁም የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የግጭቶች መከላከል ሀላፊ ጁዋኔ ማሪነር መሆናቸው አስታውሳለች።
በተቃራኒው የሽብር ቡድኑ ህጻናትን ለውትድርና ያሰለፈባቸውን ፎቶዎች በፍጹም እንዳላጋሩ አጋልጣለች፡፡
እነዚህ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሽብር ቡድኑ መሪ ደብረጺዮን ገብረ-ሚካኤል “ጦርነቱ የህዝብ ነው በመሆኑም ከልጆች ጀምሮ ማንኛውም ሰው በጦርነቱ ውስጥ መሳተፍ አለበት” በሚል የሰጡትን በቪዲዮ የተደገፈ መግለጫ በማስረጃነት እንዳይቀርብባቸው በማሰብ ወዲያውኑ ከእይታ እንዲጠፋ ማድረጋቸውን አስታውሳለች፡፡
እንደጋዜጠኛዋ መረጃ ከሆነ መዓዛ ግደይ የተባለች የሽብር ቡድኑ ደጋፊ በግል ቲውተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልዕክት በማስረጃነት መቅረብ የሚችሉ ህጻናት ወታደሮችን ወይም በህጻናት እና ሲቪሎች የተከበቡ ወታደሮችን የሚያሳዩ ፎቶዎችን እንዳትለጥፉ የሚል መልዕክት ማስተላለፏን በማሳያነት አንስታለች።
ኒውዮርክ ታይምስ እኤአ በሀምሌ 5/2021 እትሙ ላይ አሸባሪው ህወሃት ህፃናትን ወደ ጦርነት ስለማሰማራቱ ፎቶዎችን ጨምሮ መዘገቡን ያወሳችው ጋዜጠኛዋ፤ ይሁንና የጋዜጣው አዝማሚያ ህፃናት ሳይቀር በጦርነቱ ለመታገል ቁርጠኛ ሆነዋል በሚል ለማድነቅ የሞከረ እንደነበም አጋልጣለች፡፡
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የአሜሪካ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ “መሰል ተግባራትን አጣርተን ሁለቱም ወገኖች ላይ እርምጃ እንወስዳለን፤ በማለት የሽብር ቡድኑን ህወሃትን ለመወንጀል አለመፈለጋቸውን ጠቁማለች።
የታዳጊ ወታደሮች ምስል ማህበራዊ ሚዲያውን ቢያጥለቀልቀውም ተቋማቱ ዝምታን ነው የመረጡት በማለት ሞግታለች።
በአንፃሩ ባልተረጋገጡ የስልክ ጥቆማዎች ያውም ሳምሪ ከሚባሉ ተፈናቃዮች በተሰበሰበ አድሏዊ ጥቆማ ላይ ተመርኩዘው ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ለመወንጀል ወደ ኋላ አለማለታቸው ኢፍትሃዊ አካሄዳቸውን ያጋልጣል በማለትም ነው ጋዜጠኛ ፍራንሲስካ የገለጸችው።
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች አንዱን ወገን ደግፈው አንደኛውን ለመወንጀል በማሰብ የሚዘጋጁ እንደሆነ የጠቀሰችው ጋዜጠኛዋ፤ አምንስቲ እኤአ ሀምሌ 9 ቀን 2021 የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ በአክሱም ፈፀሙት ባለው የጭፍጨፋ ሪፖርቱ ከሳምሪ ወጣቶች አገኘሁት ባለው መረጃ ላይ ተመስርቶ ያወጣው ሪፖርት እንደሆነ አጋልጣለች።
አምንስቲ ይህን ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ወዲያውኑ የተጋራው የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ መሆናቸውን ገልጻ፤ የተጋሩትን መረጃ ወዲያውኑ የተጋሩት ደግሞ የዩኤስኤይድ ኃላፊዋ ሳማንታ ፖወር እንደነበረሩም ጨምራ አስታውሳለች፡፡
የዚህ አይነት በሀሰት መረጃ ላይ የተመሰረቱ ዘገባዎች እና ሪፖርቶች ሀሰተኛ መረጃዎች ከማሰራጨት ያለፈ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመቅረፍ አያስችሉም በማለትም ትገልጻለች።
እነዚህ ሁነቶች ሁሉ በጊዜያቸው እየከሰሙ ሲሄዱባቸው ሀምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም እምንስቲ ሌላ ድብቅ ዓላማን ያዘለ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች እየታደኑ እየታሰሩ ነው የሚል ሪፖርት ይዞ ብቅ ማለቱን አስታውሳ ይህም የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም የተጀመረ ኦፕሬሽን ነው የሚል ሲሆን በሪፖርቱ ላይ የተያያዘው ፎቶ ግን አንድ ፖሊስ ጥቂት ሰዎችን ሲያነጋግር የሚያሳይ እንደነበር ገልጻለች።
ከሰዓታት በኋላ ግን የታየው ፎቶ በፖሊስ ጣቢያ በር ላይ ሰዎች ሲገቡ የሚደረግ መደበኛ ፍተሻ እንደሆነ ፎቶውን ያነሳው ባለሙያ አማኑኤል ስለሺ ማጋለጡን አስታውሳለች፡፡
በዚህም እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ክስ ለማቅረብ የሚያስችላቸውን ዘገባ እና ሪፖርት በተናበበ መልኩ ሲሰሩ እንደነበር ማሳያ ነው ብላለች።
ጋዜጠኛ ፍራንሲስኮ የተራድኦ ድርጅቶቹ የከፈቱት ጦርነት በማለት ያቀረበችው ፅሁፏ በኢትዮጵያ እየሆነ ባለው ተጨባጭ ሐቅ ዙሪያ በአንድ በኩል ተቋማቱ ከምዕራባዊያን ብዙሃን መገናኛዎች ጋር ተናበው የሚተገብሩትን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አጋልጣለች፡፡