>

የዓለማየሁ እሸቴ የወርቃማው ዘመን ታዝታዎች ....!!! (ማእረግ ጌታቸው)

የዓለማየሁ እሸቴ የወርቃማው ዘመን ታዝታዎች ….!!!

ማእረግ ጌታቸው

አሜሪካ ገብተው የሆሊውድ ፊልም ተዋናይ መሆን የፈለጉት ጓደኛሞች አዲስ አበባን ተሰናብተው ምጽዋ ደርሰዋል፡፡ የያኔዎቹ ተስፈኞች ምጽዋ ገብተው ሳይጐበኟት ሊሰናበቷት  አልፈለጉም፡፡ ያረፉበትን ቤት ለቀው ማምሻውን በቀይ ባህር ነፋሻማ አየር ታጅበው ቶሪኖ የምሽት ክበብ ገቡ፡፡
 ቤቱ በሰዎች ተሞልቷል፡፡ የመርከባቸውን መልህቅ ጥለው አዳራቸውን በምሽት ቤቱ ያደረጉ የውጭ ሐገር ሰዎች እዚህም እዛም ከሙዚቃው ጋር ይወዛወዛሉ ፡፡ ሆሊውድን ሊቀላቀሉ  ለሸገር ጀርባ የሰጡት  ወጣቶችም  ለባህር ዳርቻዋ ከተማ አዲስ አይመስሉም ፡፡ በመጣው የውጭ ሙዚቃ ሁሉ አብረው ይደንሳሉ፡፡
 የኤልቪስ ፕሪስሊ ሙዚቃ ከፍ ብሎ እየተደመጠ ነው፡፡ የዳንስ ሰገነቱ ላይ ያለው ታዳጊ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል :: ዳንሱም ግጥሙንም እኩል ያስኬደዋል ::ይህ የገረማቸው የምሽት ክበቧ ታዳሚዎች በዚህ ሰው ተገርመው ሲመለከቱት ቢቆዩም ግብፃዊያኑ ግን አይተውት ዝም ሊሉ አልፈለጉም፡፡ ከሙዚቃው በኋላ ጠርተው አናገሩት፡፡ የምጽዋ ልጅ አለመሆኑን ነገራቸው :: ሆሊውድ ውስጥ የፊልም ተዋናይ ለመሆን ፈልጐ ከአዲስ አበባ ጠፍቶ መምጣቱን ገለፀላቸው፡፡
ግብፃዊያኑ መርከበኞች የሱን ምኞት የራሳቸው አደረጉት ፡፡ከጓደኛህ ጋር ሎሳንጀለስ ድረስ እንወስድሀለን አሉት ፡፡ ሩቅ የመሰለው ምኞት  ከንጋቱ ወገግታ ጋር አብሮ ሊፈካ ተቃረበ :: በቀጣይ ቀን ከግብፃዊያኑ ካፒቴኖች ጋር የሚገናኝበትን ሰዓት ውስኖ ከስደት ወዳጁ ጋር ወደ ክፍሉ ተመለሰ ::
የዓለማየሁ እሸቴን ህልም የምትፈታው  ዕቃ ጫኟ  መርከብ“ሳሂካ” ትባላለች :: የጉዞ ሰዓቷ ደርሷል :: ካፒቴኗ  ባልደርቦቹን  አሁንም አሁንም ይጠይቃል :: ፀጉረ ሉጫ የጠይም መለሎ ወጣት  ተሳፈረ ?ይላቸውል :: ምላሻቸው  አልምጣም የሚል ነው ::“ሳሂካ” መልህቋን አንስታ የአሜሪካ ጉዞዋን አንድ አለች፡፡ እነዚያ ሆሊውድን ናፍቀው ምጽዋ የደረሱ ወጣቶች ግን በፖሊስ እጅ  ነበሩ ፡፡
ነገሩን ለማጣራት ሲሞክሩ ዓለማየሁን የሚያውቅ ዘመድ ወደ አሜሪካ ከማያውቀው ሰው ጋር ሊጓዝ መሆኑን ሰምቶ ለፖሊስ አመልክቶ መሆኑ ተነገራቸው ፡፡  ብዙ አልቆዩም :: የልጅነት አምሮታቸውን እርም ብለው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ ::
1934 ዓ.ም ሰኔ 10 ቀን ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢየተወለደው ዓለማየሁ እሸቴ ገና በልጅነት ዘመኑ እናት እና አባቱ ፍች በመፈፀማቸው ያደገው አባቱ ቤት ነው ፡፡ ለዚሀ ደግሞ ምክንያቱ አባት ልጃቸውን በወይዘሮ በላይነሽ ዮሴፍ እጅ እንዲያድግ አለመፈለጋቸው ነበር  ፡፡ በ1940ዎች መባቻ እንዳብዛኛው የዘመኑ ሕፃናት የአብነት ትምህርትን አሀዱ ብሎ የጀመረው ዓለማየሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ ዘመናዊ ትምህርት እንዲከታተል በመፈለጋቸው የፈረንሳይኛ ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ ተመዘገበ፡፡
 ነገር ግን  በዚህ ትምህርት ቤት የቆየው ለወራት ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ፈረንሳይኛ ከማወቅ ይልቅ አረብኛ መማር የተሻለ ነው የሚል ምክርን የሰሙት አባቱ አቶ እሸቴ  አንዳርጌ ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንስ አስወጥተው ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤት  አስገቡት ፡፡
የኢትዮጵያዊው ኤልቪስ የማይደበዝዝ ትዝታ አንዱ መገኛም ዑመር ስማትር ትምህርት ቤት ነው ::ትምህርት ቤት ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ቤታቸው በሰዎች ተጨናንቆ ይመለከታል፡፡ የያኔው ብላቴና ነገሩ ባይገባውም እንደ ሁልጊዜው ሁሉ በቤቱ የተገኙትን እንግዶች ሰላምታ እየሰጠ አለፈ፡:
ከእነዚህ መኃል ግን አንደኛዋ ሴት በአፍታ ሰላምታ የምትለየው አልሆነችም :: ዓይኖቿ እምባ አዝለው ደጋግማ  አቀፈችው ::እንግዶቹ  ዓለማየሁን እናትህ እኮ ናት በደንብ ሰላም በላት እንጂ አሉት ::ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቱ ጋር ተዋወቀ፡፡ ይህ ትውውቅ ግን ብዙ የዘለቀ አልነበረም፡፡ ወይዘሮ በላይነሽ ተመልሳ ወደ ቤቷ አቀናች፡፡ ብላቴናውም  ዳግሞ እናቱን መናፈቅ ጀመረ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት የተከታተለው ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ  የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰደው በአርበኞች ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ታዳጊው ከአንድ የትምህርት ምእራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ የተላለፈበት ብቻ ሳይሆን ከያኒው ዓለማየሁ እሸቴ እየመጣ  መሆኑንም  ያበሰረ  ነው ::በ1951 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ የወላጆች በዓል ላይ ኢትዮጵያዊው ኤሊቪስና  ጓደኞቹ የእንጨት ጊታር ይዘው መሬት ላይ እየተንፈራፈሩ በቴሌቭዥን እንዳዮቸው ሙዚቀኞች የተዘጋጁበትን ዜማ አቀረቡ ፡፡
ዓለማየሁ በአብዮት ቅርጽ  የወደቀ እንጨትን ጊታር ባደረጉ እኮዮቹ ታጅቦ መደረክ ላይ ይሰየም እንጅ የእሱ ታዋቂነት ምንጭ ግን ተዋናይነቱ ነበር  “ኪንግ ሪቻርድስ ኤንድ ዘ አኖውን ኪንግ” የተባለው በትምህርት ቤት ቆይታው የተወነበት ቴአትርም  ዓለማየሁን ብዙ እንዲያስብ አድርጐታል፡፡ ፡፡በዚህ የተነሳም ከትምህርት እየቀረ ዘመነኞቹን ፊልሞች መመልከት አዘውተረ፡፡ …..
(በቅርቡ ለንባብ ከሚበቃው “ጠመንጃና ሙዚቃ-የወርቃማው ዘመን ታዝታዎች  “መጽሐፍ የተቀነጨበ )
ጋሼ ሕይወትክን አንብቤ ታሪክህን ላወራ ስዘጋጅ ሞት ቀደመኝ !! በሰላም እረፍ ::
Filed in: Amharic