>

"የኦሮምኛ ቋንቋ እንዳይጠፋህ አደራ....!!!" የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት

“የኦሮምኛ ቋንቋ እንዳይጠፋህ አደራ….!!!”
የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት
ዮሀንስ መኮንን

ራስ አዳል በሰኔ ወር 1871 ዓ.ም. ወደምሥራቅ ወለጋ ሲዘምቱ በዘመቻው ተሳታፊ የነበሩት የሌምቱ ጎሹ ከምሥራቅ ወለጋ (አካባቢው ያን ጊዜ ሌምቱ ነበር የሚባለው) ስምንት የኦሮሞ ሕጻናትን (ሁሉም ወንዶች ናቸው) ወደ ደብረ ጽሙና (ጎጃም) ይዘው ተመለሱ። የልጆቹ ስም አጋ፣ ደንገላ፣ ፈይሳ፣ ዋቅ ጅራ፣ ዋቅ ኬኔ፣ ጅራታ፣ አገሾ፣ እና ነገሮ ይባላል።
እነኚህ ሕጻናት ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ ከስምንቱ ሕጻናት አንዱ ነገሮ ዋቅጅራ (በኋላ ተክለ ኢየሱስ የተባሉት) ስለ ሕጻናቱ ባቆዩልን ማስታወሻ እንዲህ ይላሉ። “ሕጻናቱ እንደየ እድላቸው በተለያየ ሙያ ሲሰማሩ ጅራታ ደብረ ጽሙና ተምሮ ወልደሰንበት በሚል ሥመ ክርስትናው ቄስ ሲሆን ነገሮ ግን የቤተክህነቱን ትምህርት ተምሮ የተዋጣለት ሰዓሊ ሆነ” ብለዋል።
ነገሮ ዋቅጅራ (ተክለ ኢየሱስ የተባሉት)
የታወቁ ሊቅ ሆነው ከሥዕል በተጨማሪ ጎጃምን ማዕከል አድርገው የኢትዮጵያ ታሪክን ጽፈዋል። ይህንኑ ጽሑፋቸውን ዶ/ር ሥርግው ገላው ሀተታ ጨምረውበት በ2002 ዓ.ም. አሳትመውላቸዋል።
ነገሮ ዋቅጅራ (ተክለ ኢየሱስ) የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ስዕሎችን የሳሉ ሲሆን ከእነኚህም የዲማ ጊዮርጊስ እና የደብረ ማርቆስ አብያተክርስቲያናት ይገኙባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደብረ ማርቆስን ዝነኛውን ወንጌል ሥዕላት ያዘጋጁት እርሳቸው ናቸው።
ነገሮ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ዘንድ እጅግ የተከበሩ ባለሟል ስለነበሩ ከንጉሡ ጋር ማዕድ ሲቀመጡ እርሳቸው ብቻ የሚጠጡበት የተለየ ዋንጫ ነበራቸው። በዋንጫው ላይ “ዝ ኮልባ ዘአለቃ ተክሌ ዘወሃቦ ንጉሥ ተክለሃይማኖት” (ይህ ዋንጫ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ለተክሌ የሰጡት ነው) የሚል የተጻፈበት ነበር።
በ1881 ዓ.ም. የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የሸዋውን ንጉሥ ምኒልክን ለመገናኘት ወደ በጌምድር በሄዱበት ጊዜ ለንጉሥ ምኒልክ የሚሆነውን የሥዕል ስጦታ ያዘጋጁት ነገሮ ዋቅጅራ ነበሩ።
ነገሮ በኋላ ላይ #የቀዎ_ጊዮርጊስ_አለቃ ሆነው ሲሾሙ የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የሚከተለውን ምክር እንደሰጧቸው እራሳቸው ነገሮ ዋቅጅራ (አለቃ ተክለኢየሱስ) እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። “በዚያ ሆነህ (ቅዱሳት) ስዕላትን እየሳልክ ዘመዶችህን (ኦሮሞዎችን) ታስተምርልኛለህ። (ለዚሁ እንዲረዳህ) ግን የኦሮምኛ ቋንቋ እንዳይጠፋህ ይሁን”
ምን ለማለት ፈልጌ ነው!
(moral of the story)!
እንኳንስ ዛሬ ዓለም በሰለጠነበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይቅር እና ከ130 ዓመታት በፊት የተማሩ ኦሮሞዎች ያውም ጎጃም ላይ ቀሳውስት እና የደብር አለቆች እንዳይሆኑ ክልከላ አልነበረባቸውም። እንዲያውም ለስብከተ ወንጌል እንዲጠቅማቸው ኦሮሚፋ ቋንቋቸውን እንዳይረሱት ነገሥታቱ በአደራ ጭምር ያሳስቧቸው እንደነበር ታሪክ ሠፍረው እና ቆጥረው ያቆዩልን ኦሮሞዎቹ እነ ነገሮ ዋቅጅራ ናቸው።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን በዘመናችን ጠማማ ጠማማውን የታሪካችንን ክፍል እያፈላለጉ ቀንድ እና ጅራት እያበቀሉ የሚተርኩልን “ዐዋቂዎች” ስለበዙ ይህን የመሳሰሉ ድንቅ ታሪኮቻችን ሰሚ ጆሮ አስተዋይ አእምሮ አላገኙም።
Filed in: Amharic