>

የኢትዮጵያው ሕገመንግስት አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ መዘዝ ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያው ሕገመንግስት አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ መዘዝ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

‹‹ እንደ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ዶክተር መኮንን ቢሻው፣ፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ፣ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ዶክተር ልጅ ልኡል አስራተ ካሳ ፣የአለም ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ፣ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ጋዜጠኛ ትእግስት አብርሃም፣ ጋሼ ክበበው( ነብሳቸው ከደጋጎቹ እነኛ የዋሃ አባቶቻችን ጎን ትረፍ)፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ዶክተር በፍቃዱ፣ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ፕሮፎፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ፣አቶ አበበ ወርቄ፣ አንጋፋዎቹ ጋዜጠኞች ፣ ጋሼ ጎሹ ሞገስ፣ጋሼ ማእረጉ በዛብህ፣ጋሼ ክፍሌ ሙላት፣ጋሼ ከፍያለው ማሞ፣፣ ጋሼ ጸጋዬ ብሩ ፣ጋሼ ደርበው ተመስገን፣ጋዜጠኛ ታዬ በላቸው፣አረጋ ወልደቂርቆስ፣ልበ ሙሉው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ኤሊያስ እና ትንታጉ ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገስ ወዘተ ወዘተ  የመሰሉ ስመጥር ኢትዮጵያዊ ምሁራኖች እና ጋዜጠኞች አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል ድረስ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1994 የተዘጋጀው የኢትዮጵያው ህገመንግስት ተፈጥሯዊ ለሆነው የኢትዮጵያ አንድነት እንደማይበጅ ወይም ተጻራሪ እንደሆነ ጽፈዋል፣አስተምረዋል፡፡ የእነርሱም ሆነ የሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስኳቸው ኢትዮጵያውያን እሪ ኡ ኡ ጩሀት ግን ከመንግስትም ሆነ ከጎሳ ፖለቲከኞች አኳያ ሰሚ  አላገኘም፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ እንደውም ከፋሺስት ጣሊያን በመለጠቅ የጎሳ ፖለቲካን መርዝ በኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ላይ በመርጨት ስር እንዲሰድ ያደረገው የፋሺስት ጣሊያን የመንፈስ ልጅ የሆነው ግፈኛው የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ በስልጣን ዘመኑ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያው ህገ መንግስት የሚሻሻለው በመካነ መቃብሬ ላይ ነው ሲል ነበር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተዘባበተው፡፡

     በነገራችን ላይ ይህ አጭር ጽሁፍ የሕግ ትንተና የሚሰጥበት አይደለም፡፡ በማላውቀው የህግ እውቀት ገብቼ መዘባረቅ አልፈልግም፡፡ የኢትዮጵያን ህገ መንግስት ከአንቀጽ ‹‹39›› አኳያ የራሴን የግል ምልከታ ወይም አስተያየት ነው ለማቅረብ የምሞክረው፡፡

መግቢያ

ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በአንድ ላይ ብንደባልቃቸው ወይም ብናስቀምጣቸው ተፈጥሯአዊ አንድነት ማግኘት የሚቻል አይሆንም፡፡ ሀይድሮጅን እና ኦክስጅን የተባሉ ንጥረ ነገሮች ሲዋሃዱ ውሃ የተሰኘ እጅግ ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆነውን ውሃ እንደሚያስገኙልን ሁሉ የጤፍና የስንዴ ዱቄትን ስንደባልቅ የምናገኘው ውጤት ከስንዴና ጤፍ ተፈጥሯዊ ባህሪ ያፈነገጠ ሌላ አዲስ ድብልቅ ውህድ የእህል አይነት ይገኛል፡፡  እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ የተለያዩ አንድ የነበሩትን ነገሮች በማዋሃድ ማለትም አንድ ብቻ የነበረውን ከሌላው ጋር በማዋሃድ ሌላ የሁለት ነገሮች ድምር የሆነ ሌላ ቁስ ወይም የምግብ አይነት እናገኛለን፡፡ እንዲህ አይነት አሰራር የፋብሪካ ምርት ውጤቶችን ያስታውሰናል፡፡ ይህም ማለት ውጤቱ ሰው ሰራሽ ወይም አርቴፊሻል ነው፡፡ ለአብነት ያህል መኪና፣ሰዓት ወይም ቤት በእንዲህ አይነት ሰው ሰራስ ዘዴዎች ከተሰሩ በኋላ ነው ለሰው ልጆች ጥቅም የሚሰጡት፡፡

   ሆኖም ግን ይሁንና ከላይ ከጠቀስኩት ሃሳብ በተቃረነ መልኩ ነው ተፈጥሯዊ  አንድነት እውን ሊሆን የሚቻለው፡፡ ለአብነት ያህል የተክሎችን አበቃቀል ብንመለከት አስገራሚ ነው፡፡ አንድ የተክል አይነት ከማደጉ በፊት ዘሩ ነው የሚዘራው ፡፡ ዘሩ ተዘርቶ ካለቀ በኋላ በአየር ውሃና፣ አፈር አመሃኝነት ይበቅላል ያድጋል፡፡ አንድን ተክል የሚገነቡት ፍሬው፣ቅጠሉ፣ግንዱ ሳይሆኑ ዘሩ ነው፡፡ ዛፍም ሆነ የምግብ እህሎች የሚበቅሉትና የሚያድጉት በተፈጥሮ ነው፡፡ ነጭ ባህር ዛፍ የምናገኘው የነጭ ባህር ዛፍ ከተከልን በኋላ ሲሆን፣የጤፍ ምርትም የምናገኘው የጤፍ ዘር ከዘራን በኋላ ይሆናል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ አንድነት ነው፡፡ የጤፍና ስንዴን ዘሮች በመደባለቅ ብንዘራ የምናገኘው ምርት ተፈጥሯዊውን ጤፍ ወይም የስንዴ ምርት አይሰጠንም፡፡ የሁለቱም ሰብሎች ተፈጥሯዊ አንድነት ይናጋል፡፡ አንድ ተክል የተለያዩ ክፍሎች ያሉትና የራሳቸው ተግባር ያላቸው ናቸው፡፡ የተክሉ ስር፣ግንድ፣ቅጠልና ቅርንጫፎች የየራሳቸው ተግባር አላቸው፡፡ ተክሉ ግን ተክል የሆነው በመጀመሪያ በተፈጥሯዊ ሂደት ዘር ከተዘራ በኋላ መሆኑን አንባቢው ልብ ሊለው ይገባል፡፡ የአንዱ የተክል ክፍል መኖር ለሌላው ይበጃል፡፡ አንዱ የተክል ክፍል ከሌለ ሌላው የለም፡፡ የሰው ልጅ ህይወትም ተመሳሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር የሚመጣው ከተወለደ በኋላ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ በሰው ልጅ አካል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች የራሳቸው ተግባር አላቸው፡፡ ለአብነት ያህል የደም ስርጭትን  ተግባር በትክክል የሚያከናውኑ ደም ቅዳ እና ደም መልስ የሚባሉ ክፍሎች አሉ፡፡ እነኚህ በሰውነታችን ውስጥ የደም ዝውውሩ በትክክል እንዲካሄድ ይረዱናል፡፡ ሳምባችን ደግሞ ንጹህ አየር( ኦክሲጅን) ወደ ሰውነታችን ውስጥ፣የተቃጠለውን አየር ( ካርቦንዳይ ኦክሳይድ) ያስወጣልናል፡፡ በነገራችን ላይ አንዱ የሰውነት ክፍላችን ጤናማ መሆን በሰውነታችን ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ያግዛል፡፡ የአንዱ መኖር ለሌላ ይበጃል፡፡ ዛሬ በሰለጠነው ዘመን ፣ በሰለጠነው አለም በሰው ሰራሽ ዘዴ እንሰሳቶችን  እና ተክሎችን ማዳቀል፣ መውለድ የማይችሉ እናቶች( በተፈጥሮ መሃን የሆኑ) በሰው ሰራሽ ዘዴ እንዲወልዱ ማድረግ መቻሉን እንሰማለን፡፡ ይህ ግን እውነተኛ አንድነትን አይፈጥርም፡፡ የእናትና የአባት፣ፍቅር፣የልጁም ፍቅር ሊሆን ይቻለዋል፣ እንደ ተፈጥሯዊ እባትና እናት ፍቅር ወይም የልጅ ፍቅር አይነት ላይሆን ይቻለዋል፡፡ነውም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ በተፈጥሮ ከአንድ እናትና አባት የሚወለድ ልጅ ከወላጆቹ ጋር የሚኖረው ተፈጥሯዊው አንድነቱ እጅጉን የጠበቀ ሊሆን ይቻለዋል፡፡

ነብሱን ይማረውና የፖሊስ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ድምጻዊና የህግ ባለሙያ የነበረው ሽቅርቅሩ ሻለቃ ወጋየሁ ንጋቱ ዘጠኝ ወር ሙሉ ተሸክማ፣ተጨንቃ ወልዳ በምጥ ታማ………ብሎ አዚሞ አንዳለፈው በቤተሰብ መሃል እውነተኛ አንድነቱ ከተፈጥሮ የሚመነጭ ነው፡፡

አንድ ትክክለኛ ሰው፣የአይምሮው ሚዛኑ ያልተሰበረ፣የሞራልና ህሊና ሰው፣ ነገሮችን ማገናዘብ የሚችል ሰው በወያኔ አጋፋሪነት እባ በሸሪኮቹ የጎሳ ፖለቲከኞች ኤርትራ ተሰነይ ከተማ ተረቆ የጸደቀው የኢትዮጵያው ህገመንግስት ከተፈጥሮ አንድነት ያፈነገጠ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከብዙ ሀገራት ህገመንግስት ተፈጥሯዊ ባህሪ ያፈነገጠ ነው፡፡ እዚች ነጥብ ላይ ኢትዮጵያዊ የህገመንግስት አዋቂዎች አስተያየት እንድትሰጡበት ስጋብዝ በአክብሮት ይሆናል፡፡ እስቲ በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ የተጻፈውን አረፍተ ነገር በአንክሮ ሁላችሁም አንብቡት፡፡ 

የኢትዮጵያው ህገመንግስት መግቢያው ላይ የተጻፈው ከተፈጠሯዊው አንድነት ያፈነገጠ ነው፡፡ እጠቀሳለሁ፡-

‹‹ እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ብሔረሰብና ብሔረሰብ የሚል ነው›› በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው የበለጠ ገላጭ በመሆኑ እንደሚከተለው አሰፍረዋለሁ፡፡

‹‹ “We, the Nations, Nationalities and Peoples of Ethiopia ›› 

በማናቸውም መስፈርት ከላይ የሰፈረው አረፍተ ነገር ከተፈጥሯዊ አንድነት በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ ለአንድነት ቅድሚያ የሚሰጥ አይደለም፡፡

እርግጥ ነው፣ ከተፈጥሯዊ አንድነት ባፈነገጠ መልኩ በፌዴራል ስርአቱ ስር ያሉት የተለያዩ ክልሎች ወይም ህዝቦች፣ብሔርና ብሔረሰቦች ዲሞክራቲክ፣የሰብዓዊ መብቶችና የህግ የበላይነት የሰፈነባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን ይገነባሉ የሚል ጽንሰ ሃሳብን የያዘ አረፍተ ነገር በህገመንግስቱ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ህገመንግስቱ የኢትዮጵያን የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ፍንትው አድርጎ ሳያሳየን ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ስምምነትና ይሁንታ እውን ትሆናለች የሚል መንፈስ ያለው መልእክት ይነግረናል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ያሉት ነገዶች፣ጎሳዎችና ብሔሮች ለብዙ ሺህ አመታት አብረው ተጋብተው ተዋልደው በአንድነት መኖራቸውን መግለጽ አልተፈለገም፡፡ ለምን ? ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ አዲስ የፖለቲካ ማህበረሰብ አልተገኘም፡፡ ኢትዮጵያ ከብዙ ሺህ አመታት በፊት የተገነባች ሀገር ናት፡፡ ህዝቧም ለብዙ ዘመናት በአንድነት የኖረ ነው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የአንድ ተክል ክፍሎች የራሳቸው ተግባርና ነጻነት እንዳላቸው፣አንዱ በአንዱ ተግባር ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ከእነ ልዩነቱ ለዘመናት በአንድነት የኖረ ነው፡፡ የአንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ክፍል መጎዳት፣መታመም ሌላውን ይጎዳል፡፡ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ተግባር እያከናወኑ መኖር ከቻሉ ተፈጥሯዊ አንድነታቸውን ማስከበር ይቻላቸዋል፡፡ ከተፈጥሯዊው ሂደት በመውጣት አንድ አካል የነበሩት ልጆቿ ወደፊት አንድ ለመሆን እንነጋገራለን የሚሉ ከሆነ ከተፈጥሮ ሂደቱ የሚያፈነግጡ ይመስለኛል፡፡ መንገዳቸው ሰው ሰራሽ ነው የሚሆነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸውን አምነው ከተቀበሉ በኋላ፣ አንደኛው በሌላኛው ወንድሙ ላይ ላደረሰው በደል፣ሌላኛው፣ በቀረው ላይ ላደረሰው በደል ግን ቁጭ ብሎ በመነጋገር፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ እርቅ በማድረግ ተፈጥሯዊ አንድነትን ማስጠበቅ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ነገድ፣ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ነጻነቱ የተጠበቀ፣ፍትህና ነጻነት ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ አንደኛው የበላይ ሌላው የበይ ተመልካች ወይም ባይተዋር የሆነባት ሀገር መሆን የለባትም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ የነጻነት ምድር መሆን አለባት፡፡ ለአንድ ወገን ያደላ ቃል ኪዳን ወይም ህግ መፍትሔ የለውም፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ህገመንግስት ‹‹አንቀጽ 39›› ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ አንቀጽ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መገንጠል ለሚፈልጉ የተገንጣይ ሀይሎች መብትን የሚሰጥ ነው፡፡ ለሁሉም የጎሳ ቡድኖች የራስን እድል በራስ መወሰን በሚል የኮሚንስቶች እሳቤ እስከ መገንጠል መብት ድረስ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ የአንድነት ሀይሎች መብት ምን እንደሆነ አላሰፈረም፡፡ በዚህ ህገመንግስት በተለይም የውሃዳን ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ምን እንደሆነ በቅጡ አልተጠቀሰም፡፡ የሌሎች የህብረቱ አካሎች ፍላጎት ሳይመረመር፣ሳይጠየቅ አንድ የጎሳ ቡድን እገነጠላለሁ ብሎ ቢነሳ የሚያስቆመው ያለ አይመስልም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ አንድነት በእጅጉ የሚጎዳው የህገመንግስቱ ‹‹አንቀጽ39›› በተመለከተ የኢትዮጵያ የህግ አዋቂዎች መክረው ዘክረውበት የሚሻሻልበት መንገድ እንዲፈለግ እንማጸናለን፡፡ የዚህ ህገመንግስት  አንቀጽ 39 እጅጉን አስገራሚና አስጨናቂ ነው፡፡ በየትኛውም የአለም ሀገራት ህገመንግስት ውስጥ የማይገኘው በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ብቻ የሰፈረው አደገኛ አንቀጽ እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡

Article 39. Rights of Nations, Nationalities, and Peoples

  1. Every Nation, Nationality and People in Ethiopia has an unconditional right to self-determination, including the right to secession.

 

ስምምነት እና ሀገርን መገንባት

እንደ ጎጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1994 የወጣው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ከቀደሙት የኢትዮጵያ ህገ መንግስቶች ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር በአሸናፊዎች ይሁንታ ወይም ስምምነት እውን መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት አሸናፊዎቹ የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የጎሳ ፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ለራሳቸው በሚጠቅም መልኩ አዘጋጅተው ያጸደቁት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከማህበረሰብ ውል ጋር ወይም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበት ስለመሆኑ መመርመሩ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ወያኔ ኢህአዲግ ከአጋሮቹ ጋር ገቢራዊ ያደረገው ህገመንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ያለመከረበት ነው፡፡ወይም በነጻነት እንዲወያይ ሃሳቡን እንዲያቀርብ አልተፈቀደለትም፡፡ በሌላ በኩል እንደ ኢህአፓ፣ ኢዲሀቅና የመሳሰሉት የአንድነት ሀይሎች በህገመንግስቱ ረቂቅ እንዲካፈሉና እንዲሳተፉ በአገዛዙ አልተጋበዙም ነበር፡፡ ይህን ህገመንግስት በስምምነት ያጸደቁት የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ኮንትራታቸወን ሲፈራረሙ በፈለጉት ግዜም ለመለያየት ወስነዋል፡፡ ይህም ማለት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ላይ ያሰፈሩት እስከ መገንጠል የሚለው አንቀጽ ፍቺ ሲፈልጉ ፍቺውን እንዲያቀልላቸው እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ነጻነት የሌለበት ስምምነት መጨረሻው አያምርም፡፡ በአንድ ሀገር ላይ የማይጠገን ስብራት ትቶ ነው የሚያልፈው፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሲጸድቅ በኢትዮጵያ የሚገኙ ነገዶች፣ጎሳዎችና ብሄረሰቦች ተወካዮች የተባሉ ግለሰቦች የተስማሙ ቢሆንም‹ አጠቃላይ ምልአተ ህዝቡ በነጻነት አለመከረበትም ነበር፡፡ ስለሆነም የአንድ ሀገር ህገመንግስት የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቅ መሆን አለበት እንጂ የህዝቡን አንድነት የሚያላላ መሆን አይገባውም፡፡ የአንድ ሀገር የህብረተሰብ ስምምነት ሰነድ ( social contract) ከሌሎች ተራ ስምምነቶች እጅጉን የተለየ ነው፡፡ በሁሉም ሰዎች የሚደረገው ስምምነት እንደ አንድ ሰው ይሁንታ የሚቆጠር ነው፡፡ ሰምምነቱ አንድ አካል የሚፈጥር ነው፡፡ ብዙዎች አንድ ላይ ሆነው አንድነቷ የተተበቀ ሀገር ይመሰርታሉ፡፡ ስለሆነም የማህበረሰብ ስምምነት ነጻነት ያስፈልገዋል፣ ብርቱ ጥንቃቄም ይሻል፡፡ ይህ ስምምነት ለጋራ ብልጽግና ሲባል ነው ገቢራዊ ሊሆን የሚቻለው፡፡ ሎኪ የተባለው የህግ ፈላስፋ ስለ ማህበራዊ ኮንትራት በእንግሊዝኛ የጻፈው የበለጠ ገላጭ ስለሆነ እንደሚከተለው እጠቅሳለሁ፡፡

“the agreement which every one has with the rest to incorporate and act as one body, and so be one distinct common wealthy

Developing further his idea, Locke adds that the society acts as one body “only by the will and determination of the majority,” for the obvious reason that a truly united body is unable to split so that any division has nowhere to go except in the direction imparted by the greater force.

ስለ ማህበረሰብ ኮንትራት የማይለወጥ ተፈጥሮ በተመለከተ በብዙ የተመራመሩት እና የጻፉት ሆብስ እና ሩሶ (Hobbes and Rousseau) ናቸው፡፡

ሩሶ እንደጻፈው ከሆነ የማህበረሰብ ስምምነት መሰረቱ ስልጣን በአንድ ሰው መዳፍ ስር ወይም የሰዎች ስብስብ ስር ሲወድቅ  የሚል ነው፡፡ የአንድነት መሰረቱ ያልተገደበ የአንድ ሰው ስልጣን ነው፡፡

የሆብስ ፍልስፍና መሰረቱ ደግሞ ከሩሶ የፍልስፍና መሰረት ይለያል፡፡ በሩሶ ጥናት መሰረት ‹‹ የአንድ ሀገር አንድነት እውን የሚሆነው አንድን ሰው የበለጠ ሀይለኛ ስልጣን ያለው እንዲሆን በማድረግ ፣ በመሪው ይሁንታ ብቻ አይደለም፡፡ የአንድ ሀገር አንድነት ሊጸና የሚቻለው በምእላተ ህዝቡ አጠቃላይ ፍላጎትና ስምምነት ነው፡፡ በአጭሩ ለሩሶ ማህበራዊ ኮንትራት ማለት ስምምነቱ በማህበረሰቡ ምልአተ ውሳኔ እውን የሚሆን ነው፡፡

The irreversible nature of the social contract is even more forcefully upheld by Hobbes and Rousseau. For the former, the agreement reached by the contractors postulates that they confer “all their power and strength upon one man, or upon one assembly of men,” the expectation being that the institution of an absolute, unchallenged power will turn the consent of the members into a “real unity of them all, in one and the same person.” The monopoly of all power by one man, what else could it entail but the tight unification of the society under one will? As to Rousseau, the unifying forces is not so much the empowered individual as the general will, which is the collective being generated by the contract and is always operating under the imperative of the common good.

የኢትዮጵያ ኮንዲሽናል (Conditional ) ህብረት

ከላይ በስም ያሰፈርኳቸው ተጠባቢዎች ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ‹‹ ስምምነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ከተፈለገ  በማህበረሰቡ ላይ የአንድ ግለሰብ  ስልጣን መመንጨት ያለበት በብዙሃኑ የድምጽ ውሳኔ መሆን አለበት፡፡ በአጠቃላይ በነጻነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት፣ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች እኩል ፍትህ የሚሰጥ፣ የሚሰራና የተረጋጋ የፖለቲካ ማህበረሰብ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት ቁምነገሮችን ገቢራዊ ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያው ህገ መንግስት በርካታ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ የወያኔ ቡድን ከአጋሮቹ የጎሳ ድርጅቶች በተለይም ከኦነግ ጋር ስምምነት በማድረግ፣በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ ተመስርቶ ነበር የህገመንግስቱን ሰነድ ያጸደቀው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ህገመንግስት በብዙሃን ድምጽ  ( majority rul ሲሆን የአናሳ ድምጽ መብትን ችላ ያለ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ፓርላማ ሙሉበሙሉ በሚመስል መልኩ ወንበሩን የተቆጣጠረው የገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ( ቢያንስ አሁን ድረስ ይህ ገቢራዊ ሆኖ ይታያል፡፡) የሀገሪቱ እጣ ፈንታ በዋነኝነት የሚወሰነው በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናል፡፡

ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ከህገመንግስቱ ተቃራኒ መንገድ ተከትለው የነበረ ቢሆንም፣ የሚያስገርም አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለስልጣናቸው ሲሉ በኢትዮጵያ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም የሚፈቅድ ህግ በማንበራቸው ኢትዮጵያ ዛሬ ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ህገመንግስቱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ መዳኛው አልፋና ኦሜጋ የዜግነት ፖለቲካ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ህገመንግስት በዜግነት ፖለቲካ መሰረት ላይ መቆም አለበት ባይም ነኝ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ መቆም ያለበት ከጎሳ ፣ዘር ወይም ሀይማኖት ባሻግር ወይም ሁሉንም በእኩልነት መንፈስ ማገልገል በሚችለበት ሁኔታ  መቆም ያለበት ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት እውን ሎሆን የሚቻለው፡-

  • እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን ሲሆን
  • የህብረተሰብ ህመም ፈውስ ሲያገኝ
  • እኩልነትና ፍትህ ሲሰፍኑ እና
  • እውነተኛ ነጻነት እውን መሆን  ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራችን የመረረ ጥላቻ፣አብዮት፣የርስበርስ ጦርነት ወዘተ ወዘተ የምንፈልገውንና የምንመኘውን ዴሞክራሲ አላስገኘለንም፡፡ የሚያዋጣው ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ፣በሰለጠነ መንገድ መነጋገርና መወያየት ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የጋራ ሀገራችንን፣ቤታችንን በፍቅርና አንድነት መገንባቱ ይበጀናል፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ምስቅልቅሎሽ መሰረታዊ ችግር የሆነው የመሬት ፖሊሲ ሳይቀር በሰለጠነ መንገድ ሊሻሻል የሚቻለው  አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገመንግስት በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ መሻሻል ሲቻለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎች ፍላጎት የተመሰረተች ናት የሚል ጽንሰ ሃሳብ የያዘው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሁነኛ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባዋል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን የሚታዩት የኢትዮጵያ ችግሮች መነሻና መድረሻቸው የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡ በዚች ሀገር ላይ የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲን ለማሻሻል የፖለቲካ ፈቃደኝነት ቢታይ እና ገቢራዊ ቢሆን በርካታ የኢትዮጵያ ችግሮች እንደሚፈቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ምሁራን የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ 

ጎሰኝነትና አንድነት  (Ethnicity and Unity)

በነገራችን ላይ የህገመንግስት አዋቂዎች በተለይም የማህበራዊ ኮንትራት ንድፈ ሃሳብ ተጠባቢዎች ጥናታቸው የሚያተኩረው በግለሰቦች መብት ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በይበልጥ መብት የሚሰጠው ለጎሳዎች ነው፡፡ የግልሰብ መብት ላይ ትኩረት አላደረገም፡፡ በጎሳ በከፋፈላት ኢትዮጵያ ላይ መብትን የቸረው የክልሉ ባለቤት ለሚለው ጎሳ ነው፡፡ ለውህድ ኢትዮጵያውያን መብት የሚጨነቅ አይደለም፡፡ ወይም በህገመንግስቱ ውስጥ የውህዳን ኢትዮጵያውያን መብት በየትኛው አንቀጽ ውስጥ እንደሚገኝ አይታወቅም፡፡ አለ የምትሉ ካላችሁ አሳዩን፡፡ በነገራችን አንድ ራሱን በአንድ የጎሳ ከረጢት ውስጥ የዶለ ሰው ከሌሎች ራሳቸውን በሌላ ጎሳ ከረጢት ውስጥ ከዶለ ሰው ጋር ስለ ልዩነት እንጂ አንድነት የሚያውቀው ነገር አይኖርም፡፡ ራሱን በባህል፣ልምድ፣ቋንቋ፣ሀይማኖት ሳይቀር ለመለየት የሚዳክር አሳዛኝ ፍጡር ነው፡፡ ከጎሳ ማንነቱ ውጭ የሚታየው ሌላ አለም የለም፡፡ የጎሰኝነት እሳቤ በሰለጠነው አለም ብቻ ሳይሆን በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች እየከሰመ ከሄደ ረዥም አመታቶች የነጎዱ ቢሆንም በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ እያገነገነ መምጣቱ ሲስተዋል፡፡ ልብን ያደማል፡፡ አንገትንም ያስደፋል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ የግለሰቦች ህብረት ማለቴ ነው፡፡ የግለሰቦች ህብረት ማለት በተፈጥሮ ያገኙትን ነጻነት በሲቪል ነጻነት ለመተካት መንፈሳዊ ወኔ ሲታጠቁ የሚያሳይ ነው፡፡ ራሳቸውን አንድ አይነት ለሆነ ማንነት አሳልፈው አይሰጡም፡፡ ይህም ማለት ራሳቸውን በአንድ ጎሳ ማንነት ላይ አይሰቅሉም፡፡ ምንግዜም ቢሆን በህግ በተሰጠ ነጻነት ላይ የቆሙ ናቸው፡፡ በጎሰኝነት ፍልስፍና ማንነት የተመሰረተው በጎሳ ላይ ብቻ ነው፡፡ ጎሰኛ ሰው ማንነቱ የጎሳው አባልነቱ የሚሰጠው ማንነት ብቻ ነው፡፡ ከጎሳው ሀይማኖት፣ባህል፣ቋንቋ፣ልማድ፣ሙዚቃ…ወዘተ ወዘተ ውጭ የሚታየው አለም የለም፡፡ ከእርሱ ጎሳ ውጭ ያለው ሰው ሁሉ፣ ከእርሱ በተቃራኒ እንደሆነ ያስባል፡፡ ወደ ሄብረት፣ወደ አንድነት ለመምጣት በብዙ ይቸገራል፡፡የዜግነት ጽንሰ ሀሳብን ለመረዳት ይቸገራል ወይም ለማወቅ ፍላጎት የለውም፡፡

ይህ የሚያሳየን ቁምነገር ቢኖር፣እንደ ቁምነገር ከተቆጠረ ማለቴ ነው ጎሰኝነት ለብሔራዊ ጥምረት ወይም አንድነት ተግዳሮት ወይም ጋሬጣ እንደሆነ ነው፡፡ የሁሉም ጎሳዎች ወይም ነገዶች ወይም ብሔረሰቦች ባህል፣ቋንቋ፣ልምድ፣እምነት፣ሙዚቃ ወዘተ ወዘተ በእኩልነት መንፈስ በሆነበት ሁኔታ እንኳን ስለ አንድነት ለመጨነቅ የጎሰኝነት አስተሳሰብ የሚጋርድ ነው፡፡ ጎሰኞች በእኩልትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመስበክ እንኳን ሞራል የሌላቸው ናቸው፡፡

ህሊና የፈጠረባቸው የፖለቲካ ሰዎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ነገዶችና ጎሳዎች በሚኖሩባቸው ሀገራት

ዴሞክራሲን በማስፈን፣ፍትህን በማምጣት፣የሁሉንም ነገዶች ባህል እኩል በማክበር አንድነትን 

ማምጣት እንደሚቻል ያስተምራሉ፡፡ ለአብነት ያህል ካናዳ፣ቤልጂዬም፣ ስዊዘርላንድ እና ህንድ 

የሁሉንም ነገዶች ባህልን እኩል በማክበራቸው የየሀገራቸውን አንድነት ለማስከበር ችለዋል፡፡ 

በስም የተጠቀሱት ሀገራት የብዙ ነገዶች መኖሪያ ቢሆኑም ዴሞክራሲን በእውነት መሰረት ላይ 

በማቆማቸው ሀገራቸውን ወደ የላቀ የእድገት ደረጃ ላይ አድርሰዋል፡፡ በእርግጥ ካናዳ እና ቤልጂዬም

የብሔራዊ ጥምረት ተምሳሌቶች ሲሆኑ፣ ስዊዜርላንድ እና ህንድ ደግሞ በርካታ ነገዶችን በአንድነት 

በመያዝ ይታወቃሉ፡፡ ከእነርሱ በተቃረነ መልኩ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት አባል ሪፐብሊኮች የከሸፈ

የፌዴሬሽን ጥምረቶች ተምሳሌት ነበረች፡፡ የቀድሞዋን ሶቪዬት ህብረት ሞዴል የተከተለው የኢትዮጵያ 

የፌዴሬሽን የክልሎች ህብረት እጅጉን አሳሳቢ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው

ኢትዮጵያውያን የቀድሞዋን የፈረሰችውን ሶቪዬት ህብረት ሞዴል በመከተል ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ

በህገመንግስቷ ውስጥ እስከ መገንጠል የሚፈቅደው አንቀጽ በመስፈሩ ምክንያት የኢትዮጵያ 

መጻኢ እድል እጅጉን አሳሳቢ እንደሆነ የዘውትር ውትወቸው መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በነገራችን ላይ በተለይ ህንድ እና ስዊዘርላንድ በርካታ ነገዶች የሚኖሩባቸው ሀገር ሆነው ሳለ 

አንድነታቸውን ማስከበራቸው አስደናቂ ነው፡፡ በተለይም የህንዱ ብሔራዊ ኮንግሬስ ፓርቲ በቀደሙት 

አመታት ይህቺ የብዙ መቶ ሚሊዮኖች ህዝብ መኖሪያ ሀገር፣የብዙ መቶዎች ነገዶች ሀገር፣ 

ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሀይማኖቶች ተከታይ ሀገር፣ የብዙ ባህልና ሙዚቃ ባለቤት ህንድን 

እንዴት በአንዲት ታላቅ ሀገር ስር ለማስተዳደር እንደቻለ ለማወቅ ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡

በህንድ የነጻነት ዋዜማ ስልጣን የጨበጡት የህንድ ልሂቃን፣የተማሩ ልጆቿ፣ በመሃከለኛው ህብረተሰብ 

መደብ የሚካተቱ ንቁ ዜጎቿ የህንድን ቋንቋዎችና ሃይማኖቶችን አንድ ለማድረግ አልሞከሩም ነበር፡፡

በተቃራኒው ያደረጉት የህንድን ብዝሃነት ማቀፍ (መቀበል) ነበር፡፡ በማስከተልም ፓርቲው ራሱ የብዙ 

ነገዶች ስብስብ ለመሆን በቅቷል፡፡ ( የፓርቲው ስብስብ ግን ጎሳን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ችሎታና 

ብቃት ያላቸው የየነገዱ ተወካዮች ናቸው፡፡) ሁሉም ነገዶች በፓርቲው ውስጥ በእኩልነት ተወክለዋል፡፡

ምስጋና የብዝሃትን እኩልነት ለተቀበለው የህንድ ብሔራዊ ኮንግሬስ ይግባውና ጎሰኝነት በህንድ 

ፖለቲካዊ አውድ የለውም፡፡ በተቃራኒው በህንድ ብዝሃነት የዲሞክራሲ መብት በመሆኑ ህንዶች

በአንዲት ሉአላዊትና ጠንካራ፣የአደገች ሀገር  ህንድ መኖሩ ያስደስታቸዋል፡፡ ህንዶች ከጎሳ አስተሳሰብ

ከወጡ እረዥም አመታት ሞላቸው፡፡ ዛሬ ህንዶች ከሀገራቸው አልፈው በብዙ የአለም ሀገራት ስርተው

የሰውነት ክብራቸውን አስከብረው እየኖሩ የሚገኙ ዜጎች ለመሆን በቅተዋል፡፡ እኛ ከአዲሰ አበባ 

ኦሎንኮሚ ደርሰን ለመመለስ በምንሰጋበት በዚህ አሳዛኝ ግዜ ህንዶች በየትኛውም አለም ያለስጋት

እየሰሩና እየኖሩ የሚገኙት በሰውነት ደረጃ ላይ ስለቆሙ ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

እንደ ህንድ ሁሉ በአውሮፓዊቷ ስዊዘርላንድ የጎሳ ወይም ነገድ ተሻጋ ስርዓት ለማንበር ተችሏል፡፡ 

በስዊዘርላንድ ህብረቀለማቸው ሐጢያት አልሆነባቸውም፡፡ እነርሱ ጦር አዝምት አዚም ውስጥ ራሳቸውን

ባለመዶላቸው ምክንያት፣የሶሻል ፋብሪካቸውን በማጥበቃቸው ምክንያት አንዲት ጠንካራ፣የታፈረች 

አውሮፓዊት ሀገር ለመመስረት ችላለች፡፡ ስዊዘርላንድ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ፐርፌክት ዴሞክራሲ

አንብራለች፡፡ ይህቺ ሀገር እውነተኛ የቋንቋ እኩልነት ለማንበርም ታላለች፡፡ በዚች ሀገር የጂኦግራፊ 

ክልል ውስጥ የሚገኙ ግዛቶች ሁሉ እኩል ውክልና ያላቸው መሆኑ አስደናቂ ነው፡፡ የፖለቲካ ውሳኔ

በግልብ ካድሬዎች ወይም በአንድ ጨካኝ አገዛዝ ውሳኔ አይሰጥም፡፡ በዚች ሀገር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ

አዋቂዎች መክረው ዘክረው ከተወያዩ በኋላ በህዝብ ይሁንታ ገቢራዊ የሚሆን ነው፡፡ ጥቂቶች የስልጣን

ጥመኞች ብቻቸውን በህዝቡ ላይ እንዲወስኑ አይፈቀድላቸውም፡፡ እውነት፣ህግና ሞራል ሀገሩን 

ይመሩታል፡፡

ውድ አንባቢ ሆይ አንድ ቁምነገር ላይ እንድታተኩሩ ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡ሁለቱም ሀገራት

የተሳካላቸው በመጀመሪያ በአንድነት እና በህብረት ላይ ስላተኩሩ ነበር፡፡ የሁለቱም ሀገራት የፖለቲካ 

ፊትአውራሪዎች በሀገር ፍቅር ስሜት የተቃጠሉ በመሆናቸው የየሀገራቸውን ሉአላዊ ግዛት ማስከበርና

የህዝብን አንድነት ካጠበቁ በኋላ ነበር ወደ ብዝሃነት (diversity) ያመሩት፡፡ በሌላ አነጋገር ስለ አንድነት

ጥቅም በብዙ ካስተማሩ በኋላ ( እንደኛ ገዢዎች ደም በማፍሰስ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ በማስተማር፣

አማራጭ በማቅረብ በማለቴ ነው፡፡) ብዝሃነትን ደግሞ በክብር ፣ በማቻቸል፣የእኩልነት መንፈስ 

በማስፈን ነበር ሀገር የገነቡት፡፡ እዚህ እኛ ሀገር ከ30 አመታት በፊት በአንድነት ስም የተገደሉትን፣ከ30 

አመት ወዲህ ደግሞ የጎሳ ፖለቲካ በመቃወማቸው ብቻ በወያኔ እና ሌሎች እንደ ኦነግ በመሰሉ አክራሪ

ጎሰኞች የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ ገና ድሮ ደርግ ሳይወደቅ 

በተለይም በትግራይ ምድር የሀገር ዋርካዎችንና የአንድነት ሀይሎችን መፍጀቱን እንደ እነ አቶ 

ገብረመድህን የመሰሉ ጉምቱ ኢትዮጵያውያን ያጋለጡት ጉዳይ ነው፡፡ ህንድም ሆነች ስዊዘርላንድ

ተስፋ የቆረጡ ቡድኖችን አንድ ላይ በመሰብሰብ አልነበረም ወደ አንድነት የመጡት፡፡ ሁለቱም 

ሀገራት ስልጣን በማእከላዊ መንግስት ስር ብቻ እንዲቆይ አላደረጉም፡፡ በክልሎች (እነርሱ ካውንቲ ወዘተ

ብለው ይጠሩታል) የስራ ድርሻ ጥልቅ የሚል የመንግስት መዋቅር አልፈጠሩም፡፡ ከአንድ የጎሳ ቡድን

የወጡ ችሎታ የሌላቸው የፖለቲካ ኤሊቶች የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ለብቻቸው እንዲቆጣጠሩ

የሚፈቅድ ህገመንግስት የላቸውም፡፡ እነርሱ ጋር ችሎታ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ከሆነ ዘመናት 

ተቆጠሩ፡፡ ሌላም አብነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ቤልጂዬምና ካናዳ የግዛት አንድነትን በዲሞክራቲክ አኳያ 

ከማንበር አኳያ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡

በነገራችን ካናዳም ሆነች ቤሊጂዬም የዲሞክራቲክ ባህል የሰፈነባቸው ሀገራት ቢሆኑም ለብዙ ግዜ

ችግር ውስጥ ተዱለው እንደነበር ማስወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለአብነት ያህል ካናዳ በእንግሊዝና

ፈረንሳይ ብሔርተኞች ፉክክር ምክንያት አንደነቷን ሊጎዳ በሚችል ችግር ውስጥ ተዱላ ነበር፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በቤልጂዬም ግዛት ውስጥ የሚገኙት የደች ቋንቋ እና የፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚናገሩ 

ብሔርተኞች በፈጠሩት አለመግባባት ወይም የተሻለ የራስ ገዝ ጥያቄ በማቅረባቸው የፖለቲካ ችግር 

ውስጥ ወድቃ እንደነበር ከአለም የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁለቱም ሀገራት

ከአክራሪ ብሔርተኞች የገጠማቸውን ጋሬጣ የፈቱት በሰለጠነ መንገድ በዴሞክራሲ አካሄድ ነበር፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ስንመለስ የሚከተለውን እውነት እንረዳለን፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ 

የፖለቲካ አውድ ጎሳ ተሻጋሪ ወይም ህብረብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወለዱት በኢትዮጵያ 

የተማሪዎች ንቅናቄ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁለቱም ህብረ ብሔር ፓርቲዎች (

( በተለይም ኢህአፓ እና መኢሶን) የሶሻሊስት ርእዮትዓለም አቀንቃኝ በመሆናቸው የተነሳ ልዩነታቸውን 

በሰላማዊ መንገድ በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረው መፍታት አልቻሉም፡፡ በተቃራኒው ርስበርስ፣

መገዳደላቸውን፣ አንደኛው በተለይም ‹‹ መኢሶን›› ከደርግ ጋር በማበር ኢህአፓ እንዲጠፋ ለማድረግ

መንቀሳቀሱን፣ በመጨረሻም ሁለቱም ህብረብሔር ፓርቲዎች በደርግ ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባቸው፣

እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡ ደርግ ሁለቱንም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በማጥፋቱ ምክንያት

የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሽን እንዲፈሉ፣ጉልበት እንዲያገኙ፣ በመጨረሻም የወያኔ ቡድን 

በዋነኝነት፣ሌሎች የጎሳ ፖለቲካ ቡድኖች ጋር በአጋርነት የደርግ ወታደራዊ አገዛዝን ገረስሶ ጥሎታል፡፡

( የምእራባውያን እና የታሪካዊ ጠላቶቻችን መጠነ ሰፊ እገዛ፣እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግ

መንግስትን ፊት መንሳቱን ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡)

በነገራችን ላይ የወያኔ አገዛዝ የጎሳ ፖለቲካን የሚፈቅደውን ህገመንግስት ‹‹ በሰንአፌ ኤርትራ›› ከአጋሩ

የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት ጋር ጽፎ አጸደቀ እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ በነጻነት እንዲወስን፣ድምጸ ውሳኔ 

እንዲሰጥ አለፈቀደም፡፡ ( ይህ ህገመንግስት ይጠቅመኛል ወይም አይጠቅመኝም ከሚለው አኳያ  ህዝቡ 

በነጻነት ድምጹን አልሰጠም ነበር፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡

እዚች ላይ አንድ ቁምነገር ላይ እንድናተኩር አንባቢውን በአክብሮት አስታውሳለሁ፡፡ የወያኔ የጎሳ ቡድን

ከአንድነት፣ከህብረት ፍልስፍና መነሳት አልፈለገም ነበር፡፡ ወያኔ የኢትዮጵን የብዙ ሺህ አመታት 

የአንድነት ታሪካችንን በመካድ ወይም በመናድ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦች ፈቃድ

እንመሰርታለን ሲል ነበር የተነሳው ( በነገራችን ላይ ይህን ብሔር የሚለው ቃል ማንሳት አልፈልግም)

ወያኔ ብዝሃነትን በማስቀደም ወደ አንድነት እሄዳለሁ ባይ ነበር፡፡ ለወያኔ የብዝሃነት ጽንሰ ሃሳብ

የከፋፍለህ አገዛዙን ለማሳለጥ በሚጠቅመው መልኩ ነበር የተጠቀመበት፡፡ ወያኔ በኢትዮጵያ ብዝሃነትን

ወደ ሲኦል ነበር የቀየረው፡፡ የታደሉት፣የሰለጠኑት ካናዳ፣ህንድ፣ቤልጂዬምና ስውዜርላንድ ብዛሃንትን

ወደ እድል ሲቀየሩት ወያኔ የኢትዮጵያን ነበር ህዝብ ለመከፋፈል ነበር የተጠቀመበት፡፡ በእውነቱ 

ያሳዝናል፡፡ ወያኔ ከጎሳ አጥር በማለፍ የፖለቲካ ስርዓት ለማንበር ፈጽሞ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ 

ምክንያቱም ህብረብሄር የፖለቲካ ፍልስፍና ለወያኔ አኩይ አላማ ደንቃራ ስለነበር ነው፡፡ የዜጋ ወይም

ህብረብሔር የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ያልፈለገው፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ 

በተለይም የአምሃራና ኦሮሞ ልሂቃንን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው ፈልጎ ነበር የጎሳ ፖለቲካን

በገቢርም በነቢብም እውን እንዲሆን ያደረገው፡፡ በነገራችን ላይ ከፋፍሎ መግዛት የአንድ አገዛዝ ዘዴ 

ከሆነ አንድነት ለዚህ አገዛዙ ጠላት ነው፡፡ ባለፉት 27 አመታት ( በወያኔ አገዛዝ ስርዓት ማለቴ ነው)

ከጎሳ ባሻግር የህብረብሔር ፓርቲዎች እንዲጎመሩ አልተፈገም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ነገዶች ጉሮሮ ለጉሮሮ 

እንዲተናነቁ በማድረግ የወያኔ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት ነበር እውን የሆነው፡፡ አሸባሪው ወያኔ ዛሬ 

ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑ ዳግም ላይመለስ ተሽቀንጥሮ ወድቋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለኢትዮጵያ

አንድነት ቡግንጅ ሆኗል፡፡ ይኀውም የሆነው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው የወያኔ 

የመጨረሻው ማስታወሻው ተክሎብን የሄደው ‹‹ህገመንግስቱ›› በተለይም አንቀጽ 39 ሲሆን፣ ሌላው

ደግሞ ለሀገሪቱ ህልውና ስጋት በሆነ መልኩ የከፈተብን ጦርነት ወይም ወረራ ነው፡፡ ሰለሆነም 

የኢትዮጵያ መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ምሁራን፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ከፖለቲካ ፓርቲዎች ( የጎሳ  

ፖለቲካ ይበጀናል ወይም አይበጀንም ) ከሚሉት ጋር በውይይት፣ በንግግር፣ የኢትዮጵያን ህገመንግስት

በተለይም አንቀጽ 39 የሚሻሻልበትን መንገድ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ዜጋ

እጠይቃለሁ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከፈተውን ጦርነት ደግሞ በዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ መንገድ

በፍጥነት ለመቋጨት መንግስት መንፈሳዊ ወኔ ይታጠቅ ዘንድ እማጸናለሁ፡፡

ውድ ወገኖቼ በመጨረሻም ማስታወስ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ የኢትዮጵያው ህገመንግስት በተለይም

አንቀጽ 39 ያመጣብንን መዘዝ ለመረዳት 30 አመታቶች ከበቂ በላይ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያውያን 

ሁሉ በሰከነ መንፈስ በሰለጠነ መንገድ ፣በውዴታና በፍቅር መንፈስ የሚሻሻልበትን መንገድ በየሰፈራችሁ

ትወያዩበት ዘንድ በማስታወስ እሰናበታለሁ፡፡ሰላም እና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝብ፡፡

Once division becomes your method of achieving hegemony, unity becomes

Your enemy>>

መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

Filed in: Amharic