>

ሹመት በኢህአዴግ ቤት! (አሳፍ ሀይሉ)

ሹመት በኢህአዴግ ቤት!

አሳፍ ሀይሉ

“አለቦታው ገብቶ አለሰገባው
አሳዘነኝ ልቤ የተንገላታው”
   (- አስናቀች ወርቁ፣ የክራር ዜማ።)
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የት/ት ሚኒስትር ሆነመሾማቸውን ሰማሁ። ጥሩ ነው። እነ ገነት ዘውዴ፣ ሺፈራው ሽጉጤና ደመቀ መኮንን በተቀመጡበት ወንበር ለምን ዶ/ር ብርሃኑ ተሾመ ብሎ የብቃትን ጉዳይ ማንሳት ጤነኝነትን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።
ጥያቄው የብቃት ጉዳይ አይደለም። ጥያቄው የጉልቻ መቀያየር ጉዳይም ብቻ አይደለም። በበኩሌ ቢቻል ኖሮ ጥያቄው በማን ጉልቻ ላይ ነው የምትጣደው? ተብሎ ቢስተካከል እመርጣለሁ።
ድሮም እነ ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የኢህአዴግ ት/ት ሚኒስትር ሆነው ሞክረውት አልነበር ወይ? ከኢህአዴግ ቤት፣ ከኢህአዴግ ሕገመንግሥት፣ ከኢህአዴግ ሰዎች፣ ከኢህአዴግ መንግሥት ምን የተለየ ነገር ተጠብቆ ነው? ከእባብ ሆድ ዕቃ የእርግብ እንቁላል እንዴት ሊፈለፈል ይችላል?
በአንድ ወቅት (የዛሬን አያድርገውና) ዶ/ር ብርሃኑም ራሱ በታደመበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ50ኛ ዓመት መታሰቢያ ንግግራቸው፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋከልቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ መድረክ ላይ ሆነው፦
“ማሩኝ ለሠራሁት ይቅር የማይባልሀጢያት፣ በስሜ በተፈረሙት ሁሉይቅር በሉኝ፣ ብዙዎቹን እየመጡልኝሳላስብ ያለውዴታ የፈረምኳቸው ናቸው…።”
ብለው ነበር የተናዘዙት። ፕ/ር መስፍን በበኩላቸው 40 የዩኒቨርሲቲ መምህራንን በፊርማው ስላባረረው የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሿሚ ፕሬዚደንት ስለ ዶ/ር ዱሪ መሀመድ ሲናገሩ፦
“ሰውየው የተሰጠውን ዝርዝር ማን ማን እንደሆነ ራሱ የመመልከት ዕድሉን ሳያገኝ ዝም ብሎ የፈረመ ይመስለኛል፣ ምክንያቱም ከዚያ
በኋላ በተለያየ ጊዜ ድንገት ሲያገኘኝ ‘እገሌን ሰሞኑን አላየሁትም ምነው ጠፋ?’ ብሎ ይጠይቀኝና፣ ራሱ ካባረራቸው መሐል መሆናቸውን ስነግረው ያለመጠን ይተክዝ ነበር”
በማለት ሲናገሩ ያደመጥነው፣ ያነበብነውም ነው። የኢህአዴግ ቤት የኢህአዴግ ቤት ነው። የማይጠራ የጨቀየ የብሔር ብሔረሰቦች የእውር ድንብር ቤት።  ወደዚህ ቁርጡ የታወቀ ቤት ሰው በፈቃዱ እኖራለሁ ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ሲገባ ምን መባል እንዳለበት ግራ ይገባኛል። ያውም ምሁርን። የሚያውቅን። የህገመንግሥቱን ካንሠርነት በአውሮፓ ፓርላማ ፊት ቀርቦ ያስረዳን ሰው። ምን ይሉታል?
“ስልቻ ቀልቀሎ – ቀልቀሎ ስልቻ
ቦታ ቢለዋወጥ – ወጥ ላያጥም ጉልቻ
ልቤ ዛሬም ወደህ – ልትሆን መተረቻ
ታዲያ ምን አመጣው – ያንን ሁሉ ዛቻ”
      (- ቴዎድሮስ ካሣሁን፣ ጉራ ብቻ።)
የእውነት አጭር ትውስታ ያለን ሕዝቦች ካልሆንን በቀር ሌላ ቀርቶ፣ በዚሁ በአብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን መሠለኝ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ መሥራት አልቻልኩም፣ የተጨመላለቀው የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ በትምህርቱ ላይ ነግሶ እያቡካካው አብሬ አልጨማለቅም ብለው መልቀቂያ አስገብተው በጨዋ ደምብ ገለል ያሉት።
ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ ለምን በፈቃዳቸው የት/ት ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ለቀቁ? ምን ነገር አላሠራ ቢላቸው ነው? ለዶ/ር ጦላዬ ያልሠራ፣ እና ለዶ/ር ብርሃኑ የሚያሠራ ምን የተለየ ነገር ይመጣል ተብሎ ታስቦ ነው? ጉልቻው ቢቀያየር የተወራረሰውን ያረረውን የተከነውን የኢህአዴግ ወጥ ያጠራዋል ወይ? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው።
ቆም ብሎ ራስን መጠየቅ፣ ቢያንስ የበቀለች ችግኝ ሳትቀር በደላላ እያሰሰ ከሚጨፍረውና ከሚያጫፍረው ጋር አብሮ በሆይ ሆይታ ከመጨፈር ወረት ያድናል።
በበኩሌ ዶ/ር ብርሃኑ ወጣ፣ ቀድመው ይቅር በሉኝ ያሉት ሚኒስትር ዶ ፕ/ር በየነ በፖሊሲ አማካሪነት ካባ ተመልሰው መጡ፣ ያኛው ሄደ፣ ይሄ መጣ አይመስለኝም።
በተጠላ፣ ሀገሪቱን ለውድቀትና ለፍጅት በዳረገ፣ እና አንድ ሐሙስ በቀረው ካቅሙ በላይ በሚንጠራራ ያረጀ የብሔርብሔረሰቦች የፖለቲካ ዛፍ ላይ መንጠላጠል፣ ሥርዓቱን ከመደርመስ ያድነው እንደሆነና እንዳልሆነ በጊዜ ፈተና አልፈን የምናየው ይሆናል።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተሾመው ለሀገሪቱ ካንሰር በሆነ አይን ያወጣ የአምባገነን ሥርዓት መቃብር አፋፍ ላይ ነው። በክብር የቀረበለትን ተዝካር አልፈልግም ማለት፣ የለም የቻልኩትን እስከቻልኩ ላበርክት ማለት የግለሰቡ ምርጫ ይሆናል።
በበኩሌ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ያላየነውና ያልሰማነው አዲስ ፍፃሜ የሚኖርበት ምክንያት አይታየኝም።
“ኑሮ ጉራማይሌ፣ እንደየዘመኑ
ሁሉን ያሳየናል፣ ጊዜ በሚዛኑ
እንደዚህ ናት ህይወት፣ አታላይ ናት አለም
ካየነው ባለፈ፣ የምናየው የለም”
     (- ሐመሩ ሙዜ።)
እንዳለው ነው ገጣሚው። አንዳንዴ ይነድዳል። ነገሩ ያደባባዩን በጆሮ ዓይነት ነው። ተጥዶ ሲፈላ ሲንተከተክ የቆየውን አሁን ላይ ደርሶ ለምን formal ተደረገ? ብሎ እምቡር ማለት ስሜትን ከማሳየት ያለፈ ቁምነገር የለውም።
በፓርቲ ደረጃ ካየነው፣ ኢዜማ የ60ዎቹና 70ዎቹ መኢሶን የግብር አቻ መሆኑን ብዙዎች ብዙ ጊዜ አንስተው ብዙ ጊዜ የኮነኑት ጉዳይ ነው። ስለዚሁ አንስቶ እንደ አዲስ መፈትፈት ነገር መደጋገም ብቻ ነው። ትርፍ የለውም። ትርፉ ድካም ይሆናል።
ወትሮም የመኢሶንነት ሚና ህብረተሰቡን ለሥርዓቱ ምቹ እንዲሆን ከማስተማር፣ ከማንቃትና ከማደራጀት የተለየ አልነበረም። አይደለምም። እንግዲህ በታሪክ ፊት ከኢህአዴግ-ብልፅግና ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ዳግማዊ መኤሶንነትን የመረጠው ኢዜማ (ከመሰል አምስተኛ ረድፈኛ አጋሮቹ ጋር) መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንለት ከመመኘት በቀር ማለት የሚቻል ነገር ያለ አይመስለኝም።
ለዶ/ር ብርሃኑ ነጋም መጨረሻውን ያሳምር፣ ሥልጣን ያዳብር፣ የተማረ ያስተምር፣ ያልተማረ ይማር ብሎ በቅን ቃላት ከመሰናበት በቀር ቀድሞም ራሱን ለሥርዓቱ አገልግሎት ያጨን ወዶገብ ምሁር በሌላ ምርቃት ማወደስም፣ መገሰፅም፣ ሌላ መመኘትም የሚቻል ነገር ያለ አይመስለኝም። አይኖርምም።
“በሉ እናንተ ሂዱ፣ እኛም ወደዛው ነው 
ወትሮም መንገደኛ፣ ፊትና ኋላ ነው”
       (- ዘለሰኛ ግጥም፣ የሕዝብ።)
ታሪክ ግን ገራሚ ነው። ጊዜ ወለል አድርጎ እስኪያሳየው ድረስጨከምንም በላይ አጓጊም። ከምንም በላይ አስጨናቂም። ከማንም በላይ ፈራጅም ነው ታሪክ።
የታሪክን ፍርድ፣ የጊዜን ዳኝነት የሚያመልጥ ማንም የለም። ዕድሜ ሰጥቶ፣ የታሪክን ፍፃሜ ለማየት መብቃት ምንኛ መታደል ነው?! ያን የታሪክ ፍርድ ለማየት ያብቃን።
እስከዚያስ? እስከዚያውማ.. ዝም ሳይሻል አይቀርም። እንደኔ ትክን ብሎ፣ ወዲህ ወዲያ እየተገላመጡ፣ እየዞሩ፣ እየፎከሩ፣ እያዘኑ፣ እያሰሱ፣ እየከሰሱ ከመንገላታት፣ ዝም ቢባል እላለሁ። ቢያስችል እንደ ጊዜ ዳኛ ዝም። ጭጭ። ብሎ ማለፍ ቢቻል።
“..አጉል ነው ብለን ሳንፈርድ
ድንቅም ነው ሳንል ሳንወድ..
ከሰው ኳኳታ እንነጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ አንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል፡፡”
   (- ሎሬት ፀጋዬ፣ አብረን ዝም እንበል።)
ለሀገራችን መልካሙን ዘመን ያምጣልን።
ዕድሜ መስታወት ነው። ዕድሜ ይስጠን።
መልካም ጊዜ።
Filed in: Amharic