>

አርበኛው፣ ዲፕሎማቱ፣ አገረገዥው ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ....!!! ታሪክን ወደኋላ 

አርበኛው፣ ዲፕሎማቱ፣ አገረገዥው ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ….!!!
ታሪክን ወደኋላ

ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ከአባታቸው ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ዓባይነህ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ማዝለቂያ አያላወርቅ በወርሃ ህዳር 15 ቀን 1885 ዓ.ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ተወለዱ። የራስ እምሩ እናት ወይዘሮ መዝለቂያ የራስ መኮንን እህት የወይዘሮ እኅተ ማርያም ልጅ ስለነበሩ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አብሮ አደግና የቅርብ ዘመድም ነበሩ። ራስ እምሩ እና ደጃዝማች ተፈሪ ሁለቱም በአባ ሳሙኤል ወልደ ካሂን ጋር አብረው ተምረዋል፣ እናም ያደጉት በሃሮልድ ማርከስ የንጉሠ ነገሥቱ “እውነተኛ አባት” በሚሉት በእምሩ አባት ኃይለ ሥላሴ አባይነህ ነበር።
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ በሰገሌ ጦርነት ላይ ከሐረርጌ የጦር አበጋዞች አንዱ ሆነው ውጊያው ላይ ተሳትፈዋል። ከጠላት ወረራ በፊት የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ገዥ ፣ የወሎ ቀጥሎም የሐረር እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከጥቅምት 1935 ጀምሮ እምሩ የአውራጃውን ሠራዊት እየመራሩ በሁለተኛው የኢትዮ- ኢጣሊያ ጦርነት ላይ በግራ ጦርን በአዛዥነት በመሆን መርተዋል፣ እንዲሁም በዚያን ጊዜ በሽሬ ግንባር የጦር አዛዥ ሆነው በጀግንነት ጠላትን ተከላክለዋል። በወቅቱ በሰሜን ግንባር ጦሩ ሲፈታ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመዞር ለአንድ ዓመት ያህል በአርበኝነት ቆይተዋል። ከዚህም ታህሳስ 10 ቀን 1929 ዓ.ም ጎጀብ ላይ ከተማረኩ በኃላ ወደ ሀገረ ኢጣልያ ተወስደው በፖንዛ ደሴት ላይ በእስረኛነት ቆይተዋል።
ከድል በኋላ ራስ እምሩ ለአጭር ጊዜ የሰሜንና የበጌምድር ጠቅላይ ገዢ ሆነው ከቆዩ በኋላ የዘውድ አማካሪ ሆነው ተሹመው በሕንድና በአሜሪካ ሀገር በአምባሳደርነት አገልግለዋል። ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ሁልጊዜ የዘመናዊ እና የለውጥ አመለካከቶች ከሚባሉ ሠዎች መካከል የሚመደቡ፣ እንዲሁም በአስተዳዳሪነትና በጦር አዝማችነት እጅግ የተመሰገኑና ጥልቅ ሃይማኖተኛ ነበሩ።
ራስ እምሩ የንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ እና የንጉሠ ነገሥታዊ ባለሞያ በመሆን ቆይተዋል። ከዚያም በየካቲት 1966 ዓ.ም በመጣው ጊዜያዊ ወታደራዊው የደርግ መንግስት በመስከረም 2 1967 ዓ.ም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ሲወርዱ ድርጊቱን ለመመልከት ራስ ዐምሩን አብረዋቸው እንዲሄዱ ተጠይቀው ነበር እናም አባላቱ ንጉሡን ከመናገራቸው በፊት ለልዑል ራስ እምሩ ያወያይዋቸው ሲሆን በወቅቱ የደርግ አባላት ለንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን መውረዳቸውን ሲያስታውቁ እና ወደሚታሰሩበት ቦታ አብሯቸው እንዲሄድ ሲጠይቁ ልዑል ራስ እምሩ በሁኔታው በጣም ያዘኑ እና ተጨንቀው እንደነበር በወቅቱ በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ይናገራሉ። በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ እና ልዑል ራስ እምሩ በሹክሹክታ ከተነጋገሩ በኋላ የንጉሡ ምላሽ የነበረው በአባለቱ የተነገራቸውና ወደሚወስዷቸው ቦታ በሰላም ለመሄድ ተስማሙ። ከዚያም ልዑል ራስ እምሩ የወታደሮቹ አባላት ንጉሡን ወደ ሚወስዱበት ቦታ አብረዋቸው እንዲሄዱና እንዲሸኟቸው ያቀረቡት ጥያቄ በአባላቱ ፈቃድ አለማግኘታቸው በወቅቱ ተረብሸው ነበር።
ልዑል ራስ እምሩ ህይወታቸው ያለፈው በተወለዱ በ 87 ዓመታቸው ነሐሴ 12 ቀን 1972 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ ልዑል ራስ እምሩ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርወ መንግሥት አባል ሆነው ሳለ በሚገርም ሁኔታ የወታደራዊ ደርግ መንግሥት ዘመን የቀብር ሥነሥርዓታቸው በክብር የተፈጸመላቸው ብቸኛ ሰው ነበሩ። ስርዓተ ቀብራቸው አዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በክብር ተፈጽሟል። ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ከባለቤታቸው ከልዕልት ፅጌ ማርያም ጋር ባሳለፉት በትዳር ዘመናቸው 8 ልጆችን ያፈሩ ሲሆን እነርሱም :- ወ/ሮ የምስራች ፣ ወ/ሮ ማርታ ፣ ልጅ ሚካኤል ፣ ወ/ሮ ሂሩት ፣ ወ/ሮ ዮዲት ፣ ወ/ሮ ኢሌኒ ፣ ወ/ሮ ሩፋኤል ፅጌማርያም እና ወ/ሮ ማሜ እምሩ ናቸው።
Filed in: Amharic