የድሬ ዳዋ በረከቶች…!!!
አፈንዲ ሙተቂ
አዎን! ድሬ ዳዋ የበረከት ከተማ ናት፡፡ ልዩ ልዩ በረከቶች ይፈልቁባታል፡፡ “የበረሃ ገነት” እየተባለች የምትጠራበት አንዱ ምክንያት የበረከቶች መፍለቂያ መሆኗ ነው፡፡ እስቲ ከድሬ በረከቶች በጥቂቱ እንቅመስ፡፡
——-
የድሬ ዳዋ ዳቦ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ርዝመቱ እስከ ግማሽ ሜትር ድረስ ይሆናል፡፡ ልስላሴው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ሲበሉት እንደ ላስቲክ እየተተረተረ ይላቀቃል፡፡ እንደ አሁኑ ዳቦ ከመጠን በላይ በኸሚራ (እርሾ) የተነፋ ባለመሆኑ ከሆድ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ ደግሞም በደንብ የበሰለ ስለሆነ “ሊጡ ሆዴን ይነፋኛል” በማለት እርሱን ከመብላት የሚያፈገፍግ የለም፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ዳቦው ሳይበላሽ እስከ አምስት ቀናት ድረስ መቆየት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በድሮው ጊዜ እናቶቻችን ከድሬ ዳዋ ሲመጡ መጀመሪያ እርሱን ነው የምንጠይቃቸው፡፡ ታዲያ በቅርቡ እንደ ሰማሁት እንደዚያ ዓይነት ዳቦ ከጅቡቲ ባቡር እየተጫነ ነው የሚመጣው፡፡ ለዚህም ነው ድሬ ዳዋ በቀል ከሆነው ዝነኛው ሀሩን ዳቦ የሚለየው፡፡

ሌላው የድሬ ዳዋ በረከት “ጃጁር” ነው፡፡ ጃጁር አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ትንሽዬ ብስኩት ነው፡፡ መጠኑ አሁን አቡወለድ እና ሂፕሆፕ ከሚባሉት የብስኩት ዓይነቶች ጋር ተቀራራቢ ሆኖ በጣም ወፍራም ነው፡፡ ከውፍረቱ በላይ የሚደንቀው ግን ጥንካሬው ነው፡፡ ህጻናት በጥርሳቸው ካልሆነ በእጃቸው ሊሰብሩት አይቻላቸውም፡፡ ይህ ጃጁር በዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳርና እንቁላል ነው የሚሰራው፡፡ ጃጁር ሲሰራ ብዙ ልፋትና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ በችርቻሮ ሲሸጥም ዋጋው ይወደዳል፡፡ ሁለቱ ጃጁር ስሙኒ ነው የሚሸጠው (ሌላው ብስኩት በአምስት ሳንቲም ነው የሚሸጠው)፡፡
——

“ሙሸበክ”ም በድሬ ዳዋ በስፋት ይመረታል፡፡ በዋጋውም ከባቅላዋ ይረክሳል፡፡ ይሁንና እርሱም እንደ “ባቅላዋ” እርጥብ ነው፡፡ ደግሞም በብረት ምጣድ እየተጋገረ ነው የሚሰራው፡፡ ሙሸበክ ብዙ ወጪ አያስወጣም፡፡ እርሱን ለመስራት የፉርኖ ዱቁት፣ ስኳርና ዘይት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡
ይልቅስ ብዙ ሰው የማያውቀውን በረከት ልናገር። “ሙቀስቀስ” በድሬ ዳዋ ብቻ ሳይሆን በመላው የሀረርጌ ከተሞች ዝነኛ ሆኖ ዛሬም ይወሳል። የገጠሩ ክልል ጭምር ሙቀስቀስን ያውቀዋል። ይሁንና እርሱም ቢሆን በድሬ ዳዋ በኩል እየገባ ነበር ወደኛ የሚመጣው። በተለይም ኮንትሮባንድ በጦፈበት በዚያ የጥንት ዘመን ከድሬ ዳዋ ይመጡ ከነበሩ ሸቀጦች ቁጥር አንዱ እርሱ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ የርሱ ቀዳሚ ደንበኞች እኛ ህጻናት ነበርን እንጂ አዋቂዎች አይደሉም፡፡

አሁን ትዝ እንደሚለኝ ሙቀስቀስ በታሸገበት ፓኬት ላይ “ከአሜሪካ ህዝብ” ( from the People of United States) የሚል ጽሑፍና የኮከቦቹ አርማ ነበረበት፡፡ በመሆኑም ሙቀስቀስ እንደ “ቡክራ ወተት” ለእርዳታ የመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ኮንትሮባንዲስቶቹ ለማይመለከተው ሁሉ ቸበቸቡት፡፡ እኛም ቀመስነው፡፡ አጣጣምነው!
“ሙቀስቀስ” ተደጋግሞ ቢላስ በቀላሉ አያልቅም፡፡ አምስት “ሙቀስቀስ” በስሙኒ የገዛ ሰው ቀኑን ሙሉ ሲልሰው ይውላል፡፡ ሙቀስቀስ ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላም ለተወሰኑ ዓመታት በገበያ ላይ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡
——–
(አፈንዲ ሙተቂ፣ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ” ከተሰኘው መጽሐፌ የተወሰደ፣ 2006 )