ካሊጉላ (Caligula)!
አሳፍ ሀይሉ
*.… ትንሹ ካሊጉላና አብይ የሚመሳሰሉብኝ ለምን ይሆን…???
ለመሆኑ ካሊጉላ ማን ነው?? ካሊጉላ የጥንታዊ ሮማውያን ሦስተኛው ንጉሳቸው ነው፡፡ በዚህች ምድር የተመላለሰው ለ29 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ታሪኩ ግን ሁለት ሺህ ዓመታትን አልፎም ይነገርለታል፡፡
ካሊጉላ ከአባቱ ጀርመኒከስ እና ከእናቱ አግሪፒና አብራክ ተከፍሎ ልክ ከዛሬ 2004 ዓመታት በፊት በትንሽዬ እምቦቃቅላ ህጻን አምሣል ወደዚህች ምድር ብቅ አለ፡፡
እርግጠኛይቱ የካሊጉላ የትውልድ ቀን እ.ኤ.አ. በነሃሴ 31፤ 012 ዓ/ም ነች፡፡ የትውልድ ሥፍራው ደግሞ የወቅቱ ልዕለ-ኃያላን ታላቂቱ ሮማ – የያኔዋ አንቲየም፤ የአሁኗ አንዚዮ፤ ኢጣሊያ፡፡
ʿካሊጉላʾ ቅፅል ስሙ ነው፡፡ ወታደሮች በእርሱ እየተዝናኑ በፈገግታ ያወጡለት፡፡ በሮማውያን ዘንድ ʿʿካሊ-ጉላʾʾ ማለት ʿʿትንሹ ከስክስʾʾ ማለት ነው፡፡ የሮማ ወታደሮች ʿʿትንሹ ከስክስʾʾ ያሉት ገና በሦስት ዓመት ዕድሜው ነው፡፡
ገና በጨቅላነቱ ካቅሙ በላይ የሆነ ትልቅ የወታደር ቦቲ ጫማ በእግሮቹ ያጠልቅና.. ከአባቱ ሥር-ሥር በየአውድማው ለመሄድ ሲውተረተር ሲያዩት ነው ወታደሮቹ – “ትንሹ ከስክስ”! የሚል የሹፈት ስም ያወጡለት፡፡ በተቀረ ካሊጉላ ትክክለኛ ስሙ፡- ጋየስ ቄሣር ጀርመኒከስ ነው፡፡
እውነቱን ለመናገር ትንሹ ከስክስ ʿʿካሊጉላʾʾ ገና በህጻንነቱ ነበር ዕድሉ ከመሬት ወርዳ የተከሰከሰችው፡፡ ንጉስ ቲቤሪየስ ባላንጣዬ ይሆናሉ ያላቸውን የካሊጉላን እናትና አባት እንዲሁም አምስት ወንድምና እህቶቹን ባንድ ጀምበር ፈጀበት፡፡ ካሊጉላ ግን ህጻን ስለነበረ ቲቤሪየስ አዝኖ ተወው።
ከዚያ ቲቤሪየስ ካሊጉላን ወደራሱ እናት ዘንድ፦ “የሙት ልጅ ነው፣ በጉዲፈቻ እንድታሳድጊው ይሁን!” ከሚል አጭር መልዕክት ጋራ በሰንዱቅ ከትቶ ወደ ካፕሪ ደሴት ላከው፡፡ እና ህፃኑ ካሊጉላ ቤተሰቦቹን በጨረሰበት በቲቤሪየስ ወላጅ እናት እጅ አደገ እንደማለት ነው፡፡
ካሊጉላ ልክ 19ኛ ዓመት ዕድሜው ላይ.. የእንጀራ አባቱ ቲቤሪየስ “ይምጣልኝና አብሮኝ ከጎኔ ሆኖ ይኑር” የሚል ሁለተኛ አጭር መልዕክት ወደ ካፕሪ ላከ። መጣለትም፡፡
አሁን ግን ካሊጉላ የእንጀራ አባቱ ቲቤሪየስ ያባቱና የቤተሰቡ ገዳይ መሆኑን አውቋል፡፡ ሆኖም ሥር የሰደደ ጥላቻውንም፤ ሰማይን ሊነካ የሚደርስ ንዴቱንም፤ ከእሳተ-ገሞራ የዘለገ እልሁንም፤.. ብቻ ሁሏንም ነገር ዋጥ አድርጓት ከእንጀራ አባቱ ጋር ኮሽታ ሣያሰማ መኖር ቻለበት፡፡
አንዳንዴ ህይወት እያለቀስክ የምትልጣት እና አረረችም መረረችም.. ለህልውናህ ቅርጥፍ አርገህ የምትበላት ሽንኩርት ነች፡፡ የምታስለቅስ ሽንኩርት፡፡ ግን ሽንኩርትህን እያለቀስክ ከመብላት ሌላ – ምን አማራጭ አለህ?? ካሊጉላ እንደዚያ ነበር፡፡
ታፍኖ መኖር የሚባለውን ክፉ ዕጣ ብቻውን ጥርሱን ነክሶ ያጣጣመ ሰው መሆኑ አይረሳ። ካሊጉላ። ሁሉን ነገር መተንፈስ የማይቻልበት የብቻ ዓለም ኑሮ፣ ሁሉን ክፉ ነገር ወደ ውስጥህ እየዘረገፍክ መኖርን ያለማምዳል። እና ደመ-መራርነትን ያመጣል፡፡
መጥፎ የምትለውን በውስጥህ እምቅ እያደረግኽ ጥሩ የምትለውን ብቻ ከአፍህ ለማውጣት ስትገደድ.. ውስጥህ በታመቁ መጥፎዎች ሞልቶ ታጭቆ ይደፈርሣል – ከምትችለው በላይ የመጥፎ ነገሮች ጎተራ ሆነህም ትቀራለህ፡፡ የሚል አባባል አለ። ካሊጉላን የገጠመው ያ አሣዛኝ ዕጣ ነው፡፡
ካሊጉላ በዚህ ዓይነት 6 ከባድ ዓመታትን ከእናት ከአባቱ ገዳይ ከእንጀራ አባቱ ቲቤሪየስ ጋር አሣለፈ፡፡ በመጨረሻ ግን ቲቤሪየስ በ37 ዓ/ም (እ.ኤ.አ.) ሞተ፡፡ ቲቤሪየስ በኑዛዜው ካሊጉላንና የአጎቱን ልጅ ቲቤሪየስ ጌሜለስን “የጋራ የዙፋኔ ወራሾች ይሁኑ” የሚል ቃል ትቶ ሞተ፡፡
ካሊጉላ ግን አሁን የውስጡ ያመረቀዘ ቁስል አገረሸበት፡፡ ቆይ እስከዛሬስ ቲቤሪየስ በህይወት ሳለ ይሄ ሁሉ ንዴትህ ሁሉ የት ነበረ? Well… ምናልባት ስለማረው፣ በእናቱ እጅ ስላሳደገው፣ ውለታ ይዞት ይሆን? ማንም መልሱን አያውቀውም።
ብቻ ግን የጋራ ዙፋን ወራሽ ነህ ሲባል ካሊጉላ ያመቃቸው ሰይጣኖች ሁሉ ተጎልጉለው ወጡበት! እና የጋራ ወራሹን አልማረውም፡፡
ማርኮ የሚባል አንድ የካሊጉላ ታማኝ ሎሌ ነበረ፡፡ ያኔ “ታማኝ” ሎሌ – በህይወትህ የታመነ ሎሌ ነው፡፡ የምትበላውን ምግብ፤ የምትጠጣውን መጠጥ፤ የምትቅመውን ዱቄት በእጁ ቆርሶ፤ ቀድቶ፤ አፍሶ የሚሰጥህ፡፡ አንተ እርሱን በህይወትህ ታምነዋለህ፡፡ እርሱም ላንተ ህይወቱን አሣልፎ ይሰጥልሃል፡፡ በታማኝ ሎሌነት ውስጥ ያለው መተማመን ይህ ነበር።
እና ካሊጉላ ማርኮን እንዲህ አለው፡-
ʿʿከአንተ ሌላ ምሥጢረኛና የማምነው
ሰው ባጠገቤ የለም፤ ቲቤሪየስ ቤተሰቤን
ሁሉ በግፍ መጨረሱ ሳያንሰው አሁን
ደግሞ የወንድሙን ልጅ በኔ ዙፋን ላይ
አጣምሮ አስቀመጠብኝ፤ እኔን ታውቀ
ኛለህ፤ ወላጅ አልባ፣ የተገፋሁ፣ የዚህች
ዓለም ምስኪን ፍጡር ነኝ.. እባክህ..
ከዚህ አስከፊ ዕጣዬ ታደገኝ!ʾʾ
ሲል ካሊጉላ ማርኮን እያለቀሰ ለመነው፡፡ ማርኮ አልቻለም፡፡ ʿʿእሺ የፈለግከውን አደርግልሃለሁ – የምትጠይቀኝ አንገቴን ለተሣለ ሠይፍ እስከመስጠት እንኳ ቢደርስ!ʾʾ አለው፡፡ ካሊጉላም የሚፈልገውን ነገረው፡፡
ማርኮ ቀጥታ ወደ ምሥጢራዊዋ ቬርሙጡ ሄደና በታላላቅ ቀማሚዎች የተቀመመች መርዝ አመጣ፡፡ እና ለቲቤሪየስ የአጎት ልጅ ለጌሜለስ ሰጠው፡፡
እያዘነ ነው ታዲያ፡፡ ህይወት እጅግ ስትከፋብህ በሁለት የማትጋፋቸው ቃል-ኪዳኖች መካከል ታኖርሃለች፡፡ አንተ ደግሞ ጀግና ነህ፡፡ ህይወት በአስቸጋሪ ምርጫዎች መሞላቷን ታውቃለህ፡፡ እና አንደኛውን የግድ መምረጥ አለብህ፡፡
ሁሉንም መያዝ አይቻልም። ሁለት ዛፍ አይወጣም። አንዱን ለማዳን ሌላው መሠዋት አለበት። ይሄ የቤተመንግሥት ጣጣ ምን ዓይነት አበሳ ነው?!
እና በህይወት ላይ ልትጀግንባት ትመርጣለህ፡፡ አንዱን፡፡ መራሩን ምርጫ፡፡ ጀግና ነሃ፡፡ የህይወት ጀግና፡፡ እና ማርኮ መረጠ፡፡ ጭቁኑን ካሊጉላ፡፡ ለጭቁኑ ካሊጉላ፤ የታመነውን ጌሜለስን ከእጁ የቀዳውን በመርዝ የተለወሰ መጠጥ አሣልፎ ሰጠው፡፡
ጌሜለስ አልተጠራጠረም፡፡ ያመንከውን እንዴት ትጠራጠራለህ? ያማ የሞት-ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ጌሜለስ አይኑን ሳያሽ ከማርኮ እጅ መጥፊያ መርዙን ተቀብሎ ጠጣ፡፡ እና ላይመለስ አሸለበ፡፡
የዚህች ዓለም ነገር ግን ግርም የሚልህ ምን መሠለህ? ማርኮ አፍታም አልቆየ፡፡ ካሊጉላ ምሥጢሩን እንዳያወጣበት ሲል የታመነውን.. ለእርሱ ሲል መራሩን የክህደት ፅዋ የተጎነጨለትን… እና ያዘነለትን ያን ጀግና (እና ከሃዲ!) ማርኮን በሌሎች ሌሌዎች አንገቱን አስቀላው!!!
ተራ። ዙር። ነው ግፍ። መሠለኝ። አንዴ ከግጋር ከተገናኘህ። ደግመህ እንደምታገኘው አትጠራጠር። በሌላ ጊዜ። በተራህ። በተራው። ተረኛ ግፍ ዞሮ አድፍጦ ይጠብቅሀል። አይ ይቺ ህይወት? ይህችን ህይወታችንን – “አስገራሚ ትራጀዲ አይደለችም!” የሚል ካለ ይምጣ ፡፡ የሚል ካለ – ያላያት፣ ያልቀመሣት ብቻ መሆን አለበት።
አሁን ለማንኛውም ወደ ካሊጉላ እንመለስ፡፡ ገና በህጻንነቱ ዕድሉ የተከሰከሰችበት “ትንሹ ከስክስ” ካሊጉላ አሁን በሃያ አምስት ዓመቱ የታላቂቱ ሮማ ባለሙሉ ዙፋን ንጉሠ-ነገሥት ሆነ፡፡ እና ዓለምን በመዳፉ ጨበጠ፡፡
እና የሚገርምህ ለጥቂት ወራት መልዓክ ሊሆን ክንፎች ብቻ ቀሩት – በደግነቱ የሚወዳደረው አጥቶ፡፡ ካሊጉላ ለወታደሮች ተደርጎ የማይታወቅ ጉርሻና ድርጎ ቆረጠላቸው፡፡ አላግባብ በባርነት የተያዙትን ነፃ አወጣ፡፡ በግፍ የታሰሩትን አስፈታ፡፡
አስደሣች የሠረገላ ውድድሮችን እያዘጋጀ፤ የታወቁ ግላዲያተሮችን (እርስ በእርስ የሚፋለሙ ግዞተኞችን) ከየዓለሙ ማዕዘን እያስመጣ በአምፊ-ቲያትሮች እያደባደበና እያጋደለ፤ የትያትር ተውኔቶችን እያስቀረበ፤ የፈረስ ግልቢያ ውድድር እያካሄደ.. በነዚያም ታላላቅ ሽልማትና ክብርን ለአሸናፊዎቹ እየቸረ.. ብቻ ባጠቃላይ.. የሮማን ህዝብ ሁሉ ቀደም ሲል በሁለቱ ንጉሣን ባልታየ መልኩ ዳር እስከ ዳር በደስታ አሰከረው፡፡
ሮማ ከአፅናፍ አፅናፍ ፈነደቀች፡፡ “ቀን ወጣልኝ” አለች፡፡ ምን ዋጋ አለው?! – “ደግ አይበረክት” ይባል የለ? እና ካሊጉላም ድንገት ታመመና ክፉኛ በጣዕር ተቀሰፈ፡፡ ባሉባልታ እንደሚወራው ካሊጉላ የተቀሰፈው በተሰጠው መርዝ ነው፡፡ ሊገሉት ያሰቡት መርዙን ሰጡት – የሕዝብ ምርቃት ሆኖ ነው መሠል… ካሊጉላ ግን ከሞት አፋፍ ደርሶ ተመለሠ፡፡
ከሞት አፋፍ ደርሶ ከተመለሠ በኋላስ? የካሊጉላ አዕምሮ እጅጉን ተናወፀ፡፡ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጠረጠራቸው፡፡ እና በጉዲፈቻ የሚያሳድገውን ምስኪን ህፃን ሣይቀር.. በዙሪያው ያሉትን የቅርብ ሰዎች አንድ በአንድ ፈጃቸው፡፡
እጅግ ያዘነላቸውን ወደ ሩቅ አስከፊ ደሴቶች በባርነት አጋዛቸው፡፡ የገዛ አያቱ ይህን ከሠይጣን ከራሱ እንጂ ከሰው ልጅ ከቶውንም ሊወጣ የማይቻል የመሠላትን የክፋት መዓት በካሊጉላ ሲተገበር ስታይ – ይህን ከማይ ብላ የገዛ ራሧን ህይወት አጠፋች፡፡ ይህን አሟሟቷን አላምን ብለው ካሊጉላ ነው በመርዝ ያስገደላት የሚሉም አልታጡም፡፡
ከዚያ ካሊጉላ ራሱን የሮማ የጊዜው አማልክትና ከፊል-አማልክት (God’s and Demi-Gods) ብቻ በሚጠሩባቸው የማዕረግ ስሞች ራሱን ይጠራ ጀመር፡፡
ጭራሽ ብሎ-ብሎ እጅግ ከፍተኛ የመመለክ ክብርና ዋጋ የሚሰጣቸውንና ሁሉም ሮማዊ የሚንቀጠቀጥላቸውን አማልክት ማዕረጎችና አለባበሶች ለራሱ ሰጠ፡፡ እና በነዚያ ስሞች ጥሩኝ አለ፡፡
ባንድ ወቅት በቀን ውስጥ 20 ሺህ ሰዎች አስጨፈጨፈ ካሊጉላ – ʿʿታላቁ ዘለዓለማዊ ህያው አምላክ ጁፒተር ሆይʾʾ ብላችሁ ለምን አልጠራችሁኝም በማለት፡፡ ራሱንም እኔ ያማልክቶች ሁሉ አምላክ ሔርኩለስ ነኝ ሲል አዋጅ አስነገረ፡፡
ይህም አላረካ ሲለው ጨማመረና፡- “ሁሉንም ነኝ!” አለ፡፡ ʿʿእኔ ሔርኩለስ ነኝ፤ ሜርኩሪ ነኝ፤ ቬነስና አፖሎም ነኝ! ሁሉንም ነኝ!ʾʾ በማለት አወጀ፡፡ እና በሮማ ግዛት ሁሉ የታነፁ ታላላቅ የየአማልክቱ አምዶችና ኃውልቶች ከአንገታቸው በላይ እየፈራረሱ በራሱ ምስል እንዲተኩም አደረገ፡፡
ይህ የካሊጉላ ሁሉንምነት (ወይም ጠቅላይነት) አልዋጥለት ብሎ ግራ ሲጋባ የተገኘ ሰው ሁሉ፣ እምቢ የመጣ ይምጣብኝ’ንጂ ይሄን አልቀበልም ያለ ሁላ.. ያለ ጥያቄ አንገቱ ለሠይፍ ይሰጥ ነበረ፡፡
ጭራሽ በሠማያት ላይ ከጨረቃ ጉያ ወዳለው ወደ አምላክ ጁፒተር ቤተ-መንግስት የምጓጓዝበትን ወደላይ የሚምዘገዘግና ሠረገላዬን የሚያጓጉዝ የደረጃዎች ድልድይ ስሩልኝ በማለት – የታላቋን ሮማ አናጢዎችንና ግንበኞችን፣ ንድፍ አዋቂዎቾንና አንጥረኞችን ሰብስቦ ያስጨንቃቸው ጀመር።
ከአስማተኝነት በመለስ እስከዛሬ ተርፈው የምናያቸውን ተዓምራዊ ንድፎች የሚሰሩ የስነህንፃ ጠቢባን፤ ልሂቃንና የዘመኑን ጉደኛ ጠበብቶች ሁሉ የሠማዩን ሠረገላዬን ውለዱ ብሎ አስጨነቃቸው ካሊጉላ፡፡
እና ልክ ያሁኑን ዘመን የተራራ ላይ ወይ የወንዝ ላይ የጎብኚዎች መዝናኛ የሚመስሉ እጅግ ከፍታ ያላቸው skylons (የቀለበት መንገዶች የሚመስል ወደሰማይ በዓየር ላይ የተዘረጋ.. መጨረሻው የማይታወቅ የደረጃ ድልድይ) ያሠራቸው ጀመር፡፡ አንድ ቦታ ከፈረሰባቸው የሁሉም አንገት በሠይፍ ይቀላል፡፡ እና በሌሎች ሥራው ይቀጥላል፡፡
ይህ ሁሉ እብደት ከቤተመንግሥቱ ቅፅር ሲካሄድ የሮማ ፓርላማ (ሴኔቱ) አፉን በእጆቹ ጭኖ “ጉድ! ጉድ!” እያለ ከመመልከት በቀር ካሊጉላን ማለት የቻለው ነገር አልነበረም፡፡
ጭራሽ የሴኔቱ ዝምታ አልበቃ ያለው ካሊጉላ.. እጅግ የሚወደውንና በሮማ ታላቅ ኃውልት ያሳነፀለትን ውዱን ፈረሱን ʿʿኢንሲታተስʾʾን.. “የቤተመንግስት ደንገጡሬ ነው!” በማለት የቤተመንግስት አጋፋሪነት ማዕረግ ለፈረሱ ሰጠው፡፡
ከዚያ ማዕረግ ፈረሱ ኢንሲታተስ በወርቅ ብቻ የተሰሩ አልባሳት፤ ኮርቻዎች፤ ዘለበቶች፤ ልጓሞችና አልቦዎች እንዲጌጥለት አደረገ – ሴኔቱ ዝም አለው፡፡ ካሊጉላ እንቅልፉ ሲመጣ የሚያሸልበው ከፈረሱ ስር ነበር። በዓለም ላይ የማምነው አንድ ፍጡር አጋፋሪ ኢንስታተስን ብቻ ነው በማለት።
እና አስገራሚ አዋጅ አስነገረ ካሊጉላ፦
ʿʿእኔ ከፈረሴ ስር እያሸለብኩ በሮማ
ከተማ ኮሽ የሚል ድምፅ በስህተትም
ቢሆን ያሰማ ሰው ቢኖር አንገቱ እዚያው-
በዚያው በሠይፍ እንዲቀነጠስ ይሁን!ʾʾ
የሚል፡፡ ሴኔቱ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ጉድ ብሎ ዝም አለ አሁንም፡፡ ከዚያ ካሊጉላ ቀጠለና ሌላ አዋጅ አወጣ፦
ʿʿፈረሴን ከአሁን በኋላ የተከበረው የሮም ሴኔት አባል አድርጌ ሾሜዋለሁ፤ የሴኔቱ ስብሰባ ሲኖር የሴኔቱን አልባሳት እንዲለብስ፤ እና በሴኔቱ ቦታ ተዘጋጅቶ ለየዕለት-ተዕለት ተግባሩን እንዲያከናውን ይደረግ!ʾʾ
የሚል አዋጅ፡፡ ይህ ለተከበሩት ታላላቅ የሮም ጀግኖችና ልዑላን ከውርደቶች ሁሉ የላቀው ውርደት ነበረ፡፡ ፋንዲያውን በጉባዔ መኃል ከሚጥል ፈረስ ጋር እንደ አባል ወንበር ተጋርቶ አብሮ መሠብሰብ አስከፊው ገሃነመ-መርገም ነበር፡፡ ግን አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ በህይወት ያለሁ አምላክ ነኝ ብሏልና ምን ያድርጉት? ሰው ሆኖ የማይቻል የለም፡፡ ይህንንም ቻሉት፡፡
በመጨረሻ የ29 ዓመቱ ካሊጉላ ሮም ጠበበችው፡፡ እና ምን አለ?፦
“ወደ ግብፅ ሄጄ በህያው አምላክነቴ ዓለም ሁሉ እየሰገደልኝ በፒራሚዶች አናት ላይ ዙፋኔን መስርቼ በዚያ ዓለምን እስከ ፍፃሜዋ እገዛለሁ!”
የሚል ሕልም-አይሉት-ቅዠት አነግቦ ተነሣ፡፡ ገና ዕቃውን ሲሸካክፍና የሮምን ጀግኖች ሲመርጥ፡፡ አንድ ካሊጉላ በህይወቱ የሚያምነው – ለካሊጉላ ሲሉት ዓለምን ሊያቃጥልለት አይኑን የማያሽ – “ካሲየስ ኬሪያ” የተባለ የጀግኖች ቁንጮ የቤተመንግስት ጠባቂ የጦር አለቃ ሁሉም የፈራትን ያቺን ቃል አወጣ፦ “በቃህ!”፡፡
ካሲየስ ኬሪያ – ካሊጉላን – በቃ አለው!! ʿʿበቃ!ʾʾ፡፡ ይህቺን “በቃ!” የምትል ቃል የውስጡን ጀግንነት ሁላ አንጠፍጥፎ እስኪያወጣት ድረስ.. ድፍን አምስት ዓመት ፈጅታበታለች፡፡ በመጨረሻ ግን አወጣት፡፡ ጀግና ነው፡፡
ካሲየስ የወጣለት ጀግና ነበር። ያን ጀግንነቱን ካሊጉላ የአምላክነትን ካባ ደርቦ ወሰደበት፡፡ እና የመጨረሻዋን የቀረችውን ጀግንነት ከውስጡ ላለማስነጠቅ ለካሲየስ የቀረችው አንዲት ብቸኛ የጀግና ግብር ʿʿበቃ!ʾʾ የምትል ቃል ነበረች፡፡ እና አወጣት፡፡ ʿʿበቃ!ʾʾ፡፡
ልክ ያቺ ʿʿበቃ!ʾʾ ስትነገር… “ህያው አምላክ ነኝ” ብሎ የራሱን ያማለለው ካሊጉላም አምላክነቱ አበቃለት፡፡ እንኳን አምላክነቱ ሰውነቱ ራሱ አበቃለት፡፡ ቀኗ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 24 ቀን 41 ዓመተ ምህረት ነበረች፡፡
ካሊጉላ የፈረስ ሽምጡን ጋልቦ ደክሞት እየተመለሰ ነው፡፡ የካሊጉላ ጠባቂዎች ሠይፋቸውን መዝዘው ከፊቱ ተጋረጡበት፡፡ በታላቅም ኃይል ተጋፈጣቸው፡፡
እርሱም እኮ ክፋቱ ነው እንጂ.. ሮምን የምታህል ዓለምን ያንበረከከች ታላቅ ግዛት ከነሕዝቦቿ አንቀጥቅጦ.. ለጠላት ሣያስደፍራት የገዛ ታላቅ ጀግና እኮ ነው፡፡ እና በታላቅ መንፈስና ግርማ ከገዛ ጠባቂዎቹ ጋር ተፋለመ፡፡
ይመስለኛል በሆዱ – ያ ካሲየስ ኬሪያ መድህኔ መጥቶ ካሁን ካሁን ከሚፋለሙኝ ጠባቂዎቼ ሠይፍ ይታደገኛል – እያለ የሚያስብ ይመስለኛል በሆዱ!! እንዳሰበውም የሮማ ጀግኖች ቁንጮ ታላቁ ተፋላሚ ካሲየስ ኬሪያ ካለበት መሠሥ ብሎ ወደ ፍልሚያው ጎራ ዘለቀ፡፡
ነገር ግን ካሲየስ ራሱ ካሊጉላ የሸለመውን የክብር ጎራዴ መዘዘና በራሱ በካሊጉላ ላይ አሣረፈበት፡፡ ካሊጉላ አይኖቹን ማመን አልቻለም፡፡ ላፍታ መብረቅ የወረደበት መሠለ፡፡ የጨው አምድም ሆኖ ቀረ፡፡ አይኖቹን አፍጥጦ ትኩር ብሎ ካሲየስን አየው፡፡ እና በሮማውያን አባባል ታማኝ ጠባቂውን ካሲየስን ʿʿግን ለምን???ʾʾ አለው፡፡
ይህቺ “ለምን?” የአንድ ሺህ ለምኖችን ያህል ነበረ ጩኸቷ፡፡ እንዲያውም የሚሊዮን፡፡ ወይም የቢሊዮን ለምኖችን ያህል፡፡ ከዚያ ካሊጉላ ፍልሚያውን አቆመ፡፡ ላፍታ ሁሉም ግራ ገብቷቸው ደርቀው ቀሩ፡፡
ካሲየስ ግን ደርቆ አልቀረም፡፡ ጀግንነት ብዙ አስተምሮታል፡፡ “ለምን?” የሚሏት ጥያቄ ባብዛኛው መልስ የሌላት የህይወት ጥያቄ ናት፡፡ ህይወት ሁሉንም ለምኖችህን አትመልስልህም፡፡ አንዳንዴ ከለምንህ ጋር መኖር አለብህ፡፡
ህይወት መቀጠል አለባት፡፡ ስለዚህ ለምንን ትተህ በቆራጥነት በህይወት መድረክ መራመድ አለብህ፡፡ ለምንህ በጊዜ ሂደት መልስ ታገኝ ይሆናል፡፡ ለዝንተ ዓለምም አትመለስልህ ይሆናል፡፡ ህይወት ግን መቀጠል አለባት፡፡
ጀግናውን ካሲየስን የካሊጉላ “ለምን?” ላፍታ አስደነገጠችው፡፡ ከዚያ ግን.. ብዙ ለምኖችን አልፎ የቀረችው የመጨረሻው ለምኑ ነበረችና… ለጥያቄዋ ፊት አልሰጣትም፡፡
ይህችን ለምኑን ፊት ቢሰጣት ዳግመኛ በህይወት አይሻገራትም፡፡ እና በቃ ለምኑን ወደጎን ብሎ ፊት ለፊቱ ያለውን ካሊጉላን በጎራዴ ዳግመኛ መታው፡፡ ካሊጉላም ጎራዴውን የተቀበለው በፀጋ ነው፡፡
ዕጣ ፈንታህን – በፀጋ ትቀበለዋለህ እንጂ – ምን ልታደርገው ኖሯል!?? – ምንም!! አዎ – ትንሹ ከስክስ – ካሊጉላ – እልፍ አዕላፎችን ሲከሰክስ ኖሮ – በመጨረሻ ራሱ ተከሰከሰ!
ትወድቃለህ፡፡ ትፈራገጣለህ፡፡ ትነሣለህ፡፡ መልሰህም ትወድቃለህ፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ። ካሊጉላ ያሳዝነኛል። ህይወት እንዲህ ናት! የካሊጉላ ታሪክ አላበቃም፡፡ እኔ ግን አበቃሁ፡፡
“There’s no question why,
But to do and die.”
አልፋና ኦሜጋ የሆነ ህያው ፈጣሪ አምላካችን.. ሁላችንን በቸር ያቆየን፡፡
መልካም ጊዜ፡፡