>

ጋዜጠኛ ከፋለ ማሞ አለሜ ሲታወስ   (ጌታቸው አበራ)

ጋዜጠኛ ከፋለ ማሞ አለሜ ሲታወስ

1930-2014

ጊዜው እንደኛ አቆጣጠር 1988 ዓ/ም (እ.አ.አ. 1996)ነበር። የወያኔ/ኢህአዲግ ስርአት የኢትዮጵያዊነትን ታሪካዊ ምልክቶች ሁሉ ለማኮስመንና ለማክሰም የሚጣደፍበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የወያኔው ቀንደኛ መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ፣ “ባንዲራ ጨርቅ ነው”፣ “አድዋ ለወላይታው መኑ ነው..” ወዘተ. እያለ፣ ያለእፍረትና ማናለብኝነት የድንቁርናና የታሪክ ክህደቱን በአደባባይ የሚዘራበት ጊዜ ነበር።

በአንጻሩ ደግሞ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በያሉበት፣ ለአገራቸው ክብርና ፍቅር ቀናዒ ሆነው፣ በሚሆነው ነገር ሁሉ የተቃጠሉበት፣ ስለ ውድ አገራቸው በገዢው በወያኔ/ኢህአዲግ በየጊዜው የሚነገሩት የንቀትና የጥላቻ ቃላት በንዴት የሚንገበገቡበት ወቅትም ነበር። በዚህም የተነሳ፣ በየዓመቱ ታሪካዊ ክብረ-በዓላት በመጡ ቁጥር፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት በመሰባሰብ፣ በእልህና በቁጭት ተውጠው፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ክብረ-በዓላት በታላቅ ክብርና ከፍታ ነበር የሚያከብሩት።

በዚህን ወቅት ነበር፣ የኢትዮጵያውያን ማኅበር በሆላንድ፣ የአድዋን የመቶኛ ዓመት መታሰቢያ በታላቅ ክብርና ድምቀት ሊያከብር የተዘጋጀው፤ እናም በወቅቱ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢነጋማ) መስራች ከነበሩት አንዱና የማኅበሩ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረውን ጋሼ ከፋለ ማሞን በበዓሉ ላይ የሚታደም የክብር እንግዳ አድርጎ ከኢትዮጵያ ድረስ የጋበዘው። በዚያን ጊዜ ነበር ከጋሼ ከፋለ ማሞ ጋር ትውውቃችን የጀመረው። ከአድዋ በዓል መከበር በኋላ፣ ወደ እናት አገሩ ተመልሶ የፕሬስ ነፃነቱን ትግል ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ማቀጣጠሉን ተያያዘው። በውጭ በስደት ላይ ላለነውም ስለ አገር ቤቱ ሁኔታና ትግል የተጣራ መረጃ በደብዳቤዎቹ ያደርሰን ያዘ።

በዚያን ጌዜ ኢትዮጵያችን ከቻይናና ከቱርክ በመቀጠል፣ የነፃ ፕሬስ ጋዚጠኞችን በወህኒ በማጎርና በማሰቃየት ክፉ ዝናዋ ባለም ናኝቶ ነበርና፣ ጋሼ ከፋለ ማሞ በነፃ ፕሬስ ማኅበር ፕሬዚዳንትነቱ ብርቱ ፈተናና ከባድ ኃላፊነት እላዩ ላይ የወደቀበት ፈታኝ ወቅት ነበር። እርሱም ራሱ፣ ለተወሰነ ጊዜ የወያኔ/ኢህአዲግን እስር ቤት አይቶ ወጥቷል። በመሆኑም ለነዚያ በወያኔ ወህኒ ለሚማቅቁት የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች አንደበት በመሆን፣ ለዓለም ማኅበረሰብና ለዓለም-አቀፍ የሙያ ማኅበራት፣ በደልና ስቃያቸውን ማስተጋባት ነበረበት። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በነፃ ፕሬስና በጋዜጠኝነት ሙያ ዙሪያ የሚደረጉ ሴሚናሮችንና ስብሰባዎችን፣ የኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ማኅበር ወክሎም ተገኝቷል።

በወቅቱ ከጨካኙና ከአምባገነኑ መንግሥት ጋር ፊት-ለፊት ተጋፍጦ ለነፃው ፕሬስ ማበብ ላደረገው አስተዎጸዖም ፣ ዋና መቀመጫውን ቡሩሰልስ-ቤልጅየም ያደረገው፣ አይ ኤፍ ጄ(International Federation For Journalists) እና የኔዘርላንዱ የጋዜጠኞች ማኅበር (Dutch Association of Journalists) በሆላንድ ጸሀፊ፣ ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ በሮብ ቤከር (Rob Bakker) ስም የተሰየመውንና ለነፃ ፕሬስ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ጋዜጠኞች የሚሰጠውን ሽልማት ለማግኘት በቅቷል።

ትግሉ ሲፋፋም፣ የወያኔም የጭቆና ሰንሠለት እየጠበቀ ሲሄድ፣ ወያኔ፣ በተለይ በአለም-አቀፍ ደረጃ የመሳጣቱን ነገር መቀበል ሲያቅተው፣ ሁሌም እንደሚያደርገው ማሳደድና መውጪያ መግቢያ ማሳጣቱን አጥብቆ ስለገፋበት፣  በአገር ውስጥ ሆኖ ትግሉን መቀጠልና ተግባሩን ማከናወን እንደማይችል የተረዳው ጋሼ ከፋለ ማሞ፣ ወደ አውሮፓ በስደት ተቀላቀለን።

በሀገረ-ሆላንድ በስደት ላይ ሆኖም፣ ከአለም-አቀፍ የጋዜጠኞች ማኅበራት ጋር አስቀድሞ በፈጠረው መልካም ግንኙነት መሰረት፣ መረጃዎችን በማቀናጀት፣ ለትግሉ አይነተኛ አስተዋጽዖ ከማድረጉም በላይ፣ በወያኔ የሚደርስባቸውን አፈና፣ ሰቆቃና ስቃይ በመሸሽ፣ በየውጭ አገራቱ ለሚሰደዱ የነፃው ፕሬስ አባላትም በየተሰደዱበት አገር ከለላ እንዲያገኙ፣ የትብብርና የምስክርነት ደብዳቤዎችን በመጻፍ ለብዙዎች ቤዛ ለመሆን ችሏል።

በአውሮፓ ከተሞች ሲደረጉ የነበሩትን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባዎችንና ስለ አገር የሚደረጉ ማኅበራዊ ውይይቶችን፣ በስደት ነዋሪ ከሆነበት ከሆላንድ ውጭም፣ አንዳንዴ በጀርመን፣ በቤልጅየም፣ በፈረንሣይ… እየተገኘ፣ አገር ቤት ለሚታተሙ መጽሔቶች ዘገባዎችን ይልክ እንደነበረ የቅርብ ምስክር ነኝ። በተለይም ለተወዳጇ የጦቢያ መጽሔትና ጋዜጣ በብዕር ስሞች እየተጠቀመ ጽሁፎች ይልክ ነበር። በግሌ ከማውቃቸውና ይጠቀምባቸው ከነበሩ የብዕር ስሞቹ፣ አንተነህ ሰላሙ፣ ደስታ በጋሻው፣ አርአያ ማርቆስ ይጠቀጋሼ ከፋለ፣ ሰው ሳይለይ ሁሉንም በእኩል ዐይን የሚያይና ለሁሉም ዜጋ 

እንደ ታላቅ ወንድም የነበረ ሰው ነው። 

ለሰዎች ቀና አሳቢና ለስኬት አበረታችም ነበር። እኔ ከሆላንድ የስደት አገር ቀይሬ ወደ አሜሪካን በሄድኩበት ጊዜ፣ ትምህርት የመቀጠል ፍላጎት እንዳለኝ በነገርኩት ጊዜ፣ ልጁ ሚሚ ካፋለ ዳላስ እንደምትኖር ነግሮኝ ወደ እርሷ ዘንድ እንድሄድ አመቻችቶልኝ፣ ቤተሰባዊነታችን በሚሚ በኩል እስካሁንም እንዲቀጥልና እንዲጠናከር አስችሏል።

አሜሪካ ከገባሁም በኋላ፣ እነዚያ መካሪና አስተማሪ ደብዳቤዎቹ ተከትለውኝ ነበር። የዳላስን ማኅበረሰብ ለማገልገል፣ በማኅበረሰቡ የራድዮ ጣቢያ አማካኝነት ስንፍጨረጨርም፣ የእርሱ የዘወትር መመሪያዎችና፣ የሚድያ ‘ኮርሶች’ እንደ የተልዕኮ(የርቀት) ትምህርት ነበሩ። ወደበኋላም ከአገር ወዳድ ዜጎች ጋር በመተባበር፣ ልጁ ሚሚ ከፋለም ያለችበት “ኢትዮ-ባህል” የምትባል በአማርኛ የምትዘጋጅ ጋዜጣ ስናሳትምም፣ የጋሼ ከፋለ ብዕር በምክር ሁሌም ከጎናችን ነበር።

በደብዳቤዎቹ፤ “ለእንቅልፍ አልጋ ላይ እስክወጣ፣ ዐይኔ ከንባብ፣ እጄ ከመጻፍ ከቶውንም አይለያዩም” ይል ነበር። የአሜሪካንን አገር ሩጫ ተረድቶ ስለነበርም፣ “የቡዴናን (የእንጀራን ለማለት) ጉዳይ እያከናወናችሁ፣ የኢትዮጵያንም ጉዳይ ማስታወሳችሁን እርግፍ አድርጋችሁ እንዳትተዉ አደራ” እያለ እያዋዛ ምክሩን ይለግሰን ነበር።

በህይወቴ ከምደሰትበትና ከምኮራበት ነገር አንዱ፣ በጋሼ ከፋለ አማካኝነት ተመቻችቶልን፣ የኢትዮጵያው ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን በህይወት ሳሉ፣ በኒውዮርክ ከተማ በህክምና ላይ ሆነው፣ ከክብረት መኮንን፣ ሚሚ ከፋለ፣ ዘገየ ፍርዱና አይችሉህም አባተ ጋር በመሆን፣ ሎሬት ጸጋየ የህይወት ዘመን ታሪካቸውን፣ በራሳቸው አንደበት በቃለ-መጠይቅ መልክ ለታሪክ እንዲያስቀሩ የሆነበት መልካም አጋጣሚ ነው። ጋሼ ከፋለ ቃለ-መጠይቁን በሚገባ አዘጋጅቶና ልኮልን፣ ክብረት ከአምስተርዳም፣ የተቀረነው ደግሞ ከዳላስ-ቴክሳስ ተጉዘን፣ ኒውዮርክ ላይ በመጠኑም ቢሆን ታሪክ የተሰራ ይመስለኛል። ጋሼ ከፋለ የባለቅኔው የሎሬት ጸጋዬን የህይወት ታሪክ በሚገባ አዘጋጅቶ ከድምጽ ቅጂ በተጨማሪ፣ በጽሁፍ ተገልብጦና ተጠርዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ላለው ለኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ማዕከል ተስጥቶ ለትውልድ ዋቢ ይሆን ዘንድ ከፍተኛ ምኞቱ ነበር። በአንድ ወቅት በጻፈልኝ ደብዳቤ ላይ ይህን ብርቱ ምኞቱን እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ “እግዚአብሔር እድሜውን ከሰጠኝ፣ ኢትዮጵያ ለጸጋዬ የህይወት ታሪክ ሥራ ስል ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ከፍዬ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን መመለስ ይኖርብኛል። እንግዲህ የወያኔ መንግሥት እንዲወድቅ አምላክን የምማጸነው፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ብቻ ሳይሆን፣ የሎሬትንም የህይወት ታሪክ የማዘጋጀት ሥራዬን ዳር ለማድረስ እንድበቃም ጭምር ነው።”

ይህንን ታሪካዊ የሎሬት ጸጋዬን ቃለ-መጠይቅ በቪድዮ ከቀረጹት መሃል አንደኛው ክብረት መኮንን ከዚህ ቀደም ስራዎቹን በጽሁፍም፣ በቪድዮም እየከፋፈለ ለህዝብ እንዲደርስ ሙከራ ማድረጉን አውቃለሁ። ይህም በእጅጉ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው። ሆኖም የጋሼ ከፋለን የህይወት ዘመን ምኞት ለማሳካትም፣ ለትውልድ ቋሚ ቅርስ ለማኖርም፣ እርሱ አስቦት አንደነበረው፣ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን የህይወት ታሪክ፣ በጽሁፍ ተጠርዞ፣ በድምጽም ተዘጋጅቶ፣ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ቢበረከት፣ የባለቅኔውን ታሪክ ሊመራመሩ ለሚፈልጉ ሁሉ ታላቅ ግበዓት ስለሚሆን፣ በዚያ ቃለ -መጠይቅ ላይ ተካፋይ የነበርን ሁሉ ተባብረን ኃላፊነታችንን እንድንወጣ በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ።

አቶ ከፋለ ማሞ አለሜን በዋናነት እንዴት ነው የምናስታውሰ ቢባል፤ ከብዙ ጠንካራ ጎኖቹና ተግባራቱ፣ ለእኔ ጎልቶና ገዝፎ የሚታየኝ፤ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ሰውንና ስራዎን አጥብቆ አክባሪ፣ በእጅጉ አገሩን የሚወድ፣ ለአገሩና ለህዝቡ ሁሌም የሚቆረቆርና በጎ እሚመኝ፤ በተለይ በኢትዮጵያችን የነፃ ፕሬስ (የሃሳብ ነጻነት) እንዲሰፍንና እንዲጠናከር፣ ከፍተኛ ምኞትና ፍላጎት የነበረው፣ ያንንም እውን ለማድረግ የሚቻለውን ብርቱ ጥረት ሁሉ በተግባር ያደረገ፤ የነፃ ፕሬስ ታሪክ በኢትዮጵያ ሲወሳ፣ ስሙና መልካም ተግባሩ ሁሌም አብሮ ሲታወስ የሚኖር ጉምቱ ኢትዮጵያዊ ነው።

ይጽፍልኝ ከነበሩት ደብዳቤዎቹ ባንዱ፣ “የተለያዩ፣ ሙያን አክብረው የሚከተሉ ዜጎች አገርና ወገንን ከችግር ለማላቀቅ የተለያዩ መርሐ-ግብሮችን ይነድፋሉ፤ ያቀርባሉ፤ ጋዜጠኞች ግን ቋሚ ተለዕኮ አለን ይላሉ፤ ጊዜን አይቶ የማይለወጥ፤ ነገር ግን ሰው በዓለም ላይ እስከኖረ ድረስ ሰውን ለማገልገል የሚችል ተለዕኮ!” ብሎ ነበር። ጋሼ ከፋለ ማሞ፣ ያንን ተልዕኮ በምድር ላይ በሚገባ ፈጽሞ፣ 

በዕለተ-ማክሰኞ ጥቅምት 2 ቀን (ኦክቶበር 12) አርፎ፣ በሳምንቱ ማክሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ/ም (ኦክቶበር 19፣ 2021) ቤተሰብ፣ ወዳጅ-ዘመድና በሆላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የቀብር ሥነ-ስርዓቱ በሆላንድ-አምስተርዳም ተከናውኗል።

በመጨረሻም፣ ለልጁ ለሚሚ ከፋለና ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ፣ ለሙያ አጋሮቹና ለኢትዮጵያ ነፃ ፕሪስ አባላት መፅናናትን እመኛለሁ!  ጋሼ ከፌ! ሁሌም ትናፈቃለህ! ዘወትርም በልባችን ውስጥ ሥፍራ አለህ! እግዚአብሔር ነፍስህን በአፀደ-ገነት ያኑርልን! አሜን!

   ጌታቸው አበራ

ጥቅምት 2014 ዓ/ም

  (ኦክቶበር 2021) 

Filed in: Amharic