ከተጣድንበት የዘር-ልዩነት አስተዳደርና ፖለቲካ እንውጣ!
አሳፍ ሀይሉ
የወያኔ-ኢህአዴግ ጦርሠራዊት ኢትዮጵያን በኃይል ከተቆጣጠረ ከ1983 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ላለፉት ወደ ሶስት አሰርት ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያት ሁሉ – በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረው በዘር («በብሔር») ክፍፍል ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ የአስተዳደር ዘዴ – በሁሉም የዓለም ሀገራት ተሞክሮ ያልተሳካ – እና በመራር መስዋዕትነት ህዝቦች ታግለው ያስወገዱት «Separate but Equal» የተሰኘ የዘረኝነት ፖሊሲ ነው፡፡
ይህ ፖሊሲ የሰዎችን ወይም የዜጎችን እኩልነት ለይስሙላ ይቀበልና – ነገር ግን አንዱ ከሌላው ፍፁም የተለየ ስለሆነ፣ አንዱ ወደ ሌላው ሳይሻገር፣ ሁሉም በያለበት የየራሱን ክልል ጠብቆ መኖር አለበት – በማለት ሁሉም እንደየዘሩ በተሰመረለት የአስተዳደር ክልል ውስጥ ሌላው ሳይገባበት የራሱን ህይወት ይኑር – የሚል ነው፡፡
ይህ «Separate but Equal» ፖሊሲ በተለይ በይፋ የመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ በአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ ተተግብሯል፡፡
በአሜሪካም ጥቁሮች ሙሉ ሰው አይደሉም ከሚለው ግልጽ የህገመንግሥት ትርጓሜ ከተሰጠበት ሀገራዊ ፖሊሲያቸው ተሻሻልን ብለው ያመጡት ፖሊሲ ይሄን «Separate but Equal» ፖሊሲ ነበር፡፡
ጥቁርና ነጭ ሁለቱም እኩል ናቸው፡፡ ነገር ግን ነጩም በራሱ ክልል፣ ጥቁሩም በራሱ ክልል በተለየ የየራሳቸው አስተዳደር ተለያይተው መኖር አለባቸው የሚል ፖሊሲ ነበር፡፡
ይህ በአሜሪካ የሰብዓዊ መብት አራማጆችና የጥቁሮች ነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ ተጋድሎና መስዋዕትነት ቢያንስ በመንግሥት ደረጃ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በደቡብ አፍሪካም ከፍተኛ መስዋዕትነትን በጠየቀ ህዝባዊ ትግል የአፓርታይድ የ«Separate but Equal» ፖሊሲ ወደ መቃብር ወርዷል፡፡
ይህን «Separate but Equal» ፖሊሲ የጀርመን ናዚዎች – ኋላ ላይ ወደ ሆሎካስቱ የዘር ጭፍጨፋ ከመሸጋገራቸው በፊት – አስቀድመው በይፋ የመንግሥት ፖሊሲ አድርገው ሞክረውት፣ ፅዮናውያንንና ሌሎችን ለብቻቸው የየራሳቸውን አንዱ ወደ አንዱ የማይገባበትን ጊዜያዊ የአስተዳደር ክልል መሥርተውላቸው ለሥራና ለሌሎች ብቻ ከተቀሩት ጀርመናውያን ጋር የሚገናኙበትን አሠራር ዘርግተው ሲተገብሩት መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
እንግሊዞችም በቅኝ ግዛት ባስተዳደሯቸው ሀገሮች ሁሉ ላይ ይህን «Separate but Equal» ፖሊሲ ለመተግበር ሞክረዋል፡፡ ከአፍሪካ በተለይ በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባቡዌና በኬንያ፣ በሱዳንና በግብጽ እነዚህን በዘር ሽንሸና ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎች ተግብረዋል፡፡
ቤልጂያኖች በኮንጎና ሩዋንዳ ውስጥ፣ አሜሪካኖቹ በጥቁሮች የምትተዳደረውን የላይቤሪያን ራስ-ገዝ ቅኝ ግዛት ሲመሰርቱም ለመተግበር የሞከሩት ፖሊሲ ይሄንኑ «Separate but Equal» የመሰለ ፖሊሲ ነበር፡፡
ጃፓኖችና ፈረንሳዮች በቬትናም ላይ የተገበሩት ፖሊሲ ከዚህ ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡
ብዙዎች የሶስተኛው ዓለም የ20ኛው ክፍለዘመን የፖለቲካ ልሂቃን፣ ደራሲያን፣ የማኅበረሰብ አጥኚዎችና ምሁራን እንዲሁም በየሥፍራው የፀረ-ቅኝ ግዛት አጀንዳን አንግበው ህዝባቸውን እያስተባበሩ ብቅ ያሉ የነፃነት ታጋዮችም – ሳያስቡት የዚህ እኩይ የዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ እኩልነትን አንግቤያለሁ የሚል የዜጎች ክፍፍል አስተሳሰብ ተፅዕኖ ሥር ወድቀዋል።
ብዙዎቹ – ከምዕራባውያኑ ቅኝ ገዢዎች የተለየ የራስን ማንነት (- ለምሳሌ ያልተበረዘ አፍሪካዊ ማንነትን – ለመፈለግና ለመላበስ ሲሉ ብቻ) – አውቀውም ሆነ ሳያውቁት – ራሳቸውንና ህዝባቸውን ወደ ጎሳዊነት፣ በዘር ወይም በብሔር ማንነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ማንነት እንዳለው ህዝብ፣ ወይም በዘር ማንዘር የትውልድ ሀገር እየተቧደነ ሲገኝ አፍሪካዊነቱ እንደሚረጋገጥ ማንነት ‹‹ኦተንቲክ አይደንቲቲ›› ፈጥረው የሙጥኝ ብለዋል፡፡
ከምዕራባዊው ዓለም የተለየ አፍሪካዊ የብሔር ማንነት ብቸኛው የአፍሪካውያን ማንነት መሆኑን እንደሚሰብኩት የእነ ቼኑዋ አቼቤ ድርሰቶች፣ የእነ ኤንዌዞር፣ አፒያና የሌሎችንም አፍሪካውያን ጠበብት ሥራዎች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ያ ነጮቹን ለመታገል ስንል፣ በዓለማዊ-አተያያችንና በራስ-አተያያችን ሁሉ ከቅኝ ገዢዎቹ የተለየን መሆናችንን ለማረጋገጥ ስንል፣ ከምዕራቡ የግልሰባዊ አስተሳሰብ የተለየ አስተሳሰብ የተለየ ማኅበረሰባዊ አስተሳሰብ እንዳለን ለማስረገጥ ስንል የፈጠርናቸው ቅኝ አገዛዝን ለመታገል ያገለገሉ ‹ኮሚዩናል አይደንቲቲ ኤንድ ፕሪሚቲቪዝም› አስተሳሰቦች – ከቅኝ ግዛት ዘመንም በኋላ ኤክስፓየሪ ዴታቸው አልፎም በመላ አፍሪካውያንና ሶስተኛው ዓለም ሀገሮች አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ይህም ፖለቲካችን፣ አስተዳደራችን፣ ኢኮኖሚያችንና አስተሳሰባችን ተገቢውን ፍጥነት ጠብቆ ወደተፈላጊው ዘመናዊ ሂደት እንዳይሸጋገር ማነቆ ሆኖ ይዞታል፡፡
ሌላው ዓለም የሚበጀውን ሀገራዊ ፖሊሲ ነድፎ እያሳደገ የዛሬ ዘመናዊ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች እስከዛሬም ድረስ በጎሳ ልዩነትና በዘር ማንነት ላይ ብቻ ችክ ብለን የቀረንበት ምክንያት – ያ የነፃነት ተጋድሎ ስልት “ኤክስፓየር” ያደረገ አስተሳሰብ መሆኑን መገንዘብ ስላቃተን – እና ከገባንበት የጎሳዊ ወይም ነገዳዊ ማንነት ሰመመን በጊዜ መንቃት ስላልቻልን ነው፡፡
የሚገርመው ነገር – ሳናውቀው የ«Separate but Equal» ፖሊሲን በየሀገራችን እየተገበርን ራሳችንን የነጮቹ ቅኝ ገዢዎች ሥራ አስፈጻሚ አድርገን መኖራችን ብቻ አይደለም፡፡
ከላቲን አሜሪካ እስከ እስያ – ከአፍሪካ እስከ እስከ አውሮፓና አውስትራሊያ ድረስ – ይህ በዘር ሽንሸናና ልዩነት ላይ የተመሠረተ የ«Separate but Equal» አስተዳደራዊ ፖሊሲ በተተገበረባቸው ሥፍራዎች ሁሉ – ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገርም አለ።
ፖሊሲው በስም «Separate but Equal» ይባል እንጂ – በተግባር ግን የታየው «Separate and Unequal» (የተለያየንም ነን፣ እኩልም አይደለንም) የሚል አንድምታ ይዞ መገኘቱ ነው፡፡ በአብዛኞቹ ውስጥ በ«Separate but Equal» ስም የሆነው «Separate and Unequal» ነው፡፡
ይህ ያረጀ ያፈጀ ዘረኝነት የወለደው (ነገር ግን በጊዜ ሂደት መልኩን ቀይሮ በተለያዩ ቅርጾችና ስሞች እየተገለጠ በተለያዩ ዓለማት ሥራ ላይ የዋለው) የ«Separate but Equal» ፖሊሲ ከባድ ክስረት ስላጋጠመውና ሁሉም ግልጽ ትርጉሙና ድብቅ ዓላማው በስተመጨረሻ እየገባው ስለመጣ – ዛሬ ላይ – በሁሉም የዓለማችን ሉዓላዊ ሀገራት ሊባል በሚችል ደረጃ – ከመንግሥታዊ አስተዳደር ዘዴነት እንዲወገድ ተደርጓል፡፡
በዛሬው ጊዜ በብዙ የዓለም ሀገሮች የምናገኘው የህዝብ አስተዳደር ዓይነት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን ልዩ ባህል፣ እሴት፣ ግለሰባዊ ፍላጎትና እምነት፣ ወዘተ በብዙሃኑ ተውጦ እንዳይጠፋና እንዳይጠለሽ ይዘውና ጠብቀው ለማቆየት የሚሹበት፣ እና ሌሎችም (ትርጉሙ አሻሚነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ – ከሀገር አጠቃላይ ህግና ሰብዓዊ ግብረገብነት እስካላፈነገጠ ድረስ) ያንኑ የሰዎችን የተለየ ባህል፣ ማንነት፣ ዕምነት ወይም አስተሳሰብ ጠብቀው የሚጓዙበትን ሀገራዊ አስተዳደር ነው፡፡
በአሁን ወቅት ተግባራዊነቱ አንዱ ከሌላው ቢለያይም በብዙ ሀገሮች ተቀርጾ የምናገኘው ፖሊሲ የ«Separate but Equal» ሳይሆን «From Diversity to Pluralism» የሚል ነው፡፡
ዜጎች በዘር ልዩነት ሳይሸነሸኑ፣ ዘመናዊና አመቺ የአስተዳደር መርሆዎችን ተከትለው በተዋቀሩ ክፍላተ ሀገሮች (ወይም ክልሎች) ውስጥ የተለያየ ባህል፣ ማንነት፣ አስተሳሰብ፣ ዕምነት፣ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር ያላቸው ዜጎች በጋራ አብረው እየኖሩ – መብቶቻቸው ተከብሮላቸው የሚኖሩበት – ልዩነትን የሚያስተናግድ የብዙሃን አስተዳደር ዘይቤ ነው ያለው፡፡
ይህም በሌላ አነጋገር በአንድ ሀገር ጥላ ሥር የሚገኙ አስተዳደራዊ ድንበሮች ዓላማና የመካለል መሠረት ለአስተዳደር ካላቸው አመቺነት ብቻ እና ብቻ የተነሳ እንጂ፣ በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆንም፣ የዘር ልዩነትን አስተሳሰብ ለማስቀጠል እንዳይውልም ሆነው የሚቀረፁበት ዘመናዊ የሀገር አስተዳደር ስልት ነው በዘመናዊው ዓለም ላይ እየተተገበረ ያለው እንደ ማለት ነው።
እና በእኛ ሀገር – ሆን ተብሎም ይሁን ወይም በተለያዩ ነባራዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ-ርዕዮተዓለማዊ ምክንያቶች አስገዳጅነት – ለክፋትም ይሁን ለመልካም ዓላማ – በይስሙላም ሆነ በእውነት – ላለፉት 30 ዓመታት በተግባር ተተግብሮና ተሞክሮ የከሸፈው – እና ለዚህ አሁን ላለንበት ሀገራዊ ቀውስና ውጥንቅጥ ያደረሰን – በሌሎች ዓለማት ጉዳቱና ጦሱ ገሃድ ወጥቶ – ከዘመናዊው የሰው ልጅ የእኩልነትና የሰብዓዊ አመለካከትም ጋር አብሮ እንደማይሄድ ታውቆ የተተወ ለዘመናዊ አኗኗርና ያገር እድገት ጠንቅ የሆነ አሠራር ነው ማለት ነው።
እንዲሁም ዓለም ሁሉ የአንድ ሀገር ዜጎች በአንድ ሀገራዊ አስተዳደር ጥላ ሥር ልዩነቶቻቸው ተከብሮላቸው በጋራ ተቀላቅለው አብረው በሠላም የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ እንጂ ሁሉም ከሰው ልጅ ዘር (homosapiens species) ዝቅ እንዳለ እንደ ልዩ ልዩ እንስሳት ወይም እፅዋት በተለያየ ዝርያ (ዘር) ተሸንሽኖና ተከፋፍሎ የሚኖርበት ሥርዓት ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ማንነትና ህሊና የተገባ እንዳልሆነ ተገንዝቦታል ማለት ነው።
መገንዘብ ብቻም ሳይሆን – ‹‹ውጉዝ!›› ብሎ የጣለውን – «Separate but Equal» መንግሥታዊ (እና ህገ መንግሥታዊ) የልዩነትና የክፍፍል ሀገራዊ አስተዳደር – በጊዜ እውነታውን አውቀን ከላያችን ላይ አውልቀን መጣል ካልቻልን – የሚጠብቀን ጦስና የምናወራርደው ዕዳ ገና ብዙ ብዙ ነው፡፡
ሀገራት ሁሉ ወይም ዓለሙ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይሳካለትም አይሳካለትም – ቢያንስ በመርህና በሀሳብ ደረጃ – ዛሬ ሁሉም ተቀብሎት ከ«Separate but Equal» ወደ ኅብረ-ብሔራዊነት («Multiethnic Society») ከተሻገረ አሰርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከዚያም ተሻግሮ ደግሞ ሁሉንም በልዩነቱ ወደሚያስተናግድ ህብረትና አብሮነት ወዳልተለዩት፣ ዜጎች በመግባባት ተያይዘው (ሳይነጣጠሉ) እና ተደጋግፈው ልዩነታቸውን አክብረው የሚኖሩበትን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይን ያነገበ፣ ጠንካራ ሀገራዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት «From Diversity to Pluralism» በሚል ሰብዓዊና ዘመናዊ ፖሊሲ ወደፊት እየገሰገሰ ያለበት ዘመን ላይ ነን።
በእኛ ሀገር ይዘነው የሙጥኝ ያልነውን – እና እንዲህ ለቃላትም ለጥናትም እስከማይመች በዘር ሸንሽኖ እርስ በእርስ የከፋፈለንን፣ ያጠላላንን፣ ያለያየንንና ያፋጀንን – እያፋጀንም ያለውን – ያን ያረጀ ያፈጀ «Separate but Equal» (በዘር ልዩነት፣ ሽንሸናና ክፍፍል ላይ የተመሠረተ) ሀገራዊ ፖሊሲ ገሸሽ ማድረግ የሚጠበቅብን – ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
ለውጥ ማምጣት ማለት ይህን ነባር አፓርታይዳዊ የዘር ልዩነት ፖሊሲ ከመንግስትና ከዜጎች አሠራሮች ሁሉ ውስጥ ማስወገድ ማለት ነው። ትልቁ ፈተናችን ይህ ነው፡፡ ትልቁ ዕድልም ሆኖ ከፊታችን እየጠበቀን ያለው ይኸው ነው፡፡
“የራሳችሁን ማንነት ይዛችሁ በእኩልነት ብትለያዩ ይሻላል” “you are Separate and Equal” የተባሉት ሁሉ፣ እኩልነትም ሳይጎበኛቸው፣ እንደዚያው እንደተለያዩ ቀርተዋል።
ዓላማችን እኩልነትን አጥፍተን መለያየት ከሆነ የጀመርነው 30 ዓመት ያስቆጠረ “በልዩነት-እኩልነት” ጉዞ አዋጪ ይሆናል። አብረን እንኑር፣ እኩልነትን እናስፍን ካልን ግን የጀመርነውን ጉዞ ወደዘመናዊው ዓለም መቀልበስ የግድ ሊለን ነው። ምርጫው ከፊታችን ተዘርግቷል። ምርጫው በኛው እጅ ነው የምለውም ለዚህ ነው።
በመጨረሻም “አፓርታይዳዊነቱን” የነገርከንን Separate-but-Equal ፖሊሲ ከላያችን አራግፈን “አሃዳዊነትን” እንድንላበስ እየሰበክከን ነው ወይ? ለምትሉ አንባቢዎቼ፣ የምሰጠው መልስ ሳይሆን ጥያቄ ነው፦
“ላለፉት 30+ ዓመታት እየተመራንበት ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት የፌዴራል ፓርላማውን (የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤቱን) የሀገሪቱ የበላይ አካል በማድረግ በአሃዳዊነት ከሚታወቁት unitary states ከእነ እንግሊዝ፣ ጃፓን፣ ዴንማርክ፣ ጣሊያን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና፣ ወዘተ ሀገሮች ጋር በአንድ ተርታ እንዳሰለፈን የምታውቁ ስንቶቻችሁ ትሆኑ?” ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ።
በደቡብ አፍሪካ Separate-but-Equalን አፓርታይዳዊ ሥርዓት የተከሉት እንግሊዞች፣ ዛሬ ራሳቸውን ከዘር ክፍፍል አርቀው ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሁሉም የጋራ ሀገርን ስለመመሥረት ለዓለም የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ሆነዋል።
እኛ ብቻ የእነሱንና የከሸፉ አብዮቶችን ርዕዮታለማዊ ልቅላቂዎች ይዘን፣ ከዘመናዊው ዓለም በተቃራኒው አቅጣጫ የኋልዮሽ እያዘገምን ነው። ይህንን አይቶ፣ አስተውሎ፣ መርምሮ፣ መቀበል የመፍትሄያችን ግማሽ መንገድ ነው። የመፍትሄ፣ የለውጥ ሰዎች ይበለን።
ፈጣሪ ይርዳን፡፡