>

ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የሞርጌጅ ባንክ የተቋቋመው ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት እንጂ ዛሬ. በአዳነች አበቤ አይደለም!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የሞርጌጅ ባንክ የተቋቋመው ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት እንጂ ዛሬ. በአዳነች አበቤ አይደለም! 
አቻምየለህ ታምሩ

አዳነች አበቤ ገራሚ ፍጡር ናት። በድንቃድንቅ መዝገብ የሚሰፍር “ታሪክ” ከሰሩ ሰዎች መካከል የምትመደብ ይመስለኛል። ይህን እንድል ያስቻለኝ በአለም ታሪክ ውስጥ በአንድ የምርጫ ዘመን የሁለት ከተማ ከንቲባ ሆኖ የተሰየመ አንድ ሰው ስለማላውቅ ነው።
ከንቲባ በአንድ የምርጫ ዘመን በአንድ ከተማ ውስጥ በሕዝብ የሚመረጥ የከተማው ዋና ራስና የሕዝብ ተሿሚ ነው። አዳነች ግን በአንድ የምርጫ ዘመን የሁለት ታላላቅ ከተሞች ከንቲባ ሆናለች። አዳነች በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ከመጫኗ በፊት በኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘመን በናዝሬት ከተማ ሕዝብ ላይ የተጫነች ከንቲባ ነበረች። ዐቢይ አሕመድ በርዕሰ መስተዳድርነት ከተሰየመ በኋላ ደግሞ የመሬትና የኮንዶምኒዬም ሌባውን ታከለ ኡማን ተክታ የአዲስ አበባ ዋና ከንቲባ ሆና ተሰየመች።
በአንድ የምርጫ ዘመን፤ ሌላ ምርጫ ሳይካሄድ ከአንድ ከተማ ከንቲባነት ተነስታ በከንቲባ ይገዛ በነበረ ሌላ ከተማ ላይ ከንቲባ ሆና ስትሾም ሿሚውም አላፈረ እሷም ተሿሚዋ በአንድ የምርጫ ዘመን የሁለት ከተሞች ማለትም የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የናዝሬትና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችው የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆና በአንድ የምርጫ ዘመን ስትሰየምና ሹመቱ ሲሰጣት ሳይከብዳት ተቀበለችው። በአንድ የምርጫ ዘመን የሁለት ከተሞች ከንቲባ በመሆን ታሪክ የሰራችው አዳነች በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ እንደተጫነት ስራዋን የጀመረችው የኦነግን ተረት ወደ መሬት ለማውረድ ለሚኩራ የሚል ክፍለ ከተማ በመፍጠር ነበር።
ለሚኩራ የሚል ታሪክ የፈጠረቸው አዳነች ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ ለሚኩራ የሚመስል ታሪክ እያስኮመኮመችን ነው። በትናንትናው እለት መርቃ የከፈተችውን ጎሕ የሞርጌጅ ባንክ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሞርጌጅ እንደሆነ በመደስኮር የኦነግን ዝባንኬ እንጂ አስተዳድረዋለሁ በምትለው ከተማ ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ እንደማታውቅ አላዋቂነቷን አሳውቃለች። ለነገሩ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሞርጌጅ ባንክ እንደለሚኩራ ክፍለ ከተማ በእሷ የተመሰረተ ቢመስላት አይፈረድባትም። እንደ ለሚኩራ ተረት  አዳነች ኢትዮጵያን የምታውቃት በኦነግ የፕሮፓጋንዳ ደራጆች መነጽር ስለሆነ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ለሚኩራ አይነት የፈጠራ ታሪክ እንጂ የታሪክ እውነት ያልነበረ ቢመስላት አይፈረድባትም።  በዚያ ላይ እዚያ ቤት ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ የቀድሞ በጎ ነገር ሲነሳ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የሚሰማቸው ሕመም ስለሚቀሰቀስባቸው የአዳነች የለሚኩራ አይነት ተረት የማይጠበቅ አይደለም።
የሆነው ሆኖ እውነቱ ግን መታወቅ አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሞርጌጅ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1954 ዓ.ም. ነው። ንጉሠ ነገሥቱ የሞርጌጅ ድርጅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያቋቁሙ ዋና አላማው ያደረጉት  በማናቸውም አይነት ስራ ላይ የተሰማራ ኢትዮጵያ ሁሉ የቤት ባለቤት እንዲሆን ማድረግን ነበር። የሞርጌት ተቋሙ የተመሰረተው የመንግሥትና የግል የሽክርና ማኅበር ወይም Public-Private Partnership በመሆን ነበር። ተቋሙም የታወጀው በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ  ሚያዚያ 22 ቀን 1954 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ነበር። ይህ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት አዋጅ ከታች ተያይዟል።
በንጉሠ ዘመን የተመሰረተው ይህ የሞርጌጅ ባንክ በርካታ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን የቤትና የመኪና ባለቤት አድርጓል። ይህ ተቋም የአዲስ አበባን ሕዝብ የቤት ባለቤት በማድረግ ረገድ ስለሰራው ስራ ማወቅ የሚሻ ቢኖር በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ፣ ቀጥሎ ደግሞ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ ተፈረ ደግፌ ከማለፋቸው በፊት በ1998 ዓ.ም. ያሳተሙትን “Minutes of an Ethiopian Century” መጽሐፍ ያንብብ።
የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የሞርጌጅ ባንክ ዝነኛ ከመሆን አልፎ የአዲስ አበቤዎች መቃጠሪያ ምልክትም ነበር። አዳነች አቤቤ ግን  የአዲስ አበባ ሰው ስላልሆነች በንጉሡ ዘመን የተመሰረተው ይህ የሞርጌጅ ባንክ አዲስ አበቤዎች ልክ እንደ ብሔራዊ ቴያትር፣ ሞክሲኮ አደባባይ፣ ሰንጋተራ፣ ወዘተ ታክሲ ሲይዙና ሲወርዱ የሚጠሩት መዳረሻ መሆኑን አታውቅም።
ነጉሠ ነገሥቱ ድሀ ቆጥቦ የቤት ባለቤት እንዲሆን አስበው ያቋቋሙትና በተግባርም በርካታ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን የቤት ባለቤት ያደረገውን የሞርጌጅ ተቋም ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ “የቤቶችና የገንዘብ ቁጠባ ባንክ” በሚል ስሙን ቀየረው። ደርግ ይህንን የስም ለውጥ ያደረገው ጥቅምት 23 ቀን 1968 ባወጣው አዋጅ ነው።
ደርግ ንጉሡ ያቋቋሙትን የሞርጌጅ ተቋም ስሙን ብቻ አይደለም የቀየረው፤ አላማውንም ጭምር እንጂ። ንጉሠ ነገሥቱ ድሆች ቆጥበው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ያቋቋሙትን የሞርጌጅ ባንክ ደርግ ስሙን ቀይሮ አላማውን ካድሬዎቹና አቢዮት ጠባቂዎቹ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያደርግ የቁጥጥር ማዕከል አደረገው።
ፋሽስት ወያኔም በበኩሉ  ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ እንደገባ ደርግ “የቤቶችና የገንዘብ ቁጠባ ባንክ” በሚል ስሙን የቀየረውን የንጉሡን የሞርጌጅ ድርጅት “የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ” በሚል ስሙን ቀይሮ  ታጋዮቹ ቤት እንዲሰሩ ገንዘብ የሚያድል ድርጅት አደረገው። ካድሬዎቹንና ታጋዮቹን የቤት ባለቤት አድርጎ ከጨረሰ በኋላ ከነ ኩሳራው ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ባነጋሪት ጋዜጣ ላይ ባወጣው አዋጅ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አዋሀድሁት አለን። ፋሽስት ወያኔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን አዋሀድሁ ብሎ ሲያውጅ  ንጉሠ ነገሥቱ ድሆችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ያቋቋት የሞርጌጅ ባንክ በይፋ ተቋማዊ ኅልውናው ጠፋ።
እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ አዳነች አበቤ ግን በለሚኩራ ስሌት ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት በ1954 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመሰረቱትን ተቋም በ2014 ዓ.ም.  ለመጀመሪያ ጊዜ እሷ መርቃ መክፈቷን ለተጫነችበት ሕዝብ አበሰረችው።
በተረፈ እንደ አዳነች አበቤ የኢትዮጵያን ታሪክ በኦነግ መነጽር እያዩ፣ ሲባል የሰሙትን ሳይመረመሩ፣ ያሳጣሩና ሳያረጋግጡ መድገምን እንደ እውቀት ለሚቆጥሩ፣ ለማሰብ ፍቃደኛ ላልሆኑ አፍ ነጠቆችና  ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሞርጌጅ ባንክ ተቋቁሞ እያለ የመጀመሪያውን የሞርጌት ባንክ አቋቁመናል እያሉ ሀሳብ የሌለበትን የኦነግ ድንቁርና ለሚደግሙ ሌጣዎች «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ የዛሬውን ወግ እዚህ ላይ ላብቃ!
Filed in: Amharic