“በመንግሥት እና በሕዝቡ መሀከል አለመተማመንና መጠራጠር ስር ሰድዷል…!!!”
ዶ/ር አጥላው አለሙ
ባለፉት ዘመናት በኢትዮጵያ የተመሠረቱ መንግሥታት ሕዝቡን በማማለያ ቃላት ሲደልሉት ኖረዋል፡፡ የሕዝቡ ኑሮ ግን “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” እንደተባለው ነው፡፡ የመንግሥት አመራሮች በመድረክ ምለው ተገዝተው የሚናገሩት ቃል እና መሬት ላይ ያለው እውነት ሰማይና ምድር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ሕዝቡን አታክቶ መንግሥት የሚለውን እንዳያምን አድርጎታል፡፡ በመንግሥት እና በሕዝቡ መሀከል አለመተማመንና መጠራጠር ስር ሰድዷል፡፡ የመንግሥት አመራሮች ለቃላቸው አለመታመን ሕዝቡን በመንግሥት ላይ ተስፋ እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መሀከል የሰመረ ግንኙነት መኖር ትልቅ የልማት አቅም ነው፡፡ በሁለቱ አካላት መሀከል አለመተማመን ሲነግሥ ትልቁን የልማት አቅም አጣነው ማለት ነው፡፡
ሕዝብ በመንግሥት ላይ ተስፋ የሚጥለው መንግሥት ቃል በገባው መሠረት ቃሉን ሲፈፅም እና አቅሙ በፈቀደ መጠን በትጋት ሠርቶ ሲያሳይ ነው፡፡ በአገራችን መንግሥት ቃሉን ሲፈፅም አይታይም፤ ባለው ልክ መሬት ላይ ዕቅዱን ሲያወርድ አይታይም፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የሚናገሩትና መሬት ላይ ያለው እውነታ ሰማይና መሬት ነው፡፡ የሚወጡ ፖሊሲዎችና አፈጻጸማቸውም በዚያው ልክ በጣም የተራራቀ ነው፡፡
የመንግሥት ተግባር ተገማች ባለመሆኑ ኢኮኖሚ ላይ መላምቶችን ለመሥራት እንኳን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እሠራለሁ ይላል፡፡ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት መወሰድ ያለባቸው ቀላል እርምጃዎችን ግን ሲወስድ አይታይም፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋረት የእውነት ፍላጎት አለ ወይ? አቅምስ አለ ወይ? የሚለውን አናውቅም፡፡ መንግሥት አቅሜ ትልቅ ነው ይለናል፡፡ በሌላ መልኩ ትናንሽ ሥራዎችን መከወን ሲያቅተው ይታያል፡፡ አንዳንዴ ትላልቅ ነገር ሲፈፅም ታይቶ ትንሽ ነገር ዳገት ሲሆንበት እናያለን፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት የመንግሥትን ትክክለኛ አቅም እንወቅ? እንዴትስ ለሥራው ውጤት ቅድመ ትንበያ እንስጥ? እንዴትስ ተስፋ እናድርግ? የሚያወጣውን ፖሊሲ የሚያውቅ እና ለፖሊሲው ታማኝ የሆነ መንግሥት ቢኖር ይህ ቢደረግ ይህ ውጤት መምጣት ይቻላል ብሎ ሳይንሳዊ ትንታኔ መስጠት ይቻላል፡፡
አሁን የተመሠረተው መንግሥትስ ምን ያህል ለፖሊሲው ታማኝ ነው? መንግሥት በቀጣይ ዓመታት ራሱን መፈተሽ ያለበት በገባው ቃል ልክ ነው፡፡ በዚህ አገር የብዙ ችግሮቻችን መንስኤ ላወጣው ሕግና መመሪያ፣ ላዘጋጀው ፖሊሲ ታማኝ የማይሆን አመራር እና ሥርዓት መኖሩ ነው፡፡ ፖለቲከኞች የሚናገሩት እና መሬት ላይ ያለው እውነታ አንድ ሲሆን አይተን አናውቅም፡፡ ዛሬ የመንግሥትን ቃል ይዞ መናገር እንደ ውሸታም የሚያስቆጥር ነው፡፡
መንግሥት ገንዘብ ቢቀይር እና ቁጥጥሩን ቢያጠብቅ የዋጋ ንረት ይረጋጋል፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይቀንሳል ተብሎ ነበር፡፡ ገንዘብ ተቀይሯል፤ የዋጋ ንረቱ ግን እንዳለ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ብሔራዊ ባንክ በር ላይ እንደልብ “ዶላር ያለሽ” እያሉ በጥቁር ገበያ ይመነዘራሉ፡፡ ከበፊቱ ምን አዲስ ነገር መጥቷል?
መንግሥት በሚለው ልክ እንዳይፈጽም ምን ችግር እንደሚገጠመው እንኳን ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ብዙ ነገሩ ምጢራዊ ነው፡፡ ባለሞያዎችም ግብዓት እንዳይሰጡ ብዙ ነገር ሾላ በድፍን ነው፡፡ አዲስ የተመሠረተው መንግሥት ቃሉን ከተግባሩ የሚያዋሕድ መሆኑ ለዚህ አገር መጻኢ ዕድል እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እኛም ከሁሉ አስቀድመን የምንፈልገው ለቃሉ ታማኝ የሆነ የምናምነው መንግሥት እንዲሆን ነው፡፡