>

"በኢትዮጵያ ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችንም ማሳተፍ ይኖርበታል...!!!" (ኦፌኮ)

“በኢትዮጵያ ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችንም ማሳተፍ ይኖርበታል…!!!”

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)

 *… ህወሓትን ጨምሮ መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነፃነት ጦር ሽብርተኛ ተብለው በኢትዮጵያ መንግሥት ከመፈረጃቸው አንፃር በምን መንገድ ድርድሩ ሊካሄድ ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሙላቱ ሲመልሱ፡ – 

“ሁሉንም በሆደ ሰፊነት ችሎ ለሰላም መንበርከክ መቻል አለብን። ሁሉም ወገኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ማንም ሰው ለዚህ አገር ለብቻው ሰርቲፊኬት የያዘ የለም። ሰርቲፊኬት ሰጪና ነሽ የለም። የአንዱ ቃል ለአንዱ የሚጎረብጠው ቢሆን ቁጭ ብለን መነጋገሩ ነው ዋናው እንጂ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ መግደሉ ጀግንነት አይደለም” ብለዋል።

እውነተኛ፣ ሐቀኛ እና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይቶች ማካሄድ አገሪቱ የገባችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ መፍታት እንደሚያስችልም ፓርቲው ጥቅምት 15/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኦፌኮ እንደ ቅድመ ሁኔታዎች ካስቀመጣቸው መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ህልውና አደጋ ላይ በመጣሉ ሊቆም እንደሚገባና ተፋላሚ ወገኖችም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት ማድረግ አለባቸው ብሏል።

“በጦርነቱ አሸናፊና ተሸናፊ የለም” በማለትም የኦፌኮ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ተናግረዋል።

“ጦርነትን በማወጅ የምናመጣው ነገር የለም። ጠመንጃን የሚያነሱና በዚህ የሚያመልኩ ሰዎች ይህንን ጉዳይ ትተው ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ነው። ዕልባት ሊሆን የሚችለው በጠረጴዛ ዙሪያ አንድ ላይ ሆነን ችግሮቻችን አንድ ላይ ስንማከር ነው። ወደ ውይይት መምጣት ታላቅነት ነው፣ ጀግንነት ነው። መዋጋቱና መገዳደሉ ዋና መፍትሔ አይሆንም”” ብለዋል አቶ ሙላቱ።

ብሔራዊ ውይይቱ የአገሪቱን አንገብጋቢ ጥያቄ ሰላምን ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታትም ተቃዋሚ ታጣቂ ቡድኖችን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ አካላት ባሳተፈ መልኩ ሊሆን እንደሚገባው ፓርቲው አሳስቧል።

መግለጫው ተቃዋሚ ታጣቂ ያላቸውን ቡድኖች በስም ባይጠቅስም ነገር ግን የሁሉንም ቡድኖች ውክልና ለማስጠበቅ የሕግ እና የደኅንነት እንቅፋቶች ሊወገዱም እንደሚገባም በቅድመ ሁኔታው አስቀምጧል።

እነዚህን ታጣቂ ኃይሎች ማንነት በተመለከተ ቢቢሲ ለአቶ ሙላቱ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን የኦሮሞ ነፃነት ጦርን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የሚያካሂዱና ስማቸው የማይነሳ አካላት እንዳሉም ይናገራሉ።

ከእነዚህም መካከል “በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ታጣቂ ኃይል፣ በሰሜን በኩል ባለው ጦርነት የሚሳተፉ አካላት፣ በአፋርና በሶማሌ በኩል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ያሉ ታጣቂዎችና፣ በአማራ ክልል ውስጥ መንግሥትን የሚገዳደሩና ለመብት የሚታገሉ ታጣቂ ኃይሎች” እንዳሉና በርካታም እንደሆኑ ያስረዳሉ።

“እኛ ከጥይት የሚመጣ ምንም ነገር የለም። ከጠመንጃ አፈሙዝ ለጊዜው ሰላም ቢያመጣም ቋሚ አይደለም። ጊዜያዊ ነው” የሚሉት አቶ ሙላቱ አገሪቱ በጦርነት አዙሪት ውስጥ ለዘመናት መቆየቷ ወደ ኋላ እንደጎተታትና ብዙም መስዋዕነትም አስከፍሏል ይላሉ።

ህወሓትን ጨምሮ መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነፃነት ጦር ሽብርተኛ ተብለው በኢትዮጵያ መንግሥት ከመፈረጃቸው አንፃር በምን መንገድ ድርድሩ ሊካሄድ ይችላል? ተብሎም ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሙላቱ ሲመልሱ፡

“ሁሉንም በሆደ ሰፊነት ችሎ ለሰላም መንበርከክ መቻል አለብን። ሁሉም ወገኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ማንም ሰው ለዚህ አገር ለብቻው ሰርቲፊኬት የያዘ የለም። ሰርቲፊኬት ሰጪና ነሽ የለም። የአንዱ ቃል ለአንዱ የሚጎረብጠው ቢሆን ቁጭ ብለን መነጋገሩ ነው ዋናው እንጂ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ መግደሉ ጀግንነት አይደለም” ብለዋል።

“በጠላት ተፈራርጆ እንዴት ነው አገር የሚፈርሰው? ወደየት እየሄድን ነው ተብሎ አይታሰብም? “በማለትም አቶ ሙላቱ ጨምረው ይጠይቃሉ።

አንዳንዶች የሰላምና የድርድር ሃሳብ ሲያነሱ በህወሓት ወገንተኝነት የሚፈርጇቸው እንዳሉ አቶ ሙላቱ ጠቅሰው “ከማን ጋር ነው የምንደራደረው?” ብለው ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎችም አቶ ሙላቱ ምላሽ አላቸው።

“የፈለገ ጠላትም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ ቁጭ ብለን መደራደር አለብን። ለሰላም ስንል ወንበራችንንም ለቀን መሬት ቁጭ ብለን ተደራድረን አገራችንን ሰላም ማድረጉ አዋቂነት እንዲሁም ጀግንነት ነው” ይላሉ።

አክለውም “የምናካሂደው የእርስ በርስ ጦርነት ነው። ትውልድ የሚገደልበት፣ የሚያልቅበት፣ በጠቅላላው ሲታይ ወጣት አሰልጥነን፣ ድሮን ከውጭ አምጥተን፣ በሌለን የውጭ ምንዛሬ ጥይት ገዝተን ሄደን አንደኛውን መግደል እብድነት ነው” በማለትም ያስረዳሉ።

አቶ ሙላቱ ከጦርነቱ በተጨማሪ የተፈጥሮ ሁኔታና ረሃብም አገሪቱን እያቆረቆዛት ይገኛል በማለትም በትግራይና በአማራ ክልሎች ጦርነቱን ተከትሎ ከተከሰቱ ረሃቦች በተጨማሪ በጉጂና አካባቢው፣ ቦረናና ደቡብ በኩል ከፍተኛ ድርቅ መኖሩንና በየአቅጣጫው በተፈጠረው ችግር አገሪቱ እየተጎዳች መሆኑ አሳሳቢ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ሆኖም መፍትሄውና የአገሪቱ የመዳን እጣ ፈንታ በኢትዮጵያውያን ላይ መሆኑንም ጠቅሰው “ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሪቱ የገባችበትን እልቂት፣ ረሃብና አዘቅት በማት ልንታደጋት ይገባል። ሕዝቡም ቢሆን ይህ እልቂት የሚፈጠረው ለምንድን ነው ብሎ ሊጠይቅ ይገባል” በማለትም መፍትሄውም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት እንደሆነም አስምረዋል።

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ፣ ብልፅግና ያቀረበው ብሔራዊ ውይይት አንዳንዶች ዘግይቷል ሲሉ ማጣጣላቸውን የጠቀሰው መግለጫው ኦፌኮ በበኩሉ ዘግይቶም ቢሆን መካሄዱም እንደ ጥሩ እመርታ እንደሚያየው አስታውቆ ሆኖም እውነተኛና በሃቀኛ መንገድ ሊካሄድ እንደሚገባውም አመልከቷል።

ብሔራዊ ውይይቱ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ባለው እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና እና ድጋፍ ባለው ገለልተኛ አካል ሊካሄድም እንሚገባም ፓርቲው እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

“አገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በአገር ውስጥ ገለልተኛ እና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ታማኝ አካል ማግኘትም አስቸጋሪ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል” በማለትም አትቷል።

ከዚህም በተጨማሪ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና በዚህም ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑም ኦፌኮ በመግለጫው ጠይቋል።

በቅርቡ በመስቀል አደባባይ የአዲስ መንግሥት ምስረታና በዓለ ሲመት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አካታች ውይይት እንደሚካሄድ አመልክተው ነበር።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሸናፊ ብቻውን የሚገንበት ሳይሆን የመግባባትና በጋራ የመሥራት እንደሚሆን በንግግራቸው ጠቁመዋል።

እንዲሁም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሁሉን አካታች የሆነ ብሔራዊ ውይይት እንደሚካሄድ በመንግሥት ምስረታው ወቅት መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ሆኖም ከአገሪቱ መሪዎች ከተናገሩት ውጪ ብሔራዊ ውይይቱ እንዴት እንደሚካሄድ፣ ማንን እንደሚያሳትፍ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን በተመለከተ መረጃ እንዳልደረሳቸው አቶ ሙላቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት እና ከዚያም በፊት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኢትዮጵያን ስር የሰደደ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የሚያግዝ ትርጉም ያለው አገራዊ ውይይት እንዲደረግ በተደጋጋሚ መጠያቁን አቶ ሙላቱ ያስታውሳሉ።

ከዚያን ጊዜም ጀምሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የኦፌኮ አመራሮች በስብሰባዎችም በአካልም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን “ደካማውን ሽግግር” ለመታደግ እና አገሪቱን ወደከፋ ትርምስ ውስጥ እንዳትገባ የውይይት እና የድርድር ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱንም መግለጫው ጠቅሷል።

ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ኦፌኮ የአገሪቱን አንገብጋቢ የፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚወያይበት የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር የሚረጋገጥበት የጋራ ፍኖተ ካርታ የሚቀረጽበት አገር አቀፍ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ተማፅኗል በማለትም ጠቅሶ ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ ሰሚ እንዳላገኙም አትቷል።

በኦፌኮ ግምምገማ መሰረት በአገሪቱ በልሂቃን መካከል ያለው አለመተማመን ለወቅታዊው ቀውስ ትልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉት መካከል አንዱ ነው በማለት “በብሔራዊ ውይይት ስም ሁሉን አቀፍ ያልሆነ ስብሰባ ማድረግ መተማመንን የበለጠ እንደሚሽርና ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት በውይይት መፍታት እንኳን የማይቻል ያደርገዋል” በማለት አስፍሯል።

ስለዚህ ኦፌኮ ከዚህ ቀደምም እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ በመጥራት ግንባር ቀደም የነበረ ቢሆንም የመጪው ብሔራዊ ውይይት ኦፌኮ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እስካላሟላ ድረስ “በግማሽ ልብ የሚደረግ ተሳትፎ ትርጉም የለሽ እና አጠቃላይ ሁኔታው ከንቱ ነው” በማለትም አስቀምጧል።

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት በዚህ ዓመት እንደሚካሄድ የገለጸ ሲሆን ይህ ውይይት ማንን እንደሚያካትና መቼ እንደሚካሄድ አስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር ለም።

https://bbc.in/30XiA4V

Filed in: Amharic