እስክንድር ነጋ ማን ነው . ..???
ሰለሞን አላምኔ
እስክንድር ነጋ ፈንታ በ1960 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወለደ። አባቱ የአሜሪካው ሩትጋርት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቤሩት አስተማሪ ነበሩ። በኋላም በአዲስ አበባ የግል የጤና ተቋም አቋቁመው በመንግሥት ንብረቶቻቸው እስከወረሰባቸውና ሥራቸውን እስካስቆመበት ጊዜ ድረስ ሀገራቸውን በብዙ አገልግለዋል።
እስክንድር እድሜው ለትምህርት ሲደርስ አዲስ አበባ በሚገኘው ሳንፎርድ ኢንግሊሽ ስኩል መማር ጀመረ።
ትምህርት ቤቱ የተሻለ የትምህርት ጥራት እና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች አሉት፡፡ በሙያዊ ብቃታቸው የተመሰገኑ መምህራን ያሉት ሲሆን ተማሪዎችን ለማስተማር ት/ቤቱ የሚያስከፍለው ገንዘብም ከሌሎች ት/ቤቶች ሲነፃፀር ከፍተኛ የሚባል ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዚሁ አጠናቆ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በሰሜን አሜሪካ ተምሯል።
ከዚያም ዋሽንግተን በሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ በመግባት ‘ኢኮኖሚክስ’ እና ፖለቲካል ሳይንስ አጥንቶ የማስተርስ ዲግሪውን ይዟል። በተማሪነት ጊዜውም የደርግን አምባገነናዊ ሥርዓት በመታገል አሳልፏል።
የወታደራዊው አስተዳደር ደርግ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በከስክስ ጫማው ሲቀጠቅጥ ‹‹ለምን?›› በማለት ተቃውሟል። ቤተሰቦቹም ቢሆኑ ይህንኑ ሥርዓት አምርረው ተቃውመዋል። በአሜሪካ አደባባዮች በተደረጉ ደርግን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች እስክንድር ከነቤተሰቦቹ የፊት ተሰላፊ ነበር።
የሀገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው እስክንድር ነጋ በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ከጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጋ በመሆን በ1985 ዓ.ም. ‘ኢትዮጲስ’ የተባለች ሳምንታዊ የፖለቲካ ጋዜጣ አቋቁመው የወያኔን ሀገር አፍራሽ አገዛዝ መቃወም ጀመሩ። ጋዜጣዋ በሕዝብ እጅግ ተወዳጅ ነበረች። የተጻፈላት መሸጫ ዋጋ 75 ሳንቲም ቢሆንም በሽሚያ እስከ 7 ብር ድረስ ትሸጥ ነበር። ሆኖም የመንግሥት አፈና የገጠማት ገና በሁለተኛዋ ዕትም ነበር። የታፈነችው ጋዜጣዋ ብቻ አይደለችም፤ እስክንድርም በተደጋጋሚ ይታሰርና ይፈታ ጀመር። አንደኛውን ጋዜጣ ሲዘጉት ሌላ እያቋቋመ በፅናት ለፕሬስ ነፃነት ታገለ።
ሐበሻ፣ ምኒልክ፣ አስኳል፣ ሳተናው እና ወንጭፍ የተባሉ ጋዜጦችን ማዘጋጀቱን ቀጠለ። እስክንድር በሥራ አስኪያጅነት በሚመራው ሰርካለም አሳታሚ ሥር ከሚታተሙ ጋዜጦቹ መካከል ምኒልክ፣ አስኳልና ሳተናው በተመሳሳይ ጊዜ ይታተሙ ነበር። ከሀበሻ በስተቀር ሌሎቹ ጋዜጦች በአማርኛ የሚታተሙ ሲሆን ሐበሻ ጋዜጣ በእንግሊዝኛ ነበር የምትታተመው። በይዘት ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነች፤ ልዩነቱ የቋንቋ ነው። ብዙ ጊዜ በእንግሊዝኛ የሚታተሙ ጋዜጦች በምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የማተኮር ዝንባሌ አላቸው። ሐበሻ ግን ሙሉ ትኩረቷ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነበር።
ሀበሻ ጋዜጣ ተነባቢነቷ ሲጨምር በአማርኛም ለማሳተም እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። በአማርኛ ልትጀምር መሆኗን የሚያበስር ማስታወቂያ ‹‹ጎበዝ አምስት አመት ሞላን እኮ›› ከሚል ጉልህ ጽሑፍ ጋር በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በየመብራት እንጨቶች፣ በየአጥሩ እና በየግድግዳው ላይ ተለጠፈ። ማስታወቂያውን እስክንድር ከሌሎች ሰዎች ጋር ራሱ እየዞረ ነበር የለጠፈው። የሐበሻ ጋዜጣ ማስታወቂ በከፋፋይ ወያኔዎች ላይ ድንጋጤን ፈጠረ። በተለይ ‹‹ጎበዝ አምስት ዓመት ሞላን እኮ›› የሚለው አስከፋቸው። የሚችሉትን አደረጉና እስክንድርን አሠሩ። ጋዜጣዋም ሳትታተም በማስታወቂያ ቀረች።
ሁሉም ጋዜጦች የወያኔ/ኢሕአዴግን ሸፍጥ ፊት ለፊት የሚያወጡ ነበሩ። በዚህም ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ታስሯል። እስክንድር ነጋ ለሃሳብ ነፃነት፣ ለሀገር ሰላምና አንድነት ሲል በቆራጥ ጋዜጠኝነቱ ለአስር ዓመታት ያህል በወያኔ ታስሯል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲልም አብራው ስትታሰር ኖራለች። በገዥው ፓርቲ የሚፈፀምባቸው ግፍ ከባልና ሚስቱም አልፎ ለልጃቸውም ወርዷል፤ ይኸውም ልጃቸው ናፍቆት እስክንድርም በቃሊቲ እስር ቤት መወለዱ ነው፡፡ እናቱ ሠርካለም ስላልተፈታች ናፍቆት ለአያቱ በመሰጠቱ ጡት የመጥባትን የህፃን ልጅ ወግ አላየም። በአንድ ግቢ ውስጥ ታስረው የሴትና የወንድ በሚል አጥር ተከልለው እስክንድር ሚስቱ በጥላቻ በሰከሩ አረመኔዎች ከለላ ሥር ሆና ስታምጥ ከጎኗ መገኘት አልቻለም። የቅርብ ሩቅ ሆኗል። ከዚህም በኋላም ለልጁ የቤት ውስጥ አባት መሆን አልቻለም፤ ከቤተሰቡ ይልቅ ትኩረቱን ለሀገሩ አድርጓልና።
እስክንድር በ2013 ዓ.ም. በቅርቡ በችሎት የተናገረውን ብናስታውሳችሁ፦ “በሕወሓት ጊዜ 10 ዓመት ታስሬያለሁ። በዚህኛው ሥርዓት ደግሞ ይኸው አንድ ዓመት ታሰርኩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ልጄን አጥቸዋለሁ። ባለፈው ጊዜ ከእስር ቤት ወጥቼ ስሄድ ‹‹ማን ነህ?›› አለኝ። ዳኞች ቤተሰባዊ ጉዳያችንንም አስባችሁ ፍረዱ” አለ።
የፅናት ምልክቱ እስክንድር ነጋ በብዕሩ ወያኔን ሲፋለም ከአራት በላይ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እስር ቤት ውስጥ ሆኖ አሸንፏል። ከእነዚህም መካከል በ2004 ዓ.ም. ፔን ባርባራ ጎልድስሚዝ የተባለ የጸሐፊያን ነፃነት ሽልማትን አግኝቷል። በ2006 ዓ.ም የወርቃማ ብዕር ሽልማት ተሰጥቶታል። በ2009 ዓ.ም. ከዓለም አቀፍ የፕሬስ ኢንስቲትዩት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና ሽልማትን በውድድር አሸንፏል። በ2010 ዓ.ም. ከኦክስፋም ኖቪ የብዕር ሽልማትን አግኝቷል።
እስክንድር ከወያኔ የእስር ካቴና እጁን ካላቀቀ በኋላም አዲሱን የኦሮሙማ የአብይ አሕመድ መንግሥት ለመቃወም ቀድሞ የተገኘ የማንቂያ ደወል ነው። ሀገሪቱ ወደ ኦሕዴድ አምባገነናዊ ተረኝነት መሸጋገሯን እንደ እርሱ ቀድሞ የተረዳ የለም።
በዚህ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እምቢተኛ ባህሪው የተነሳ እስክንድር ነጋ ተመልሶ ወደ እስር ቤት ከገባ እነሆ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር አለፈው።
በመጨረሻም በእስክንድር ነጋ ላይ ምስክር መሰማት ከጀመረ ሳምንታት ቢያልፉም አንድም ቀን በእስክንድር ነጋ እና የትግል አጋሮቹ ላይ ሊያስፈርድ የሚችል ምስክርነት ቃል ሊገኝ አልቻለም። እንዴውም በተቃራኒው ምስክሮቹ እናማን እና ምን አይነት ስብዕና ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ወደ ፊት ለታሪክ ትውልድ እንዲማርበት ሆኖ የሚቀርብ ይሆናል።
ድል ለዲሞክራሲ