>

ደሴን መቆጣጠር ማለት . . . (ዶክተር  ምስጋናው ታደሰ )

ደሴን መቆጣጠር_ማለት . . .

             በዶክተር  ምስጋናው ታደሰ 

   ሆን ተብሎ እና ተፈልጎ እስኪመስል ድረስ ወሎ የጦርነት ቀጠና ከሆነ ዉሎ አድሯል፡፡ አሁን ደግሞ የጠላት ጦር የወሎ መዲና የሆነችዉን ደሴን እና የበርካታ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ማዕከል የሆነችዉን ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር ያለ የሌለ ኃይሉን አሰልፎ አሰፍስፏል፡፡
ደሴን እና ኮምቦልቻን መንግሥት እንዲታደግ ስንጠይቅ መንደርተኝነት ተጠናዉቶን ወይ ደግሞ እጅግ ጠበን ስለ ሁለት ከተሞች ብቻ እያሰብን (እየተናገርን) አይደለም፡፡ እርግጥ ነዉ ደሴ የወሎ የባህልና የታሪክ ማህደር ናት፡፡ ለሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያም የአይን ብሌን ናት፡፡
ነገር ግን ደሴ እና ኮምቦልቻን ታደጉ ስንል የሀገሪቱን መዲና፣ የጠቅላይ  ሚኒስትሩንም ቤተ መንግሥት ታደጉ እያልን ነዉ፡፡ ደሴ በሰሜን በኩል ለሚመጣ ወራሪ የመጨረሻዋ ምሽግ ናት፡፡ ደሴን አልፎ የሄደ ጠላት አዲስ አበባን ከመቆጣጠር የሚያግደዉ ነገር የለም፡፡ የአካባቢዉ ታሪካዊ ዳራም  ይህንኑ እዉነት ነዉ የሚያረጋግጥልን፡፡ ሁለቱን ታሪካዊ አጋጣሚዎች እዚህ ላይ ማስወታስ ያስልጋል፡፡
በ1928ቱ የጣልያን ወረራ ወቅት በሰሜን በኩል የመጣዉ በማርሻል ባዶግሊዮ የተመራዉ  ወራሪ ኃይል ሰኞ በሚያዝያ 12 ቀን 1928 ዓ.ም  ደሴን ተቆጣጠረ፡፡ ከ12 ቀናት በኋላ ሚዝያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በጅቡቲ በኩል አድርገዉ ወደ ለንደን ተሰደዱ፡፡ ከሃምሳ አምስት ዓመታት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ደሴን ተቆጣጠረ፡፡
 ከሦስት ቀናት በኋላ ግንቦት 13 ቀን መንግስቱ ሃይለማርያም በቦሌ በኩል ወደ ሐራሬ ሄዱ፡፡ እንግዲህ ደሴን መቆጣጠር ማለት . . . ያልኩት ከዚህ የተነሳ ነዉ፡፡
አሁንም ደሴን መቆጣጠር ማለት አዲስ አበባን መቆጣጠር እንደማለት ነዉ፡፡ የጁንታዉ ጦር ደሴን መቆጣጠር ከቻለ በቀናት ዉስጥ ወደ መዲናዋ መዳረሱ አይቀሬ ነዉ፡፡
በዚህ ጊዜ ዶ/ር አቢይ አህመድ በጂቡቲ በኩል አድርገዉ ወደ ለንደን ወይንም በቦሌ በኩል ወደ ሃራሬ ወይንም ወደሌላ መዳረሻ ይሄዳሉ ብየ አላስብም፡፡ አሁን ጊዜዉና ሁኔታዉ ሌላ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን ጁንታዉ ደሴን አልፎ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ድርድር ሊመጡ ይችሉ ይሆናል የሚል ስጋት ጭምጭምታም አለ፡፡
ይህ ሁሉ ዜጋ ካለቀ  በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸዉን ካጡ፣ ሚሊዮች ከተፈናቀሉ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ከወደመ በኋላ ለመደራደር ማሰቡ በራሱ ከሀገር ክህደት ወንጀል የሚበልጥ ወንጀል ነዉ፡፡
ከዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ቀዉስ ለመዉጣት መንግስትም ሆነ የአካባቢዉ ማህበረሰብ ተባብሮ ወረራዉን መቀልበስ ብሎም ወራሪዉን ጠራርጎ ወደመጣበት መመለስ፤ እንዲሁም ይህንን በዚህ ዘመን የበቀለ ክፉ አረም ነቅሎ እና አቃጥሎ ኢትዮጵያ እንድታርፍ ማድረግ አማራጭ የሌለዉ ለነገም ቀጠሮ የማይያዝለት መፍትሄ ነዉ፡፡ የአካባቢዉ ማህበረሰብ የሚችለዉን እያደረገ ነዉ፡፡ ከዚህ በላይም መደራጀት እና መደገፍ ይኖርበታል፡፡
 የመንግሥት ቁርጠኝነት ደግሞ የነገሩ ሁሉ ማሰሪያ ነዉና ወደ መጨረሻዉ እርምጃ እዲገባ፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችን እንዲያግዝ፣ በዜጎቹ ላይ እየደረሰ ያለዉን ስቃይ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡
Filed in: Amharic