አሳፍ ሀይሉ
(መነሻና መዳረሻዎቻችን)
በወያኔ-ኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን የሥርዓቱን አገዛዝ ያለርህራሄ በማብጠልጠል የሚታወቀው የኦነጉ የተባ ብዕረኛ ሞቲ ቢያ “በለውጡ” ዋዜማ ላይ “የኦሮሚያ ትግል ከየት ወደየት” የሚል መፅሐፍ አሳትሞ በአማርኛ ተተርጉሞ ቀርቦለት ነበር።
ሞቲ በዚያ መፅሐፉ ያለምንም መደባበቅ በግልፅ ያስቀመጠው የለውጡ ዓላማ ሁሌ ሲገርመኝ ይኖራል። ሁሉንም አሁን በኢትዮጵያ ስም ደጋፊ እያሰባሰቡ የጥቅም ያቋመጠውን የዘረኝነት አጀንዳ ያለምንም ይሉኝታ እያስፈፀሙ ያሉትን የተረኞቹን ፍላጎትና ግብ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።
ሞቲ ቢያ የለውጡን ዓላማ ሲናገር አራት ነጥቦችን ነው ያስቀመጠው፦
1ኛ) ነፍጠኛ (አማራ) እስከ አፄው ዘመንና እስከ ደርግም ሥርዓት ድረስ ለዘመናት ኢትዮጵያን ገዝቷል፣
2ኛ) ትግሬውም ከነፍጠኛው ጋር ለዘመናት ኢትዮጵያን በፈረቃ ከመግዛቱም በላይ ላለፉት 27 ዓመታት በወያኔ አማካይነት ኢትዮጵያን ገዝቷል፣
3ኛ) በመሆኑም አሁን የኦሮሞ የገዢነት ተራ ነው፣ ይህም ምንም አሻሚነት የሌለው ታሪካዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄ ነው፤
ይልና በመጨረሻ ወደ መፍትሄው ሲገባ እንዲህ በማለት ይጠቁማል፦
4ኛ) “ነፍጠኛው አከርካሪው ተሰብሮ እንዳይነሳ ሆኖ በትግሬው ተቀጥቅጦ የተገዛ፣ እንዳያንሰራራ ሆኖ ከጥቅም ውጪ የተደረገ ሕዝብ ሆኗል፣ ደግሜ ገዢ እሆናለሁ ብሎ ቢነሳ በወደቀበት ከመላላጥና ከመፈራገጥ በቀር የሚያመጣው አንዳች ለውጥ የለም፣ ይልቁንም ነፍጠኛው ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ተባብሮ አረመኔውንና ጨካኙን ህወሀትን በመቅበር፣ በተረኛው የኦሮሞ ገዢ ሥር የሚቸረውን ፍትሀዊ የፖለቲካ ተጠቃሚነት ዕድል እንዲቋደስ የጋራ የትግል ጥሪ ያቀርባል።
ከዚህም በፊት እንዳልኩት ነፍጠኛ ከሚለው የከረመ ኦነጋዊ አታሞ ወጥቶ ነፍጠኛ ያለውን አማራውን የኦሮሞ ስትራቴጂክ አጋር እንዲሆን በይፋ ጥሪ ያቀረበ የታተመ ኦነጋዊ ሰነድ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት በዚህ የሞቲ ቢያ መፅሐፍ ላይ ነው።
ይህም የሞቲ ቢያ ግልፅ ትንተና ምናልባትም ከዚህ ቀደም “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” በሚል መፅሐፉ፣ “የኦሮሞ ትግል ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹን ካላካተተ ግቡን ሊመታ አይችልም” በማለት ለኦሮሞ ትግል ስትራቴጂክ አጋሮችን የማሰለፍን አስፈላጊነት ዳር ዳር ብሎ ጀምሮት ከነበረው ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ቀጥሎ 2ኛው መሠል ትንተና የተስተናገደበት ህትመት ያደርገዋል።
ቀደም ብሎ ዶ/ር ነጋሶ “ኦሮሞ ለረዥምና እልህ አስጨራሽ ትግል መዘጋጀት አለበት” በማለት ያለችኮላና በዘዴ የኦሮሞን ሕልም “ከሌሎች አጋሮች ጋር” (ማለትም በእኔ አተያይ ስተረጉመው “በሌሎች ኪሣራ”) ብቻ ለማሣካት የሚቻል መሆኑን ሲመክር፣ ለመሆኑ ያ የኦነግን ደጃፍ በረገጡና በስብከቱ በተማረኩ ሁሉ የሚነገረው የኦሮሞ ህዝብ ትግል የመጨረሻ ግብ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ የሚቀር አይመስለኝም።
በእኔ እይታ፣ በዶ/ር ነጋሶ በተቀነቀነው የትግል ቀመር እና በሞቲ ቢያ በታተመው የትግል አጋርነት ጥሪ መካከል የልዝብናና የምሁራዊ አገላለጉዳይ ካልሆነ የትንተናም የዓላማም ልዩነት የለም። ዶ/ር ነጋሶ ከሴት አያቴ ከሲዮሪ አፍ ተረዳሁት የሚለውን የነፍጠኛ አገዛዝ ለመተንተን ብዙ ምዕራፎችን እንደወሰደው ሁሉ፣ ሞቲ ቢያም በተጋነኑ ስዕላዊና ስሜታዊ አገላለፆች አጅቦ የሚያቀርበው ያንኑ ነገር ነው።
ይኸው ተመሣሣይ አቋም ደግሞ በእነ ሌንጮ ባቲና በእነ ዳዑድ ኢብሳ በአገም-ጠቀም አካሄድም ቢሆን እየተራመደ ከሚገኘው አሁናዊ ስትራቴጂክ አሰላለፍ ጋር የሚለየው አንዳችም ነገር የለም። ምናልባት ነፍጠኛ የተባለውን አማራ ካለማመንና ያንሠራራብናል ብሎ ከመፍራት ከሚመነጭ የጎንዮሽ ፀረ-አማራ የኃይል እንቅስቃሴዎች በስተቀር የሚለየው የለም።
ይሄ ራሱ የተሻሻለ ኦነጋዊ አስተሳሰብ፣ ሁሉም በጋራ ተወያይቶ ኦሮሞ በቁመቱ ልክ የሚገባውን ድርሻ የሚያገኝበትን ሥርዓት እንፍጠር ብሎ ከሚወተውተውና፣ ይህ ካልሆነ ታላቋ ኦሮሚያ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ እውን እንደምትሆን ከሚሰብከው ከጃዋር ሲራጅ መሀመድ አቋም ጋር የችኮላና የክረት መጠን ካልሆነ በቀር የሚለየው ነገር የለም።
እንዲያውም ልክ እንደ ሞቲ ቢያ ጃዋርም ያለውን አረዳድ አልደበቀም፦ “ይሄኮ ግልፅ ነገርኮ ነው፣ ኦሮሞ ተረኛ መንግሥት ነው፣ አዎ ነው፣ ይሄ የሚያከራክር ነገር የለውም!” ብሎ በአደባባይ አውጆልናል።
ዝርዝሩ ብዙ ነው። ብዙው የኦሮሞ ቅቡል ፖለቲከኛ ከጃዋር ሲራጅ እና ሞቲ ቢያ ወይም ከሌሎቹ የሚለይበት ጉዳይ ኢምንት ነው።
በድራማ በተቀነባበረ መልኩ እና በስልታዊ አካሄድ ይህንኑ የእነ ጃዋርን ዓላማ በተለሳለሰና “convince or confuse” መንገድ እያዋዙ ዳር ለማድረስ እየተጉ ባሉት በእነ ታዬ ደንደአና በእነ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ወይም በሌሎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች መካከል፣ የአካሄድና የአሰላለፍ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የምታገኘው አንዳችም የዓላማ ልዩነት የለም።
የሁሉም የመጨረሻ ግብ አንድ ነው። በአንድ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ግብም ነው። ወይ ተረኛ ገዢነታችንን እመኑና በተራችን ኢትዮጵያን እንግዛ የሚል “የፈረቃ” ጥያቄና፤ ይህ ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ ግን ታላቋን ኦሮሚያ ለመመሥረት ከስትራቴጂክ አጋሮቻችን ጋር እንሠራለን የሚል ነው።
በዚህ መሠረት የትግራዩ ወያኔ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለቋመጡለት “ፍትሃዊ” የተረኛ ገዢነት ፍላጎታቸው ትልቁና አደገኛው ተግዳሮት ሆኖ አግኝተውታል።
ስለዚህም “በለውጡ” በፊት ከእነ ዶ/ር ለማ መገርሳ ቀድሞ፣ በዶ/ር ነጋሶ ተለሳልሶ በቀረበውና፣ በሞቲ ቢያ በግልፅና በማያወላዳ አነጋገር በቀረበው የኦሮሞ-አማራ የጋራ ፀረ-ወያኔ የትግል ግንባር አጋርነት ጥሪ መሠረት፣ የአማራው የፖለቲካ ኃይል ከወያኔ የባሰ ጠላት የለንም በማለት፣ የኦሮሞውን ተረኛ ገዢ አይን-ያወጡ የተረኝነት ተግባራት ሁሉ እንዳላየ እንዳልሰማ በሆዱ ዋጥ አድርጎ፣ በወያኔ ላይ ተባብሮ መዝመትን መርጧል።
ይህ ሁሉ ፀረ-ወያኔ “የኦሮማራ” ስትራቴጂክ የትግል ወይም የጦርነት አጋርነት ሲፈጠር ግን፣ የኦሮሞው ኃይል ወደ ጦርነቱ የገባው ሁለት አማራጮችን ይዞ ሲሆን፣ የአማራው ሀይል ግን ከትግሬው ላይ የሚጠይቃቸውን ታሪካዊ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎች በሀይል የሚመለሱበት ወቅት መድረሱን በማመን ነበር።
የኦሮሞው ተረኛ ሀይል በኦሮማራ ጥምረቱ በሁለት ቢላዋ ነው ለመብላት የተዘጋጀው ስንል ምን ማለታችን ነው?
በአንዱ ቢላዋ ተረኛ ገዢ መንግሥት ሆኖ ወያኔዎችን በመቅበር ለሚገኝ የገዢነት ጥቅምና የወደፊቷ ኦሮሚያ ግብ ከአማራና ከሌሎች ጋር ተሠልፎ ወያኔን የሚወጋበት ቢላዋ ነው።
ሁለተኛው ቢላዋው ደግሞ ወድቆ ተሰባብሯል ተብሎ የሚታመንበት የነፍጠኛው አማራ ኃይል ከገባበት ጦርነትና መባላት እንዳይወጣ፣ በኦሮሚያ ምድር አንዳችም ነፍጠኛ እንዳይቀር፣ እና ለምናልባቱ ወያኔ ከሞት ብትተርፍ ተብሎም ደግሞ የተዘጋጀ PLAN-B ቢላዋ ነው።
በዚህ በ2ኛው ቢላዋ የተለያዩ የኦነግ አንጃዎችንና ፓራሚሊቴሪ ኃይሎችን (እነ ኦነግ ሸኔን) ከወጣት ህዝባዊ ክንፎች (ከእነ ቄሮ) ጋር በማቆራኘት፣ ቀደም ብላ ወያኔ ባዘጋጀችለት የፀረ-አማራ የጋራ ትርክትና የጋራ ፀረ-አማራ የጭቁን ሕዝቦች ግንባር ተመልሶ ከወያኔ ጋር በመሠለፍ፣ አማራውን ወግቶና አስወግቶ የአማራው ሀይል እንዳያንሠራራ አድርጎ ለመቅበር ያለመ ነው።
በዚህም ከወያኔ ጋር ከሚገኘው ግዳይ የሚደርሰውን ድርሻ ተቀራምቶ የኦሮሚያን መብት አስጠብቆ ለመኖር፣ አሊያም በእነ ፕ/ር እዝቅኤል ጋቢሳ በኩል ሲቀነቀን እንደነበረው ከወያኔና ከሌሎች በተረኛው አስተሳሰብ “ፀረ-ኢትዮጵያ” ናቸው ካላቸው ሀይሎች ጋር ተስማምቶ፣ እንደ ዩጎዝላቪያ ያለ፣ ወይም በህገመንግሥቱ አንቀፅ 39 እንደተፃፈው የመሠለ፣ የመበታተን ወይም የፍቺ ስምምነት የማድረግንም ብዙ ደም-ከመገበር የሚያድነውን አማራጭ አጥብቆ ይማትራል።
ይህ ሁለተኛው ካራ በዚህ የዩጎዝላቪያን ሀይሎች (ብሔሮች) በሚመስለው ስምምነት መሠረት ታላቋን ትግራይ፣ ታላቋን ኦሮሚያ፣ እና ሌሎች በአምሳያቸው የተሠሩ “ታላላቆችን” በኢትዮጵያ መቃብር ላይ እውን የሚሆንበትን መንገድም ለማመቻቸት ያለመ ፀረ-ነፍጠኛ፣ እና አፍቃሪ-ወያኔ የመንታ ትግል ስትራቴጂ አደገኛና ፅንፈኛ ቢላዋ ነው።
በአጭሩ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞው ተረኛ ገዢ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የቀመረውና የቆመረው አደገኛና ደም አፋሳሽ የፖለቲካ ግብ በአጭሩ ከላይ የተገለፀው ነው።
የዚህ ሲወርድ ሲዋረድ በኦነጋዊው አስተሳሰብ ሲቃኝ ቆይቶ፣ አሁን ከፍ ያለ ድፍረትንና የረቀቀ ስልታዊነትን ተላብሶ የመጣው የኦሮሞ ተረኛ ገዢነትንና ታላቋን ኦሮሚያን በአንድ ድንጋይ ለማምታት ያለመ አካሄድ አደገኛ የሚሆነው፣ በጋራ የዜጎች እኩልነት ላይ ለምትመሠረት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ቦታ የሌለው መሆኑና፣ ዓላማውን ለማስፈፀም የግድ የአንዱን ተቀናቃኝ ይሆንብኛል የተባለን ሕዝብ ወይም የሌላውን ሀይል በመርገጥ ወይም በመቅበርና በማሽመድመድ ብቻ እውን የሚሆን ሕልም የመሆኑ ጉዳይ ነው።
የተረኛው ፅንፈኛ ገዢ ህልሞች እውን እንዲሆኑ የአማራው፣ የትግሬው፣ አሊያም የሁለቱም ሕዝቦች አከርካሪ መሰበርና መመታት የግድ ነው።
የኦሮሞው ተረኛ ገዢ ተረኝነቱን ለማረጋገጥ የተከተለው ስትራቴጂ አደገኛ የሚሆነው ለንግሥናው እንቅፋት የሆነበትን የትግሬ ሀይል መቅበርንና በአማራው ላይ የበላይ መሆንን የግድ የሚል ስትራቴጂ ስለሆነ ነው።
ይህም ባይሳካለት ደግሞ ሁለተኛውን ቢላዋ መዝዞ፣ በቁጥር አናሳነቱን አምኖ የብዙሃኑን ኦሮሞ ሀይልና ተረኝነት አምኖ ከሚቀበል፣ አሊያም ኢትዮጵያን በጋራ ከሚቃረጥ የወያኔ ሀይል ጋር ተጣምሮ የአማራውን የቀረ አከርካሪ መሠባበርና በአማራው መቃብር ላይ የኦሮሚያን የተረኛ ገዢነትና የነፃ ሀገርነት ምኞት እውን ማድረግን ያለመ አረመኔያዊ ስትራቴጂ በመሆኑ አደገኝነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።
የዚህ ሁሉ የትግል ስትራቴጂ ቀመር ከማን የተኮረጀና፣ ከማን የመጣ ነው? ቢባል መልሱ ቀላል ነው። ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ሂደት ውጤታማ መንገድ መሆኑ ከታመነው ከሻዕቢያ የተቀዳ የትግል ስትራቴጂ ነው።
/የዚህን መሠሉ እኩይ ፀረ-ኢትዮጵያ ሴራ ጉንጎና ከሁሉ አስቀድሞ የመነጨው በቅድመ ቅኝ ግዛት በያቅጣጫው ካንዣበቡ የአውሮፓ ተስፋፊ ሀይሎች በኩል ስለመሆኑና፣ በቅኝ ግዛትና ድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን ቨምን ዓይነት አኳኋን በኢትዮጵያ ላይ እንደተተገበረ የሚገልፁ ፅሑፎችን ከዚህ በፊት ማስነበቤን ለማስታወስ እፈልጋለሁ። ጊዜው ያለው መለስ ብሎ ከ3 ዓመት በፊት ገደማ አከታትዬ ያጋራኋቸውን የታሪክ ዳሰሳዎች ማየት ይችላል።/
ይህን ሁሉ አሁናዊ አሠላለፍ ስንመለከት፣ በመጨረሻ የሚመጣብን ጥያቄ የአማራው ሕዝብ ወይም የአማራውን ሕዝብ ወክያለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአማራው መንግሥታዊ ሀይል ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው? የሚለው አሳሳቢ ጥያቄ ነው።
በእኔ አመለካከት የአማራው ሕዝብ እንደ ሕዝብ በጋራ የገባበት አሁናዊ ወታደራዊና የፖለቲካ ቅርቃር (አጣብቂኝ) ከላይ የተገለፀው ነው።
አማራው ከገባበት አደገኛ አጣብቂኝ ለመውጣት ምን ቢያደርግ ይሻል ነበር? አሁንስ ምን ቢያደርግ ይበጃል? ለሚሉት ጥያቄዎች በአስተውሎት ላይ የተመሠረተ አዋጪና ኃላፊነት የተሞላበት ምላሽ መስጠት የግድ አስፈላጊ ነው። አንገብጋቢ (ጊዜ የማይሰጠውም) ነው።
በወቅታዊ አሁናዊ ትንተናዎች ላይ የጋራ እውነቶችና ስምምነቶች ላይ ሳይደረስ የሚወሰድ የመፍትሄ አቅጣጫ ሁሉ የእንቧይ ካብ ነው። የአማራ ህዝብ የገባበትን አጣብቂኝ የተመለከቱ ልጆቹ እንደ አሳምነው ፅጌ በጊዜ ተወግደዋል።
ሌሎች በፅሞና አሁናዊውን እውነታ ቆም ብሎ መረዳትና የተያዘውን ስትራቴጂ ደጋግሞ ማጤን፣ መከለስና በምትኩ ሩቅ ያለመ ስትራቴጂ በቶሎ መንደፍ ከአማራው ሕዝብ ልጆች የሚጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው የቤት ሥራ ነው።
በትግራዩ ሀይል (በወያነ ሐርነት) በኩል የእስከዛሬው በዘር ክፍፍልና ሽንሸና ላይ የተመሠረተ፣ አማራውን በጠላትነት የሚፈርጅና፣ ለሻዕቢያ ጥቅም ሲባል በተነደፈ ያረጀ ትንተናና ደም አፋሳሽ ስትራቴጂ ላይ የሙጥኝ የማለቱን አዋጪነት ከትግራይ ህዝብ አቋምና አቅምና አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር ተመልክቶ፣ “በመቃብሬ ላይ ካልሆነ” እያለ የያዛቸውን አቋሞቹን አስተውሎ ደግሞ ደጋግሞ መከለስ ለወደፊቱ ለራሱና ለሚጋደልለት ሕዝብ ሲል የግድ የሚለው የቤት ሥራው ነው።
የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመጠቆም በቅድሚያ በገባንበትና በተፈጠረው አሁናዊ እውነታ ትንተናዎች ላይ መግባባት አለብን። ማን ለምን ዓላማ ምን አደረገ፣ ምንስ ለማድረግ ነው ዕቅዱ፣ መዳረሻ ግቡ፣ አሁን ያለው ዕድልና የተጋረጠበት አደጋ? ለሚሉት ጥያቄዎች ሀቀኛ መልስ ያሻል። ከዚያ በኋላ ወደ መፍትሔ ሀሳቦች።
ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም።
መፈራረጅና በስሜት መነዳት ካሰብንበት ያስቀረናል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።