>
3:37 am - Monday July 4, 2022

የትብብሩ አመራሮች ‹‹ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ›› ወንጀል ተከሰሱ[ ነገረ ኢትዮጵያ]

‹‹ህገ መንግስቱን ማየት አለብኝ›› ዳኛው

በሰላማዊ ሰልፉ ታፍሰው አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ታስረው የሚገኙት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አመራሮች፣ አባላትና የሰልፉ ተሳታፊዎች ‹‹ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ›› ወንጀል ተከሰው 14 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ አቶ አርጫፎ ኤርዳሎ፣ አለሳ መንገሻና ሌሎቹም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አመራሮች፣ አባላትና በሰልፉ ላይ የታፈሱ ዜጎች አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ለታህሳስ 13/2007 ዓ.ም ተቀጥሮባቸዋል፡፡

ችሎቱ በዝግ የታየ ቢሆንም ሶስተኛ ከሚገኙት ሴት ታሳሪዎች ጠይቀን ማረጋገጥ እንደቻልነው ‹‹ሁከት በመፍጠር ህገ መንግስቱንና ህጋዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ እና መንግስት ያልፈቀደው ሰልፍ በመውጣት›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ በበኩላቸው ‹‹እኛ ህጋዊና ሰላማዊ ታጋዮች ነን፡፡ በህጉ መሰረት ሰልፉን እንደምናደርግ አሳውቀናል፡፡ በመሆኑም የዋስ መብታችን ተከብሮ ልንለቀቅ ይገባል›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አቃቤ ህግ ‹‹ምርመራዬን አልጨረስኩም፡፡ የምሰበስበው ተጨማሪ መረጃ አለ፡፡ መረጃዎችን ይደብቁብኛል፡፡ ሌሎች ተባባሪዎችም አሉ፡፡›› ሲል የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ በሌላ በኩል ዳኛው ‹‹ህገ መንግስቱና ሌሎቹም ህጎች ለሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቅ እንጅ ማስፈቀድ አይጠበቅም የሚሉ ከሆነ ህገ መንግስቱንና ሌሎቹንም ህጎች ማየት አለብኝ፡፡›› ብለው 14 ቀጥረውባቸዋል፡፡ አቃቤ ህግ ‹‹የምሰበስበው ተጨማሪ መረጃ አለ፡፡›› ባለው መሰረት የአብዛኛዎቹን ታሳሪዎች ቤት ሊፈትሽ እንደሚችልም ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከታሳሪዎቹ መካከል 9ኝ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ለየብቻቸው ቅዝቃዜ የበዛበትና ጨለማ ቤት ውስጥ እንደታሰሩ የታወቀ ሲሆን በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሆነም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ሆኖም ዳኛው የቀረበውን አቤቱታ ትኩረት ሳይሰጡ እንዳለፉት ታሳሪዎቹ ገልጸውልናል፡፡ ታሳሪዎቹ አራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ችሎቱ በበርካታ የፌደራል ፖሊስ ታጥሮ ታይቷል፡፡ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል በርካታ ህዝብ ተገኝቶ የነበር ቢሆንም እንዳይገባ ተከልክሎ ችሎቱ በዝግ ታይቷል፡፡

Filed in: Amharic