>
5:13 pm - Sunday April 18, 4793

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ....!!! (ክፍል 2  አንዳርጋቸው ጽጌ)

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ….!!!
 ክፍል 2
አንዳርጋቸው ጽጌ

የነስብሃት ነጋ መፈታታ ለጦርነቱ የፖለቲካ መቋጫ ለማግኘት ከሆነስ?
ይህን ጉዳይ በሁለት ከፍሎ ማየቱ የተሻለ ነው። ከአሜሪካ መንግስት ፍላጎትና ከኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት አንጻር።
1) በአሜሪካኖች የሚገፋ የፖለቲካ መቋጫ
በተደጋጋሚ የሰማነው ነው። አሜሪካኖች እና ምእራባውያን በወያኔ ጀማሪነት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተከሰተው ግጭት ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል ሲሉን ነበር። የምእራባውያን ሚድያዎችም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ነበር። ይህን ይበሉ እንጂ ለዚህ አቋማቸው መነሻው “ማናቸውም ግጭቶች መጨረሻቸው ፖለቲካዊ ነው” የሚል መርህ አልነበረም። “የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል” የሚለው ሃሳባቸውን በቋሚነት የሚገፉት አልነበረም።
ወያኔ ጉልበቱ አይሎ አዲስ አበባ የሚገባ መስሎ ሲታያቸው የኢትዮጵያን መንግስት የሚተካ ሌላ መንግስት ሲያዘጋጁ ነበር። በዛን ወቅት “ተደራደሩ” የሚል ሃሳብ ጠፍቶ ነበር። “ወያኔን የሚይስቆመው ሃይል የለም። የወያኔ ወታደሮችና መሪዎች ጀግኞች ናቸው። አትችሏቸውም።” በማለት ሌሎች ኢትዮጵያውያን እጃቸውን ለወያኔ እንዲሰጡ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሲሰሩ ነበር።  ዶ/ር አብይ እንደነገረንም “ተደራደር ሳይሆን ሃገር ለቀህ ብትወጣ” የሚል ምክር ይለግሱት እንደነበር ነው።
የአሜሪካና የምእራባውያን  አቋም ወደ ተደራደሩ የሚያደላው ሁሌም የኢትዮጵያ መንግስት ጉልበት አይሎ ሲያዩት ነበር። ወያኔ የሚሸነፍ ሲመስላቸው መንግስት ከወያኔ ጋር እንዲደራደር ሃሳብ ያቀርባሉ፤ ጫና ይፈጥራሉ። የዚህ ግፊት አላማ በድርድር በሚፈጠረው መንግስት ውስጥ ወያኔን ቦታ እንዲኖረው በማድረግ የተላላኪነት ስራውን እንዲቀጥል ማስቻል ነው።
አሁንም በቅርቡ አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ መንግስት እያሳዩት ካለው መለሳለስ ጋር በወያኔ ላይ የያዙትን አቋም በእርግጠኛነት ባናውቅም ወያኔ ላይ ተጽእኖ አድርገው ወደ ድርድር እንዲመጣ የሚፈልጉ ይመስላል። የነስብሃት መፈታት የአሜሪካ መንግስት “ወያኔንና የኢትዮጵያን መንግስት ለማደራደር ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል” በማለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የተፈጸመላቸው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መረን የለቀቀ ሊሆን አይችልም።
እዚህ ላይ ማንሳት የሚገባን ጉዳይ ሁኔታዎች ቢመቻቹ እውን የኢትዮጵያ መንግስት ከወያኔ ጋር ለመደራደር ወስኗል ወይ? የሚለው ነው። ለመደራደር ከወሰነ ለመሆኑ የመደራደሪያ ነጥቦቹ ምን ሊሆኑ ነው? ከወያኔ ጋር በመደራደር እውን በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ይሰፍናል ወይ? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማንም የሚሰጠን አልሆነም። የአሜሪካኖች አቋም ግን ግልጽ ነው። ወያኔን የስልጣን ተጋሪ በማድረግ በጉልበት ማስወገድ ያልቻሉትን የአብይን መንግስት፣ ወያኔን ጉያው ውስጥ ጨመረው ማዳከም ነው። በወታደራዊ ጉልበት የአብይን መንግስት መጣል ካልተቻለ ሌላው ቢቀር የእነሱ ጥቅም አስከባሪ የሆነ ሃይል ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እንዳይጠፋ ማድረግ ነው።
ብዙዎቻችን ምን እየተካሄደ እንደሆነ አናውቅም። የሚያውቁ የሚመስሉንም የመንግስት ባለስልጣናት አናውቅም እያሉን ነው። ስለዚህ በበኩሌ ይህን ጽሁፍ የምጽፈው በግምት ነው። በክፍል 1 በግምት የጻፍኳቸው ጉዳዮች፣ በተለይ አሜሪካኖች ኢትዮጵያን ለመደለል ብዙ እርቀት ሊሄዱ ይችላሉ ያልኩት ጉዳይ ትክክል ሆኖ ተገኝቷል።  በዚያ ግምት ላይ ተመስርቼ ከአሜሪካ ለሚገኝ ማናቸውም እርጥባን ሲባል የሚወሰዱ አቋሞች በደንብ እንዲመረመሩ ለመንግስት ባለስልጣናት ማሳሰቢያ ለመስጠት ተገድጃለሁ። ይህን የማደርገው እንዲህ አይነት ጉዳዮች በጥልቀት የሚፈተሹበት፣ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸው ግለሰቦች የተካተቱበት መንግስትን የሚያማክር የፖለቲካ ካዎንስል በሃገራችን መኖሩን በመጠራጠሬ ነው። ወይም እንደነዚህ አይነት ጉዳዮችን በሚገባ የሚያጤኑና የሚመረምሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የጥናት እና የምርምር ተቋማት በሃገራችን አለመኖራቸው ነው። ከሁሉም በላይ “መንግስታዊ ስልጣን ላይ ያሉትን አካላት ይጠቅማል” ከሚል እሳቤ ነው።
ከዚህ ተነስቼ አሁንም አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ የወገኑ መስለው የኢትዮጵያ መንግስት ከወያኔ ጋር እንዲደራደር የሚሰሩት ስራ ካለ የኢትዮጵያ መንግስት በደንብ ሊያስብበት ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ጉዳይ ነቅቶ መከታተል አለበት። እኔ የመንግስት ባለስልጣን አይደለሁም። ከአሜሪካን መንግስት በህዝብ ስም በሚሰበሰብ እርዳታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቼ  መኖሪያዬ አላደረግሁም። ወይም “በአሜሪካ መንግስት ጥቁር መዝገብ ውስጥ መግባት ዋጋ ያስከፍለኛል” የሚል ስጋት የለብኝም። ከዚህ በላይ የጠቅስኳቸው አካላት በየራሳቸው ምክንያቶች ስለአሜሪካን መንግስት ሴራና ደባ በፊት ለፊትና በድፍረት ለህዝብ መናገር አይችሉም። እንደኔ አይነቶቹ ሰዎች ግን የአሜሪካን መንግስት እኩይነት ደግመን ደጋጋመን ለህዝባችን መናገር ይገባናል።
አሜሪካኖች “ጦርነቱ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገውል” ሲሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዝነው አይደለም። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት ውስጥ መርዝ ለመትከል የሚያደርገው ጥረት መሆኑን መገንዝብ ይገባል። ወያኔ እንደ ድርጅት የሚተርፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።
ወያኔ እስካለ ከሰላሳ አመታት በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፋሎ እርስበርሱ እንዲጠራጠር እንዲተላለቅ ያደረገው መሰሪ አስተሳሰብና ለዚህ አስተሳሰብ ህጋዊ ሽፋን የሰጠው ህገ መንግስት እንዲሁም መንግስታዊና አስተዳደራዊ መዋቅር የሚቀጥልበት ሁኔታ አይቀሬ ነው። ይህን የወያኔ አመለካከት ተሸክመው ጭፍን በሆነ የሃገር፣ የዘር፣ የእምነት ጥላቻ ለሚንቀሳቅሱ ወያኔን ለመሰሉ ሃይሎች ተጨማሪ ጉልበት ነው።
የወያኔ እድሜ መራዘም፣ በሃገራችን በወያኔ የተስፋፋው የሙስና እና የዘረፋ ባህል፤ ከወያኔም በኋላ በሚያስፈራ ደረጃ እየቀጠለ ያለው ይህ ነውረኛ ባህል የበለጠ ስር ሰዶ፣ ድህነት በኢትዮጵያ መድሃኒት ወደሌለው ካንሰር የሚያድግበትን ሁኔታ  የሚፈጠር ነው። በሙስና በኑሮ ውድነት፣ በስራ አጥነት እየተጠበሰ አስካሁን በሃገሩ ተስፋ ያልቆረጠውን አዲስ ትውልድ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የብልጽግና ተስፋ የሚቀብርና በመቃብሩ ሳጥን ላይ የሚመታ የመጨረሻው ሚስማር ነው።
ከዚህ በላይ ያልኩት እውን የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት እሺ ብሎ፣ ወያኔም ተስማማቶ ድርድር የሚደረግ ከሆነ ነው። በእኔ እይታ፣ እስካሁን ከሆነውና በመንግስት ባላስልጣናት ከተሰጡ ማብራሪያዎችና ካዘጋጇቸው ሰነዶች ተነስቼ የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱን በፖለቲካ ውሳኔ ለመቋጨት ሲል ለወያኔ ብዙ ነገሮችን አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እንዲህም ሆኖ ትልቁ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ምን ነገሮች ለወያኔ ቢሰጥ ነው ወያኔዎች ማርካት የሚችለው?
ወያኔዎች ባላፉት 27 አመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት 4 የለውጥ አመታታ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ወንጀል እንኳን ይቅር ቢባሉም ከዚህ በላይ ተሻግረው የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች፣ ከድርድር የሚጠብቋቸው ውጤቶች የኢትዮጵያ መንግስት ፈጽሞ ሊያሟላቸው የሚችላቸው ናቸው ብዬ አላምንም።  የወያኔን ጥያቄዎች በሙሉ  መንግስት በድርድር ስም አሟላለሁ ብሎ ቢነሳ ለወያኔ እጅን ከመስጠት ልዩነት አይኖረውም። ይህ አካሄድ በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘነድ የሚቀሰቅሰውን ቁጣና ሁካታ መንግስት የሚያስቆመው አይሆንም። ይህን በማጤን የደርድሩ ጉዳይ ሳይወልድ የሞተ ነገር ይመስላል። ለምን ታዲያ እርቅ፣ ሰላምና ድርድር እንደሚቻል ተደርጎ በመንግስት አካላት ውዥንብር ይነዛል? ግጭቱን ለመቋጨት የሚያስችል ሌላ አማራጭ አላታያቸው ብሎ ይሆን?
2) ግጭቱን የፖለቲካ መቋጫ ለመስጠት በኢትዮጵያ መንግስት የተወስነ ውሳኔ ከሆነስ?
3)
የነስብሃት ነጋን መፈታት አስመልክቶ ሰማይና ምድሩ እንዲዞርብን የሚያደርጉ የተለይያዩ በርካታ ማብራሪያዎች በመንግስት ተሰጥተዋል። ከእነዚህ መሃል አንዱ መንግስት ሰላማዊ የፖለቲካ መቋጫ ለግጭቱ መስጠት እንደሚፈልግ፣ የነስብሃት መፈታታም የዚህ የፖለቲካ ውሳኔ አካል እንደሆነ ነው። ይህ ጉዳይ የገና እለት በድንገት እንደቦንብ ለሁላችንም የፈነዳ ቢመስለንም የብልጽግና አባላት ፓርቲው ባሰናዳው ሰነድ አማካይነት ውይይት እንዳደረጉበት ተነግሮናል። ከዚህ በመነሳት “የነስብሃት ነጋን መፈታት እንደ ዱብ እዳ ማየት የለባችሁም” የሚል ማብራሪያ ተሰጥቶናል።  ወደ ቁም ነገሩ ከመግባታችን በፊት በዚህ ነጥብ ላይ አንድ ነገር ማለት ይገባል።
የብልጽግና ፓርቲ አባላት ውይይት እንዲያደርጉበት ፓርቲው ያዘጋጀው ሰነድ ሚስጥራዊ ሰነድ አልነበረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሚስጥር እንደማይሆን እየታወቀ አንዳንድ በሰነዱ ውስጥ መካተት የማይገባቸው ጉዳዮች መካተታቸው ተገቢ አልነበረም። ይህ ሰነድ በወያኔ እጅ የገባ ሰነድ ነው። በሲ አይ ኤ፣ በአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት እጅ የገባ ሰነድ ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶችም ሆኑ ወዳጆች ከአማርኛ ቋንቋ ወደራሳቸው ቋንቋ አስተርጉመው የያዙት ሰነድ ነው። አብዛኛው የሰነዱ ክፍል ለጠላት የሚሰጠው መረጃ ባይኖርም በጣም ጥቂት የሆኑ ነጥቦች ግን የመንግስትን አስተሳሰብና አካሄድ እንዲሁም አቅም ጭምር በማመላከት ለጠላት እቅድ በግብአትነት ሊያገልግሉ የሚችሉ ናቸው። ይህንና ሌሎችንም ጉዳዮች ስናጤን ሰንዱ የበቂ ምክክር ውጤት አለመሆኑን መገንዝብ እንችላለን።
ይህን ሰንድ እንደወያኔ እና እንደ ሲ አይ ኤ፣ ከብልጽግና ፓርቲ አባላት እኩል እኛም አግኝተን አይተነዋል። እንደ መንግስት የሁሉም ስብሰባዎች ሪፖርት ባይደረሰንም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የነበሩ የተወሰኑ ውይይት ሪፖርቶች ለእኛም ደርሰውናል። ውይይቱ “ግጭቱን በሰላም መቋጨት” ከሚለው ጥቅል አጀንዳ በታች ወርዶ ከወያኔ ጋር መወያየት” የሚል እንደምታ ይዞ ሲመጣ ተሰብሳቢዎች ተቃውሟቸውን እንደገለጡ ሰምተናል። አንዳንድ ስብሰባዎች ሳይቋጩ መበተናቸውንም መገንዘብ ችለናል። ሰነዱ ዝርርዝ ከሆነ የሰላም አስፈላጊነትና ከጠላት ጋር ተደራድሮ ግጭትን በሰላም መቋጨት በላይ ተሻግሮ ስለ እስረኞች መፈታታ፣ የግለሰቦችን ሰም ማንሳቱ ቀርቶ፣  በጥቅሉም እንኳን ያቀረበው ነገር የለም።
የፓርቲ አባላቱ “ሰዎች እንደሚፈቱ አናውቅም ነበር” የሚሉትን ጉዳይ በሰነዱ ላይ ከሰፈረው የውይይት ነጥብ ተነስቶ እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ ብቻ አይደለም ሰነዱ፣ የትግሉም፣ የመከራውም ተካፋይ፣ የተገኘውም ድል ባለቤት በሃገር ውስጥና በውጭ የሚኖረው መላው የሃገሪቱ ህዝብ እንደሆነ ይናገራል። ይህን ብሎ ግጭቱን ለመቋጨት መደረግ የሚገባውን የሰላምና የድርድር ጥረት ከብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ብቻ ወስኖ አስቀርቶታል። ይህ ራሱን የቻለ ትልቅ ጥፋት ነው። ያስከተለውም መዘዝ ቀላል አይደለም።
ሰንዱ  በፓዎር ፖይንት የተዘጋጀ ባለ 41 ገጽ ሰንድ ነው። አብዛኛው የስነዱ ክፍል ምንም እንከን የማይወጣለት ለአባላትም ይሁን ለመላው ማህበረሰብ ጭምር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚሰጥ ሰነድ ነው። በስፋት ተሰራጭቶ ቢሆን። ከዛም አልፎ የሃገራችንን ጠላቶች ምንነት፣ የጦርነት አስከፊነትና የሰላምና መረጋጋት እጦት የብልጽግና ጸር መሆን፣ እርቅና ድርድር እየመረረንም እንኳን ቢሆን ተቀብለን፣ ጦርነትን አቁሞ ፊትን ወደሃገር ግንባታ ማዞር ለምን እንደሚያስፈልግ በሚገባ ያስረዳል። እነዚህ ሁሉ ነጥቦች ችግር የሌለባቸው ናቸው። በሌላ በኩል ግን ሰነዱ ሰላምና ድርድርን የተሳካ ለማድረግ ግጭትን ለማስቀረት በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነ ይዘረዝራል። ሰነዱ ይህን በተመለከተ ቃል በቃል እንዲህ ይላል።
“ሌላኛውም ግማሽ መንገድ እስካልመጣ፣ ይልቁኑም ተቃራኒውን መንገድ ከመረጠ  ያኔ ግጭት  አይቀሬ ይሆናል። ሰላም በአንድ ወገን ፈቃድ ላይ ብቻ የሚመሰረት አይደለምና። ሰላም የሁለት አካላትን ፍላጎት  የሚሻ፣ የሁለት አካላትን ተሳትፎ የሚፈልግ ነው። ሰላም ወዳድ በመሆንና ጦርነትን በመሸሽ ግጭት ከሕይወታችን  ውስጥ ይሰረዛል  ማለት ዘበትም ሞኝነትም ነው።”
ይህ ነጥብ አጠቃላይ ሃቅን ያስቀመጠ ቢመስልም፣ ወያኔ የሰላም አጋር መሆን እንደማይችል በመጠርጠር የተጻፈ ይመስላል። ይህን ምልከታ ትክክል እንደሆነ የሚያሳየው ነጥብ በሚቀጥሉት መስመሮች ተጽፎ እናገኘዋለን።
ሰነዱ ከግጭቱ በፊት ወደነበሩ ሰላማዊ ወቅቶች በመመለስ ይጀመራል፤
“የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ሲመጣ አንግቦ የተነሣው ከቀደመው ‹የጉልበት ሰይፍ› የተሻለውን ሰላማዊ የ‹ሰይፍ› መንገድ ነበር።መርሑም ‹በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር› የሚል ነበር በዚህ መርሕም ያለፈውን የፖለቲካ ታሪካችንን በይቅርታ ዘግተን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍን በፍቅር ለመጀመር ተነሣሽነትን ተወስዷል።” ይለናል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰነዱ የወያኔን ወቅታዊ የአስተሳስብ ቅላጼ ሲገመግምና መጭውን አስቸጋሪ ወቅት ሲያመላክት እንዲህ ይለናል።
“ሽብርተኛው ህወሓት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጸብ አጫሪነቱንና እብሪቱን ማሳየቱ አይቀርም፡፡ ከቻለም ለዳግም ወረራ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ስለሆነም ከህወሓት ጋር የሚኖረው ቀጣይ ትግል ዘርፈ ብዙ እና በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ላይሆን እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል፡፡ስለሆነም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አደረጃጀትና ሁለንተናዊ አቅም የበለጠ ማጠናከር ይገባል፡፡” ይለናል።
እንዲህ አይነት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እይታዎች የያዘ ሰነድ ወደ ዋናው የውይይቱ ርእስ ሲገባ ለሰላምና ለድርድር  የሚሰጣቸው ምክንያቶች አንዳቸውም ከወያኔ ባህሪ ጋር የሚያያዙ ሆነው ግን አናገኛቸውም ።
በ4.4. ላይ ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በሚለው ርእስ ስር  የምናነበው አብዛኛው ነገር፣ ጦርነት ጉዳት ያለው መሆኑን፣ የልማትና የብልጽግና ጸር መሆኑን፣ ጦርነት አቁሞ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ከወጭ ተጽእኖ መላቀቅን የሚያመላክት ነው። ጦርነቱን ለማቆም ሃገራዊ ምክንያቶች ከደረደረ በኋላ ግን አስገራሚው ነጥብ፣ “ስለሆነም” በሚል ማስተሳስሪያ የሚጀምረው አረፍተ ነገር ነው። “ስለሆነም ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር ለአለም ማሳየት አለብን።” ይላል።
ቀጥሎም “ተገደን የገባንበትን ጦርነት ለመቋጨት ወደ ሰላማዊ ውይይት መግባት ይኖርብናል፡፡ ይህንን በማድረጋችን አሰፍስፈው ሊውጡን የተዘጋጁ የውጭ ኃይሎችን ማለዘብም ማሸነፍም እንችላለን፡፡” ይላል።
እነዚህ ሁለት ተያያዥነት ያላቸው አረፍተነገሮች ጦርነቱን አቁመን ወደ ሰላማዊ ድርድር የምንገባው የውጭ ሃይሎችን ፍላጎትና ጫና ለማርካት እንጂ “እውን ከወያኔ ጋር ሰላም የመፍጠር እድላችን ሊሳካ ይችላል” ከሚል ግምገማ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ናቸው። ቀደም ብሎ ሰነዱ ወያኔ ከለውጥ መባቻ ጀመሮ የቀረበለትን የሰላም የፍቅር መንገድ የረገጠ መሆኑ ግልጽ አድርጓል።አሁንም ለሰላም ሲባል ከትግራይ ድንበር ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ ቢቆምም ወያኔ ውጊያ የማያቆም፣ ውጊያ ስለማቆም ከኢትዮጵያ መንግስት የተወሰነውን ውሳኔ  ለጦርነት የሚዘጋጅበት ግዜ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ይገልጻል። ሰንዱ የተነበየው እውነት ሆኗል። ወያኔ ከአፋር ክልል ተቀጥቅጦ ከወጣ በኋላ ራሱን አደራጅቶ የአፋር ክልልን ወሯል። የአማራ ክልልን ለመውረር በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው።
በዚህ የሰነዱ ክፍል የቀረቡ ነጥቦች፣ በወያኔ ላይ የመረረ ጥላቻ ያላቸውን አባላት ለማሳመን የቀረቡ ይመስላሉ። ከዛም ተሻግሮ ጦርነቱን በሰላም መቋጨት በአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ፊት ለሚኖረን የመልካም ገጽታ ግንባታ የሚጠቅም እንደሆነ ይገልጻል። በጣም የሚገርመው ጦርነቱን ከጀረባ ሆነው የሚዘውሩት ረጃጃም የቅርብና የሩቅ እጆች አጀንዳ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን ስለምንረዳ በውይይት ማጠናቀቅ ተገቢ ይሆናል። ይህ የሰንዱ ወሳኝ ክፍል ከላይ ስለወያኔ ምንነት ግልጽ በሆነ መንገድ የተቀመጡትን ነጥቦች ወደ ጎን አስቀመጦ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ምክንያት ያላቸውን የተግበሰበሱ ነጥቦች በአንድ ላይ አምቆ ይዞ መጥቷል። ምክንያቶቹ አራምባና ቆቦ የሚረግጡ፣ ጥቅል ከሆኑ የግጭት አፈታት አስተያየቶች ተነስቶ ወደሚገርሙ በሃገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ ጉዳዮች ተሳስሮ ተደምድሟል። አንባቢ በውል እንዲረዳው ይህን ክፍል እንዳለ አቀርበዋለሁ።
“ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በየትኛውም አለም ጦርነትን በውይይት መፍታት የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንኳንስ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት መስራች አባላት ሆነን ይቅርና ባንሆንም ጦርነትን በውይይት  መፍታት አለምአቀፍ መርሆ ነው፡፡ ይኸ ማለት የሚቆረቁር፣ የሚያም፣የሚጎረብጥ ነገር የለም  ማለት አይደለም፡፡ምንም ይሁን ምን በአለምአቀፍ አደባባይ ሞጋችና አሸናፊ እንጂ ጠላቶቻችን እንደሚከሱን ጦር ነት አፍቃሪ ሆነን መገኘት የለብንም፡፡ ስለሆነም ጥቅሞቻችንን ከማስከበር መለስ ለውይይት መቀመጥ ብልህነት ነው፡፡ የቀጠለ ጦርነቱን በውይይት ማጠናቀቅ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት በመንስኤውም ሆነ በፈጠረው የሰው ሕይወት፣ የንብረትና የሀገር ገጽታ ጥፋት ያስከተለውን ሀገራዊ ጉዳት በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል። ጉዳዩን ከሁሉም በላይ መራራ የሚያደርገው ደግሞ ጦርነቱ የጥቂት ግለሰቦችንና የወንጀለኛ ቡድኑን ህልውና ፈቃድ ለማሳካት ተብሎ የተጀመረ መሆኑ ነው። ሆኖም በሂደት የብሔር መልክ እየያዘ መሄዱ ጉዳዩ ከተገመተው በላይ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ጦርነቱን ከጀርባ ሆነው የሚዘውሩት ረጃጅም የቅርብና የሩቅ እጆች አጀንዳ ምን እንደሆነ ጠንቅቀን ስለምንረዳ በውይይት ማጠናቀቅ ተገቢ ይሆናል”
ቀጥሎ በሰነዱ ማጠቃለያ የቀርበውን እንመልከት
“ለግጭቱ እልባት መፈለግ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅ ዋነኛ ጉዳይ ነው። በርግጥ የግጭቱ ጠንሳሾች ብዙ የሰላም ዕድሎችን በማምከን የተካኑ ናቸው። ታሪክ አበክሮ የሚነግረን ነገር ቢኖር ብዙዎቹ ግጭቶች ዘላቂ እልባት የሚያገኙት በንግግር፣በድርድርና በስምምነት ነው። ተጠቂውም ምላሹን በኃይል ይመልሳል።ግጭቱም ቢሆን ያወደመውን ንብረት አውድሞ፣የቀጠፈውን ሕይወት ቀጥፎ፣የኋላኋላ መጠናቀቁ አይቀርም። ልዩነቶች በውይይት መጠናቀቅ ሳይችሉ ሲቀሩና ፍላጎትን በሰላማዊ መንገድ ማሳካት ሲያቅት፣ሀገር ከሀገር፤ቡድን ከቡድን ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። ዓለማችን ለብዙዎች እልቂት የዳረጉ ግጭቶችን አስተናግዳለች።
በመንግስት ደረጃ ስለነስብሃት ነጋ መፈታታ እስካሁን ከተሰጡን ምክንያቶች የተሻለ መረጃ የምናገኘው ከዚህ ሰንድ ነው። የቀናትን ቅደም ተከተል ተከትለን የሆነውን ካየነው ይህ ሰንድ ከአሜሪካኖች የአቋም ለውጥ በፊት የተጻፈ ነው። ጸሃፊው የወያኔን ደጋፊዎች እነአሜሪካንን በአንድ አይኑ እያየ እንደሆነ ነው። አሜሪካና ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያለዝቡ ከማሰብ ጭምር ነው።
በዚህ መንገድ ካየነው አሜሪካኖች ወደ ኢትዮጵያ ከረሜላቸውን ይዘው ይቅረቡ እንጂ ከወያኔ ጋር መደራደር የሚለውን ሃሳብ የውጭ ሃሎችን ለማለዘብ በማሰብ የቀረበው በኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ ነው። “ለውጭ ሃይሎች አልተንበረከክንም የተነበረከኩት እነሱ ናቸው” የሚለውን የመንግስት አባባል እንደገና እንድንፈትሽ የሚያደርግ ነው።
በጦር ሜዳ የወያኔ መሸነፍና የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ አይነት የሰላምና የእርቅ ሃሳብ ይዞ መውጣቱ አሜሪካ ከረሜላዋን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ለመጠጋቷ ዋናው ምክንያት ነው።  ኽርማን ኮን ሳይቀር “ወያኔ በወታደራዊ ጉልበት የኢትዮጵያን መንግስት መግደርደር አይችልም። መሪዎቹ ያላቸው ምርጫ ህወሃትን አፍርሰው ስደት መሄድ ነው” ብሏል። ይህ አቋሙ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው አቋሙ 180 ዲግሪ የተቀየረ ነው። ይህ የአቋም ለውጥ የግለሰብ ብቻ አይደለም። የአሜሪካ ፖሊሲ መቀየሩን የሚያሳይ ነው። እንደገመትነውም በ27/1/2022 ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ አሜሪካ ኢትዮጵያን ስትራተጂክ አጋሯ አድርጋ እንደምታይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ቀድሞው ስትራተጂክ ግንኙነት እየተመለሰ እንደሆነ፣ እርዳታ ለማቅረብ፣ ጦርነት ያፈረሳቸውን ከባቢዎች ለመገንባት ነዋይ እንደምታፈስ አዲሱ የአሜሪካ መልእክተኛ እንደተናገሩ ነው። ባለፈው ጽሁፌ እኔም ከዚህ የተለየ ነገር አልጻፍኩም። አሜሪካ ትናንና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ ለተነሳ ወገን አግዛ ቆማ እንደነበር ማስታውስ ያስፈልጋል።
እየዋለ እያደረ የታዘብነው “እነስብሃት ነጋን መፍታትና ከወያኔ ጋር ድርድር ማድረግ” የሚለው ውሳኔ የተለያዩ ምክንያቶችና ግፊቶች ውጤት እንደሆነ ነው። በዚህ ጽሁፍ አሁንም መልሰን መላልሰን ማንሳት የሚገባን ጉዳይ እነስበሃት ነጋን መፍታት የሚለው ጉዳይ መጀመሪያ በማን ተቀነቀነ የሚለው እንዳልሆነ ነው። የመፈታቱ ሆነ የመደራደሩ ጉዳይ ከአሜሪካኖች የመጣ ከሆነ ምን ያህል ኢትዮጵያን የሚጎዳ እንደሆነ በዝርዝር ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ያለማንም ተጽእኖ በመንግስት በራሱ የተቀነቀነ ሃሳብ ከሆነም  ስለጉዳዩ የምናነሳውን መሰረታዊ ጥያቄ አይቀይረውም።  ትልቁ ጥያቄ ያለው ከወያኔ ጋር ድርድር ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚደረግ ድርድር ሃገርና ህዝብን ይጠቅማል ወይ? የሚል ነው።
ከላይ እንደተመለከትነው የብልጽግና ሰነድ “ወያኔ ሰላም እርቅ ድርድር የሚባል ነገር የማይገባው ነው። ለሰላም እድል ለመስጠት ጦርነት ስናቆም ወያኔ ፋታውን ለጦርነት መዘጋጃ ያደርጋዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው እነስብሃት ስለተፈቱ ጦርነት አቁሞ ወያኔ ወደ ድርድር የሚመጣው? ከነስብሃት መፈታታ በኋላ ወያኔ አፋርን ወሯል። ከአማራ ክልል ጠቅልሎ አልወጣም። በአማራ ክልል ላይ ተጨማሪ ወረራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። በበኩሌ እነዚህ ጭብጦች የሚያሳዩት በስሜት የምንነዳው የነስብሃትን መፈታት የተቃወመው ስፊ ህዝብ ሳይሆን የወያኔን ምንነት በግልጽ እያስቀመጠ፣ “ለሰላም ለድርድር የሚመች ባህሪ የሌላቸው ናቸው” እያለ ጦርነት እንዲቆም ካለው ቀና ፍላጎት ብቻ በመነሳት ወያኔ ለሰላምና ለድርድር የሚጠራው መንግስት ነው።
የብልጽኛ ፓርቲ ስለግጭት አፈታት አለም አቀፍ ተመክሮ በሰነዱ ላይ ያስቀመጠው እንዳለ ሆኖ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ስለማይቻልባቸው ሁኔታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶችን ሰነዱ አያካትትም። ለምን ይህ እንዳልተደረገ አላውቅም። ሆኖም ግን በአለም ላይ ብዙ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ ድርድር የተቋጩትን ያህል በጦርነትም የተቋጩ አሉ።37 አመታታ የፈጀው የሲሪላንካ መንግስትና የታሚል ታይገሮች ግጭት የተጠናቀቀው በጦርነት ነው። የአለም አቀፍ ተመክሮ የሚያሳየው በሰላማዊ ድርድር የሚፈቱ ግጭቶች ሁሌም ግጭት ወስጥ ከገቡት ሃይሎች ምንነት ጋር የተሳሰረ ነው። ግጭት የቀሰቀሰው ጉዳይ በምክንያት የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ በምክንያት ላይ ተመስርቶ ግጭትን በደርድር መፍታት የሚችልባቸው እድሎች አሉ።
ነገር ግን ወደ ግጭት የገባው አካል ተጨባጭ ግብ የሌለው፣ ለራሱ ምድራዊ ወይም ሰማያዊ ተልእኮ የሰጠ ከሆነ፣ ከእንዲህ አይነቱ ሃይል ጋር ድርድር አይቻልም። “በሙስናና በግፍ የተጨማለቀውን የኢምፔሪያሊስቶች አለም በሽብር እናጸዳዋለን” የሚል ግብ ከነበራቸው የጣሊያን እና የጀርመን እንዲሁም የሌሎችም አገሮች የቀይ ብርጌድ ድርጅቶች ጋር ድርድር ማድረግ አይቻልም ነበር። ለድርድር የሚቀርብ ነገር ስላልነበራቸው። በተመሳሳይም እምነትን መሰረት ካደረጉ፣ ከእምነት ጋር በተያያዘ ሽብር ውስጥ ከገቡ እንደ አልቃይዳ አይነት ድርጅቶች ጋርም ድርድርና እርቅ ማድረግ አይቻልም። የመደራደሪያ መነሻ የሚሆን ምክንያት ስለማይኖር።
ከዚህ ውጭ ዘረኝነትን ዋንኛ የመደራጃ ርእዮእተ አለም አድርገው ከተነሱ የጀርመኑ ናዚ መሰል መንግስታት ጋር ሰላምና እርቅ የሚባል ነገር አይቻልም። ከእንዲህ አይነቶቹ አካላት ጋር የሚጀመር ግጭት የሚያልቀው በጦርነት፣ በመሸናነፍ ነው። ትልቁ ጥያቄ ያለው ወያኔ በየትኛው ምድብ የሚፈረጅ ድርጅት ነው? የሚለው ነው። ወያኔ ለ27 አመታታ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ዘረፋና እንዲሁም ባላፈው አመት ወያኔ በአማራና በአፋር ክልል ያኪያሄደውን የሽብር ስራ ከተመለከትን ዘረኛነትን መሰረት ያደረገ ንበር። ለሌሎች ዘሮች ካለው ጥላቻና ንቀት የሚመነጭ እንደሆነ ነው። የወያኔ የግጭት አላማ በግጭቱ ለሚገኝ የተወሰነ ግብ ሳይሆን በፍጹም ጠቅላይነት ወይም በፍጹም አውዳሚነት የተቃኘ ነው።
መንግስትም “ወያኔ፣ እርቅ ፍቅር መቻቻል፣ ድርድር የማይገባው ድርጅት ነው” እያለን ነው። ሁላችም ያየነው የወያኔ ባህሪይ እና ድርጊት የሚጠቁመው ከወያኔ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ወያኔን በማጥፋት የማይጠናቀቅ ከሆነ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷ ክብሯና ጥቅሟ የማይከበር፣ ሰላም የሚባል ነገር እንደማይኖራት ነው። ይህን ማስፈጸም ሽህ ጊዜ ከባድ መስሎ ቢታይም ከዚህ ያነሰ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ክብርና ጥቅም እንዲሁም ሰላም የሚሰጥ አማራጭ የለም።
የሚታየን እውነተኛ መፍትሄው ከባድ ስለሆነ ብቻ፣ የማይሰራ መሆኑን እያወቅን ቀላል መትሄ መመኘት በልብ ወለድ ድርሰት ወስጥ እንጂ በእውነተኛው የፖለቲካ አለም ቦታ የለውም። ከእውነታ የራቀ የቀላል መፍትሄ መሻት ከባዱን መፍትሄ ተግባራዊ ለማድረግ ከምንከፍለው መስዋእትነት በላይ የከፋ መስዋእትነት ያስከፍለናል።
በእዚህ መንገድ ተጉዘን እስካሁን ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ወያኔዎች በይቅርታ በፍቅር እንሻገር ሲባሉ፣ በጥላቻ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አርደው ጦርነት ከፈተው ሰቆቃ ፈጽመው ማንነታቸውን አሳዩን። ለጥሞናና ለገበሬዎቻቸው የማረስ እድል ለመስጠት ከትግራይ የመከላከያ ሰራዊት እንዲወጣ ሲደረግ አማራና አፋርን ወረው ግፍ ውርደትና ውድመት ፈጽመው አሳዩን። “ከአፋርና ከአማራ ክልል እናስወጣቸዋለን ነገር ግን ትግራይ አንገባም። ይህ ድርጊታችን ወያኔዎችን ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሌላው ቢቀር በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሱትን መከራ እንዲፈትሹና ስለሰላም እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ተባልን። ይህ ውሳኔያችን ለወያኔዎች ሌላ ዙር ወረራ የመፈጸም አቅም ያደራጁበትን እድል ሰጣቸው እንጂ ወደ ሰላም አላመጣቸውም።
የወያኔ ምንነት፣ በባህርይ ሆነ በተግባር የተገለጸው ምንነቱ፣ ወያኔን የተከፈለውን መስዋእትነት ከፍለን ወያኔን እንደ ድርጅት ከመቅበር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ነው። አይን ያፈጠጠው ሃቅ ይህ ነው። አዎን ጦርነቱ በመራዘሙ በፍጥነት ፊታችን ወደ ልማት ማዞር አንችልም። ጦርነቱ በመራዘሙ የሚከፈለው ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ ትልቅ ነው። ሆኖም የሰላሙ አማራጭ የማይሰራ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል። የሰላሙ አማራጭ የአሜሪካ ተላላኪ የሚያደርገን ከሆነ፣ የሰላሙ አማራጭ ለወያኔ ልንሰጠው የማንችለውንና የማይገባንን ገጸ በረከት እንድንሰጥ በማድረግ ወሳጣዊ አንድነታችንን አናግቶ ቀውስ ውስጥ የሚጨመረን እና ለከፋ ኪሳራ የሚዳርገን ከሆነ ድርድር ቢቀርብን ይሻላል።
በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የከባድ ምርጫዎች ሰአት የሚባሉ ወቅቶች አሉ። የኢትዮጵያ መሪዎች በዚህ አይነቱ የከባድ ምርጫዎች ወቅቶች ውስጥ ይገኛሉ። የሚመርጡት ምርጫ የሃገርና የህዝብ ህልወናን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የሚታደግ ሊሆን ይችላል። ባላንበት ወቅት የወያኔን ምንነት እያወቁ፣ የአሜሪካንና የምእራባውያንን ምንነት እየታወቀ ወያኔ ለሰላማዊ የድርድር ሂደት ራሱን ክፍት ሊያደርግ ይችላል በሚል ቀቢጸ ተስፋ መዋተት ትልቅ ስህተት ነው።
ለማጠቃለል፣ በጽሁፌ መጀመሪያ ለነስብሃት መፈታታ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ካስቀመጥኳቸው አራት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱን ሰፋ አድርጌ ተመልክቻቼዋለሁ። የቀሩት ሁለቱን በአጭሩ በመዳሰስ ጽሁፌን አጠቃልላለሁ። ሁለቱም ምክንያቶች ከተለያዩ የመንግስት ባላስልጣናትና ከራሱ ከዶ/ር አብይ አስተያየቶች ያገኘናቸው እንጂ እኛ የፈጠርናቸው አይደሉም። የመጀመሪያው የነስብሃትን መፈታታ በወያኔ ካምፕ ውስጥ ልዩነቶች በመቀስቀስና ክፍፍል በመፍጠር ጦር ሰባቂውን ወገን ለማዳከም የሚለው ነው። የውሳኔውን ከባድነት ግምት ውስጥ በማስገባት “ይህ ከባድ ወሳኔ በዚህ ተልካሻ ምክንያት የተፈጸመ ነው” ብሎ ማመን ይቸግራል። ስለሆነም ይህ ነጥብ ብዙ ውይይት የሚያስፈለገው አይመስልም።
የመጨረሻው ነጥብ ውሳኔውን ከእምነት የመነጨ የእርቅና የምህረት ውሳኔ የሚያደርገው ነጥብ ነው። ከዶ/ር አብይ አንደበት የነስብሃት መፈታታ ፈጣሪ ካዘዘው ትእዛዝ ጋር የተገናኘ መሆኑ ተነግሮናል። በዚህ  ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በጥቅሉ አንድ መሰረታዊ ነገር ተናግሮ ማለፍ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አደገኛና አስፈሪ የሆነ የሀገራዊ ቀውስ ምክንያት መሆን የሚችል ጉዳይ ቢኖር የፖለቲካ አቋምን ከእምነት የመቀላቀል ጉዳይ ነው። አዎን ኢትዮጵያ የአማኞች አገር ናት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ፈሪሃ እግዚአብሄር የሚሰማው መሪ ማግኘቷ በበጎ የሚታይ ነው።  ቢሆንም፣ የትኛዎቹም የፖለቲካ መሪዎቿ የፖለቲካ ውሳኔያቸውን ከሚከተሉት እምነት ጋር አያይዘው የሚወስኑት ከሆነ ሁሉም እምነቱን እያጣቀሰ ለሚወስደው የተለያያ አቋም መመዘኛ የሆነ የጋራ መስፈርት የሚያሳጣን ይሆናል። ይህ ሃገርን የሚበትን እንጂ የሚያቆም አይሆንም።
ፈጣሪ የኢትዮጵያን ህዝብ በጥበቡ ይጠብቅ !
Filed in: Amharic