>

"የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታሪክ ሲወሳ ሊታወሱ የሚገባቸው ብላታ ወልደ ማርያም አየለ....!!!" አቻምየለህ ታምሩ

“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታሪክ ሲወሳ ሊታወሱ የሚገባቸው ብላታ ወልደ ማርያም አየለ….!!!”
አቻምየለህ ታምሩ

አገራችን ኢትዮጵያ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት ጥቂትም ቢሆኑ አገር አውል፣ አሰላሳይ፣ መሬት ጠብ የማይል ጥልቅ ምክር የሚሰጡ፣ አገር ወዳድና አርቆ አሳቢ የሆኑ ሊቃውንት ነበሯት። ከነዚህ የኢትዮጵያ ሊቃውንት መካከል የኋላ ታሪካቸው ያላማረ ቢሆንም እጅጉን አርቆ አሳቢና አሳላሳይ የነበሩት ብላታ ወልደ ማርያም አየለ ቀዳሚው ናቸው። ብላታ ወልደ ማርያም አየለ ኢትዮጵያ የራሷ ባንክ እንዲኖራት ያደረጉበት ታሪክ እንዲህ ነው።
እንደሚታወቀው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በ1897 ዓ.ም. የተቋቋመው “ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ” በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ባንክ ነው። የባንክ እውቀት ያለው የአገሬው ሰው ባለመኖሩ ባንኩን  በበላይነት ይቆጣጠርና ይመራው የነበረው በወቅቱ የእንግሊዛውያን ንብረት የነበረው የግብጽ  ብሔራዊ ባንክ ነበር። ባንኩ የተቋቋመው የራስ መኮንን ይዞታ በነበረው የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ [6ኪሎ  ቅጥር ግቢ] ውስጥ ሲሆን ባንኩ ስራ የጀመረው ራስ መኮንን ግቢ በወቅቱ ከነበሩት የሳር ክዳን ቤቶች ውስጥ በአንዷውስጥ ነበር። ባንኩ በራስ መኮንን ግቢ ስራ የጀመረባት የሳር ክዳን ቤት ፎቶ ከታች ታትሟል።
“ባንክ ኦፎ አቢሲኒያ” አስተዳደሩ በእንግሊዞች ይሁን እንጂ ሙያተኞችና ባለ አክሲዮኖቹ አሜሪካኖች ነበሩ። ዳግማዊ ምኒልክ ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም ሲፈቅዱ ከእንግሊዞች ጋር የገቡት አንድ ውል ነበራቸው። ይህም ውል ባንክ ኦፎ አቢሲኒያ ከቆመበት ቀን ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ባንክ እንዳይቆም የተስማሙበት ነበር።
ይህ ዳግማዊ ምኒልክ ወቅቱ አስገድዷቸው የገቡበት ውል የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ በሞኖፖል እጅ እንዲገባ የሚያደርግና ውሎ አድሮ ለሕዝብም ሆነ ለመንግሥት ጉዳት የሚያመጣ በመሆኑ የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መንግሥት ባፋጣኝ መፍትሔ እንዲያበጅለትና የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የራሱ ባንክ እንዲኖረው ምክረ ሀሳብ ያቀረቡት ባለታሪካችን ብላታ ወልደ ማርያም አየለ ነበሩ።
የብላታ ወልደ ማርያም ምክረ ሀሳቡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው መሆኑ ታምኖበት  በአፍሪካውያን ንብረትነት በአፍሪካ ውስጥ የተመሰረተውና  የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ባንክ በብላታው ምክር ሚያዚያ 23 ቀን 1924 ዓ.ም ተቋቋመ።
ብላታ ወልደ ማርያም አየለ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተፈረመው “የባንክ ኦፎ አቢሲኒያ” ውል አንድ መፍትሔ የሚያገኝበትንና ለኀምሳ አመታት ሌላ ባንክ እንዳይቋቋም የተላለፈው እግድ እንዲነሳ ለአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ያቀረቡት ተራማጅ ምክረ ሀሳብ የሚከተለው ነበር፤
_____________________
ይድረስ ከልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን
 
ልዑል ጌታዬ 
የኢትዮጵያ ባንክ ነገር ለመንግሥታችንም ለሕዝባችንም እጅግ ያስቸገረ ሆኗል። ባንኩ የቆመበት ውል ባንኩ ከቆመበት ቀን ጀመሮ ለመንግሥትም ለሕዝብም በብርቱ አስቸጋሪ ነው። ከዚሁም ችግር ለመላቀው ከሦስቱ አንዱን ለገር መያዝ ያስፈልጋል።
አንደኛው ነገር የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ጥቅምና ሥልጣን የሕዝቡንም ጥቅም ለእንግሊዝ ባንክ ለቅቆ ሰላሳ ዓመት [ይህ ምክር ሀሳብ የቀረበው ባንኩ ከቆመ ከሀያ ዓመታት በኋላ በመሆኑ ኀምሳ ዓመት እንዲቆይ የተፈረመው ውል ለማለቅ ሰላሳ ዓመታት ይቀሩታል] ድረስ እኖራለሁ የሚል እንደሆነ ለባንኩ የተሰጠውን ውል አክብሮ ጠብቆ መኖር አለበት። በእውነቱ ይህንን ይሁን ብሎ ለመታገስ ነጻ ለሆነ አገር የሚቻል አይደለም።
ሁለተኛው ነገር ይህንን የባርነት ውል ታግሶ ለመኖር የማይቻል ከሆነ በውሎ ላይ ተከራክሮ እንደሌላው አገር ሁሉ የተስተካከለ ደንበኛ የባንክ ውል አሻሽሎ መጻፍ ያስፈልግል። ይህንንም ውል አሻሽሎ ለመጻፍና ያውም ከእንግሊዞች ጋር መከራከር ከገደል እንደመጋፋት ያህል ማስቸገሩን ማስተዋል ይስፈልጋል።
ሶስተኛው ነገር ከዚህ ችግር የሚያወጣን በማናቸውም ዋጋ ቢሆን ባንኩን [ባንክ ኦፎ አቢሲኒያን] መግዛትና ከእንግሊዞች መላቀቅ ከሁሉም የሚሻል ነው።  ለዘመናችን ስም፣ ለኢትዮጵያና ለመንግሥቱ ጥቅም የሚሆን መስሎ  የታየኝን ይህን ምክረ ሀሳብ እግዚያብሔር ስልጣል ለሰጠው ልዑል ጌታዬ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ደፍሬ አመለክታለሁ።
ታኅሣሥ ፳ ቀን ፩፱፻፲፫ ዓ.ም.
ተዛዥዎ ወልደ ማርያም አየለ
_____________
[ምንጭ፡ ከቤተ መንግሥት ዶሴ፡ የብላታ ወልደ ማርያም መዘክር ገጽ 63]
ይህ የብላታ ወልደ ማርያም አየለ ምክረ ሀሳብ ሰውዬው ምን ያህል ተራማጅ፣ ከዘመናቸው ቀድመው የሚያስቡና እያንዳንዱ የሚያቀርቡት ምክረ ሀሳብም ከወቅቱ ተጨባጭ አገር አቀፍና አካባቢያዊ  ጂኦ ፖለቲካ አኳያ የሚያስከትለውን መዘዝ አበክረው የሚያሰላስሉ ጠንቃቃ ምሑር መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ያ የተረገመ ትውልድ አድሀሪ፣ ኋላ ቀርና ጨለማ ተደርጎ  አድርጎ የሳለው የአባቶቻን ዘመን እንዲህ አይነት ተራማጅና ዘመናትን ቀድመው የሚያስቡ አሰላሳዮች የነበሩበትን የተስፋ አርአያዎችን የብርሀን ዘመን ነው።
እንግዲህ! በዚህ የብላታ ወልደ ማርያም አየለ ምክረ ሀሳብ መሰረት ነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ሚያዚያ 23 ቀን 1924 ዓ.ም ባንክ ኦፎ አቢሲኒያን ከእንግሊዝ ማኅበር ላይ በስምምነት ገዝተው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተፈረመው ውል እንዲሻር በማድረግና ይህንንም በሕግ አሳወቀው ስሙን በመቀየር የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ተብሎ እንዲሰየም ያደረጉት።
በዚህ አኳኋን በብላታ ወልደ ማርያም ምክር ተገዝቶ ስሙን ከ”ባንክ ኦፎ አቢሲኒያ” ወደ  “ኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ” የቀየረው ይህ ባንክ  በታኅሣሥ ወር 1956 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመባል ለሁለት ተከፈለ።
ብላታ ወልደ ማርያም አየለ ያንን ተራማጅ ምክረ ሀሳብ ባያቀርቡና ንጉሠ ነገሥቱም ሀሳቡ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ የሚጠቅም መሆኑን ምክረ ሀሳቡን ባይቀበሉ ኖሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ሊደርስ አይቻለውም ነበር። በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ታሪክ ሲወሳ አሳላሳዩና ምጡቁ ምሑር ብላታ ወልደ ማርያም አየለ አብረው ሊወሱ ይገባል!
ማሳሰቢያ፡-
ሰለ ብላታ ወልደ ማርያም አየለ ታሪክ ተጨማሪ ነገር ማንበቢ የሚሻ ቢኖር “ከቤተ መንግሥት ዶሴ፤ የብላታ ወልደማርያም መዘክር” በሚል መኩሪያ መካሻ የተዘጋጀውን የብላታውን ማስታወሻ፣ በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የተዘጋውን “የአክሊሉ ማስታወሻ” እና ልጃቸው ፓስካል ወልደ ማርያም  “የሚስማ ጆሮ ቢኖር ኖሮ፡ የብላቴን ጌታ ወለደማርያም አየለ ታሪክ” በሚል የጻፉትን የሕይዎት ታሪክ ያንብብ!
Filed in: Amharic